Sunday, 18 February 2018 00:00

ለሰሞኑ የኦሮሚያ አድማና ተቃውሞ መነሻው ምንድን ነው?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

  አንጋፋ ፖለቲከኞች መንግስትን ተጠያቂ ያደርጋሉ

       ሰሞኑን በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችና ዞኖች እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ከተሞች ለሁለት ቀናት አድማና ተቃውሞ ተደርጓል፡፡ ይሄን ተከትሎም የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ቆሞ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ በበርካታ ንብረቶችም ላይ ውድመት ደርሷል፡፡ የ7 ሰዎች ህይወትም ጠፍቷል፡፡ ያነጋገርናቸው አንጋፋ የተቃዋሚ ጎራው ፖለቲከኞች፣ ለሰሞኑ ብጥብጥ፣ መንግስትን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ በምን ምክንያት እንደሆነም ያብራራሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣የፖለቲከኞቹን አስተያየት ከእነ መፍትሄ ሃሳቦቻቸው እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ነው፡፡


              “መንግሥት ቃሉን ሳይሸራርፍ መፈጸም አለበት”
                 አቶ ገብሩ ገ/ማርያም (የመድረክ ም/ሊቀ መንበር)

    መሰረታዊ ችግር ያለበት ስርዓት ሁልጊዜ ችግሮች አይለዩትም፡፡ ብዙ ጊዜ ደጋግመን እየተናገርን አድማጭ ያጣንለት ጉዳይ የመንግሥት የፖሊሲ ችግር ነው፡፡ ፖሊሲውን እንዲያሻሽል እንዲፈትሽ ተደጋጋሚ ጥሪ ብናቀርብም እስከ ዛሬ ሰሚ አልተገኘም፡፡ ሌላው ትልቁና ቸል የተባለው ጉዳይ የህግ መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ ያለመተግበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጐች ከህግ አግባብ ውጪ እየታፈሱ  ነው አሁንም የሚታሰሩት፡፡ ይሄ ህዝቡ በሚገባ የሚያውቀው ነው፡፡
ዛሬ መንግስት እስረኞችን ለቅቄያለሁ ሲልም ህዝቡ እንደ ትልቅ ቁምነገር የማይቀበለው ከዚህ አንፃር ነው፡፡ እርግጥ ነው ፖለቲከኞች መፈታታቸው ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በአፈታት ሂደት ደግሞ ቅድመ ሁኔታ እያስቀመጡ፣ “ይሄን ፈርም ያንን አድርግ” ማለቱ ህዝብን ያስቆጣል፡፡ መንግሥት ይህን ማጤን አለበት፡፡ አጢኖም ብዙ ሃተታ ሳያበዛ፣ እፈታለሁ ባለው መሰረት፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና ግርግር ነው፣ እስረኞችን መፍታት  የሚገባው፡፡
 ከዚህ በኋላ የአገር ህልውና ነው ከምንም  በላይ ሊያሳስበን የሚገባው እንጂ የስልጣን ወይም የመንግስትነት ክብር  አይደለም፡፡ ይህቺ አገር ህልውናዋን ጠብቃ  እንዴት ወደፊት ትራመድ የሚለው ነው አሁን አንገብጋቢው ጥያቄ፡፡ ይሄ ጥያቄ ተስፋ እያገኘ ሲሄድ ደግሞ መንግስት በህዝብ ዘንድ  አመኔታ ለማግኘት ማሞከር ይችላል፡፡ አንዱ ጥያቄና የሃገሪቱ ችግርም  መንግሥት በህዝቡ ዘንድ  ያለው አመኔታ ጉዳይ ነው፡፡ እስረኞችን ያለ ቅድመ ሁኔታ መፍታት ራሱ የህዝብ አመኔታ ወደ ማግኘቱ ሊወስደው ይችል ነበር፡፡ ሰሞኑን የተፈጠረውን አድማና ተቃውሞውንም ያስነሳው ይኸው የመንግሥት ግትር አቋም ነው፡፡ መንግሥት ከህዝቡ ጋር የሚታረቅበትን ዕድል ነው ለማግኘት መጣር አለበት፡፡ ቃል የገባኸውን አልፈፀምክም ወይም እየፈፀምክ አይደለም የሚል መልዕክት ነው ያለው የሰሞኑ አድማ፡፡ ይሄን መንግሥት መገንዘብና ግትርነቱን መመርመር አለበት፡፡ በሻሸመኔ ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ ጥያቄ ስለመቅረቡ መረጃ አለን፡፡ ይሄን መንግሥት ተረድቶ መፍትሄ ማበጀት አለበት፡፡
በሌላ በኩል፣ ከፓርቲዎች ጋር እደራደራለሁ ብሏል፡፡ እኛም እውነተኛ ድርድር ጠይቀናል፡፡ በሃገራችን ለተከሰተው ችግር በድርድር በመሳተፍ፣ የመፍትሄው አካል መሆን እንፈልጋለን። ለዚህ ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበናል ግን ምላሽ የለም። ህዝቡ ይሄን ያያል፤ ይከታተላል፡፡ ፖለቲካውን በሙሉ አትኩሮት ነው የሚከታተለው። ይሄን ገዢው ፓርቲ ማወቅ አለበት፡፡
ከእሳት ማጥፋት በመለስ ያሉ ተራማጅ መፍትሄዎችን ማፈላለግ አለበት፡፡ ቃል የገባቸውን ጉዳዮች በሙሉ ሳይሸራርፍ መተግበር ይኖርበታል፡፡ ይሄን ማድረጉ ደግሞ የመሸነፍና የማሸነፍ ጉዳይ አይደለም፡፡ አገር የማገልገል ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ የፖለቲካ ትርፍ የሚያገኝ አይኖርም፤ ሀገርን ነው የሚያድነው፤ ህዝባችንን ነው የሚታደገው፡፡ እስካሁንም እንደ አገር የቆየነው፣ በዚህ ህዝብ ጨዋነት ነው፡፡ በሌላው ዓለም  ትንሷ ነገር፣ ብዙ ውድመት ስታደርስ አይተናል፡፡


------------


           “ህዝቡን ሊያረጋጋ የሚችለው የበለጠ ዲሞክራሲ እንጂ አፈና አይደለም”
               አቶ ተመስገን ዘውዴ (ፖለቲከኛ)


     መንግሥት በአንድ በኩል መታሰር ሳይገባቸው የታሰሩ ፖለቲከኞችን ለመፍታት ሙሉ ፈቃዱ እንደሆነ ሲገልፅ እንሰማለን፤ በሌላ በኩል ወደ ኋላ ተመልሶ ቅድመ ሁኔታ የማስቀመጥ አዝማሚያ ይታያል፡፡ ይሄ ፈፅሞ ሊሆን የሚገባው አይደለም። እርግጥ ነው መንግሥት በሀገሪቱ እየሆነ ያለውን በሙሉ ይገነዘበዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን የግንዛቤ እጥረቱ ያለው፣ ሁኔታዎችን ለማሻሻል በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ ነው፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ ሁላችንንም ባሳተፈ መልኩ፣ ያገሪቱ መፍትሄ አካል መሆን ሲገባን፣ አሁንም በተለመደ መልኩ በተቋጠረ መንገድ ነው እየተሄደ ያለው፡፡
 ገዢው ፓርቲ የአገሪቱን ችግሮች አሁንም አሳንሶ ነው እየተመለከተ ያለው፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ነገሮች መስመራቸውን ይስቱና በኋላ ወደ መስመር ለማስገባት የሚያስችል ቀና አመለካከትም አይኖርም፡፡ ስለዚህ ከወዲሁ መንግስት እንደ መንግሥት፣ ገዢው ፓርቲ እንደ ገዢነቱ ልበ ሰፊ በመሆን አረጋጊ፣ የአገር አድን እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው፡፡ አሁን የሚካሄዱ አድማዎችና ተቃውሞዎች፣ ሃይለኛ መልዕክት ነው ያላቸው፡፡ ሀሳብ አለን፣ ሀሳባችንን መግለፅ እንፈልጋለን ብለን በምንጠይቅበት ወቅት “ይሄ መብት አይገባችሁም” እየተባልን፣ እየታፈንን ነው እዚህ የደረስነው፡፡ ይሄን የመተንፈሻ መንገድ ተከልክሎ የቆየ ህዝብ ነው ያለን፡፡ አሁን ግን በራሱ ተነሳሽነት፣ “ሃሳብ አለኝ” ብሎ ነው የተነሳው፡፡ ገዢው ፓርቲ፣ ይሄን መነሳሳት ከእንግዲህ ወደ ኋላ መመለስ የሚችልበት እድል የለውም፡፡ ይሄን ሁኔታ ከማረጋጋት ባለፈ እናፍናለን ማለት ሀገሪቱን ለሌላ ቀውስ መጋበዝ ነው፡፡ የህዝቡን ጥያቄ በብልሀት መያዝ ያስፈልጋል።  የህዝቡን ሁኔታ ከእንግዲህ ሊያረጋጋ የሚችለው የበለጠ ዲሞክራሲ እንጂ አፈና አይደለም፡፡  


-------------


              “አሁን የገጠመን የአመራር ቀውስ ነው”
                ዶ/ር ንጋት አስፋው (የዩኒቨርስቲ መምህርና ፖለቲከኛ)

    ዛሬ የተቃውሞና የግጭት አዙሪት ውስጥ ልንገባ የቻልነው፣ ላለፉት 27 ዓመታት፣ በዲሞክራሲ ላይ ጠንካራ ስራ ባለመሰራቱ ነው፡፡ መንግሥት ተቃውሞውን በፀጥታ ኃይሉ ለማስቆም ጥረት አድርጓል ግን አልቻለም፡፡ ይኸው 3 ዓመት ሙሉ እንዲሁ አስከፊ ዜናዎችን እየሰማን ነው፡፡ በየጊዜው ተቃውሞ መልኩን እየቀረየ ሲሄድ ነው የምናየው፣ ዓለምም ይሄን ሂደት እየታዘበ ነው፡፡ መንግስት ግምገማ አድርጎ፣ በአጠቃላይ በአገሪቱ ለተፈጠሩ ችግሮች  ኃላፊነቱን ወስዶ፣ ይቅርታ በጠየቀ ማግስት፣ ወደ ተቃውሞና አድማ መገባቱ፣ ችግሩ ምን ያህል የጠለቀ መሆኑን ያሳየናል፡፡ መንግሥት እስረኞችን እንደሚፈታ ሲያስታውቅ፣ የተወሰነ ተስፋ ፈንጥቆ  ነበር፡፡ ሆኖም የአፈታት ቅድመ ሁኔታዎች ሌላ ችግር ነው የወለዱት፡፡ የሕግ ሂደቶች መጣስ ባይኖርባቸውም፣ አንድ የሀገር መሪ ፖለቲከኞችን እንደሚፈታ ለህዝብ ከገለጸ  በኋላ ሌላው በሱ የሚታዘዝ አካል፣ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጥ የለበትም፡፡ ከቅድመ ሁኔታዎችም የሚገኝ ትርፍ የለም፡፡ እስረኞችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታቱ ነው ትርፉ የሚያመዝነው፡፡ ይኸው ጉዳይ ሰሞኑን አገሪቱ ላይ ብጥብጥ ፈጥሯል፡፡ ለዚህ ኃላፊነቱን ማነው የሚወስደው?
አሁን ከመንግሥት የሚጠበቀው ስብሰባና ግምገማ በማካሄድ፣ የመግለጫ ጋጋታ ማቅረብ አይደለም፡፡ ህዝቡ የሚፈልገው ውጤታማ የሆነ፣ መሬት ጠብ የሚል ተግባራዊ ምላሽ ነው። በስስት የሚሰጡ ምላሽና እርምጃዎችን ህዝብ አሁን  አይፈልግም፡፡ እንደ እኔ ሃሳብ፣ አንድ የብሄራዊ መግባባት ኮሚቴ መቋቋም አለበት፡፡ አሁን የገጠመን የአመራር ቀውስ ነው፡፡ ይሄ መንግሥት ደግሞ ቀውሱን እንዲፈታ ህዝቡ ጊዜ እየሰጠው ነው፡፡ ግን እስካሁን ጊዜውን ተጠቅሞ ወሳኝ እርምጃ እየወሰደ አይደለም፡፡ ይሄን በጥልቀት ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ምሁራን በጉዳዩ ላይ ጠንካራ ውይይት የሚያደርጉበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡

Read 4611 times