Saturday, 28 April 2012 12:43

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

በትግራይ የተወለደው የ10 ዓመቱ ታዳጊ ኃይለአብ ተክሉ፤ ከአገሩ የወጣው አባቱ ዘወትር በሚፈጽምበት ድብደባ ተማርሮ ነው፡፡ በእርግጥ የዛሬ ሁለት ዓመት ታላቅ ወንድሙ ነበር እናትህ ጋር እወስድሃለሁ ብሎ ወደ አዲስ አበባ ያመጣው - ምንም እንኳን እናቱን ባያገኛቸውም፡፡ አሁን ኃይለአብ ፖስታ ቤት ፊትለፊት በሚገኘው ኢትዮ - ኩባ ወዳጅነት ፓርክ ውስጥ ተጠልሎ ያድራል - ከወንድሙ ጋር፡፡ ሃይለአብ ቀን ቀን ለምኖ የሚያገኛትን ገንዘብ ከጓደኞቹ ጋር ያጋጭና የጫማ ማስቲሽ ይገዛል፡፡ ማስቲሹ በትንሽዬ የውሃ ፕላስቲክ 35 ብር ሲሆን ይሄንንም ከባልንጀሮቹ ጋር ይካፈላል፡፡ ከዚያም  በውሃ አቅጥነው ይስቡታል - ረሃብና ብርድን ለመከላከል፡፡

ቀደም ሲል ቤንዚን በአፍንጫቸው ይስቡ እንደነበር የሚናገሩት የጐዳና ተዳዳሪዎቹ፤ የማስቲሽ ሃይል ከፍተኛ በመሆኑ አሁን ወደ እሱ መዞራቸውን ይናገራሉ፡፡

የ7 ዓመቱ ህፃን ዳንኤል ተፈራ፤ በየቀኑ ከጐላ ሚካኤል አካባቢ ትምህርቱን እየተወ የኢትዮ - ኩባ ወዳጅነት ፓርክ የሚመጣው ሳይክል ለመንዳት ነበር፡፡ ሆኖም ት/ቤት በየቀኑ እያረፈደ በማስቸገሩ ተባረረና የቀን ውሎው ሙሉ በሙሉ እዚያው ሆነ፡፡ ልክ ከትግራይ ክልል እንደመጣው ኃይለአብ ሁሉ ዳንኤልም ብቻውን አይደለም፡፡ ታላቅ ወንድሙ ይሳቅ ተፈራ አብሮት ይውላል - አብረውም ማስቲሽ ይስባሉ፡፡ ወደ ፓርኩ ስንገባ ህፃን ዳንኤል ደም እየተፋ ነበር ያገኘነው - በሳበው ማስቲሽ የተነሳ፡፡

ቢጩ በሚል ቅጽል ስሙ በጓደኞቹ ዘንድ የሚታወቀው የዘጠኝ ዓመቱ መኩሪያ ደግሞ ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ከእናቱ ጋር ሲሆን ማደርያቸው ጐዳና ነበር፡፡ እናቱን በመኪና አደጋ በሞት ከተነጠቀ በኋላ ነው በኢትዮ - ኩባ ፓርክ ውስጥ ማደር የጀመረው፡፡ እነዚህ ሁሉ ህፃናት ማስቲሽ በአፍ ወይም በአፍንጫቸው የሚስቡና በሱስ ክፉኛ የተጠመዱ ናቸው፡፡

ትራፊክ መብራት ላይ  የጐዳና ተዳዳሪ ህፃናቱ ብጫ ፈሳሽ የያዘ ፕላስቲክ በለበሱት ሹራብ ከልለው በአፍንጫቸው ሲስቡ ይታያሉ፡፡ ቀደም ሲል ለብርድና ለረሃብ ማስታገሻ በሚል ነዳጅ ይስቡ ከነበሩት ታዳጊዎች አንዳንዶቹ ለከፍተኛ በሽታ፣ ሌሎች ደግሞ ለሞት መዳረጋቸውን በህይወት ያሉ የጐዳና ተዳዳሪ ጓደኞቻቸው ይመሰክራሉ፡፡

ህፃናቱ ማስቲሹን ከሳቡ በኋላ ለ12 ሰዓታት ሳይነቁ ሊተኙ ይችላሉ፡፡ የረሃብ ስሜት ሳይሰማቸው፡፡ ለሁሉም ግን ውጤቱ ተመሳሳይ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ አዕምሮአቸውን ይስታሉ፡፡ ሌሎችን ደግሞ ደም ያስተፋቸዋል፡፡ ማስቲሽ ስቦ ሲለፈልፍ የነበረ ታዳጊ እዚያው ፓርክ ውስጥ ገጥሞናል፡፡

የ13 ዓመቱን የኔሰው፤ ከደሴ አዲስ አበባ የምትገኝ እህቷ ጋር የሰደደችው እናቱ ነበረች - ትምህርት እንዲማር፡፡ እህትየው መጠጥ ቤት እንዳላት እናት ሳታውቅ ነበር  የላከችው፡፡ የመጠጥ ቤቱ ጫጫታ ያልተስማማው የኔሰው፤ ከጫጫታ የሸሸ መስሎት ራሱን ጐዳና ላይ አገኘው፡፡ ይሄም ሳያንስ ማስቲሽ በመሳብ ጦስ ደም እየተፋ ተሰቃይቶ ህይወቱ እንዳለፈ የአገሩ ልጅ እንደሆነ የሚናገረው ባልንጀራው ገልጿል፡፡ ሁሉም የጐዳና ተዳዳሪዎች የማስቲሽ ሱሰኞች እንደሆኑ የጠቆመው ይሄ የ17 ዓመት የደሴ ተወላጅ፤ መሳብ የሚያቆሙት በአፋቸው ወይም በአፍንጫቸው ደም ሲተፉ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እንዲያም ሆኖ ማስቲሽ መሳቡን የሚያቆሙት ለጊዜው እንጂ ነገ እንደ አዲስ እንደሚጀምሩት የደሴው ተወላጅ ጠቁሟል፡፡

“ከቤ ወንዷ” የኢትዮ - ኩባ የወዳጅነት ፓርክ “ጉልቤ” እንደሆነች የሚናገሩ የጐዳና ተዳዳሪዎች፤ የካቴድራልና የጥቁር አንበሳ ተማሪ ፍቅረኛሞችን አምስት ብር እያስከፈለች በፓርኩ እንዲዝናኑ ታደርጋለች ይላሉ፡፡

ፓርኩን በጨረታ ያሸነፈ ባለሀብት እንደነበረ የሚናገሩ ምንጮች፤ ሆኖም ለረዥም ጊዜ ያለስራ መቀመጡን ይገልፃሉ፡፡ በዚህም የተነሳ የጐዳና ተዳዳሪዎች ማደሪያ እንደሆነ፤ ጫትና አደንዛዥ እፆችም ይሸጥበት እንደነበር ምንጮች ጠቁመው፤ አሁን አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ድርጊቱ እየቀነሰ እንደመጣ ይናገራሉ፡፡

የማስቲሽ ተጠቃሚ የጐዳና ተዳዳሪዎች ገንዘብ ሲቸግራቸው በቀጥታ የሚያመሩት “ከቤ ወንዷ” ጋ ነው - ማስቲሽ በዱቤ ስለምትሰጣቸው፡፡ ማስቲሽ ይዘው የተገኙ ልጆችን እየያዙ እንደሚቀጡ የሚናገሩ የአካባቢው ፖሊሶች፤ ሆኖም አንዳቸውም ማስቲሽ ከመሳብ አልተላቀቁም ብለዋል፡፡ ለምን ሲባሉ? ብርዱንና እረሃቡን የሚያስታግስልን እሱ ነው ይላሉ፡፡

በውስጥ ደዌ ህክምና ስፔሻላይዝ ያደረጉት ዶ/ር መሐመድ ሽኩር እንደሚሉት፤ ማስቲሽ በውስጡ ኢታኖል የያዘ ሲሆን ከቤንዚን ሁለትና ሦስት እጥፍ ጉዳት ያደርሳል፡፡ ማስቲሽ መሳብ ሳንባን፣ ጉበትንና ኩላሊትን ለከፍተኛ ጉዳት ከመዳረጉም በተጨማሪ ሙሉ በሙሉ ወደ ካንሰርነት እንደሚለወጥም ባለሙያው ይናገራሉ፡፡

 

 

Read 2619 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 12:49