Saturday, 28 April 2012 12:22

አሜሪካና አውሮፓ - ከኢኮኖሚ ቀውሱ በኋላ!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

የአለምን ኢኮኖሚ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ነገሬ ብለው በጥሞና ሲከታተሉ የነበሩ ባለሙያዎች የ2008 ዓ.ም ሁኔታ ጨርሶ አላማራቸውም ነበር፡፡ እናም የአለምን የኢኮኖሚ መዘውር በዋናነት ይዘውሩት ለነበሩት የተለያዩ ሀገራት የሀገራችን ሰው “አያ በሬ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” እያለ እንደሚተርተው፣ የአለም ኢኮኖሚ ለምለሙን ሳር ብቻ በማየት ወደ ገደሉ እየተጣደፈ እንደሆነ የሚያስገነዝብ የማስጠንቀቂያ ደወል አሰምተው ነበር፡፡

ነገር ግን ይህ የማስጠንቀቂያ ደወላቸው ያጋጠመው እጣ “ፈላስፋዎቹ የትንሳኤ ቀኑ ያልደረሰ እውነት” የሚሉት አይነት ነበር፡፡ ከአሜሪካ እስከ ድፍን አውሮፓ ድረስ ጉዳዬ ብሎ ጆሮውን የሚሠጠው ሀገር ማግኘት ሳይቻለው ቀረ፡፡

ይልቁንም የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ እንደ ክፉ መርዶ አርጂና የምጽአት ቀን ሟርተኛ ተቆጥረው በአራቱም ማዕዘን ከትልቁ ፕሬዚዳንት እስከተራው ሰራተኛ ድረስ የውግዘት ናዳ ወረደባቸው፡፡

የፈረንጆቹ 2008 ዓ.ም ተፈጽሞ አዲሱ 2009 ዓ.ም ገና የአንድ ወር እድሜውን እንኳ ሳይደፍን እንደ ካብ ላይ እባብ አድፍጦ ሲያደባ የነበረው የኢኮኖሚ ቀውስ ድፍን አለሙን ድንገት ሳያስበው አንገቱ ላይ ተጠመጠመበት፡፡ ከሁሉም ሀገራት በተለየ አሜሪካንንና አውሮፓን የያዛቸው ጨርሶ ሳይታጠቁና እርቃናቸውን ሳሉ ነበር፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥም ቢሆን የኢኮኖሚ ቀውሱን በድንገት እንደመጣና በድንገት እንደሚያልፍ የአንድ ሰሞን አነስተኛ እንቅፋት እንጂ ዲካውንና ሰንቆት የመጣውን የጥፋት መጠን በትክክል ለመረዳትና የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ የተጣደፈ ፖለቲከኞች “ባለ ድርሻ አካል” እያሉ የሚገልፁት የጉዳዩ ዋነኛ ተዋናይ የሆነ አካል አልነበረም፡፡

የየሀገራቱ መሪዎችና ፖለቲከኞች፣ ችግሩን የንግዱ ማህበረሰብ በአፋጣኝ ይፈታዋል በሚል በግማሽ ልብ ሆነው ችላ ሲሉት፤ የንግዱ ማህበረሰብ ደግሞ በፈንታው ቀውሱን መንግስትና ፖለቲከኞች ለራሳቸው ሲሉ የደረሰውን የኢኮኖሚ ቀውስ ይፈቱታል በሚል ነገር አለሙን ሁሉ ቸል ብለው ህይወታቸውን እንደቀድሞአቸው መምራት መቀጠል ላይ አተኮሩ፡፡

አንገታቸው ላይ ድንገት አድብቶ የተጠመጠመው የኢኮኖሚ ቀውስ እባብ፤ ሁሉም እንዳሰቡትና ተስፋ እንዳደረጉት ጭራውን አሊያም አንገቱን በቀላሉ ተይዞ የትሜናው የሚወረወር ተራ እባብ ሳይሆን፤ በተናጠልም ሆነ በአንድነት ሰብስቦ የመዋጥ ታላቅ አቅም ያለው ዘንዶ መሆኑን ማሳየትና ግዳዩን እየጣለ ማስቆጠር የጀመረው አንዲትም ደቂቃ እንኳ ሳያባክን ነበር፡፡

አሜሪካኖች ከዚህ እጅግ ሀይለኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ዘንዶ ጋር ፊት ለፊት የተገጣጠሙትና የጉልበቱንም ሃያልነት አይተው በፍርሃትና በጭንቀት ጉልበታቸውን ብርክ የያዘው፤ ዘንዶው ለዘመናት የኢኮኖሚ ሃያልነታቸው ዋነኛ ምልክቶች የሆኑትንና በግዙፍነታቸውም የተነሳ መቸም ቢሆን ጨርሶ ሊወድቁ አይችሉም ይባሉ የነበሩትን ታላላቅ የገንዘብና የማምረቻ ተቋሞቻቸውን እንደ ተራና ከሲታዋ ጥጃ በቀላሉና በብርሃን ፍጥነት እንደሠለቀጠባቸው ነበር፡፡

እነዚያ ግዙፍ ታላላቅ የገንዘብና የማምረቻ ተቋማት፤ ተራ በተራ በዘንዶው ፊት አይሆኑ ሲሆኑ ሁኔታውን በቅርብም ሆነ በሩቅ የታዘበው ህዝበ አዳም በከፍተኛ መገረም ራሱን ይዞ “አጃኢብ ነው” ሲል ከዚህ በፊት እከሌ ይፈታዋል በሚል አንዱ ባንዱ ላይ ሀሳቡን ጥሎ የነበረው ሁሉ አቅሉንና ጨርቁን ጥሎ ከወዲያ ወዲህ እንደ ጥንቸል መራወጥ የጀመረው ወዲያውኑ ነበር፡፡

ያኔ የደረሠው የኢኮኖሚ ቀውስ በትሩ እጅግ ረጅምና ህመሙ ልብን የመንሳት አቅም ያለው ነበር፡፡ ይህ የቀውስ በትር አሜሪካንን ሲመታ በርህራሄ የተወላት ቦታና የህብረተሠብ ክፍል ጨርሶ አልነበረም፡፡ ይግረማችሁ ያለ ይመስል በትሩን ያለ አንዳች ፋታና ርህራሄ በጭካኔ ያሳረፈባቸው፣ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ባላቸው የአሜሪካ ዜጐች ላይ ነበር፡፡

የተለያዩ አምራችና አገልግሎት ሠጪ የነበሩ የአሜሪካ ተቋማት፣ የኢኮኖሚ ቀውሱ ሲያንኮታኩታቸው፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሠራተኞቻቸው በአንዲት ጀምበር ስራ አጥ ሆነው ሜዳ ላይ ተበተኑ፡፡ ላለመውደቅ ይውተረተሩ የነበሩት ደግሞ እንደዚሁ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቻቸውን ለመቀነስ ተገደዱ፡፡ እንደ ሌሎቹ የንግድ ግንባታና ሽያጭ ታላላቅ ተቋማቱን ሲውጣቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ጉዳታቸው ተደራራቢና በእንቅርት ላይ ዶሮ ደግፍ የምንለው አይነት ነበር፡፡

የኢኮኖሚ ቀውሱ በትር በጭካኔ ከመታቸው ሀገራት እንደ አሜሪካ ሁሉ በዋናነት አውሮፓም ተጠቀሽ ናት፡፡ እንደ አሜሪካ ሁሉ አውሮፓውያንም የማስጠንቀቂያውን ደወል ለመስማትና የመፍትሄ እርምጃዎችን በወቅቱና በፍጥነት ለመውሰድ እጅግ ዳተኞች ነበሩ፡፡ የመፍትሄ ሀሳቡን ለማመንጨትና እርምጃውን ለመውሰድም አንዳቸው አንዳቸውን በመተማመን አገር አማን ብለው ተኝተው ነበር፡፡

አውሮፓውያኑ ከዚህ እንቅልፋቸው ሲነቁ ራሳቸውን ያገኙት የኢኮኖሚ ቀውሱ ዘንዶ ከእግራቸው እስከ አንገታቸው ድረስ ያለውን አካላቸውን ውጦ፣ ጭንቅላታቸውን ሠልቅጦ ሊገላግላቸው ሲታገል ነበር፡፡ የዚህን የኢኮኖሚ ቀውስ የጥፋት በትር ለመግለጽ በሚያስቸግር ሁኔታ የከፋባቸው በዋነኛነት ግሪክ፣ ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ አየር ላንድ፣ ጣሊያንና አይስላንድ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሀገራት ውስጥ ይበልጥ በችግሩ ክፉኛ ተደቁሳ በሞትና በህይወት መካከል ሆና የምታጣጥረው ግሪክ ናት፡፡

ግሪክ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ያዩ ሁሉ “ይናገራል ፎቶ” እንደሚባለው የድሮ የስልጣኔና የፍልስፍና ፈር ቀዳጅና የአለም ቀንዲልነቷን ለታሪክና ለትዝታ ትታ አሳዛኝ አሟሟት የሞተች ሀገር ሆናለች ይሏታል፡፡ ይህ አባባል ትንሽ የየጭካኔ ቃና ቢኖረውም ምንም አይነት ማጋነን የለበትም፡፡ ግሪካውያን እንደ ህዝብም ሆነ እንደ ሀገር አለን ብለው ራሳቸውን ለመቁጠር በረጅም ዘመን ታሪካቸው በእጅጉ የተቸገሩበት ጊዜ ቢኖር  የአሁኑ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በትንንሽ ሀገራት ብሔራዊ ክብሯ የተዋረደባትና መዘባበቻ የሆነችበት፣ ከገባችበት የቀውስ ማጥ እንዲያላቅቋት አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራትን እርቃንዋን ተንበርክካ፣ የእግራቸውን ጫማ የሳመችበትና ክብረ ነክ ለሆኑ የተለያዩ ተረቦችና ቀልዶች የተጋለጠችበት የታሪክ ጊዜ ቢኖር የአሁኑ ጊዜ ብቻ ነው፡፡

በአውሮፓ የአራተኛው ትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤት ናት የምትባለው ስፔንም እንደ ግሪክ አይሁን እንጂ የኢኮኖሚው ቀውስ ያደረሠባት መመሠቃቀል እንዲህ በቀላሉ የሚወራ አይደለም፡፡ ይህ ቀውስ በሥራ አጥ ዜጐቿ ቁጥር ከአውሮፓ ብቻ ሳይሆን ከአለም ግንባር ቀደምት ሀገራት ጐራ ውስጥ እንድትሠለፍ አድርጓታል፡፡ ከጠቅላላው የዜጐቿ ቁጥር ሀያ ሶስት በመቶ የሚሆኑት ቀውሱ ለስራ ፈትነት ዳርጓቸዋል፡፡ በጣሊያን፣ በፖርቹጋል፣ በአየርላንድና በአይስላንድ የተከሰተው የኢኮኖሚ ምስቅልቅል ከመጠን ልዩነት በቀር በይዘቱ ከግሪክ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

የሆኖ ሆኖ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአውሮፓ ሀገራት ዜጐች ተነግሮ ለማያልቅ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስ ተዳርገዋል፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት የራሳቸውንና የቤተሠባቸውን ህይወት ለማቆየት፣ ከቆሻሻ መጣያ ገንዳዎች ላይ የተጣሉ ምግቦችን በመፈለግ እያንዳንዱን እለታቸውን ያሳልፋሉ፡፡ ይህንን እጅግ አስቸጋሪ የእለት ተዕለት የህይወት ፈተና ለመጋፈጥና ለመቋቋም አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ አቅም ያጡት ራሳቸውን በማጥፋት ከአስቸጋሪውና ከአስጨናቂው የህይወት ፈተና ተገላግለዋል፡፡

እንግዲህ ህዝቦቻቸው ለእንዲህ አይነት ችግርና ፈተና የተጋለጡባቸው የአሜሪካም ሆነ የአውሮፓ መንግስታት፣ ምንም እንኳ ዘግይተውም ቢሆን የመፍትሄ እርምጃ በመውሰድ ከችግሩ ለመላቀቅ በየበኩላቸው ጥረት አድርገዋል፡፡ ከባዱ የኢኮኖሚ ቀውስ ባስከተለባቸው ፈርጀ ብዙና ተደራራቢ ችግሮች አውሮፓና አሜሪካ ተመሳሳይ ቢሆኑም ለመፍትሄነት በወሠዷቸው የኢኮኖሚ እርምጃዎች ግን በእጅጉ የተለያዩ ናቸው፡፡ በዚህ የተለያየ የመፍትሄ እርምጃዎቻቸውም የኢኮኖሚ ባለሙያዎችንና የፖለቲከኞችን ብቻ ሳይሆን የመላውን አለም ቀልብና ትኩረት መሳብ ችለዋል፡፡

የአሜሪካ መንግስት ያጋጠመውን ታላቅ የኢኮኖሚ ቀውስ ለመቋቋምና ብሎም ለመቀልበስ የተጠቀመበት ሥልት የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ዘዴ ሲሆን የአውሮፓ መንግስታት የተጠቀሙበት ዘዴ ደግሞ ከአሜሪካ ተቃራኒ ነው፡፡ የአሜሪካ መንግስት በኢኮኖሚ ቀውሱ ሳቢያ ለከፍተኛ የገንዘብ እጥረት የተዳረጉት የቢዝነስ ተቋማት ሁሉ የማምረትና የአገልግሎት ስራቸውን ለማስቀጠል፣ ባጠቃላይ ቀውሱ ያኮማተረውን የሀገሪቱን ጠቅላላ ኢኮኖሚ ከተኮማተረበት እንዲፍታታ በማሰብ፣ በመቶ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ በኢኮኖሚው ውስጥ በማፍሠስ እንዲነቃቃና እድገት ማስመዘገብ እንዲችል ለማድረግ በእጅጉ ጥሯል፡፡

በአስቸጋሪ ጊዜ የፕሬዚዳንትነቱን ስልጣን የተረከቡትና ከሳቸው በፊት የነበሩት ፕሬዚዳንት አፈር ድሜ ያስጋጡትን ኢኮኖሚ የወረሱት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ ይህን የኢኮኖሚ ማነቃቂያ እርምጃ ሲወስዱ በሁሉም ዘንድ አበጀህ ተብለው አልተወደሱም፡፡ ከላይ እስከ ታች የእርግማንና የውግዘት መአት አስተናግደዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ የውግዘት መአት ቢወርድባቸውም ቅሉ ግን ከአቋማቸው አላፈገፈጉም፡፡ ሳያወላውሉ በከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ለተመታው የሀገራቸው ኢኮኖሚ ከፍተኛ ገንዘብ አቀረቡለት፡፡

መቸም በንግድ የደም ስር ውስጥ የሚዘዋወረው ደም ገንዘብ ነውና በገንዘብ እጥረት ተሽመድምዶ የነበረው የአሜሪካ ኢኮኖሚ ከቀን ቀን የተኮማተረው የደምስሩ እየተፍታታ፣ በገንዘብ እጥረት የተነሳ መላወስ አቅቶት የነበረው አካሉ እየተነቃቃ እጆቹና እግሮቹ መላወስ ጀመሩ፡፡ ቀን አልፎ ቀን ሲተካ ደግሞ በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ተውጦ የነበረው የንግዱ ማህበረሰብም ሆነ ጠቅላላው የአሜሪካ ዜጋ የተስፋ መቁረጡ ስሜት እየቀነሰ በዋሻው ጫፍ ላይ የብርሃን ጭላንጭል መፈንጠቅ ጀመረ፡፡

እርግጥ ነው የኢኮኖሚው ቀውስ የፈጠረው ምስቅልቅል፤ መሠረቱ ጥልቅ ስፋቱም የትየለሌ ስለሆነ ግብግቡ ገና ተጀመረ እንጂ ጨርሶ አልተጠናቀቀም፡፡ ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት ኦባማ የወሰዱት የኢኮኖሚ ማነቃቂያ እርምጃ፣ ፍጥነቱና መጠኑ የልብ አድርስ ባይሆንም ውጤት ማሳየቱን ግን ቀጥሏል፡፡ ዛሬ የአሜሪካንን ኢኮኖሚ በማስመልከት የሚቀርቡ ዘገባዎች በጉድለትና በጐዶሎ ቁጥሮች ሳይሆን በእድገትና በጭማሪ ቁጥሮች የተደገፉ መሆን ጀምረዋል፡፡ መነቃቃት የጀመረው ኢኮኖሚ ከወር ወር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ የስራ እድሎችን መፍጠር ጀምሯል፡፡ ይህ ደግሞ ከሶስት አመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሰማት የቻለ አሪፍ ዜና ነው፡፡

በአሜሪካ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከምንም አይነት ጉዳይ ይልቅ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው የኢኮኖሚ ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል ነው፡፡ ለአሜሪካኖች ከገንዘብ መያዣ ቦርሳቸው የበለጠ ምንም አይነት አንገብጋቢ ጉዳይ የላቸውም፡፡ እናም የትኛውም ፕሬዚዳንት እንደ ቀድሞው ፕሬዚዳንት እንደ ጆርጅ ቡሽ አይነቱም ቢሆን ያን የገንዘብ ቦርሳ በዶላር መሙላት ብቻ የዋይት ሃውስ ቤተመንግስትን ቁልፍ በቀላሉ መረከብ የሚችልበት እጅግ ሠፊ እድል አለው፡፡

የቀጣዩ ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪዎች በኢኮኖሚው ድቀት የተነሳ ባራክ ኦባማን በቀላሉ ማሸነፍ እንደሚችሉ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋ አድርገው ህዝቡም ተመሳሳይ ግምት ነበረው፡፡ አሁን ግን ይህ ተስፋና ግምት ከበፊቱ ቦታው ላይ የለም፡፡

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ብዙ የተተቹበትና የተወገዙበት የኢኮኖሚ ማነቃቂያ እርምጃቸው ያነቃቃው የአሜሪካንን ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ለሁለተኛ ጊዜ በፕሬዚዳንትነት የመመረጥ እድላቸውንም ጭምር ነው፡፡

የተጋረጠባትን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመቋቋም አሜሪካ የወሰደችው የኢኮኖሚ ማነቃቂያ በቀላል አቀራረብ ሲገለጽ፤ ኢኮኖሚው የጐደለውን ነገር ማሟላት ማለት ነው፡፡ የአሜሪካ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ የተመታው በፋይናንስ ቀውስ ስለነበር የባራክ ኦባማ መንግስት ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው በማስገባት እንዲነቃቃ ለማድረግ ችለዋል፡፡

በሌላ በኩል ወደ አውሮፓ ስንመጣ የምናገኘው ታሪክ ከአሜሪካ በእጅጉ የተለየ ምናልባትም ተቃራኒውን ነው፡፡ እንደ አሜሪካ ኢኮኖሚ ሁሉ የአውሮፓ ኢኮኖሚም በከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ ተመቷል፡፡

የአውሮፓ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችና መንግስታት ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል ብለው የቀየሱትና የወሰዱት እርምጃ፣ ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ በማስገባት ማነቃቃት ሳይሆን ይልቁንም ቀበቶን የማጥበቅና የመንግስትን ወጪ የመቀነስ እርምጃ ነው፡፡

በዚህም መሠረት በቀውሱ የተመቱት የአውሮፓ ሀገራት፤ የትምህርት የጤና የማህበራዊና የሌሎች አገልግሎቶች በጀታቸውንና ወጪዎቻቸውን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሰዋል፡፡ የችግሩ ግንባር ቀደም ተጠቂ የሆነችው ግሪክ የወሰደችው እርምጃ ከዚህም በላይ ነው፡፡ የመንግስት ሠራተኞችን ከስራቸው ብቻ ሳይሆን ደመወዛቸውንም በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሳለች፡፡

የጡረታና ሌሎች ክፍያዎችንም ጭራሹኑ የሌሉ ያህል ጐምዳለች፡፡ የጤናና የሌሎች መንግስታዊ የማህበራዊ አገልግሎቶችን ጨርሶ የመዝጋት ያህል ቀንሳለች፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የስራና የገቢ ግብርን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምራለች፡፡ የወጪ ቅነሳ እርምጃው የትኛውን የኢኮኖሚ ዘርፍ እንደሚምርና መቼ እንደሚያበቃ፣ እንኳን እኛ ግሪካውያን ራሳቸውም አያውቁትም፡፡ የግሪክ መንግስት እየወሰደ ያለው የቀበቶን ማጥበቅ እርምጃ ለግሪካውያን ከሚችሉትና ከሚቋቋሙት በላይ ሆኖባቸዋል፡፡ አብዛኞቹ ግሪካውያን አሁን የሚያጠብቁት ቀበቶ የላቸውም፡፡ እናም ተቃውሞአቸውን የሚገልጹት አደባባይ በመውጣት ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን በመግደል ጭምር ሆነአል፡፡  የዚህ እርምጃ ሌላው አስጨናቂ ነገር ይህ ሁሉ አይነት እርምጃ ተወስዶ ኢኮኖሚው ይበልጥ እየደቀቀ እንጂ አንዳች አይነት የመሻሻል ፍንጭ ማሳየት አለመቻሉ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ለመረዳት ደግሞ የኢኮኖሚ ጠቢብ መሆን ጨርሶ አይጠበቅብንም፡፡ ሁሉም አይነት የገቢ ምንጮቹ በመንግስት የተወሰዱበት ሰው፤ መንግስት መልሶ የጫነበትን ግብርና ታክስ ከየት አምጥቶ መክፈል ይችላል? ሁሉም አይነት የገንዘብ እንቅስቃሴ የተገደበበት ኢኮኖሚ በየትኛው የገንዘብ የደም ዝውውር ነፍስ ዘርቶ መንቀሳቀስና መነቃቃት ይቻለዋል?

ይህን ሁኔታ በጥሞና የተከታተለው እውቁ አሜሪካዊ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ ተንታኝ ስቴፋን ሬክተር፤ “ትራጀዲ የሚለው ቃል የግሪክ ቃል ነው፡፡ የግሪክ ኢኮኖሚስቶችም ዛሬ ራሳቸው ትራጀዲ ሆነዋል፡፡ ትራጀዲ የሆነውን የሀገራቸውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመፍታት ያቀረቡት የመፍትሔ ሃሳብ በራሱ ታላቅ ትራጀዲ ነው፡፡” በማለት በትረባ አሽሯቸዋል፡፡ እናንተ ምን እንደምትሉ አላውቅም እንጂ እኔ የስቴፋን ሬክተር አባባል ትክክል ነው እላለሁ፡፡ በትንፋሽ እጥረት የተነሳ ሊሞት የሚያጣጥርን ሰው አፉን ማፈን ከቶ በምን አይነት መስፈሪያ መፍትሔ ነው ተብሎ መቆጠር ይችላልን? የግሪክ የገንዘብ ሚኒስትር የሆኑት ኢቫንጀሎ ቬኒዚሎስ፣ ቀደም ብለው ስልጣናቸውን ከለቀቁት አለቃቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ፓፓንድሪው ጋር ለሠአታት ሲወዛገቡ ቆይተው ወደቢሮአቸው ሲመለሱ፣ በብርጭቆ ውሃ ላቀረበችላቸው ረዳታቸው በስጭት ብለው የነገሯት እንዲህ ብለው ነው፡- “አየሽ እስታቭሩላ … አሁን አሁን የኢኮኖሚው ቀውስ የደቆሰው የሀገራችንን ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የእኛን የማሰብ ችሎታም ጭምር እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ጀምሬአለሁ፡፡” ግሪኮችን በተመለከተ እኔም የማስበው ልክ እንደእሳቸው ነው፡፡

 

 

Read 2816 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 12:32