Print this page
Sunday, 25 February 2018 00:00

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና የጠ/ሚኒስትሩ ከስልጣን መልቀቅ (ተቃዋሚዎች ምን ይላሉ?)

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

   መንግስት ባለፈው አርብ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ለ6 ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና የህግ ባለሙያዎች የተጣለውን አዋጅ በተመለከተ ምን ይላሉ? የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን መልቀቅስ፣ ፖለቲካዊ ለውጥ ያመጣል ብለው ያስቡ ይሆን? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ከህግ ባለሙያዎች ያሰባሰበውን አስተያየት እንደሚከተለው አቀናብሮታል፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ነው፡፡


           “መብትን በሰላማዊ መንገድ መጠየቅ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አይዳርግም
             ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም (ዓለማቀፍ የህግ ባለሙያ)

    የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲሁ በዘፈቀደ የሚደነገግ አይደለም፡፡ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው አዋጁ ሊጣል የሚችለው፡፡ አንደኛው ግልፅ ጦርነት ሲኖር ነው፡፡ ያንን ጦርነት ለመወጣትና በሀገር ላይ የተቃጣን ጥቃት ለመከላከል ሲባል፣ በጊዜያዊነት የሰብአዊ መብቶች ሊገደቡ ይችላሉ፡፡ ሁለተኛው የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ነው፡፡ ለምሳሌ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የጎርፍ አደጋ የመሳሰሉትን በሙሉ አቅም ለመቋቋም ሲባል፣ አዋጁ ሊታወጅ ይችላል፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ፣ ሰው አደባባይ ወጥቶ፣ በሰላማዊ ሰልፍ መብቱን ነው  የጠየቀው፡፡ ይሄን ያህል ለሀገር ደህንነት የሚያሰጋ ነገር ስለመኖሩ አስረጂ ማግኘት አይቻልም፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚጠይቅበት አይደለም፡፡ የህዝቡ ጥያቄ የመብት ጥያቄ ነው፡፡ ይሄ ጥያቄ የበለጠ መብትን የሚጥስ አዋጅ በማወጅ አይመለስም፡፡ ምላሽ ሊያገኝ የሚችልበት ብቸኛ መንገድ፣ ውይይትና ፖለቲካዊ ማሻሻያ ነው። አሁን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ግን ይሄን ውይይትና የፖለቲካ ንግግር ለማድረግ አይመችም። አዋጁ የበለጠ ጉዳዩን አክርሮ፣ በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ እንዳይፈጥር ስጋት አለኝ፡፡ ጉዳዩንም የበለጠ ያሰፋዋል እንጂ አያሻሽለውም። ህግና ቅጣት ማብዛት ወንጀልን አይቀንስም፡፡ የበለጠ ያባብሰዋል፡፡ በአጠቃላይ እንደኔ ምልከታ፣ ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚጋብዝ አይደለም፡፡
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን መልቀቃቸው ብዙም የሚያመጣው ለውጥ አለ ብዬ አልገምትም፡፡ ኃይለማርያም ቢሄዱ ሌላ ይመጣል፡፡ ሰውን መለወጡ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ ዋናው ስርአቱን ነው ማስተካከል የሚያስፈልገው፡፡ የአቶ ኃይለ ማርያም መለወጥ የፖሊሲ ለውጥ አይሆንም፡፡ የህዝቡ ጥያቄ የግለሰብ ለውጥ ሳይሆን የፖሊሲ ለውጥ ነው፡፡ ወሳኙ ጉዳይ፣ መሰረታዊ የህዝብን ጥያቄዎች መመለስ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ገዥው ፓርቲን፣ ተቃዋሚዎችን እንዲሁም የሲቪክ ማህበራትን ያካተተ የሽግግር መንግስት ቢቋቋም መልካም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡  

------------

            “መንግስት ከህዝብ ጋር እልህ መጋባት የለበትም”
               አቶ ሙሉጌታ አበበ (የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት)

    የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ በፍፁም የሀገሪቱን ችግር አይፈታም፡፡ ህገ መንግስታዊ ቢሆንም አዋጁን ዝም ብሎ ያለ ቦታውና ያለ አስፈላጊነት ማወጅ ህዝብንም መረበሽ ነው፡፡ እርግጥ ነው የተጀመሩ ለውጦች አሉ፡፡ የፖለቲካ እስረኞች እየተፈቱ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ፖለቲከኞችን እፈታለሁ፣ የሀገሪቱን ፖለቲካ አሻሽላለሁ ብሎ፣ ለተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ  ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ እንደገና ወደ አዋጅ መግባቱ ችግሩ ምን ያህል የተወሳሰበ መሆኑን ያሳየናል፡፡ ዛሬም ያልተፈቱ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት አሉ፣ የሃይማኖት አባቶች አሉ፡፡ የእነዚህን ወገኖች መፈታት ስንጠብቅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ተገቢ አይሆንም፡፡ እኛ በፓርቲ ደረጃ “ኢህአዴግ ለውጥ እያመጣ ነው፣ እየተሻሻለ ነው” ብለን እንቅስቃሴውን በበጎ እየተመለከትን ባለበት ወቅት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ እምነታችንን አጨልሞታል፡፡ የህዝቡንም ጥያቄ ሆነ የኛን ጥያቄ የሚያዳፍንና ለውጥ ሊያመጣ የማይችል ውሳኔ ነው፡፡ መንግስት ሆኖ ከህዝብ ጋር እልህ መጋባት ተገቢ አይደለም፡፡
ህዝቡ ዲሞክራሲንና ለውጥን ሲጠይቅ፣ በተቃራኒው ዲሞክራሲንና መብትን የሚገድብ አዋጅ ማወጅ ጤናማነት አይደለም፡፡ ህዝቡ እኮ ያን ያህል ትልቅ ነገር አልጠየቀም፡፡ የጠየቀው ዲሞክራሲ፣ ነፃነትና መብት ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከዚህ አንፃር ያለ ጊዜውና ያለ ቦታው የመጣ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን እለቃለሁ ማለታቸው፣ ያን ያህል ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያለው አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሀገሪቱ ከፍተኛ ስልጣን ያለው በፓርቲው እጅ ነው፣ እሳቸውንም በቀጥታ የመረጣቸው ፓርቲያቸው ነው፤ ስለዚህ አዲስ ነገር የለውም፡፡ ሰውየው ስልጣን ላይ ሆነው፣ በብሄራዊ መግባባትና በሀገራዊ እርቅ ላይ መስራት ነበረባቸው፡፡ ምናልባት ይሄን ቢያደርጉ ኖሮ፣ የህሊና ነፃነት ያገኙ ነበር፡፡

------------

              “ለህዝቡ ጥያቄ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መልስ አይሆንም”
                 ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ (የመድረክ አመራር)

    ባለፈው ዓመት ለ10 ወራት የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የፈጠረው አዲስ ነገር አልነበረም። የህዝቡ ጥያቄ ሳይመለስ  ነው ወደዚህኛው የተሸጋገረው። እርግጥ ነው በወቅቱ ሰው ጎንበስ ብሎ አሳልፎት ሊሆን ይችላል፤ ግን ጥያቄውን በውስጡ ይዞ ነበር። ለዚህ ነው አሁን በድጋሚ የተነሳው፡፡ ይህም አሁን የተጣለው አዋጅ ከዚህ የተለየ ውጤት አይኖረውም። ወሳኙ የህዝቡን ጥያቄ በመመለስ ማረጋጋት ነው፡፡ መንግስት ይሄን ማድረግ አልቻለም፡፡
ለህዝቡ ጥያቄ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መልስ አይሆንም፡፡ አዋጁ ሲነሳ ተመልሰን ወደ ችግሩ መግባታችን  አይቀርም። ለዚህ አርቆ ማሰብ እንዴት ያቅታል? እርግጥ ነው፣ አዋጁ ገዥው ፓርቲ፣ ጊዜ ለመግዣ ይጠቅመዋል፡፡ የገባበትን ንፋስ አስወጥቶ ስልጣኑን ለማጠናከርም ጊዜ ይሰጠው ይሆናል፡፡ በመጨረሻ ግን መልካም ውጤት አያመጣም፡፡ በየትም ሀገር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ዘላቂ መፍትሄ ሆኖ አያውቅም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ ስልጣን መልቀቃቸው፣ ያን ያህል ፖለቲካዊ ትርጉም ያለው አይደለም፡፡ አቶ ኃይለማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት የድርጅቱ ሊቀ መንበር ስለሆኑ ነው  እንጂ በህዝቡ በቀጥታ አይደለም የተመረጡት። ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚሉት ጉዳይም ከሰላማዊ ሽግግር ውጪ ምን አማራጭ አላቸው? ያስብላል፡፡
ምክንያቱም አቶ ኃይለማርያም በፓርቲ ግምገማ ብዙዎችን ጥለው ሊቀ መንበር እንደሆኑ ሁሉ፣ በፓርቲ ግምገማ ከሊቀ መንበርነታቸው መውረዳቸው አይቀርም፡፡ ይሄ በኮሚኒስት ስርአት ውስጥ የተለመደ ነው፡፡
ስለዚህ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚሉትም ሆነ ስልጣን መልቀቃቸው እምብዛም ትርጉም የለውም፡፡ ዋናው የስልጣን አቅም ያለው ድርጅቱ ላይ ነው፡፡ ሀገሪቷን እያስተዳደረ ያለው የፓርቲ መስመር እንጂ አቶ ኃይለማርያም አልነበሩም፡፡ ወሳኙ ጉዳይ፣ የዚህ መስመር መሻሻል ወይም መለወጥ ነው፡፡

--------------

             “የአዋጁ መታወጅ ጤናማ አይደለም”
               መላኩ መለሰ (የኢራፓ ዋና ፀሐፊ)

    በማንኛውም ሀገር ለህዝቡ ጥፋትና ለሀገሪቱ ህልውና አስጊ ሁኔታ ሲፈጠር  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የተለመደ ነው፡፡ ወደኛ ሀገር ስንመጣ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው   ኢትዮጵያውያን አደጋ ላይ በሚወድቁበት ጊዜ ሳይሆን የመብት ጥያቄ በሚያነሱ ወቅት ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ የስልጣን ማስጠበቂያ ነው የሆነው፡፡ መንግስት በጥልቀት ታድሻለሁ ባለበት ወቅት፣ ወጣቶች ጥያቄ በሚያነሱበትና ሀገሪቱ የለውጥ ፍላጎት ባሳየችበት ሰአት ይሄ አዋጅ መታወጁ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ መንግስት ይሄን አዋጅ ለማወጅ ያነሳሳው ምናልባት ከሚቀርብበት ተቃውሞ ፋታ ለማግኘት አሊያም ጥያቄዎችን በጉልበት ከማፈን ፍላጎት ይሆናል፡፡ ይህ አይነቱ አካሄድ መድረሻችንን አደገኛ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ምናልባትም ወደ ወታደራዊ አገዛዝ ወርደን ወደ ባሰ አረንቋም ልንዘፈቅ እንችል ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ የአዋጁ መታወጅ ጤናማ አይደለም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን መልቀቃቸው በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ እንደሚታሰበው፣ ያን ያህል ለውጥ የሚያመጣ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ የእሳቸው ስልጣን መልቀቅ ሁለት ነገሮችን ያመላክተናል፡፡ አንደኛው ኢህአዴግ ራሱ መረጋጋት እንዳቃተው፣ ሁለተኛው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲወርዱ፣ ህዝቡ ፓርቲው እንደወረደ አድርጎ በማሳየት የፖለቲካ ማደናገር ስራ ለመስራት ሊሆን ይችላል፡፡ ከእነዚህ ውጪ ሌላ ዓላማ አይኖረውም፡፡


--------------

               “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለኢህአዴግ ድርጅቶች የተጣለ ይመስለኛል”
                  አቶ ተማም አባቡልጋ (የህግ ባለሙያ)  


     አሁን ባለው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያስጥል ምክንያት  የለም። በኦሮሚያም በአማራም ክልሎች የምናየው የመብት ጥያቄዎች እንጂ ጦርነት አይደለም፡፡ ጦርነት በሌለበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የሚደገፍ አይደለም፡፡ ህጋዊ መሰረትም የለውም። ምናልባት ፖለቲካዊ ትርጉም ሊኖረው ይችላል። በህውሓት፣ ኦህዴድና ብአዴን መካከል ያለው ልዩነት እውነት መሆኑን የበለጠ እንድንገምት ያስገድደናል፡፡ ምክንያቱም መሬት ላይ ባለው ሃቅ፣ ይህን አዋጅ ለማወጅ የሚያስችል በቂ መነሻ የለም፤ ስለዚህ የውስጥ ችግራቸውን ለማስታመም ያወጁት ነው የሚመስለው፡፡ እኔ በፓርላማው ይፀድቃል የሚል እምነትም የለኝም፡፡
ህጋዊ ስላልሆነ ተቀባይነት አይኖረውም። የቀድሞው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በህዝቡ ላይ የተጣለ ነበር፡፡ ይሄኛው ግን በራሳቸው ድርጅቶች ላይ የጣሉት ነው የሚመስለው፡፡
በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልቀቅ በጎም ሆነ መጥፎ ውጤት አያመጣም፡፡ ምክንያቱም ስልጣን የተያዘው በነፃ አውጪዎች ነው፡፡ የነፃ አውጪዎች ኃይል፤ የዲሞክራሲ ምንጭ መሆን አይችልም፡፡ ሀገሪቱ እስከ ዛሬም በእነዚህ ኃይሎች እጅ ነው ያለችው፡፡ ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከዚህ አንፃር ያላቸው ስልጣን፣ ከሳቸው በኋላ ማን ይመጣል? የሚለውን የሚያስጠይቅ  አይደለም፡፡
የእሳቸው መውረድ የህዝብን ጥያቄም አይመልስም፡፡ ምክንያቱም የህዝቡ ጥያቄ፣ አቶ ኃይለማርያም ከስልጣን ይውረዱ የሚል አይደለም። ችግሮች የተያያዙት ከስርአቱ ጋር እንጂ ከግለሰብ ጋር አይደለም፡፡ አቶ ኃይለማርያም ራሳቸው የአሰራር ሰለባ ናቸው፡፡ ስለዚህ የእሳቸው ሥልጣን መለቀቅ ምንም ፖለቲካዊ ለውጥ አያመጣም፡፡

Read 3434 times