Print this page
Sunday, 11 February 2018 00:00

ህዝብ ለወደደው ይገዛል፤ ያመነውን ያነግሳል!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(24 votes)

    ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአንጋፋ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪነት የዘለቁት የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ከእስር መፈታታቸውን ምክንያት በማድረግ፣ የአምቦ ከተማ ህዝብ ሞቅ ደመቅ ያለ አቀባበል አድርጎላቸው ነበር፡፡ (አንዳንዶች፤”A hero’s Welcome” ሲሉ ዘግበውታል) “ፖለቲከኛው የንጉስ አቀባበል ተደረጋላቸው” የሚል መንፈስ ያለው ዘገባም አንብቤያለሁ፡፡ በእርግጥም ህዝብ የወደደውን “ንጉስም” “ጀግናም” ያደርጋል፡፡ መቼም “ኢህአዴግ ነፍሴ”፣ ምሁሩን  ፖለቲከኛ በየአካባቢው ለመቀበልና ድጋፉን ለማሳየት የወጣውን ወፈ ሰማይ ህዝብ ሲመለከት፣ ”ለምን አሰርኳቸው” ብሎ ሊጸጸት እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ (ግምት ነው ብያለሁ!)  በሌላ በኩል፣ ዶ/ር መረራም ቢሆኑ ለሳቸው ክብር የወጣውን አገር ሙሉ ህዝብ ሲያዩ፣ እንኳንም ከፖለቲካ ትግል ከመገለሌ  በፊት ይሄንን በረከት ለመቋደስ በቃሁ እንደሚሉ እጠረጥራለሁ። በዚህም የተነሳ “መታሰሬ ለበጎ ነበር!” የሚል ሃሳብ ቢመጣባቸው አይፈረድባቸውም፡፡ ወዳጆቼ፤ የፖለቲከኞች አንጡራ ሃብት ህዝብ ነው፡፡ (ሥልጣን ሲደላቸው ይዘነጉታል እንጂ!)   
በነገራችን ላይ “የህዝብ ማዕበል” ቀልቤን ወስዶት ነው እንጂ የወጌ ዋና ጭብጥ ለዶ/ር መረራ የተደረገው ህዝባዊ አቀባበል አልነበረም፡፡ ቢሆንም በጥቂቱ አንስቼ ማውጋቴን አልጠላሁትም። በእርግጥ ላወጋችሁ የፈለግሁት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝብ ተሰባስቦ ወደ አደባባይ የሚወጣበት አጋጣሚ በተፈጠረ ቁጥር ስጋት እንደሚሰማኝ ነው፡፡ ብዙዎችም ተመሳሳይ ስጋት እንደሚጋሩ እገምታለሁ፡፡ ለምሳሌ በአምቦ ከተማ  ለዶ/ር መረራ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ስሰማ ሰግቼ ነበር፡፡ አደባባይ ከሚወጣው አያሌ ቁጥር ያለው ህዝብ አንፃር፣ በመሃል የአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ድንገት ወደ ተለመደው ተቃውሞ ተለውጦ፣ ግጭት እንዳይፈጠርና የዜጎች ህይወት እንዳይቀጠፍ በእጅጉ ፈርቼ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ለሌላ ጊዜ ቢተላለፍ ሁሉ ተመኝቼ ነበር፡፡ (ለመቼ እንደሚተላለፍ ባላውቅም!)
የዶ/ር መረራ የአቀባበል ሥነ ስርዓት ብቻም ሳይሆን በጥምቀት ማግስት በባህር ዳር ከተማ የተደረገው የቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር ጉዞ” ኮንሰርትም በዚህ ክፉ ወቅት ባይካሄድ እመርጥ ነበር - በግሌ፡፡ (ቴዲ ለአድናቂዎቹ የማቀንቀን መብቱን ከእገዳ ያላቀቀበት አጋጣሚ ቢሆንም!) ልብ አድርጉ! ድምፃዊው በአዲስ አበባ ስንት ጊዜ ኮንሰርት ሊያቀርብ አቅዶ፣ ስንት ጊዜ እንደታገደበት። (ያውም ባልተፃፈ ህግ!!) ምን ኮንሰርቱ ብቻ፤ የአልበሙ ምርቃትም በ11ኛው ሰዓት ላይ በቀጭን ትዕዛዝ ታግዶበታል፡፡ (አሁንም ባልተጻፈ ህግ!!) ግን ደግሞ ያልተጻፈው ህግ፣ የህጎች እናት የሚባለውን “ህገ መንግስታዊ” መብት ሊደፈጥጥ እንደሚችልም ታዝበናል፡፡ እናም በባህርዳር ከተማ፣ ኮንሰርት የማቅረብ ፈቃድ ማግኘቱ፣ ለድምፃዊው ያለ አግባብ የተነጠቀውን ህገ መንግስታዊ መብቱን ዳግም የማስከበርያ አጋጣሚ ነበር፡፡ (በአገሩ ተስፋ ከመቁረጥ ያዳነው አጋጣሚም ሊሆን ይችላል!) እንዲያም ሆኖ ግን በኮንሰርቱ ላይ ብዙ ሺ ወጣቶች እንደሚታደሙ በመገመት፣ ድንገት ተቃውሞ ተቀስቅሶ፣ እንደተለመደው ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት እንዳይፈጠርና የዜጎች ህይወት በከንቱ እንዳይጠፋ ስጋት አድሮብኝ ነበር፡፡ ብዙዎችም እንደኔው ሊሰጉ እንደሚችሉ ሳይታለም የተፈታ ነው። (በተለይ ብላቴናዎቻቸው ወደ ኮንሰርቱ እንደሄዱ የሚያውቁ ቤተሰቦች፣ እንዴት በስጋት እንደሚናጡ አስቡት!) እኛ አገር ተቃውሞ ከተነሳ፣ በአብዛኛው ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ግጭት መፈጠሩ አይቀሬ እየሆነ መጥቷል። ግጭቱ የሚቋጨውም በዜጎች ሞትና በንብረት ውድመት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ዘር-ተኮር ጥቃት ተጨምሮበታል። (ወደ ፈንጂ ወረዳ እየገባን ነው!) አመሻሽ ላይ ወይም በነጋታው ደግሞ ቤት ለቤት እየተዞረ፣ ግጭቱን የቀሰቀሱ ወጣቶች ተለቅመው ወህኒ ይወረወራሉ፡፡ በአንድ በኩል ባለፉት ግጭቶች የታሰሩት በምህረት ሲፈቱ፣ በሌላ በኩል በአዲሱ ግጭት ተሳትፈዋል የተባሉ ደግሞ በተራቸው ይታሰራሉ፡፡ (አስከፊ የቀውስ አዙሪት!)
እናላችሁ … በባህርዳሩ የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት፣ ረብሻና ግጭት የሚቀሰቀስበት ዕድል ከፍተኛ ነበር፡፡ ሆኖም ረብሻና ግጭት እንዳይከሰት ተብሎ በተደረገው የቅድሚያ ጥንቃቄና ጥበብ የተሞላበት የማስተባበር  ሥራ፣ ኮንሰርቱ ያለ ኮሽታ ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ ቀላል ነበር ማለት አይደለም። በአስማትና በተዓምር የተከናወነም አልነበረም። በዋናነት የማስተባበሩ ሥራና ሙሉ ኃላፊነት፣ ለባህር ዳር ወጣቶች በመሰጠቱ ነው ኮንሰርቱን ያለ ሁከትና ብጥብጥ ማካሄድ የተቻለው፡፡ ይሄ ደግሞ አስቀድሞ በቅጡ ማሰብ፣ መጨነቅና መጠበብን ይጠይቃል፡፡ አዎ ረብሻና ግጭት ሳይፈጠር፣ የዜጎች ህልፈት ሳይከሰት----ፕሮግራሙ እንዲከናወን በቅጡ ማሰብና ማቀድ የግድ ነው!! ድንገት ረብሻ ቢከሰት እንኳን እንዴት አደጋ ሳያስከትልና ሳይሰፋ በእንጭጩ መግታት እንደሚቻል አቅዶና ዘይዶ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ለረብሻና ግጭት የሚያነሳሱ ወይም የሚገፋፉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች ከማድረግ መቆጠብም ወሳኝ ነው፡፡ በብዙዎቹ የጎዳና (አደባባይ) ላይ ተቃውሞዎች እንዲህ ያሉ ቅድመ ጥንቃቄዎች ብዙም እንደማይታሰብባቸው ከአሰቃቂ ውጤቶቹ መረዳት እንችላለን፡፡ (ተቃውሞ - ግጭት - የህይወት መጥፋት!)
መቼም መንግስትን በዘፈንም ይሁን በስድብ እየተቃወሙ ያሉ ወጣቶችን፣ በትዕዛዝና እልህ በተቀላቀለበት ሃይለ ቃል ከተቃውሞአቸው መግታት አይሞከርም፡፡ ይበልጥ ማባባስ እንጂ። ደግሞስ ተቃውሞአቸውን በሰላማዊ መንገድ እስከገለጹ ድረስ ለምንስ መግታት ያስፈልጋል? (ህገ መንግስታዊ መብታቸው አይደለም እንዴ?) በነገራችሁ ላይ አንዳንድ ኢህአዴግ የሚቆጭባቸው (በመጽደቃቸው ማለት ነው!) ህገ መንግስታዊ መብቶች እንዳሉ መጠርጠር ከጀመርኩ ቆይቻለሁ።
እናላችሁ---300 የሚደርሱ የባህርዳር ከተማ ወጣቶች በጥንቃቄ ተመልምለው፣ ኃላፊነቱን በወሰዱበት የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ላይ አብዛኛው ወጣት ታዳሚ፣ ለተቃውሞ አቆብቁቦ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ድምፃዊው፤ “ጃ ያስተሰርያል” የሚለውን ኢህአዴግን የሚተች ዘፈን (ፖለቲካዊ ትችት በዜማ በሉት!) እንዲያቀነቅን በእጅጉ  ተፈታትነውት ነበር - ታዳሚያኑ፡፡ ከቴዲ አፍ እየተቀበሉ፤ “አዲስ ንጉስ እንጂ መቼ ለውጥ መጣ” ለማለት ከመጠን በላይ ጓጉተው ነበር፡፡ ይሄን ያህል ያጓጓቸው ደግሞ ዘፈኑ እንዳይቀነቀን መታገዱን ስለሚያውቁ ነው፡፡ (ያው ባልተፃፈ ህግ!!) በነገራችን ላይ የ27 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረው ዲሞክራሲያችን፣”ጃ ያስተሰርያል” የሚለውን ዘፈን፣ የሚሸከምበት ጫንቃ እንኳን አላበጀም! (“ዲሞክራሲ ሂደት ነው” አሉ!) እንግዲህ ይሄ ዘፈን የእገዳ ማዕቀቡ የሚነሳለት (በአሳዛኝ ሁኔታ!) ኢህአዴግ ከሥልጣን የወረደ ዕለት ነው ማለት ነው?!  
ወደ ተነሳንበት ዋና ጭብጥ ስንመለስ፣ ከባህርዳር ከተማ ወጣቶች በተጨማሪ፣ ራሱ ቴዲ አፍሮ፣ ኮንሰርቱ በሰላም ተካሂዶ እንዲጠናቀቅ፣ ጥበብና ፍቅር የተመላበት ስትራቴጂ ተጠቅሟል። “ፍቅር ያሸንፋል” እያለ የታዳሚውን ቀልብና ስሜት በፍቅር በመማረክ፣ ”ታሪካዊ ኮንሰርት” ማቅረቡን ብዙዎች መስክረዋል፡፡ ለዓመታት በህዝብ ዘንድ የገነባው ተወዳጅነትና ተደናቂነትም፣ ከ60 ሺ በላይ የሚገመቱት ታዳሚያን ከቃሉ እንዳይወጡ ለማድረግ አስችሎታል፡፡ ቃሉ ደግሞ ሌላ አይደለም፤ “ፍቅር ያሸንፋል” ነው፡፡ ከአገር መሪዎች፣ ከፖለቲከኞች፣ ከምሁራኑ፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ወዘተ--የሚጠበቀው እንዲህ ያለውን ግርማና ሞገስ የተጎናፀፈ፣ የህዝብ አክብሮትና ፍቅር ነበር፡፡ ሆኖም ለዚህ በረከት አልታደሉም፡፡ (ያሳዝናል!)
አሁን ለአፍታ ወደ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የአምቦ ከተማ አቀባበል ልመልሳችሁ፡፡ በነገራችን ላይ ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ቢሆንም በአምቦ ለእኚህ አንጋፋ ምሁርና ፖለቲከኛ የ”ጀግና” አቀባበል ለማድረግ የወጣው ህዝብ 100ሺ እንደሚደርስ የገመቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ እኔ ግን በፎቶ ላይ እንደተመለከትኩት፣ ወፈ ሰማይ ህዝብ፣የሚለው አገላለጽ የልቤን አድርሶልኛል፡፡
በስቴዲየም በተካሄደው አጭር የአቀባበል ሥነ ስርዓትም አንዳንድ ወጣቶች፣ በስሜታዊነት ለተቃውሞ ተነሳስተው እንደነበር የወሬ ወሬ ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን ዶ/ር መረራ ከተቀመጡበት ብድግ ብለው፣ በኦሮምኛ አንድ ሁለት ቃል ሲናገሩ፣ ወዲያው በአክብሮትና በፍቅር ትዕዛዛቸውን ተቀበሉ፡፡ እንደተረጋጉም ሥነ ሥርዓቱ ተጠናቀቀ ብለውኛል - መረጃው ያላቸው ወገኖች።  (አያችሁ፤ ህዝብ ለወደደው ይገዛል! ያመነውን ያነግሳል!)
በነገራችን ላይ አዲሱ የኦህዴድ አመራር፣ ስልጣን ከተቆናጠጠ ወዲህ በአገራችን የዘመናዊ ፖለቲካ ታሪክ ተከስተው የማያውቁ አስደናቂም እንግዳም የሆኑ ሁነቶች ወይም ክስተቶች ተራ በተራ ማየት ጀምረናል፡፡ አጃኢብ የሚያሰኙና በትንግርት እጅን አፍ ላይ የሚያስከድኑ የፖለቲካ ሁነቶች!! ፈጣሪ ሊክሰን አስቦ ነው መሰለኝ፣ ብዙዎቹ ደግሞ አዎንታዊ አንደምታ የሚፈጥሩ፣ ህዝብን ከዳር እስከ ዳር ሳይነጋገር የሚያግባቡ  ክስተቶች ናቸው። የጨለመውን ተስፋችንን የሚያፈኩ! የነገዋን ኢትዮጵያችንን የሚያስናፍቁ! እኛም ወግ ሊደርሰን ነው በሚል ጉጉታችንን በእጅጉ የሚያንሩ ናቸው - እኒህ እንግዳ የሚመስሉ ፖለቲካዊ ሁነቶች---- እንግዳ የሚመስሉ ክስተቶች--- እንግዳ የሚመስሉ እውነታዎች! እንግዳ ይመስሉ እንጂ ቅዠቶች አለመሆናቸውን ግን መቶ በመቶ እርግጠኛ ነኝ፡፡
እናላችሁ … በዶ/ር መረራ የአምቦ ህዝብ አቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ የከተማዋ ፖሊሶች ለእኚህ የህዝቡ “ጀግና”፣ የመንግስት ባለስልጣን ዓይነት ጥበቃና እንክብካቤ ማድረጋቸውን ሰምቻለሁ፡፡ (ተጋንኖ ካልሆነ በቀር!) ግን አንድ ነገር በእርግጠኝነት አውቃለሁ፡፡ ዶክተሩ በስተመጨረሻ ለከተማዋ ፖሊሶች ከፍተኛ ምስጋና ማቅረባቸውን!! አዎ ላደረጉት መስተንግዶና ቀልጣፋ የማስተናበር ሥራ በይፋ አመስግነዋቸዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ፣ ፖሊስን ሲያመሰግን ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? (በተለይ በጦቢያ!) እኔ በበኩሌ አላውቅም። ፖሊስም የተቃዋሚ መሪን ሲያስተናግድና ደጋፊዎቹን ሲያስተናብር ገጥሞኝ አላውቅም፡፡ ስለዚህ ተዓምር ቢሆንብኝ አትፍረዱብኝ፡፡ የዚያኑ ዕለት የታየው ሌላው አስገራሚ ነገር፣ ባጃጆችና መኪኖች ላይ  የፕሬዚዳንቱ አቶ ለማ መገርሳ፣ የምክትላቸው ዶ/ር አብይና የዶ/ር መረራ ጉዲና ምስሎች (ፖስተሮች) ተርታውን መለጠፋቸው ነው፡፡ (“እንወዳችኋለን፤ አንድ ሁኑልን” ለማለት ይሆን!?) ትርጉሙ ምንም ይሁን ምን ደስ ይላል። እንኳን ለዚህ አበቃን!! ከ40 ዓመት በኋላ የመጠፋፋትና የመጠላለፍ የጥላቻ ፖለቲካ ሊቀየር ይሆን?  ግዴለም ተስፋ እናድርግ፡፡
በወጣት ኃይል (New blood እንዲሉ!) የተዋቀረው የአቶ ለማ መገርሳ የአመራር ቡድን፣ በየጊዜው ትኩረት የሚስቡና የሚያነቃቁ አዎንታዊ ውሳኔዎችና የለውጥ እርምጃዎች በመውሰድ አብዛኛውን ኢትዮጵያውያን ማስደነቃቸውንና ማስደመማቸውን ቀጥለዋል፡፡ አሁንም ድረስ የአቶ ለማን የአመራር ቡድን በጥርጣሬ የሚመለከቱ ወገኖች ግን አልጠፉም፡፡ ለጥርጣሬያቸው የሚያቀርቧቸው ምክንያቶችም አሏቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ ለ27 ዓመታት የምናውቀውን በኢህአዴግ “ተጠፍጥፎ የተሰራ” ኦህዴድ የተባለ ድርጅት የሚዘውሩ፣ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም የተጠመቁ፣ ሶሻሊስት ዘመም አመራሮች ስለሆኑ ለውጥ አያመጡም ባይ ናቸው፡፡ እኔ ደግሞ ኦህዴድን በቅድሚያ ለውጠው፣ ለሌሎቹም እህት ድርጅቶች ይተርፋሉ ባይ ነኝ፡፡ ምናልባትም ኢህአዴግን ሊታደጉትም ይችላሉ፡፡
የኦህዴድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሰሞኑ የወሰነው ጉዳይ ትንሽ ለየት የሚል ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታት  መብቶቼንና ጥቅማ ጥቅሞቼን ያለ አግባብ ተነጥቄ፣ 2ሺ ብር የማይሞላ ወርሃዊ የጡረታ ክፍያ ብቻ ነው የማገኘው የሚሉትን የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ችግርን መርምሮ ሊደግፋቸው መወሰኑን የኦህዴድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡ በዚህም መሰረት፣የአገር ውስጥና የውጭ አገር ሙሉ የህክምና ወጪያቸውን ለመሸፈን የወሰነ ሲሆን በሁለት ሳምንት ውስጥ መኪና ተገዝቶ እንደሚሰጣቸውም ታውቋል። ሥራ አስፈጻሚው መጠነኛ የገንዘብ ድጋፍም አድርጎላቸዋል፡፡ ይሄ እንግዲህ የአቶ ለማ መገርሳ የአመራር ቡድን ትሩፋት ነው፡፡ እስቲ አስቡት---የኦህዴድ ሥራ አስፈጻሚ፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንትና የፓርላማ አባል ሆነው ያገለገሉ ሰው ናቸው፡፡ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት በመያዛቸው ብቻ ከመንግስት የተሰጣቸው ቤትና መኪኖች የተወሰደባቸው ሲሆን 10 ሺ ብር የሚደርስ ወርሃዊ መተዳደሪያቸውም ተቀንስ 1750 ብር ብቻ ሲከፈላቸው ኖረዋል። ይሄ መቼም የአገሪቱን ስምና ክብር የሚያጎድፍ  ከመሆኑም በላይ አገራቸውን ላገለገሉ ሰዎች ውለታ ቢስ መሆን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ስናየው፣ የእነ አቶ ለማ ውሳኔ ቀናነታቸውንና አርቆ አሳቢነታቸውን የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የኢህአዴግንና የመንግስትን ገበና ለጊዜውም ቢሆን ሸፍነውለታል። ለነገሩ ኢህአዴግ ያገለገሉትን ሰዎች በክብር ሸልሞና የሚገባቸውን አድርጎ የመሸኘት ባህል ያለው አይመስለኝም፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ከ30 ዓመት በላይ ካስተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተሰናበቱት፣ ተመስግነውና ተሸልመው አይደለም፡፡ በተሰናበቱ ማግስት ከመኖሪያ ቤታቸው እንዲወጡ ነው የተደረገው፡፡ የፈለገ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቢሆኑ፣ ዩኒቨርሲቲውን ለ3 አስርት ዓመታት ያገለገሉ አንጋፋ ምሁር መሆናቸው ሊዘነጋ አይችልም፡፡ በህይወት እስካሉ ድረስ በነጻ እንዲኖሩበት ቢፈቀድላቸው ከሰጡት አገልግሎት አንጻር ፈጽሞ አይበዛባቸውም፡፡ ይሄ ደግሞ እርዳታ ሳይሆን ለአገራዊ ውለታቸው ካሳ መክፈል ነው። ይሄኔ ነው ከኦህዴድ የሰሞኑ ውሳኔ ትምህርት መቅሰም የሚያስፈልገው፡፡
የኦህዴድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከሚገኙ የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ጥሪ ያስተላለፈውም በዚሁ ሳምንት ነው፡፡ (ፈር-ቀዳጅ እርምጃ ነው!) ይሄ መቼም ለእኔ ተዓምር ነው የሆነብኝ፡፡ (ሰምቼ አላውቅማ!) በእርግጥም በድሮው የኦህዴድ ሂሳብ ከሆነ፣ ይሄ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ግን የአሁኑ የእነ ለማ የአመራር ቡድን ኦህዴድ ነው፡፡ አዲሱ ኦህዴድ፡፡ በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያ፣የፓርቲና የባለሥልጣናት ልሳን ሳይሆን በሚዛናዊነት ለህዝቡ በቂ መረጃ እንዲያቀርብም ሳይወሰን አይቀርም፡፡
ወጌን ከማጠናቀቄ በፊት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፤ ከባለሃብቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ከተናገሩት ጥቂት የተመረጡትን ላጋራችሁ፡፡ ፕሬዚዳንቱ አመራር  ብቻ ሳይሆን አነጋገርም ያውቁበታል፤አንደበተ ርቱዕ ናቸው፡፡ (“ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!” ለእኔ የዓመቱ ምርጥ ጥቅስ ነው!)  
“…80፤ 60፤ 100 እና 3ሺህ ዓመት እየቆጠርን፣ ያ ትውልድ እኮ የመሰለውን ሰርቶ አልፏል። ጥሩም ይሁን መጥፎ በመሰለው መንገድ የራሱን ግዴታ ተወጥቶ አልፏል። እኛ ሌላ ትውልድ እኮ ነን! ለምን የራሳችንን ታሪክ አንሰራም? የራሳችንን ታሪክ! ሁልጊዜ ወደ ኋላ በማየት ወደፊት መራመድ አንችልም። ተደናቅፈን እንወድቃለን…”
“…የኋላውን ጥሩም ይሁን መጥፎ ለታሪክ እንተወው! ዛሬ ያለን ትውልድ የራሳችንን ታሪክ አዲስ ታሪክ እንስራ። አዲስ ታሪክ፤ እኛም የማናፍርበት፣ የነገውም ትውልድ እኛ የሰራነውን እንደ ጥሩ ተምሳሌት ወስዶ የራሱን ታሪክ የሚሰራበት፣ የራሳችን አዲስ ታሪክ እንስራ…”
“የሞተ ኦህዴድ ለኢህአዴግም አይጠቅምም። የተኮላሸ ኦህዴድ ለሀገሪቷም አይጠቅምም። ለሀገሪቷም ቢሆን ጠንካራ ኦህዴድ ነው የሚጠቅመው፡፡ ይህ ድርጅት ጠንክሯል እያለ ስጋት የሚሰማው ሰው ካለ ተሳስቷል፡፡ ይሀ ድርጅት ከጠነከረ ነው፣ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከጠነከረ ነው፣ ሀገሪቷም ሀገር የምትሆነውና የምትጠቀመውም፡፡ ሀገሪቷም የምትጠነክረው ያኔ ነው፡፡ ሌላውም ይሀን ማወቅ አለበት፡፡”
“ይህ ድርጅትና መንግስት፣ህዝቡ አለኝታዬ ነው የሚለው መሆን አለበት፡፡ ደግመን ደጋግመን እየተናገርን ነው፡፡ ህዝቡን እንስማ፡፡ ከህዝቡ ጋራ ሆነን ህዝቡ የሚፈልገውን እንስራ፡፡ ሌላ ነገር አይደለም እንስራ እያልን ያለነው፡፡ Rocket science እንፍጠር፣ እየተፈላሰፍን ከአቅማችን በላይ እንንጠራራ እያልን አይደለም፡፡ ይህ አይነት ፍላጎት የለንም፡፡ ለዚህ ህዝብ እንስራ ነው እያልን ያለነው፡፡”
(የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ ከባለሀብቶች ጋራ በኦሮሞ ባህል ማዕከል ያደረጉት ውይይት ፤ሚያዝያ 12፣ 2009 ዓ.ም.)
ምንጭ፡- (ከሆርን አፌርስ የተወሰደ)

Read 9630 times