Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 28 April 2012 12:32

ችሎት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ዜጐች በከሳሽነትም ይሁን በተከሳሽነት ወይም ደግሞ በምስክርነት ፍ/ቤት የሚቀርቡበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡ በተለይ ተከሳሽ ሆነው ሲቀርቡ ስለ ፍ/ቤቱ አሰራርና ሂደት እንዲሁም ስለ አጠቃላይ ህጉ መጠነኛ ግንዛቤ ከሌላቸው አለመግባባት የሚከሰቱባቸው ሰፊ ክፍተቶች ይፈጠራሉ፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ዳኛ የገጠማቸውን ሲነግሩኝ፤ ተከሳሽ አባወራ ጐረቤቱን ይገድለውና ይከሰሳል፡፡ ፍርድ ቤት ቀርቦም ድርጊቱን አልፈፀምኩም ሲል ይከራከራል፡፡ ድርጊቱን ላለመፈፀሙ ዳኛው  “መከላከያ አለህ?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡ የመከላከያ ምስክር አለህ ለማለት ተከሳሽም “አዎን” ይላል፡፡

“አስመዝግብ”

“ቤት ነው ያለው”

“ምንድነው?”

“ጠመንጃ” በመጨረሻም ዳኛው “መከላከያ” ምን ማለት እንደሆነ ካስረዱ በኋላ ችሎቱ ቀጥሏል፡፡ ዳኞቹ ከተከሳሾች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት በመግባባት የተሞላ እንዲሆን የቱን ያህል ይጥራሉ? እና ሌሎች ከዳኝነት ሙያ ጋር የተያያዙ ጥቂት ጥያቄዎች በመያዝ ወደ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ የከባድ ወንጀል ችሎት የሄደችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው፤ ችሎቱ ላይ የሚሰየሙትን ሦስት የረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸው ዳኞች አነጋግራለች፡፡ እነዚህ ዳኞች በሽብርተኝነት የተከሰሱትን የእነውብሸት ታዬን፣ የእነ አንዱአለም አራጌንና ሌሎችም ጉዳዮችን የመረመሩ ናቸው፡፡

“ዋናው ጥንቃቄ የዳኞች አሿሿም ላይ ነው”

በህግ የማስተርስ ድግሪ ያላቸው አቶ ሁሴን ይመር፤ ከ1995 እስከ 96 ዓ.ም በከፍተኛ ፍ/ቤት በረዳት ዳኝነት የሰሩ ሲሆን፤ በመቀጠል በመጀመርያ ደረጃ ፍ/ቤት ዳኛ በመሆን አገልግለዋል፡፡ አቶ ሁሴን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ ከፍተኛ ፍ/ቤት የተዛወሩ ሲሆን በ3ኛ የከባድ ወንጀል ችሎት የግራ ዳኛ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ከተከሳሾች ጋር ያላችሁ ግንኙነት የሰመረ እንዲሆን የምታደርጉት ጥረት ምን ይመስላል?

አንድ ተከሳሽ ፍ/ቤት ሲቀርብ በህገመንግስቱ የተቀመጡ የተከሳሽነት መብቶች አሉ፡፡ ያ ሊከበርለት ይገባል፡፡ ፍ/ቤት ቀርቦ ያለፍርሃት መስተናገድ አለበት፡፡ ምክንያቱም በፍርሃት የተነሳ ስማቸውም የሚጠፋቸው አሉ፡፡ እነሱ በደንብ መከራከር አይችሉም፡፡ በደንብ ቀርቦ ካልተከራከረ የመደመጥ መብቱ በተዘዋዋሪ ይጐዳል፡፡ የመደመጥ መብት ከተጐዳ ደግሞ ትክክለኛ ፍትህ ላይ ለመድረስ ትልቅ መሰናክል ነው፡፡ ስለዚህ ከታራሚዎች ጋር ያለው ግንኙነት የሰመረ እንዲሆን ልምድ ያላቸውን ዳኞች መመደብ ያስፈልጋል፡፡ ዳኞች ችሎት የሚያስተናግዱበት መንገድ ከልምድ የተገኘ ስለሆነ የተከሳሹን መብት ባላጠበበ መልኩ፣ ሳይፈራ ነገር ግን ፍ/ቤቱን አክብሮ ጉዳዩን የመግለፅና የማሰማት መብቱን እንዲጠበቅ አድርጐ መናገር እንዲችል ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ ሆስኒ ሙባረክ ሲዳኙ አይተናል፡፡ የግብፅ ፍ/ቤት ሁካታ ይበዛዋል፡፡ በሌላ በኩል የአሜሪካኖች ደግሞ ፀጥታው የተጠበቀ ነው፡፡ እኛም አገር እንዲህ መሆን አለበት፡፡ ሁካታን ፈጥሮ ተከሳሹ መስተንግዶን እንዳያገኝ የሚያደርግ ደረጃ ላይ መድረስ የለበትም፡፡ በተቻለ መጠን የዳኝነት ሥራ ስናከናውን ተከሳሾች ፍ/ቤቱን አክብረው ያለ ፍርሃት መናገር የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን፡፡

ዳኞችን ለሙስና ሊያጋልጧቸው የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው?

የዳኛውን ለሙስና ተጋላጭነት የሚወስነው ባህርይው ነው፡፡ መኪና፣ ቤት፣ ገንዘብ ቢሰጠው ባህርይው እስከሆነ ድረስ ለሙስና ተጋላጭነቱን ሊለውጠው አይችልም፡፡ ሙስና ሥነልቦናዊ የሆነ ነገር ነው፡፡ ከአስተዳደግ እና ከሌሎች ከብዙ ነገሮች ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ ጥቅማጥቅሞችን በማሟላት ብቻ ሙስናን ማጥፋት አይቻልም፡፡ ነገር ግን የተወሰነ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል፡፡ አምስት በመቶም ብትሆን ዳኞችን ከችግር ሊታደግ ይችላል፡፡ ሆኖም ዋናው ጥንቃቄ መደረግ ያለበት የዳኞች አሿሿም ላይ ነው፡፡ ተጠንቅቆ መሾም ያስፈልጋል፡፡

በሥራችሁ ላይ ጫና ደርሶባችሁ ያውቃል … ከመንግስት ወይም ከግለሰብ?

ጫና ሲባል ብዙ ሰው ከመንግስት ብቻ ነው የሚጠብቀው፡፡ ነገር ግን ከግለሰብ ጫና ሊደርስ ይችላል፡፡ በገንዘብ ተፅዕኖ ፈጥሮ ዳኛው እማይገባ ነገር ከሰራ ጫና አድርሷል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ለእንዲህ ዓይነት ጫና የማይገዙ ዳኞችን መፍጠር ይገባል፡፡ ከመንግስት የሚደርስ ጫና አለ ወይ ለተባለው እዚህ የምንሰራው ሦስታችን ነን፡፡ እራሳችን ተነጋግረን እራሳችን ነን የምንወስነው፡፡ መንግስት በማንም ጣልቃ ሳይገባ በሦስታችን ብቻ የሚወሰን ነው፡፡ የሥራ ጫና ግን አለ፤ ሆኖም በተገቢው መንገድ እየሰራን ነው ያለነው፡፡ እያንዳንዱን ሁኔታ በጥንቃቄ መስማትና ማየት ያስፈልጋል፡፡ ችሎቱ የከፍተኛ ወንጀል ስለሆነ በወር ምናልባት 500 መዝገቦችን እናያለን፡፡ ይሄ ከፍተኛ ቁጥር ነው፡፡

ገጠመኝ…

የዛሬ ሶስት አራት አመት አካባቢ ነው፡፡ አሮጊት ሴትዮ ተከሰው ቀርበው ችሎት ላይ ውሳኔውን አነበብኩላቸው፡፡ ክሳቸው ተፈርዶላቸው “የወጪ ዝርዝር ማቅረብ ይችላሉ” ስላቸው ሴትየዋ ወጣች፡፡ አሮጊቷ ቆመው ቀሩ፡፡ ይሄኔ “ሳልደመጥ” አሉ “ተፈርዶሎታል፤ የወጪ ዝርዝር አቅርቡ ነው ያልኩት” አልኳቸው፡፡ የጆሮ ችግር አለባቸው መሰለኝ “ይግባኝ እላለሁ” አሉ፤ ከኋላቸው የነበረ ሰው “ለእርሶ እኮ ነው የተፈረደው” ይላቸዋል፡፡ “ለእኔ” አሉና እልልታቸውን አቀለጡት፡፡

 

 

==========“የዳኝነት ሙያ በራሱ ለሙስና ያጋልጣል ብዬ አላምንም”

 

በህግና በኧርባን ፕላኒንግ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን የያዙት አቶ እንደሻው አዳነ፤ በደቡብ ክልል በከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንትነት ለአምስት ዓመት አገልግለዋል፡፡ በዳኝነት ለአስራ አምስት አመት የሰሩት አቶ እንደሻው፣ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ፍ/ቤት የ3ኛ ከባድ ወንጀል ችሎት ሠብሳቢ (የመሃል) ዳኛ ናቸው፡፡

ከተከሳሾች ጋር ያላችሁ ግንኙነትና መግባባት ምን ይመስላል?

በችሎቱ የሥራ ጫና ቢኖርም ታራሚዎችን በቅንነት ነው የምናስተናግደው፡፡ ይሄ አሰራር በሌሎችም ችሎቶች ይኖራል የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ ፍ/ቤቱ ውስጥ የሚመጣ ማንኛውም ተገልጋይ የሚፈልገውን አግኝቶ እንዲሄድ ከተፈለገ አገልግሎቱን ከሚሰጠው ጋር በቀላሉ መግባባት አለበት፡፡ ቋንቋ አስተርጓሚ እንደሚመደበው ሁሉ ምን እንደተባለ፣ ዳኛው በትክክል ሊረዳ ይገባል፡፡ ተከሳሹም እኛ የሰጠነውን ውሳኔ በሚገባ እንዲረዳ እንፈልጋለን፡፡ የሰጠነውን ውሳኔ በትክክል መዝኖት ተገቢ ነው ካለ ሊቀበለው፤ ተገቢ አይደለም ካለ ይግባኝ ማለት እንዲችል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከከሳሹ ወይም ከተከሳሹ ጋርም ቢሆን የሚኖረን ግንኙነት የሚፈልገውን መልዕክት በትክክል አስተላልፎልኛል ወይም የጠየቀውን ዳኝነት በትክክል ተረድቼዋለሁ አልተረዳሁትም የሚለውን ለማወቅ ስለሚረዳ ነው፡፡ ተገልጋዩ በፍ/ቤት የሚፈልገውን አገልግሎት በትክክል ማግኘት የሚችለው ዳኛው በትክክል ሲረዳው ነው፡፡ በፅሁፍ ሲሆን እንኳን አማክሮ ስለሚመጣ ብዙ ችግር የለውም፡፡ በቃል ሲሆን ግን ሊከብድ ይችላል፡፡ በተለይ ተከሳሹ ታራሚው በሚሆን ጊዜ እያንዳንዱን ጉዳዩን ባለመረዳት የሚሰጥ ቀጠሮ በሰውየው ላይ እስር የሚያሰጡ ናቸው፡፡ ተከሳሹ ጉዳዩን በሚገባ መረዳትና ማስረዳት ሲችል ክርክሩን በአፋጣኝ ለመጨረስ ይረዳል፡፡ ተከሳሽ ወደ ፍ/ቤት እንዳይመላለስም ያደርጋል፡፡

ሰዎች ፍ/ቤትና ዳኞችን ለምንድነው የሚፈሩት?

አንዳንድ ሰዎች ፍ/ቤትን ከንጉሱ ጀምሮ የሚያውቁትን በአስፈሪ ሁኔታ በመሆኑ ፍርድ የሚለውንም ፈረደብኝ፣ ጫነብኝ በሚል መንፈስ ነው የሚቀበሉት፡፡ ለዳኞች የሚሰጡት ክብርም ከፍተኛ ስለሆነ ፍርሃት ያድርባቸዋል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ወደ ሌላ ቢሮ ሲሄድ እንደማይፈራና የጠየቀው ነገር ተፈፃሚነት እንደሚያገኝ እንደሚያውቅ ሁሉ ዳኝነትም ከዛ የተለየ ሥራ አይደለም፡፡ የፍ/ቤትን አገልግሎት ለማግኘት አስቦ እስከመጣ ድረስ ማግኘት እንዳለበት ማወቅ አለበት፡፡ በእርግጥ ፍ/ቤት እንደሌሎች አካባቢዎች መሆን የለበትም፡፡ የፍ/ቤትን ሥርዓት ማስጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ በተረፈ ፍ/ቤቱን አስፈሪ ያደረጉት ነገሮች የመጡት ከቀድሞ ዘመን ነው፡፡

ዳኞች ለሙስና የተጋለጡ እንዳይሆኑ ምን መደረግ አለበት? - የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ በማሟላት ሙስና እንዳይዘፈቁ ማድረግ ይቻላል ብለው ያምናሉ?

አይቻልም፤ አንዴ ብልሹ የሆነን ሰው ማስተካከል ከባድ ነው፡፡ ለዳኝነት ሲመለመል እንደዚህ አይነት ባህሪ የሌለበትን እጩ መምረጥ ነው የሚሻለው፡፡ በእርግጥ ዳኞች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሁሉ ማሟላት ተገቢ ነው፡፡ ሆኖም በተለይ ዳኛ ሆኖ የተሾመ ሠው እነዛ ጥቅማ ጥቅሞች አልተሟላልኝም ብሎ ሙስና ውስጥ ይገባል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ግን መሟላታቸው በራሱ የሚያመጣቸው ጠቀሜታዎች አሉ፡፡ ዳኛውን ለሙስና የሚያጋልጠው ከራሱ ከዳኛው ባህሪ ጋር የተያያዘ ነገር ነው፡፡ በተረፈ የዳኝነት ስራ እንደማንኛውም ሙያ አገልግሎት መስጠት እስከሆነ ድረስ ስራው በራሱ ለሙስና ያጋልጣል ብዬ ግን አላስብም አላምንም፡፡

በሥራችሁ ላይ ጫና ደርሶባችሁ ያውቃል?

በራሱ ችሎቱ ከባድ ወንጀል ችሎት ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ እነዛ ጉዳዮች ሊታዩ የቻሉት ለነዚያ ጉዳዮች ተብሎ መንግስት ችሎት አቋቁሞ አይደለም፡፡ ማንኛውንም ተራ ውንብድና ሳይቀር የሚታይበት ነው፤ ስለዚህ ችሎቱ ከባድ ወንጀል ችሎት በመሆኑ እንጂ ለተለዩ አገራዊ ጉዳዮች ብቻ ተብሎ የተደራጀ ችሎት የለም፡፡ ይሄ ችሎት ቀደም ሲል የነበረ እና ከአስራ አምስት አመት በላይ የሚያስቀጡ ወንጀለኞች የሚቀርቡበት ነበር፡፡ አሁንም ከፀረ ሙስና ክሶች ውጪ ያሉና ከ15 ዓመት በላይ የሚያስቀጡ ጉዳዮች የሚታዩበት ነው፡፡ የሥራ ጫና ይበዛል የሚለውን ስናነሳ ግን በእኛ ችሎት በቀን በአማካይ ሀያ መዝገብ ይታያል፡፡ በቀን የሚገጥሙንን ጉዳዮች ስንወስን በሥራችን ማንም ጣልቃ አይገባብንም፡፡ መዝገቦችን ተነጋግረን  የምንወስነው እራሳችን ስለሆንን በዚህ በኩል ከመንግስትም ሆነ ከሌላ ወገን ጫና ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ፍ/ቤት ጫና ለማድረግ የሚመጣ ማንም ሊኖር አይችልም፤ ማንም መብት የለውም፡፡

ገጠመኝ

በሌላ ችሎት ላይ በምሰራ ወቅት ነው፡፡ የሠራተኛና አሪ ክርክር ነበር - ጉዳዩ፡፡ ለሠራተኛው በስር ፍ/ቤት ተወስኖለት ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ይልና ያስቀርባል አያስቀርብም የሚለው ከተመረመረ በኋላ “አያስቀርብም” ተብሎ ተወሰነ፡፡ ከዚያም አሠሪውም ሠራተኛው በተገኙበት “የስር ፍ/ቤቱ ውሳኔ ፀንቷል” ስል አሰሪው ተከፋ፡፡ ሰራተኛው ግን ተነሳና “አቦ ይመችሽ” አለ፤ በጣም ሳቄ መጣ፡፡

============“መንግሥት ጫና ፈጥሮብኝ አያውቅም”

ሙሉጌታ ኪዳኔ ይባላሉ፡፡ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡ ከትግራይ እስከ ፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በዳኝነት ለ///// ዓመት ያገለገሉት አቶ ሙሉጌታ፤ በአሁኑ ጊዜ በ3ተኛ የከባድ ወንጀል ችሎት የቀኝ ዳኛ ናቸው፡፡

ከተከሳሾች ጋር ያላችሁ ግንኙነት የሰመረ እንዲሆን የምታደርጉት ጥረት ምን ይመስላል?

ከሌሎች የተለየ አቀራረብ አለን ለማለት ይከብደናል፤ ግን አንድ ዳኛ ማድረግ ያለበት ነገር በህገመንግስቱ የተቀመጠ አለ፡፡ ታራሚዎች ማድረግ ያለባቸውን ነገር እንዲያደርጉ ጥረት ማድረግ ይገባናል፡፡ ከዚህ አንፃር አብዛኛዎቹ ታራሚዎች በፍ/ቤት ቀርበው የማያውቁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ጠበቃ አቁሞ የመከራከር መብት እንዳለው ታዳሚው ላያውቅ ይችላል፡፡ በጠበቃ ታግዞ ቢከራከር የበለጠ ፍትህ ያገኛል የሚለውን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ በህገመንግስቱ የተቀመጡ ነገሮችን ደግሞ ለታራሚው የማሳወቅ ግዴታ አለብን፡፡ ጠበቃ አቁሞ መከራከር እንደሚችል መግለጽ አለብን፡፡ ካልሆነ ግን ፍትህ ሊዛባ ይችላል፡፡ መብቱ ነው፤ ጠበቃ አልፈልግም ማለት ይችላል፡፡ ጠበቃ ማቆም አልፈልግም ካለ የራሱ መብት ነው ግን እንደ ፍርድ ቤት በጠበቃ ቢከራከር ጥሩ ፍትህ ሊያገኝ እንደሚችል መምከር አለብን፡፡ ይሄ ችሎት ሲታይ ከባድ ችሎት ነው፡፡ ከመጠን አንፃርም ብዙ መጠን ያለውን ፋይል ያያል፡፡ ለምሳሌ ከባድና ቀላል ግድያ፣ የሽብር ወንጀል፣ የዕፅ ማዘዋወር፣ የሰዎች ዝውውር የመሳሰሉ እና ከ15 አመት በላይ እስራት የሚያስወስኑ ወንጀሎች እዚህ ነው የሚታዩት፡፡ ስለዚህ ይሄ ብዙ መዝገብና ከባድ ጉዳዮች የሚታዩበት ችሎት ነው፡፡

ዳኞችን ለሙስና ሊያጋልጧቸው የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ሙስናን በተመለከተ ዋናው የዳኛው ባህሪ ነው፡፡ በርግጥ በቂ ደመወዝና ጥቅማጥቅም የሚያገኝ ከሆነ የሚከፋ አይደለም፤ ጥሩ ነው፡፡

በተወሰነ ደረጃ ለሙስና ተጋላጭነት አይዳርግ ይሆናል፡፡ በዋናነት ግን እሱ አይደለም፤ የእራስ ባህሪ ነው፡፡ ብዙ ገንዘብና ሃብት ወደ ሙስና የሚገባ ይኖራል፡፡

ዋናው ወሳኝ ነገር የሰው ባህሪ ነው፡፡ ለሙስና ተጋላጭ ፍ/ቤት ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ ከፍርድ ቤት ውጪ የሆኑ ቦታዎች ለሙስና ሲጋለጡ ይታያሉና እዚህ ብቻ አይደለም፡፡

በሥራችሁ ላይ ጫና ደርሶባችሁ ያውቃል … ከመንግስት ወይም ከግለሰብ?

ጫና ከመንግስት፣ ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከፍ/ቤት ሃላፊዎች ሊመጣ ይችላል፡፡ እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን እንደዚህ አይነት ነገር አልገጠመንም፡፡ ቢያጋጥምም ሊቋቋም የሚችል ዳኛ መሆን አለበት፡፡ ቤተሰብ ተነስቶ ጓደኛም ቢሆን ይሄንን አድርግልኝ ሊል ይችላል፡፡

ይሄ ሆነ ማለት በምክር ቤት ቀርበህ የገባኸውን ቃለ መሀላ አፍርሰሃል ማለት ነው፡፡ አያጋጥምም ለማለት አይቻልም፤ ሊያጋጥም ይችላል፡፡

ግን ይሄን መቋቋም የማይችል ዳኛን ዳኛ ለማለት አልደፍርም፡፡ እኔ እስከዛሬ ስሰራ ይሄንን ካላደረክ ብሎ መንግስት ጫና ፈጥሮብኝ አያውቅም፡፡ እዚህ የነበሩ ዳኞችም (ጓደኞቼ) ይሄንን ያረጋግጣሉ፡፡

 

 

 

 

 

 

Read 17812 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 14:25