Sunday, 28 January 2018 00:00

የፖለቲካ እስረኞች መፈታት - ተስፋውና ፈተናው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 መንግሥት፤ ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ 115 የፖለቲካ እስረኞችን ክስ በማቋረጥ ከእስር መፍታቱን  ሂውማን ራይትስ ዎች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል አድንቀዋል፡፡ “የሚበረታታ ነው፤ ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የመፍትሄ መነሻ ይሆናል” ያሉት የሰብአዊ መብት ተቋማቱ፤ መንግሥት ቀሪ እስረኞችንም እንዲፈታ መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡
የተቃዋሚ  ፓርቲ አመራሮችም የተቋማቱን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ ብዙ ፖለቲከኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ የሚገልጹት  አመራሮቹ፤ በአገሪቱ ላይ ትርጉም ያለው የለውጥ እርምጃ እንዲጀመር መንግስት ቃል በገባው መሰረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፣ የታሰሩ ፖለቲከኞችን በሙሉ መፍታት እንዳለበት በአንድ ድምጽ ይናገራሉ። መንግስት ይሰማቸው ይሆን? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በጉዳዩ ዙሪያ የአንጋፋ ፖለቲከኞችን አስተያየት አሰባስቦ እንዲህ አጠናቅሮታል፡፡ አሁንም ለፖለቲካዊ ችግሮቻችን  ፖለቲካዊ መፍትሄ ያስፈልጋል!


            “በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ተፈተው ማየት እንፈልጋለን”
              ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ

   ለአንድ ትልቅ ችግር ግማሽ መፍትሄ የለውም። የተሟላ መፍትሄ መሻት እንጂ ዝም ብሎ እየቀነጫጨቡ ማቅረቡ  ውጤት አያመጣም፡፡ አሁን የሚደረገው ነገርም ውጤቱ መሬት ላይ  አይታይም፡፡ የተወሰኑ እስረኞችን በመፍታት፣ነገሮችን ለማረሳሳት የሚደረጉ ሙከራዎች፤ በህዝቡ ከቀረቡ ጥያቄዎች ጋር የማይመጣጠኑ ሆነው ነው የሚታዩኝ፡፡ ተፈቱ ከተባሉትም ውስጥ መጥቀስ የሚቻለው ዶ/ር መረራን ብቻ ነው፡፡ ሌሎች የየክልል ተጠሪዎቻችን እንደታሰሩ ነው ያሉት፡፡ ዝም ብሎ ለማሳያነት ዶ/ር መረራን ፈትተው፣ ሌላውን አግተው ነው የያዙት፡፡ ይሄ አደገኛ የፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡
የሀገሪቱ ችግሮች ብዙ እንደመሆናቸው፤ ለኔ የሰሞኑ የእስረኞች ፍቺ ሁኔታ፣ ምኑ ተይዞ ጉዞ ነው የሚሆንብኝ፡፡ ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሌላው ባለስልጣን የሚናገሩት ነገር ለየቅል የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሉት መሰረት፤ ሁሉም ያለቅድመ ሁኔታ ይፈታሉ ብለን ነበር፤ በኋላ ግን ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ጉዳዩን ወደ ኋላ መልሰውታል፡፡ ቅድመ ሁኔታ እንዳለው ነው የነገሩን፡፡ ፍትህ ስርአቱን ተግባራዊ ማድረግ ወደሚል መልሰውታል፡፡ ስለዚህ እኔ ሂደቱን እንድጠራጠር አድርጎኛል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ተፈተው ማየት እንፈልጋለን፡፡
ከለዚህ በመለስም የችግርች ሁሉ እናት የሆነው የዲሞክራሲ ምህዳር መጥፋት፣ የሚቀረፍበትን ሁኔታ የሚያመቻች እርምጃ ሲወሰድ እያየን አይደለም፡፡ ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ካላቸው ፓርቲዎች ጋር መነጋገር አይፈልጉም፡፡ ይሄ ሁሉ ተደማምሮ፣ ለኔ ብዙም የሚታየኝ ተስፋ የለም፡፡ መጀመሪያ ላይ የተናገሩት አጓጊ ነበር፤ በኋላ ግን አጠራጣሪ ነው ያደረጉብን፡፡
ከሰሞኑ መገናኛ ብዙኃንን የሚያሸማቅቅ ንግግርም እየሰማን ነው፡፡ ይሄ ቀልድ አይደለም፡፡ የሚዲያውን ስም እየጠሩ ማሸማቀቅ አዝማሚያዎቹ ሁሉ የማያምሩ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ የብልጣብልጥ ንግግር በማቅረብ የሚደረገው ነገር ብዙም ተስፋ እንዳንጥል እያደረገን ነው፡፡
እገሌ የሚባል ሚዲያ፤ “የድሮ ስርአት ናፋቂ ነው” ይላል፣ “እገሌ ደግሞ የተሰማውን አልዘገበም”፣ “እገሌም ዘፈን አቅርቧል” እየተባለ መገናኛ ብዙኃንን ማሸማቀቅ፤ መጀመሪያ ለኔ በጣም አሳፋሪ ነገር ነው፡፡ የሰውን ተስፋ በዚህ አይነት ማሸማቀቆች፣ ባያጨልሙት መልካም ነው።

---------------

              “ግማሽ እውነት መፍትሄ አይሆንም”
                  አቶ ልደቱ አያሌው

    የፖለቲካ ሰዎችን መፍታት ይጠቅማል፡፡ ምክንያቱም ህብረተሰቡ በዚህ ረገድ ቅያሜ አለው። በሀገሪቱ ውስጥ የሰብአዊ መብትና ሀሳብን በነፃነት የማራመድ መብት እየተረገጠ ያለው አንዱ የፖለቲካ ሰዎችን በማሰር ነው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው፣ ከዚህ አንፃር ጠቃሚ ነው፡፡ ግን ከዚህ በላይ ጠቃሚ የሚሆነው መንግሥት በሀገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞች መኖራቸውን ሲያምን ነው፡፡ አሁን ግን ወንጀል የሰሩ ፖለቲከኞችን ነው የምፈታው እያለ ነው፡፡ ይሄ ማለት የፖለቲካ እስረኞች አሉ ብሎ ለማመን ተቸግሯል ማለት ነው፡፡ ይሄ የተሃድሶ እንቅስቃሴ እውነት ነው ብለን እንድንቀበል ከተፈለገ፣ በሀገሪቱ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ስርአቱ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቷል ልንል የምንችለው፣ መንግስት የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉት በግልፅ ሲያምን ነው፡፡ ለተፈጠረው ችግርም መፍትሄ ያመጣል ብለን እምነት ሊያድርብን የሚችለው፣ ይሄን ሲያምን ነው፡፡ ይሄን አምኖ ካልተቀበለ፣ የተሃድሶ ጉዳይ እውነት ነው ማለት አይቻልም፡፡ እሱ ወንጀል የሰሩ ያላቸው ፖለቲከኞች ስለተፈቱ፣ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግር ይፈታል ማለት አይደለም። አስቀድሞ እነዚህን ሰዎች በወንጀለኛነት ፈርጇቸዋል፡፡ ወንጀል ስለሰሩ ነው ያሰርኳቸው ብሏል፡፡ ይሄ ከሀገሪቱ እውነታ ጋር አይሄድም፡፡
እኔ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው የመንግስት እርምጃ መሆን ያለበት፣ የፖለቲካ እስረኞች መኖራቸውን አምኖ መቀበል ነው፡፡ በነገራችን ላይ የሚሰጡ መግለጫዎችም እርስ በእርስ ይቃረናሉ። በአንድ ወገን፤ መንግስት ለተፈጠሩ ችግሮች “እኔ ኃላፊነት እወስዳለሁ” አለ፤ ይቅርታም ጠይቋል። በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ሰበብ የታሰሩ ሰዎች ወንጀለኞች ናቸው ይላል፡፡ ይሄ ከመንግስት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ወንጀለኛ ናቸው እያለ ዝም ብሎ ቢፈታ፣ ለእኔ ትርጉም የለውም፤ ምንም እንኳ ሰዎቹ መፈታታቸው ቢያስደስትም መንግስት ሳያምን መፍታቱ ዘላቂ ውጤት አያመጣም፡፡
መንግስት መጀመሪያ ፖለቲከኞችን እፈታለሁ ሲል አወጀ፤ ቆየት አለና ደግሞ አጣርቼ ነው የምፈታው አለ፡፡ ይሄ አይነት አካሄድ ለህዝብ ተስፋ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት ባለው ጉዳይ የታሰሩ ሰዎች በሙሉ ይፈቱ ነበር - የህዝቡ ጥያቄ፡፡ እነዚህ ሰዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ነበር መፈታት የነበረባቸው፡፡ በነገራችን ላይ በይፋ የምናውቃቸው ብቻ አይደሉም - ስማቸው የማይታወቅ በርካታ የፖለቲካ እስረኖች አሉ፡፡ ጋዜጠኞችም አሉ፡፡ ኦሮሚያ አካባቢ በኦነግ፣ ሶማሌ አካባቢ በኦብነግ፣ አማራ አካባቢ በአርበኞች ግንቦት 7 … እየተባለ የታሰሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ከዚያም ውጪ የሰራዊቱ አባል የነበሩ ጀነራሎች፤ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ዝግጅት አድርገዋል ተብለው ታስረዋል፡፡ እነ ጀነራል አሳምነው ፅጌ የታሰሩት በዚህ ነው፡፡ በተግባር ያደረጉት ነገር የለም፡፡ በየአካባቢው ደግሞ ሁከትና ብጥብጥ አስነስታችኋል ተብለው የታሰሩ አሉ፡፡ እነዚህንና ሁሉንም፣ ከፖለቲካ ጋር የተገናኙ እስረኞችን መፍታት ያስፈልጋል፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲህ ያሉ ቀልዶችን ግማሽ እውነት እየተነገረ የሚቀመጥ መፍትሄ የትም አያደርስም፡፡ ህገ መንግስቱ፣ የፌደራል አደረጃጀቱ መፈተሸ አለበት፡፡
ጥቂቶችን ከእስር በመልቀቅ፣ የሀገሪቱ ችግር አይፈታም፡፡ ዛሬ ለምንድን ነው የትግራይ ህዝብ ተጠቂ እየሆነ ያለው? የህውሃት የበላይነት በመኖሩ ነው፡፡ “ፅንፈኛው ኃይል” ደግሞ በህውሓትና በትግራይ ህዝብ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ለማየትና ለመፈተሽ አልሞከረም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ክረት እንዲኖር ካደረጉ መካከል ዋናው የህውሓት የበላይነት ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን አምነው መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ይሄን አምነው ሲቀበሉ፣ የትግራይን ህዝብ መታደግ ይችላሉ፡፡ ይሄ የድርጅት እንጂ የትግራይ ህዝብ ችግር አይደለም የሚለውን በግልፅ ማሳየት አለባቸው፡፡ የትግራይ ህዝብ በምን ፍዳው ነው … ድሮ በደርግ፣ አሁን ደግሞ በዚህ ስርአት ተጠቂ ሊሆን የሚገባው? ይሄን የበላይነት አምነው በመቀበል ህዝቡን ሊታደጉት ይገባል፡፡ ህዝቡ መጠቃቱ በየትኛውም መመዘኛ ተገቢ አይደለም፡፡ ህዝቡ በምን እዳው የነሱን እዳ ይቀስዳል? ይሄ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
የኢህአዴግ አመራሮች የፖለቲካ ጨዋታ ነው የሚጫወቱት፤ ግን አላወቁም ይሆናል እንጂ ከዚህ በኋላ ሁለተኛ እድል የላቸውም፡፡ ሙሉ ችግሩን አምኖ፣ ሙሉ መፍትሄ መስጠት እንጂ በጥቂቱ አምኖ፣ ጥቂት መፍትሄ ማስቀመጥ፣ ሀገሪቷን አይጠቅምም፤ ለነሱም አይበጅም፡፡
አቶ ለማ መገርሳ፤ ከልባቸው ይሁን ባላውቅም፤ ሁለት ጠቃሚ ነገሮች ተናግረዋል፡፡ አንደኛ፤ ይሄ የመጨረሻ እድላችን ነው ብለዋል፡፡ ይሄን ሁሉም ድርጅቶች መረዳት አለባቸው፡፡ ሁለተኛው፤ ይሄን ችግር ካልፈታነው ሀገራዊ ህልውናችን ይፈርሳል ነው ያሉት፡፡ ይሄንንም ሁሉም ድርጅቶች በእኩል መረዳት አለባቸው፡፡ አሁን ጥያቄው የፖለቲካ ጥያቄ አይደለም፤ ሀገርን የማዳን ጥያቄ ነው፡፡ አቶ ለማ ሌላው ያሉት፤ “ጉዳያችን ሃገርን ማዳን ነው፣ የማናችንም ስልጣን ገደል ይግባ” ይሄም የሁሉም የኢህአዴግ አባላት እምነት መሆን አለበት፡፡ ግማሽ መፍትሄ ሰጥቶ ለማለፍ መሞከር ውጤት አያመጣም፡፡ የኛን ፓርቲ የማፍረስ ስራ መሰራቱ በራሱ የመድበለ ፓርቲ ስርአተ ለመገንባት ያለው ፍላጎት አነስተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ ኢህአዴግ ወደእነዚህ ለውጥ ካልመጣ ራሱንና ሀገርን ይዞ ነው የሚጠፋው፡፡  


-------------

             “ከውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አዙሪት መውጣት አለብን”
               ኢ/ር ይልቃል ጌትነት

    ኢህአዴግ ወሳኝ እርምጃ ሲወስድ አናየውም፤ የሚወሰደው እርምጃ መሰረታዊ መፍትሄ የሚያስገኝ ሆኖ አይታይም፡፡ እንዲሁ ለፈረንጆችና ለተወሰኑ ሚዲዎች ፍጆታ የሚውል ነው። በባህሪውም ድርጅቱ መሰረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቶ መራመድ የሚችል እንዳልሆነ እያየን ነው። አንዳንዴ ያለውን ነገርም መፈፀም እያቃተው መሆኑን እንመለከታለን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ የለውጥ እንቅስቃሴ የማድረግ አቅም የላቸውም፡፡
ለኔ እንደ ዶ/ር መረራ አይነት መከበር የሚገባቸው ሰዎች፤ መንገላታታቸውና መሰቃየታቸው የሚያሳዝነኝ በመሆኑ፣ መፈታታቸውን በጥሩ አየዋለሁ፡፡ በሀገር ደረጃ በሚያመጣው ለውጥ ላይ ግን ብዙም ተስፋ አላደርግም፡፡ ያን ያህል ፖለቲካዊ ለውጥም አያመጣም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት፤ ለብሄራዊ መግባባትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ አድርገው ነበር፡፡ በኋላ ግን ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፤ በቅድመ ሁኔታ እንደሆነና ሌላ መስፈርትም እንደወጣ ጠቁመው፤ ጥቂቶቹን ነው የፈቱት፡፡
ከዚህ አንፃር፤ ኢህአዴግ ቃል የገባውን ማስፈፀም እየቻለ አይደለም፡፡ ለኔ ኢህአዴግ ውስጥ ትልቅ ችግር እንዳለ ይሰማኛል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ “በምህረት ይፈታሉ” ያሉትን ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፤ በይቅርታ ነው እሱም መስፈርት አለው ብለውናል። ይሄ ታዲያ እንዴት ነው ብሄራዊ መግባባት የሚያመጣው? የኔ ምኞት፤ ሁሉም የሀገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ተቀራርበው፣ ለሀገሪቱ መፍትሄ የሚያስቀምጡበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው፡፡ ከውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አዙሪት መውጣት አለብን፡፡ ህዝቡ በስርአቱ ላይ መሰልቸቱን መረዳት ይቻላል፡፡

-------------

               “ኢህአዴግ የፖለቲካ ጦርነትን ማስረዘም የለበትም”
                 አቶ ጥሩነህ ጉምታ (የኦፌኮ አመራር)

    አንድ ለወደፊት “ታግዬ ስልጣን እይዛለሁ” የሚል ፖለቲከኛ፤በገዥው ፓርቲ የሚወሰድ አበረታች እርምጃዎችን ጥላሸት መቀባት አይገባውም፡፡ ለኛ ዶ/ር መረራ አንድ አባል ብቻ ሳይሆን መሪያችን ናቸው፤ እሳቸውንና ሌሎችን መፍታታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ ይህ የህዝብን ጥያቄ መመለስ መጀመር ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ቅንጭብ እርምጃ፣ ህዝብን ለማዘናጋት የተወሰደ እንዳይሆን ስጋት አለኝ፡፡ ከዶ/ር መረራ በፊት የታሰሩ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ፣ በሶማሌ፣ በቤኒሻንጉልና በሌሎችም ክልሎች፤ በአንድም ይሁን በሌላ፣ የመብት ጥያቄ አንስተው የታሰሩ ይጠቀሳል፡፡
እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ አንዷለም አራጌ፣ እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የመሳሰሉት የፖለቲካ ሰዎችና ጋዜጠኞች አሉ፡፡ ከኛ ውስጥም አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ እነ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ ደረጀ መርጊያ፣ ተስፋዬ ሊበን፣ አዲሱ ቡላላ፣ ጉርሜሳ አያኖ የመሳሰሉት እስር ቤት በስቃይ ላይ ናቸው፡፡ የተሰደዱ አባላትም አሉን፡፡ ወደው አይደለም የተሰደዱት፤ ባይሰደዱ ይታሰሩ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎችም የዚህ እድል ባለድርሻ ቢሆኑ መልካም ነው፡፡ እኔ እስርን ቀምሻለሁ፤ አንድ ቀን በእስር ቤት ማሳለፍ፣ እንደ አንድ ዓመት ነው የሚቆጠረው፡፡ ኢህአዴግም የፖለቲካ ጠላትነትን ከዜጎች ጋር ማስረዘም የለበትም፡፡
ለኢትዮጵያ እድገት ከቻለ አስተባብሮ መምራት፣ ካልቻለ ደግሞ ለሚችሉ ሰዎች በሰላም ለቆ፣ ሀገሪቱን ማዳን አለበት፡፡ እኛ አደረጃጀታችን ብሄራዊ ቢሆንም፣ ለኢትዮጵያ ጥልቅ ፍቅር ነው ያለን፡፡ መንግስት ሁሉንም ፖለቲከኞች መልቀቅ ቢችል የበለጠ መግባባትን እየፈጠረ ይሄዳል እንጂ የሚጎዳው ነገር አይኖርም፡፡ እነዚህ ሰዎች የማንንም ንብረት አልዘረፉም፣ ሴት አልደፈሩም፣ ሰው ነፍስ አላጠፉም፤ ስለዚህ የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት ማመንታት አይገባም፡፡  

Read 3587 times