Sunday, 04 March 2018 00:00

እጩ ጠ/ሚኒስትሮች፤ የምረጡኝ ዘመቻ ያድርጉ!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(30 votes)

  · ለቀውስ ዘመን የሚመጥን፣ ብቃትና አቅም ያለው ጠ/ሚኒስትር ያስፈልገናል
   · የኢህአዴግ አባል ያልሆነ ጠ/ሚኒስትር መሾምም የማይቻል አይደለም
   · ኢህአዴግ፤ ከመረጠው ህዝብ ጋር “እንተዋወቃለን ወይ?” ይበል
         
    ላለፉት 27 ዓመታት ግድም በሥልጣን ላይ የዘለቀው ኢህአዴግ ነፍሴ፤ መቼም ከአፉ ተለይቶት የማያውቅ አንድ ዝነኛ አባባል አለው፤ “ዲሞክራሲ ለዚህች አገር የህልውና ጉዳይ ነው” የሚል፡፡ (ነው እንዴ?) ደጋግሞ የሚጠቅሰው ጉዳይ በመሆኑም ብዙዎች ሳይሸወዱ አልቀሩም፡፡ (ከአንጀቱ መስሏቸው!) ለበርካታ ዓመታት፤ “ጠንካራ የተቃዋሚ ፓርቲ የመፍጠር ህልም አለኝ” የሚል ኮሜዲ የሚመስል አነጋገር ነበረው፡፡ (ግን በምን ትዝ አለኝ!)
እናላችሁ-- አንዳንድ ደፋሮች፤”ያንን የህልውና ጉዳይ ነው ያልከውን ዲሞክራሲ የት አደረስከው?” ብለው ሲጠይቁት፣ ምን ይላል መሰላችሁ? “ዲሞክራሲ በአንድ ጀንበር የሚመጣ ሳይሆን ሂደት ነው!!” (ግልግል!) ግን “ሂደት”በዓመት ሲመነዘር ስንት ይሆናል? ይሄን ማለት ከጀመረ እኮ 30 ዓመት ሊሆነው  ነው!
በእርግጥ ኢህአዴግ ነፍሴ፣ በታሪኩ ገጥሞት የማያውቅ ህዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል ከገጠመው ወዲህ እንዲህ ዓይነቱን ዋዛና ፈዛዛ እርግፍ አድርጎ ትቶታል፡፡ (“እዬዬም ሲዳላ ነው” አሉ!) በውጥረትና በድንጋጤ ወቅት እንዴት ሊያፌዝ ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ “ልማታዊ ፓርቲያችን” ኢህአዴግ፤ ከህዝባዊ ተቃውሞና አመፁ አያሌ ዓመታት በፊት የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት ከመናዘዝ ችላ ብሎ አያውቅም። (በግምገማ ባህሉ!) እናም -- የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የፍትህ እጦት፣ ኢ-ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ወዘተ-- ህዝቡን እንዳማረረው አሳምሮ ያውቅ ነበር፡፡ ምናልባት የማያውቀው---- ብሶትና ምሬት የተከማቸበት  ህዝብ ምን እንደሚያደርግ ነው፡፡ (አጋጥሞት አያውቅማ!) እናም አመጽና ተቃውሞው ዱብዳ ሳይሆንበት አልቀረም፡፡ እንኳን ዕድሜ ልኩን ህዝባዊ መሰረት አለኝ ሲል የከረመ መንግስትን ቀርቶ ማንም ያስደነግጣል። ቁም ነገሩ ከድንጋጤው ሲወጣ ምን ሰራ ነው? (ራሱን አረጋግቶ አገር ማረጋጋት ግን አልቻለም!) ለካስ አገርን በሰላም ዘመን መምራትና በቀውጢ ዘመን መምራት ለየቅል ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ብለው ብለው ሲያቅታቸው ነው፤ ሥልጣን እለቃለሁ ያሉት፡፡ (ዘገየ እንጂ ይደነቃል!)  
የኢህአዴግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አለመሳካቱን ሳስብ ሁሌም ትዝ የሚለኝ፣ የህውሓት አንጋፋ ታጋይና የአየር ሃይል አዛዥ የነበሩት ብ/ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት የተናገሩት ነው፡፡ ብ/ጄኔራሉ በአንድ ወቅት ለዚሁ ጋዜጣ እንደገለጹት፤ “ኢህአዴግ የ60ዎቹ አማፂ ትውልድ ስብስብ በመሆኑ ዲሞክራሲን ሊያሰፍን አይችልም፤ ዲሞክራሲን ማምጣት የሚችለው ወጣቱ ትውልድ ነው፡፡”
ብ/ጄነራል አበበ እንደሚያስረዱት፤ “ኢህአዴግ ታግሎ ደርግን ከገረሰሰና ነፃነት ካመጣ በኋላ በሥልጣን ላይ መቆየቱ ነው ጥፋቱ፤ ለወጣቱ ትውልድ የስልጣን ሽግግር ማድረግ ነበረበት፡፡” ይሄን ባለማድረጉም ነው ዲሞክራሲ እስካሁን ድረስ በአገሪቱ መስፈን ያልቻለው፤ ይላሉ - አንጋፋው የህውሓት ታጋይ። (ለእሳቸው ዲሞክራሲን የማምጣት ተስፋ ያለው በወጣቱ ትውልድ ላይ እንጂ በአማፂው ትውልድ ላይ አይደለም!) አብዛኞቹ በሥልጣን ላይ የሚገኙ የኢህአዴግ አመራሮች፣ ይሄን ሀሳብ እንደሚያወግዙት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ (ሃሳብን በሃሳብ ከማሸፈን ይልቅ ማውገዝና መፈረጅ ይቀናቸዋል!)
ሆኖም ግን አመራሮቹም ራሳቸው ጨርሶ የማይክዱት አንድ እውነት አለ፡፡ ለግማሽ ክ/ዘመን ሲገዙት በቆዩት አገር ላይ ተስፋ ሰጪ የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዲያቆጠቁጥ እንኳን አላደረጉም! (ልማትና ዲሞክራሲ ለየቅል ናቸው!) ራሱን ኢህአዴግን ጨምሮ የአገሪቱ አያሌ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ዛሬም እንደ ትላንቱ፣ ችግሮችን በውይይትና በመነጋገር የመፍታት፣ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል አላደበሩም፡፡ እስቲ እንጠያየቅ----በእነዚህ ሁሉ ዓመታት፣ተዓማኒ የፍትህ ሥርዓት፣ የፖሊስ ተቋም፣ ነፃ ሚዲያ፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የምርጫ ቦርድ… ወዘተ (ኢህአዴግም ተቃዋሚዎችም በእኩል የሚያምኗቸው!) መፍጠር ችለናል?  
እናም --- ኢህአዴጎች ከ25 ዓመታት በላይ በሥልጣን ላይ የመቆየት ዕድል አግኝተው፣ በአገሪቱ ላይ የዲሞክራሲን ጭላንጭል ሊያሳዩን ካልቻሉ፣ ብ/ጄነራል አበበ ያሉት እውነት ሳይሆን አይቀርም። (አማራጭ እውነት የለንማ!) እናም ዲሞክራሲን ከወጣቱ ትውልድ ላይ ተግተን እንሻለን፡፡ በእርግጥም ደግሞ የተስፋ ጭላንጭል መታየት ጀምሯል፡፡ ምጸቱ ምን መሰላችሁ? የኢህአዴግ የእጅ ሥራ ውጤት ነው የሚባለው “ኦህዴድ”፣ ወጣት አመራሮች የዲሞክራሲ ተስፋ የሚፈነጥቅ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ሙጭጭ ኩምጭጭ የማይሉ፣ የለውጥ አራማጅ ወጣት አመራሮች! ከግል ሥልጣንና ከፓርቲ ክብር ይልቅ፣ ለህዝብና ለአገር ክብር ቅድሚያ እንደሚሰጡ በይፋ ያወጁ ብልህ፣ ዘመኑ የፈጠራቸው መሪዎች! (ኢህአዴግማ ሊፈጥራቸው አይችልም!) እንዲያም ሆኖም ግን ሊኮራ ይገባዋል፡፡ (እህት ድርጅቱን እየመሩ በመሆኑ!)
ወደ እናት ድርጅታችን ልመልሳችሁ፡፡ ኢህአዴግ ነፍሴ፣ ዛሬም ድረስ የሚፈታተነው ዋና ችግር፣ ለለውጥ ዳተኛ መሆኑ ነው፡፡ “በጦቢያ ምድር ላይ እኔና የእኔ ሃሳብ ብቻ ናቸው የሚነግሱት!” ከሚለው አቋሙ በተጨማሪ ማለት ነው፡፡ የትኞቹም ግን አልጠቀሙትም፡፡ ለምሳሌ፡- የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና አገራዊ መግባባት ለመፍጠር እንደሚጠቅም አምኖ፣ እርምጃ ለመውሰድ ስንት ዘመን ፈጀበት? ምናልባት ይሄን እርምጃ ከአንድ ዓመት በፊት ወስዶ ቢሆን ኖሮ፣ የብዙዎችን ህልፈት ይታደግ ነበር፡፡ ብዙ ንብረቶችንም ከውድመት ያተርፍ ነበር፡፡
የሆኖ ሆኖ ኢህአዴግ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን (በአጠራሩ ባይስማማም!) ከእስር መፍታቱ አይካድም፡፡ ያጣውን አመኔታ ለማግኘት በሚችልበት መልኩ ግን አልፈጸመውም፡፡ ጭራሽ የሌለ ቅድመ ሁኔታ ፈጥሮ፣ ተጨማሪ ተቃውሞና ብጥብጥ ፈጥሮ አረፈው፡፡ (ኢህአዴግና መርጦኛል የሚለው ህዝብ፤ “እንተዋወቃለን ወይ?” ያባባሉ!) ለነገሩ ኢህአዴግ ፖለቲከኞቹን የፈታውም ወዶና አምኖበት ሳይሆን ተገፍቶና ተገዶ ነው ይላሉ - ተቃዋሚዎች!! በሌላ በኩል፤ አንዳንድ የኢህአዴግ ካድሬዎች፣ የእስረኞችን በገፍ መፈታት አይተው፣ ወህኒ ቤቶች ኦናቸውን ሊቀሩ ነው ብለው መስጋታቸውን ሰምቻለሁ፡፡ (እኔም ስጋታቸውን እጋራቸዋለሁ!) ከእስር የተፈቱ አንጋፋ ፖለቲከኞች በበኩላቸው፤ “ከተፈታነው በላይ ታሳሪዎች በየወህኒ ቤቶቹ ስለሚገኙ እነሱም በአፋጣኝ ይፈቱ” ሲሉ መንግስትን ጠይቀዋል። (የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ ታሳሪዎች የሚፈቱበት እንጂ ተረኞች የሚታሰሩበት መሆን የለበትም!) ያለዚያ እኮ በቀውስ አዙሪት መቀጠላችን ነው፡፡(አንድዬ ይሁነን!)
በነገራችን ላይ ፖለቲካዊ መፍትሄ ዘግይቷል ወይም ረፍዶበታል አይባልም፡፡ እናም … የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ አሁን ጥያቄው ምን መሰላችሁ? እስረኞች ተፈቱ፤ ከዚያስ? ቀጣዩ እርምጃ ምንድን  ነው? የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፤ የእስረኞች መፈታት ብቻውን በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ የሚያመጣው  ለውጥ አይኖርም፡፡ (ኢህአዴግ ነፍሴን ብዙ ቀጣይ ሥራዎች ይጠብቁታል ማለት ነው!) ለዚህ ዝግጁ ይሆን? (የብዙዎች ጥያቄና ጥርጣሬ ነው!)
ከተቃዋሚዎችና የአገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል ከሚሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይትና ድርድር ማካሄድ፣ የዲሞክራሲ ተቋማትን እንደገና ማዋቀር፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር… እንዲሁም ለህዝብ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት  የኢህአዴግ አጣዳፊ ሥራዎች ናቸው፡፡ (ለዓመታት የተወዘፉ በመሆናቸው ውስብስብና ፈታኝ ይመስላሉ!) ግን ደግሞ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ እርግጠኛ ነኝ… ኢህአዴግ፤ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት ብቻ እፎይ ብሎ እንቅልፉን ሊለጥጥ አያስብም። (መች ተነካና!)፡፡ እናላችሁ ፖለቲከኞችን ከእስር እንደፈታው ሁሉ ፖለቲከውንም ከእስር መፍታት ይጠበቅበታል - ከተቀፈደደበት የብረት ካቴና ነፃ ማውጣት! በነገራችን ላይ የህግ የበላይነትን በማስፈንንና ህገ መንግስቱን ሳይሸራረፍ በማክበር ብቻ የሚፈቱ አንዳንድ ችግሮች አሉ፡፡ (ክፋቱ ግን ያቃተን እሱ ነው!!)  
ወደ ኦህዴድ እንመለስ፡፡ የእነ አቶ ለማ መገርሳ አመራር፣ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት ትኩረትና ተቀባይነት ማግኘት እንደቻለ የሚታወቅ ነው፡፡ አንደኛ፤ መሪዎቹ መናገር ይችሉበታል - አንደበተ ርዕቱ ናቸው። ተናግረው ያሳምናሉ፡፡ ህዝብ ያከብራሉ፡፡ በዚያ ላይ ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን በማቀንቀን፣ ህዝቡ ላለፉት 27 ዓመታት የጎደለበትን የአገር ፍቅር ስሜት ሞሉለት፡፡ በኢትዮጵያዊነት መንፈስና ጸጋ አጥለቀለቁት፡፡ በቀላሉም የብዙዎችን ልብ አሸነፉ። የለማ መገርሳ፤ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!” ዝነኛ አባባል የዓመቱ ሳይሆን የክፍለ ዘመኑ ጥቅስ ነው!! ዶ/ር አብይ አህመድ ደግሞ በአንድ ንግግራቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፡- “--እቺ አገር ካለፈው ትውልድ የወረስናት ሳይሆን ከመጪው ትውልድ ላይ የተዋስናት ናት--” (ማራኪ ጥቅስ ነው!)  
አዲሱ የኦህዴድ አመራሮች፣ የአገራችንን ለዘመናት የዘለቀ፣ እርስ በእርስ የመጨራረስና የመጠላለፍ፣ የጥላቻ ፖለቲካ፤ ታሪክ (ተረት!) ሊያደርጉት ጉዞ የጀመሩ ይመስላሉ፡፡ ኦህዴድ በቅርቡ ባወጣው መግለጫው፤ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ  ለሚገኙ የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአብረን እንስራ ጥሪ በማቅረብ ፈር ቀዳጅ ሆኗል። (በእርግጥ ጥሪ ማቅረብና አብሮ መሥራት ለየቅል ናቸው!) ሌላ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በቅርቡ ከእስር ለተፈቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ የኦሮሚያ ህዝብ ደማቅ አቀባበል ባደረገላቸው ወቅት ከክልሉ ፖሊስ የጠበቃቸው የወትሮው ወከባና ማስፈራሪያ አይደለም፡፡ አጀብና ጥበቃ እንጂ፡፡ (ህዝብን ማክበር ማለት ይሄ ነው!) በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እንደውም፣ የከተማዋ ከንቲባ ሳይቀሩ በአቀባበሉ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል አሉ፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ፣ አዲስ ክስተት ይመስለኛል፡፡ “Only in Oromia” በማለት ብቻ የሚገለጽ!! (ለጊዜው በሌላ ቦታ አይታሰብማ!)
ሌላ “Only in Oromia” ልጥቀስላችሁ። ያን ሰሞን የኦህዴድ ሊቀመንበሩ የአቶ ለማ መገርሳ፣ የምክትላቸው ዶ/ር አብይ አህመድና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ዶ/ር መረራ ጉዲና ፎቶዎች፣ አንድ ላይ ተደርድረው፣ በመኪናና ባጃጆች ላይ ተለጥፈው ታይተዋል፡፡ (ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚ በአንድ ላይ ማለት ነው!!) አያችሁ ህዝብ ሲወድ እንዲህ ነው!! (ፓርቲ ለይቶ አይደለም!)
የኦህዴድ ወጣት የአመራር ቡድን፤አዎንታዊ የለውጥ እርምጃ (“የመጨመር ፍልስፍና” በሉት!) ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ለቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ለዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በቅርቡ ያደረገው በጎ ተግባር አነቃቂ ነው - ለተደረገላቸው ብቻ ሳይሆን መረጃውን ለሰሙት ጭምር፡፡ (አገር ዜጎቿን ስታከብር፣ ለራሷም ክብር ነው!!) እናላችሁ -- ከራሳቸው ከዶ/ር ነጋሶ አንደበት እንደሰማናው፤ ከኢህአዴግ በገዛ ፈቃዳቸው በለቀቁ ማግስት የተለየ የፖለቲካ አቋም መያዛቸውን ተከትሎ፣ ላለፉት 13 ዓመታት ከመንግስት ማግኘት የሚገባቸውን መብቶችና ጥቅማጥቅሞች ተነፍገው ቆይተዋል። በዚህም የተነሳ ለከፋ የኑሮ ችግር መዳረጋቸውን የቀድሞው  ፕሬዚዳንት ይናገራሉ፡፡ ከጀርመናዊት ባለቤታቸው ጋር የሚበላ አጥተው የተቸገሩበት ጊዜ እንደነበረ ያስታውሳሉ፡፡ ለ13 ዓመታት የህክምና ወጪያቸውን የሸፈኑላቸው ጀርመናዊት ባለቤታቸው ነበሩ - ነጋሶ እንደተናገሩት፡፡ (ጀርመናዊቷ፤ የፖለቲካ ሥርዓታችንን መታዘባቸው አይቀርብም!?)
የኦህዴድ ወጣት አመራሮች፣ ደግነትን ከፍቅር ባጣመረ እርምጃቸው፣ የጥላቻ ፖለቲካን ሰብረውታል። (የጥላቻ ማርከሻው ፍቅር ብቻ ነው!!) የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ ለቀድሞው ፕሬዚዳንት ለዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ የ3ሚ. ብር ዘመናዊ አውቶሞቢል በስጦታ አበርክቶላቸዋል። የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር የህክምና ወጪያቸውም ይሸፍንላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ በአማካሪነት እንዲሰሩ ቦታ በመስጠትም የወር ደሞዝ እንደሚቆረጥላቸው ታውቋል፡፡ (ጀርመናዊት ባለቤታቸው ሳይቀሩ፣ ኦህዴድን አመስግነዋል!)
እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ዜጎችና  የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በኦህዴድ ተግባር ተደስተዋል፡፡ ለድርጅቱም  የነበራቸውን አመለካከት እንደለወጡ ይናገራሉ፡፡ (ዕድሜ ለመሪዎቹ!) ከኢህአዴግ ነፍሴም እንዲህ ዓይነት ለውጥ እንሻለን - ሥር ነቀል!! በእርግጥ ይሄን የኦህዴድ ለውጥ፤ሌሎቹ እህት ድርጅቶች እንዴት እንዳዩት (መቼም በጎሪጥ አይሆንም!) ማወቅ በእጅጉ ያጓጓል፡፡  
ከጠ/ሚኒስትርነት ሥልጣናቸው የመልቀቅ  ጥያቄ ያቀረቡትን ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርም ደሳለኝ፣ የሚተካ አዲስ ጠ/ሚኒስትር በቅርቡ እንደሚሾም ይጠበቃል - በተለመደው ኢህአዴጋዊ አሰራር። እናም ከብአዴን አቶ ደመቀ መኮንን፣ ከዴህዴን አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ከኦህዴድ ዶ/ር አብይ አህመድ የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ለመሆን በእጩነት ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል ዶ/ር አብይ አህመድ ተከታዩ ጠ/ሚኒስትር ሆነው ሊመረጡ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡ (እኔም በግሌ አቶ ለማ መገርሳ ወይም ዶ/ር አብይ ቢመረጡ ደስታዬ ነው!) ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ለጠ/ሚኒስትርነት የሚመረጠው ግለሰብ እንዳለመታደል ሆኖ “የሰላም ዘመን መሪ” አይደለም፡፡ ይልቁንም “የቀውስ ዘመን መሪ” ነው የሚሆነው፡፡ እናም… አገሪቱን ከገባችበት ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ በማውጣት፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የማምጣት ልዩ ጥበብና ብልሃት የታደለ መሪ መሆን  ይገባል። ይታያችሁ --- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ የምትገኝ አገር ነው ተረክቦ የሚመራው፡፡  
ባለፈው ሳምንት ተፈሪ መኮንን የተባሉ ጸሀፊ፤ “የጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ዘመን” በሚል ርዕስ ባስነበቡት መጣጥፍ፤ “የዛሬዋ ኢትዮጵያ ልዩ ችሎታ ያለው፤ አዲስ ጎዳና ለመከተል የማይፈራ መሪ ትፈልጋለች” ብለዋል፡፡ እኔም ሃሳባቸውን እጋራለሁ። ግን ከየት ይመጣል ነው? ስጋቴ፡፡ ያውም በኢህአዴጋዊ አመራረጥ፡፡ እንደኔ በአሁን ሰዓት ከብአዴን፣ ከኦህዴድ፣ ከህውሃት ወዘተ በሚለው ላይ ባናተኩር ነው የሚሻለው። በየዓመቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅባት አገር፣ የፓርቲ ክብርና ሥልጣን ሊያስጨንቀን አይገባም፡፡ (“የአስቸኳይ ጊዜ ጠ/ሚኒስትር” ነው የሚያስፈልገን!) ከሁሉ አስቀድሞ እቺን አገር ከጥፋት ልናድናት ይገባል። አገር ሲኖር ነው ሥልጣንም የሚኖረው፡፡ (እዬዬ ሲዳላ ነው!) እናም ጠ/ሚኒስትሩ የኢህአዴግ አባል ባይሆኑም እንኳን ሊያሳስበን አይገባም። ዋናው ነገር፤ አገሪቱን የሚታደግ ብቃት ያለው መሪ ማግኘቱ ነው፡፡ (እዚህ ድረስ ማሰብ አለብን!) በ97 ምርጫ ማግስት፣ በአዲስ አበባ ከንቲባነት የተሾሙት  የኢህአዴግ አባል አልነበሩም!!
በሌላ በኩል፤ ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች የተወከሉ እጩ ጠ/ሚኒስትሮችም ቢሆኑ ከወትሮው በተለየ መንገድ ቢመረጡ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ። የምንሻው አገሪቱን ከቀውስና ከውስብስብ ችግሮች የሚያወጣ መሪ እንደመሆኑ፣ እጩዎቹ በቴሌቪዥን የምረጡኝ ዘመቻ ለምን አይወዳደሩም፡፡ እጩዎቹ፤ እንዴት አገሪቱን ከተዘፈቀችበት ፖለቲካዊ ቀውስ እንደሚያወጧትና እንደሚያረጋጓት፣ የህዝቡን ጥያቄዎች እንዴት በአፋጣኝ እንደሚመልሱ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩበትን አማራጮች፣ በእጅጉ የጠበበውን የፖለቲካ ምህዳር እንዴት እንደሚያሰፉት፣ ለተቃውሞ የሚወጡ ዜጎች ህይወት ሳይጠፋ ተቃውሟቸውን ገልጸው በሰላም ወደ ቤት የሚገቡበት መንገድ፣ ከዳግም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዴት እንደሚገላግሉን፣ ምን ዓይነት ለውጥ እንደሚተገብሩ፣ እንዴት በህዝቡ ውስጥ  አገራዊ የአንድነት ስሜት መፍጠር እንደሚችሉ… ወዘተ ጥበብና ብልሃታቸውን በዝርዝር ይንገሩን፡፡ እናም በመጨረሻ አንጀት ላይ ጠብ የሚል አሳማኝ ሀሳብ ያቀረበው እጩ ተወዳዳሪ፤ የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ሆኖ ቢመረጥ ይበጃል ብዬ አስባለሁ፡፡ መሃል መንገድ ላይ ወገቤን ብለው ከሚያቋርጡ መጀመሪያውኑ ቢጣሩ ለነሱም ለአገርም ይጠቅማል፡፡ ለምሳሌ ከጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ፣ የአመራር ዘይቤ በምን ይለያሉ? የማይለዩ ከሆነ እሳቸውን መድገም ነው የሚሆነው? (ከንቱ ድካም!!)
የምስራቅ አፍሪካ የጂኦ ፖለቲካ ምሁር፣ ፕሮፌሰር መድኃኔ ታደሰ፣ ተተኪው ጠ/ሚኒስትር የአገሪቱን ችግር እንዴት ሊፈቱ ይችላሉ የሚለውን በተመለከተ ሰሞኑን ለሚዲያ በሰጡት አስተያየት፤ ”አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ምን ዓይነት የፖሊሲ ለውጥና የፖለቲካ ሂደት ይከተላሉ የሚለው ነው ዋናው ጉዳይ፤ተተኪው ጠ/ሚኒስትር የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በትክክል ማንበብና የችግሮቹን ጥልቀትና ስፋት በትክክል የሚረዱ ከሆነ መልሱ ቀላል ነው፡፡” ብለዋል፡፡ (ያቅልልን!) ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!!!

Read 8195 times