Saturday, 28 April 2012 12:41

ዳያስፖራው ዘንድሮም እሮሮ!

Written by  ኤልሳቤት ዕቁባይ
Rate this item
(0 votes)

ሰሞኑን በውጪ ጉዳይ ሚ/ር አስተባባሪነት በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን  ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣኖች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡ በአብዛኛው በእሮሮ የተጠቀለለ አስተያየትና ጥያቄዎች በተስተናገዱበት መድረክ፣ አያሌ አስገራሚ ንግግሮች ከዳያስፖራው ተደምጠዋል፡፡ “ዳያስፖራውም ብሶት እኛም ብሶት ካወራን ለውጥ አናመጣም” ሲሉ - ምክትል ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ የተናገሩትም ወደው አልነበረም፡፡

ከአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በተጨማሪ የስራና ኮንስትራክሽን ልማት ሚ/ር አቶ መኩሪያ ሀይሌ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ነጋ ፀጋዬ እና የብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ዮሐንስ አያሌው በውይይቱ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡

የአምስት አመቱ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ የደረሠበትን ደረጃ በተመለከተ በምክትል ጠ/ሚኒስትሩ የተሰጠውን ማብራሪያ ተከትሎም የዳያስፖራው ጥያቄዎች ተስተጋብተዋል፡፡

በቅርቡ በወጣው የሊዝ አዋጅ ዙርያ ንብረት ከማፍራት መብት ጋር በተያያዘ የቀረበው ጥያቄ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱን ያሳቀ ቢሆንም ጥያቄውን ተከትሎ የቀለጠው የዳያስፖራ ጭብጨባ ግን ከመድረኩ ማሳሰቢያ እንዲሰጥ ማስገደዱ አልቀረም፡፡ “እንዲህ ከቀጠልን ለጥያቄ ሊኖረን የሚችለው ጊዜ ሊያጥር ይችላል” ብለዋል - አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ፡፡

አንድ የዳያስፖራ ተወያይ በሰነዘሩት አስተያየት፤ “ስለ ዳያስፖራ ስታወሩ ይህን ያህል ብር አመጣ እንጂ ይህን ያህል እውቀት አመጣ አትሉም፤ ለዳያስፖራው እውቀት ትኩረት አይሰጥም፤ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈለ ከህንድና ከአሜሪካ ምሁራን ከሚያመጣ ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው ዳያስፖራዎች እውቀታቸውን ማካፈል የሚችሉበት የዕውቀት ማዕከል ለምን አይቋቋምም” ብለዋል፡፡ ደቡብ ኦሞ ላይ ድልድይ ባለመሠራቱ ስራ እንዳጓተተባቸው የተናገሩ ሌላ ዳያስፖራ፤ ጉዳያቸው ያለበትን ሁኔታ ሲጠይቁ ጠቅላይ ሚ/ር ቢሮ ተይዟል እንደሚባሉ ጠቁመው፤ “ጉዳያችን ጠቅላይ ሚ/ር ቢሮ ተይዟል ይባላል እንጂ ግብርና ሚ/ር ለጉዳያችን መልስ የለውም፤ ጠቅላይ ሚ/ር ቢሮ ሁሉንም ነገር ነው እንዴ የሚሠራው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ቢሮክራሲውን መቋቋም አቃተኝ ያሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ፤ ጉዳያቸውን ለማስፈፀም ለጉምሩክ 178 ደብዳቤዎች መፃፋቸውን ገልፀው፤ አላስካ ለአሜሪካን ስትሸጥ እንኳን ይህን ያህል የዶክመንት ልውውጥ አልነበረም በማለት ተሰብሳቢውን ፈገግ አሰኝተዋል፡፡ የመንግስት አሰራርን የሚገዳደሩ ጥያቄዎችና ቁም ነገር ያዘሉ አስተያየቶች የተሰሙትን ያህል የተምታቱና ብስለት የጐደላቸውም አልጠፉም - በዳያስፖራው ውይይት፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ እንዲህ አሉ፡- “እኔ በምኖርበት አውስትራሊያ ነፃ ገበያ አለ፡፡ በደንብ ይጠቀሙበታል፡፡ እዚህ እኔ ጠዋት ስመጣ ሻይ የጠጣሁት በአስር ብር ነው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ በሁለት ብር ይሸጣል፡፡ መንግስት ይህን መቆጣጠር አለበት” አይገርምም! በአንድ በኩል ስለነፃ ገበያ ይሰብካሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስለ ቁጥጥር፡፡ ነፃ ገበያ ለኢትዮጵያ እንግዳ ሳይመስላቸው አልቀረም፡፡

ሌላ የዳያስፖራ ተናጋሪ ደግሞ “ጎንደር ብትሄዱ ይገርማችኋል … የቤተሰቦቼ መሬት ያለአግባብ ተወስዶብኛል፡፡ እንዲያውም ሚ/ሩን በህልሜ አይቻቸዋለሁ፡፡ ችግሬን አሁኑኑ እዚህ ፍቱልኝ” ሲሉ በተወያዮች ዘንድ ግርምትን ፈጥረዋል፡፡

በህጋዊ መንገድ የገዙት መኪና ህገወጥ እንደተባለባቸው የገለፁ ሌላ ተናጋሪ፤ በፊት እንደማውቀው ሃይማኖት ብዙ ነው፤ መንግስት ግን አንድ ነው፤ አሁን ግን መንግስት ሁለት ሆነብኝ ሲሉ ግራ መጋባታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

“ኬኒያ ለ20 ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረ ቢዝነስ ነበረኝ፡፡ ይህን አገሬ ላይ ላደርገው አስቤ መጣሁ ግን ምንም መስራት አልቻልኩም፣ ወጣቱ በጣም ሰነፍ ሆኗል፡፡ የመንግስት ሠራተኞችም ቁጭ ብድግ እያደረጉ ነው የሚያስተናግዱን፤ አብረውኝ አፈር እንደፈጩ “ማነሽ አንቺ” ይሉኛል፤ ማንነቴን ሳያውቁ!  ሰነፍ ህዝብ እና ሰነፍ አገር ስለሆነ ኋላ ቀርተናል፡፡” ያሉም ሌላ ተናጋሪ ነበሩ፡፡

እዚህ አገር የገጠሟቸው ሁሉ የሙያ ችሎታ የሌላቸውና ሥራ የማይሠሩ እንደሆኑ የጠቆሙ አንድ ዳያስፖራ ደግሞ፤ ስራ ግዴታ መሆን አለበት የሚል መብትን የሚፃረር አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ ከውጪ ስንመጣ የሚቸግረን ቤት ነው፡፡ ሆቴልም በጣም ውድ ነው፡፡ ያሉ አስተያየት ሰጪ፤  “አንድ ጓደኛችን ለሶስት ወር ከአሜሪካ አስፈቅዶ መጥቶ፣ ከኑሮ ውድነቱ የተነሳ በሁለት ሳምንቱ ተመልሷል” ብለዋል፡፡ አስከትለውም፤ “120 እና 150 ካሬ ሜትር መሬት የተነፈግነው ለምንድነው? አገራችን የኛ ነው፡፡ በሊዝ የሚያሸንፉን እዚህ ያሉት ናቸው፡፡ እኛ ሌብነቱን አቋርጠን መሄዱን አንችልበትም፤ እነሱ መንገዱን ያውቁታል፡፡ ሲሉ ምሬት አከሉበት፡፡

ከአንደኛ ዓለም የመጣን ስለሆንን ጥሩ አፓርትመንት ውስጥ የኖርንና መኪና ያለን ነን ያሉት  ሌላ ተናጋሪ፤ እዚህ ስንመጣ ቤትና መኪና የለንም፤ ቤት ሊዘጋጅልን፤ ከታክስ ነፃ የሆነ መኪና ሊፈቀድልንም ይገባል ሲሉ የመብት ጥያቄያቸውን አስረግጠው አቅርበዋል፡፡

አንድ ተወያይ ደግሞ የኢህአዴግ ካድሬ ላይ ነው አስተያየት የሰነዘሩት:- “ስለ ልማት ለማውራት ሺህ ካድሬ ከዚህ ከምትመድቡ እዛ ያለ ሰው መጥቶ አይቶ ቢመለስና ቢያስተዋውቅ ለውጥ ያመጣል” ብለዋል፡፡

ሌላ አስተያየት ሰጪ በሰነዘሩት ትችት፤ “ቢሮ ተቀምጠው ይህን ህዝብ በፖለቲካ ብቻ የሚያደነቁሩትን ተዋቸውና ስልጠናና ስራ ላይ ይተኮር …” የሚል ገንቢ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ በዳያስፖራው ውይይት ላይ የተጠናቀረውን ፅሁፍ የምቋጨው ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ተናጋሪ በሰነዘሩት አዝናኝ አስተያየት ነው “ደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እንደ ዳያስፖራ ያለማየት ችግር አለ፡፡ እኛ ለአገራችን የምናደርገው አስተዋፅኦ ግን ከሌሎች አያንስም፡፡”

 

 

Read 2122 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 12:48