Sunday, 01 April 2018 00:00

የፖለቲካ አለመረጋጋቱን የፈጠረው የኢኮኖሚ ችግር ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 *የገንዘብ አስተዳደሩ ከፍተኛ ችግር እንዳለበት መንግስት መገንዘብ አለበት
     *ተቃውሞዎቹ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ነው
     *የገበያ መር ኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው መተግበር የነበረብን

    ባለፉት አስር ዓመታት በአገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ቢመዘገብም ከሌሎች ጥያቄዎች በተጨማሪ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አለመስፈን የፖለቲካ አለመረጋጋት ፈጥሯል፡፡ የፖለቲካው አለመረጋጋት በኢኮኖሚው ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው? ዘላቂ ጉዳቱ በምን ይገለጻል? እንዴት ከዚህ ውስብስብ ችግር መውጣት ይቻላል? መንግስት የፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ ዝግጁ ነው? በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ፤ በፖለቲካው አለመረጋጋትና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖው ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

    በአገሪቱ የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት በኢኮኖሚው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑ ይነገራል። ለአለመረጋጋቱ  መንስኤው ምንድን ነው ይላሉ?
ለአለመረጋጋቱ ዋነኛ መንስኤው ኢኮኖሚ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ችግሩ ባለመረጋጋቱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በልማታዊ መንግስት ስርአት ውስጥ ሃገርን ለማሣደግ ሦስት ምሰሶዎች ናቸው ያሉት፡፡ አንዱ መንግስት ነው፡፡ መንግስት ፖሊሲ፣ስትራቴጂና መዋዕለ ንዋይ በማዘጋጀትና ዋስትና በመስጠት የራሱን ሚና ይጫወታል። የሃገሪቱን እቅድም ያወጣል፡፡ መዋዕለ ንዋይ በማመንጨት እርሻና ኢንዱስትሪን በማስፋፋት፣ ከየኮሌጁ የሚወጡትን የሰው ሃይል በመቅጠር ደግሞ የግል ዘርፉ የራሱን ሚና ይጫወታል። ሦስተኛው የአካዳሚክ ማህበረሰቡ ነው፡፡ በሃገራችን የተጀመረው የዩኒቨርሲቲ መስፋፋትን ተከትሎ፣ የሚሠሩ ምርምሮች፣ የተለያየ ሃሣብ በማቅረብ ሃገሪቱን ማሳደግ የሚል የፖሊሲ ሀሳብ በማመንጨት፣ለመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ ግብአት ያቀርባሉ፡፡
በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በህግና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ አካዳሚክሱ ሰፋፊ የጥናት ውጤቶችን በማቅረብ፣ ለፖሊሲና ህግ አውጪዎች ማቅረብ አለባቸው። በትክክለኛው የልማታዊ መንግስት አስተሳሰብ የሚመሩ መንግስታት እነዚህን ሦስት ነገሮች ነው በዋናነት የሚጠቀሙት፡፡ ለምሣሌ ቻይናን ብንመለከት፣ ስልጣን ላይ ያለው የኮሚኒስት ፓርቲ ሆኖ፣ በየጊዜው የሚቀርቡለትን ማሻሻያዎች እየተቀበለ፣ ራሱን እያደሰ ይሰራል። በዚህም ምክንያት ዛሬ በዓለም የታወቁ ኩባንያዎች መሰባሰቢያቸውን ቻይና እያደረጉ ነው፡፡ የአሜሪካኖቹ ታዋቂ ኩባንያዎች አፕል፣ ማይክሮሶፍት የመሳሰሉት እስከ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ሃብት ቻይና ውስጥ ነው እያንቀሳቀሱ ያሉት። ስለዚህ የፖሊሲ ፍተሻና ለውጥ እንደውም በየዓመቱ ነው መካሄድ ያለበት፡፡ ወደዚህ አቅጣጫ የምንሄድበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል። ለምሳሌ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ሃገር ቤት ይመጣል ይባላል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ኢንቨስተሮች ሲወጡ እናያለን፡፡ ለምሣሌ በእርሻ ላይ የተሠማሩ የውጭ ኢንቨስተሮች በሙሉ ለቀው መውጣታቸው ተሰምቷል፡፡ ለምንድን ነው እነዚህ ኢንቨስተሮች እየወጡ ያሉት? ችግሩ የቱ ጋ ነው ያለው? እነዚህ ጉዳዮች በየጊዜው በሚደረግ የፖሊሲ ፍተሻ ምላሽ ማግኘት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በየዓመቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ከዩኒቨርሲቲ እየወጡ ነው። ይህ ሃይል የት ነው የሚገባው? ለዚህ ሃይል ምን የተመቻቸ ነገር አለ? እነዚህ ሁሉ በፖሊሲ ፍተሻ መልስ የሚሹ ናቸው፡፡
አሁን ያለውን ያለመረጋጋት ያመጣው አንደኛው ጉዳይ በርከት ያሉ የተማሩ ወጣቶች ስራ አጥ መሆናቸው ነው፡፡ እነዚህን ስራ ያጡ ወጣቶች፣ በየትኛውም አጀንዳ ጠልፎ የአመፅ አካል ማድረግ ቀላል ነው፡፡ በኢትዮጵያ አንድ ጎሣ ሌላኛውን ሊያጠፋ የተነሣበት ጊዜ በታሪክ የለም፡፡ አሁን ግን እንዲህ ያለው ነገር እየተለመደና እየተስፋፋ ነው፡፡ ስለዚህ በትኩረት ሊታሰብበትና መፍትሄ ሊበጅለት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ያሉት ጥያቄዎች ዋነኛ ምክንያት አድጓል የምንለው ኢኮኖሚ ህዝብ ጋር አለመድረስ ነው፡፡
መንግስት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ፍላጎት ያሳየበት ወቅት አለ? አሁንስ ማሻሻያ ለማድረግ ዝግጁ ነው ይላሉ?
በሽግግሩ ጊዜ አንድ የኢኮኖሚክ ሲምፖዚየም ተካሂዶ ነበር፡፡ የሲምፖዚየሙ አላማ ደግሞ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለማውጣት ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ወደ አራት መቶ ያህል ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ባለሙያዎች ተጋብዘው ነበር፡፡ የአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የባንክ ሃላፊዎችን ጨምሮ በርካታ የሃገሪቱ ምሁራን ተሳትፈውበታል። መድረኩን እኔ ነበርኩ ያስተባበርኩት። ያን ጊዜ የወጣው የገበያ መር ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትክክለኛ ፖሊሲ ነበር፡፡ እሱን ፖሊሲ ነበር መተግበር የነበረብን። እዚያ ፖሊሲ ውስጥ ለምሳሌ የፋይናንስ ስርአቱ አሁን እየተተገበረ ባለው መንገድ መሆን እንደሌለበት ይጠቁማል፡፡
የገበያ መር ኢኮኖሚ ሲባል፣ አንድ ገበያ የሚያስፈልጉትን ነገሮች በሙሉ ማደራጀት ይጠይቃል። ሰዎች አክሲዮን የሚሸጡበትና የሚገዙበት፣ ለግል የቢዝነስ ፈጣሪዎች ብድር የሚመቻችበት፣ ብድሩን ተጠቅመው አዳብረው የሚመልሱበት አካሄድ መከተል ያስፈልግ ነበር። አሁን እነዚህ ሁሉ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ አልተተገበሩም፡፡ ለምሣሌ ባንኮችን ብንመለከት፣ ጅቡቲ ምንም ኤክስፖርት የምታደርገው ነገር ሳይኖራት ከኢትዮጵያ የወደብ ኪራይ በመቀበል ብቻ 8 ያህል የውጭ ባንኮችን አስገብታለች፡፡ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ ተመሳሳይ ነገር ነው ያደረጉት። ታዲያ እኛ ከማን ነው የምንለየው? ከዚህ አንፃር ጥሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አልተገበርንም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመመርያ ደረጃ ነው መውጣት ያለበት እንጂ በህዝብ ተወካዮች በተደነገገ ህግ አይደለም፡፡
የፖሊሲ ችግር አለ ሲባል ምን ማለት ነው?
አንዴ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ስንል፣ እሱ አልሠራ ሲል ደግሞ ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስት እያልን ነው የመጣነው፡፡ በዚህ መልኩ ሃገሪቱ ላይ ሙከራ እየተሰራ ነው ዛሬ  ያለንበት ደረጃ ላይ የደረስነው፡፡ ረብሻና ብጥብጥ ውስጥ የገባነው ለዚህ ነው፡፡ አቶ ሃይለማርያም ስልጣን ሲለቁ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ መሰለኝ፤ ከፀሃፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ በኋላ። አቶ ሃይለማርያም በተደላደለ የፖለቲካ ሁኔታና በአንድ ፓርቲ በምትመራ ሃገር ላይ “ስልጣን እለቃለሁ” ሲሉ ትርጉሙ ስራ መስራት አቅቷቸዋል ማለት ነው። የህዝቡን ጥያቄ መመለስ ስላልተቻለ ነው ስልጣን የለቀቁት። የኢትዮጵያ ህዝብ 17 አመት ሙሉ ደርግን ችሎ ኖሯል፡፡ በአሁኑ መንግስት የተሠራው ልማት ደግሞ ምናልባትም በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛው ነው። 5ሺህ ኪ.ሜ የባቡር መስመር፣ 70 ሺህ ኪ.ሜ መንገድ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ግድቦች፣ የንፋስ ሃይል ማመንጫ የመሣሠሉ ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር ሊወስዱን የሚችሉ ስራዎችን የሠራ መንግስት ነው። ነገር ግን ህዝቡ የት ነው ያለው? ምን ደረጃ ላይ ነው? የሚለውን ዞሮ ማየት አልቻለም፡፡  
በልማት በኩል ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል፤ ኢኮኖሚውም በየዓመቱ 11 በመቶ እድገት እያስመዘገበ መሆኑን ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ኢኮኖሚያዊ እድገትና  የህዝቡ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዴት ነው የሚታረቁት? በሌላ በኩል ህዝባዊ ተቃውሞና የንብረት ውድመት በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ እንዴት ይገለጻል?
አሁንም ተቃውሞዎቹ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ነው እየፈጠሩ ያሉት፡፡ ኢንቨስተሮች ስራቸውን መስራት ያልቻሉበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። የፖለቲካ ችግር ያለባቸው ክልሎች ደግሞ ሰፊ የማምረቻ መሣሪያ የሚንቀሳቀሱባቸው፣ መሠረታዊ ጥሬ እቃዎች ያሉባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ የኢንዱስትሪ ማዕከላት፣ የውሃና መብራት ምንጮች በስፋት ያሉት በእነዚህ አካባቢዎች ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች  ኢንቨስተሮች መስራት የማይችሉ ከሆነ ምርት ማመንጨት አይቻልም፡፡ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ የውጪ ምንዛሬ እጥረቱ አለ፡፡ ፋብሪካዎች በጥሬ እቃና መለዋወጫ እጦት እየቆሙ ነው ያሉት፡፡ የገንዘብ አስተዳደሩ ከፍተኛ ችግር እንዳለበት መንግስት መገንዘብ አለበት። እኔ የሚያሳዝነኝ ነገር በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት አለመደረጉ  ነው፡፡ ህዝባዊ ውይይት የለም፡፡ በሚዲያ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች ሰፊ ውይይት ሊካሄድበት ይገባል። ይሄ በአገራችን ገና አልተጀመረም፡፡ በአንፃሩ እነ ኒውዮርክ ታይምስ፣ ፎሬይን ፖሊሲ ማጋዚን የመሳሰሉት “የኢትዮጵያ የብሔር ፌደራሊዝም አልሠራም፤ ሃገሪቱ ልትፈራርስ ነው” እያሉ የውይይት አጀንዳ ሲያደርጉት፣ እኛ ጋ ውይይቱ የለም፡፡
እነ ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ ትልቅ የቲንክ ታንክ ስብስብ ያላቸው ቡድኖች ናቸው፡፡ የኛን ጉዳይ እነሡ ናቸው የሚተነትኑት፡፡ ይህ ለምን ሆነ? እዚያ ደረጃስ ለምን ደረሰ? ኢትዮጵያ እኮ የአንድ ፓርቲ ብቻ ሳትሆን የ105 ሚሊዮን ህዝብ እንዲሁም የብዙ ምሁራንና ልሂቃን ሃገር ነች፡፡
 የአሜሪካ የንግድ ውድድሮችን ይመራ የነበረው’ኮ ኢትዮጵያዊ ነው - በኦባማ ዘመን። በአፍሪካ ልማት ባንክ የአሜሪካ ተወካይ ኢትዮጵያዊት ነበረች፡፡ በከፍተኛ የአመራር ደረጃ ላይ ተቀምጠው የአሜሪካን ግዙፍ ባንኮች የሚመሩ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ኢትዮጵያ አሁን አምስት የተባበሩት መንግስታት ምክትል ዋና ፀሃፊዎች አሏት፡፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ በራሳቸው ጥረትና ባላቸው እውቀት እዚያ የደረሱ እንጂ በሹመት የሄዱ አይደሉም። እነዚህ ሰዎች ወደ አገራቸው መጥተው የሚሰሩበትን ዕድል ማመቻቸት አለብን። በሃገር ውስጥም ብዙ ችሎታ ያላቸው ሰዎች አሉ። እነዚህንም ሰዎች ማሰራትና ማሳተፍ ያስፈልጋል። መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንከር ያለ አቋም በመውሰድ  ሃገሪቱ ወደፊት የምትገሰግስበትን ሁኔታ መፍጠር  አለበት፡፡
ይህቺ ታሪካዊ ሃገር እንዳትፈራርስ፣ ተጠናክራ እንድትቀጥል ከፍተኛ ጥረት መደረግ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ለምሣሌ በሶማሌ ክልል ነዳጅ ተገኝቷል። ክልሉ ከኦሮሚያ ጋር ያለውን ችግር እንደ ሰበብ አድርጎ፣ አንቀፅ ጠቅሶ፣ ልገንጠል ቢል ምን ሊኮን ነው? ይሄ በጥልቀት መታሰብ አለበት፡፡ የውጭ ሚዲያዎች ይሄን ስጋት ነው የሚጽፉት፡፡ ለምሣሌ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ማለትም እነ ሂውማን ራይትስዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የመሳሰሉት አዲስ አበባ መጥተው ቢሮ ቢከፍቱ፣ መንግስት ሆን ብሎ የሰው መብት አይጥስም፣ የፖለቲካ እስረኞችን አያሰቃይም ነበር። በእኔ እምነት፤ የፖለቲካ ምህዳሩ ብቻ ሣይሆን የማህበራዊ መድረኩ ሰፋ ብሎ በነፃነት ሃሳቦች ሊንሸራሸሩ ይገባል፡፡
መንግስት ከህዝቡ ጋር ቀጥተኛ ውይይት ማድረግ አለበት እንጂ የወረዳ አስተዳደር ብቻ መግለጫ መስጠት የለበትም፡፡ የሙስና ተጠያቂነት መጠናከር አለበት። ለምሣሌ በስኳር ኮርፖሬሽን 77 ቢሊዮን ብር ጠፋ ተባለ፤ ግን የተጠየቀ ሰው አላየንም፡፡ በእንዲህ ያሉ ጉዳዮች መንግስት ብዙ ሥራዎች ይጠብቁታል፡፡
በየጊዜው የሚካሄዱ አድማዎች በኢኮኖሚውና በኢንቨስትመንት ላይ የሚያደርሱት ተጽዕኖ  ምን ያህል ነው?
እንኳን ለቀናት ስራ ማቆም ይቅርና ለአንድ ቀን ማቆም ከፍተኛና የተወሳሰበ ችግር ነው የሚፈጥረው። ትልቁ ችግር ወጣቱ “ለካ ይሄን ማድረግ እችላለሁ” በሚል ሁኔታውን ተለማምዶ፣ ለወደፊቱ ትንንሽ ሽፍታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። በሁለተኛ ደረጃ ብዙ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሾች በፍርሃት ስራቸውን እንዲያቆሙ ያደርጋል። ለምሳሌ ከሰሞኑ የነዳጅ አመላላሽ ተሸከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ በመባሉ ፈርተው መኪናቸውን ያቆሙ ባለንብረቶች እንዳሉ አውቃለሁ። ምክንያቱም ከተቃጠለባቸው ኢንሹራንስም የሚከፍላቸው አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ አድማዎች የሚፈጥሩት አንዱ ችግር፣ ስጋትና ፍርሃት ነው። በሶስተኛ ደረጃ ከውጭ የሚመጡ እቃዎች በተስተጓጎሉ ቁጥር የገቢው እና የአቅርቦት ስሪት ይበላሻል፡፡ ይሄን ለማስተካከል ጊዜ ይፈጃል፡፡ በሌላ በኩል “መንግስት የለም” የሚል አመለካከትም እንዲፈጠርና መተማመን እንዲጠፋ ያደርጋል፡፡ ይሄም ችግሩን ዘላቂ ሊያደርገው ይችላል፡፡
በአንድ አገር ላይ የፖለቲካ አለመረጋጋት የሚፈጥረው ዘላቂ ጉዳት ምንድን ነው?
ጉዳቱ ለትውልድ የሚቀር ነው የሚሆነው። ይሄ በሌላው የአፍሪካ ሃገርም የምናየው ነው፡፡ በፀረ ቅኝ አገዛዝ ፅንፈኝነት፣ እነ ናይጄሪያ አሁንም ድረስ እየታመሱ ነው ያሉት፡፡ ናይጄሪያ በተባበሩት መንግስታት ሃላፊነት ሰርቻለሁ፡፡ በስምንት ወታደር  ታጅቤ ነበር ቢሮ የምሄደው፡፡ በደቡብ አፍሪካ፣የፀረ አፓርታይድ በነበረው አስተሳሰብ ዛሬም ጥቃቶች ይፈፀማሉ፡፡ የባህል የአመለካከት ለውጥ ያመጣል። ሰው ተስማምቶ የማይሠራበት ሁኔታ ይፈጠራል። መጀመሪያ ላይ ብዙ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ ጎርፈው የመጡት እኮ ሠላም አለ፤ ህዝቡ ጨዋ፣ ሃይማኖተኛ ነው በሚል ነበር፡፡ አሁን ግን ወጣቱ ንብረት እያነደደ መሆኑን ሲመለከቱ ይደነግጣሉ። ይህን ስርአት ማስያዝ ካልተቻለ ወጣቱ ድርጊቱን እየተለማመደው ይሄዳል፡፡ ስለዚህ ነባሩ ባህላችን እንዳይበላሽ፣ ከፍተኛ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመድሃኒትና የሸቀጦች ዋጋ እየጨመረ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው?
አንዱ የምንዛሪ መጨመር ነው፡፡ ብሄራዊ ባንክ ለምን የብር የመግዛት አቅምን እንደቀነሰ ማንም እስካሁን አልገባውም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በሃገሪቱ  የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ያመጣው ደግሞ ሃገሪቱ ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክት መዘርጋቷና ለእነዚህ የምታሟላው ግብአት በውጭ ምንዛሪ የሚገዙ መሆናቸው ነው። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ የውጭ ካፒታል አለመኖሩ ነው፡፡ የውጭ ባንኮችና የፋይናንስ ኩባንያዎች ወደ ሃገር ውስጥ ካልገቡ ችግሩ ይቀጥላል፡፡

Read 2524 times