Sunday, 01 April 2018 00:00

“መንግስት ጉልበቱን እንዲቀንስ መታገል አለብን”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 • ወጣቶች በሁሉም ዘርፍ የሚሳተፉበትን መንገድ መሻት አለብን
 • ውጤት የሚመጣው መንግስት ህዝብን መፍራት ሲጀምር ነው
 • ኢህአዴግ ያለ ህዝብ ቅቡልነት የትም ሊደርስ አይችልም
 • ምን ዓይነት ዲሞክራሲ እንደምንፈልግ ግልፅ አይደለም

     ኢህአዴግ ዶ/ር አብይ አህመድን የኢህአዴግ ሦስተኛው ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡ ከአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ምን ይጠበቃል?
አገሪቱን ከገባችበት ፖለቲካዊ ቀውስ የማውጣት አቅምና ብቃቱ ይኖራቸው ይሆን? በአገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት አቶ ክቡር ገና፤ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡

    የአዲሱን ጠ/ሚኒስትር ምርጫ እንዴት አገኙት?
አሁን ጥሩ አካሄድ የተጀመረ ይመስለኛል፡፡ በኢህአዴግ በኩል ባለፉት ሳምንታት ነገሮች የመጡበት ሂደት አበረታች ናቸው። ለህዝብ ግልፅ ባይሆንም ኢህአዴግም በስብሰባው የተለያዩ ጉዳዮችን ተመልክቷል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በመጨረሻም አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ተመርጧል፡፡ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የለውጥ አንቅስቃሴም የህዝቡ የለውጥ ፍላጎት አጋዥ የሚሆን ይመስለኛል፡፡
አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መመረጡ ብቻውን ትርጉም አያመጣም፤ የፖሊሲ ለውጥ ያስፈልጋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡--
በመጀመሪያ የኢህአዴግን አሰራር ማወቅ አለብን፡፡ እንደ ፓርቲ፣ ከሌሎች ፓርቲዎች የተለየ ነው፡፡ የተለየ የሚያደርገው ጠቅላላ ኢትዮጵያ ውስጥ የራሱ የእግር አሻራ ይታያል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎች የሱን ያህል ስፋትና ውክልና አላቸው ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ ሁለተኛ አሰራሩ ራሱ የመንግስት ስርአቱ አካል እንዲሆን አድርጎታል። ህግ አውጪ፣ ህግ ተርጓሚና ህግ አስፈፃሚ ከሚባሉት ሦስት የመንግሥት አካላት በተጨማሪ ኢህአዴግ ራሱ አራተኛው ነው ማለት እንችላለን። በዚህ አይን ስናየው፣ በጠቅላይ ሚኒስትር አመራረጥ ላይ አሁን የተገኘው ለውጥ፣ ከበፊቱ በተሻለ መልኩ ወደሚፈለገው ለውጥ ለመሄድ የሚያስችል ይመስለኛል፡፡
የኢህአዴግን  የ27 ዓመታት የፖለቲካ ጉዞ  እንዴት ያዩታል?
ከአጀማመሩ አሁን እስካለንበት ወቅት ድረስ የኢህአዴግ አካሄድ የህዝብ አመኔታ ነበረው አልነበረውም የሚለው አከራካሪ ነው፡፡ እርግጥ ነው በልማቱ መስክ የተገኙት ውጤቶች የፖለቲካውን ያህል አከራካሪ አይደሉም፡፡ የልማት መንደርደሪያ ሊሆኑ የሚችሉ መሰረተ ልማቶች ተሰርተዋል፡፡ ግድቦች፣ የባቡር መስመሮች ተዘርግተዋል፡፡ የኢኮኖሚ እድገትም ታይቷል፡፡ ድርቅም በመጣና በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በረሃብ በተጠቃ ጊዜ፣ ያንን ችግር ለመፍታት ጥሩ ጥረት አድርጓል። እነዚህ ጥሩ ነገሮች ናቸው፡፡ ለቀጣይ መሰረትም ይሆናሉ፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ህዝብ የሚጠይቀው አለ፡፡ አጠቃላይ ኢኮኖሚው (GDP) እድገት ቢያመጣም በየቤቱ ግን አልገባም፤ ሁለተኛ በዲሞክራሲ ተሳትፎ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ናቸው፤ ይሄን እድል ያገኙት፡፡ እነዚህ የህዝቡ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እስካሁንም መልስ አላገኙም፡፡ ለወደፊት ይመጣሉ ብለን ተስፋ ከምናደርግባቸው መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ባለፉት 27 ዓመታት ኢህአዴግ የህዝብ ተደማጭነት አለኝ ብሎ ቢጓዝም በመጨረሻ ግን እሱ ራሱ “በእርግጥ የህዝብ ተደማጭነትና ቅቡልነት አለኝ?” ብሎ እንዲጠይቅ የተገደደበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ኢህአዴግ “ውስጣችን ተበላሽቷል፣ ህዝቡ በሚፈልገን ልክ አልሆንም” የሚለው ከዚህ ግምገማው በመነሳት ይመስለኛል፡፡ አሁን  እሱን መልሶ የማግኘት ትግል እያደረገ ያለ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ ማወቅ ያለበት ከዚህ በፊት ያስመዘገባቸው ስኬቶች፣ ለትናንሽ ድክመቶቹና ስህተቶቹ ዋስትና ሊሆኑት እንደማይችል ነው፡፡
ኢህአዴግ በኢኮኖሚው ላይ ያስገኘውን ውጤት በዲሞክራሲው ላይ ለምን መድገም አቃተው?
በሁሉም ነገር ውጤት ይመጣል ብሎ ማሰብ ያስችግራል። ለአንዱ የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለሌላው ጉዳይ ላይሰጥ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ለኢኮኖሚው የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ስለነበር ጥሩ ውጤት ተገኝቷል፡፡ ለዲሞክራሲው የተሰጠው ትኩረት ግን አነጋጋሪ ነው፡፡ ምን አይነት ዲሞክራሲ እንደምንፈልግ በግልፅ አይታወቅም፡፡ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ እንፈልጋለን ይባላል ነገር ግን ለመድብለ ፓርቲ ስርአት የሚመሩንን መንገዶች አንከፍትም፡፡ በአንድ በኩል በብሄር መጓዙ ትክክል ነው እንላለን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ማራመድ እንፈልጋለን፡፡ እነዚህ ነገሮች በሙሉ እንደገና ሊታዩና ሊጣጣሙ በሚችሉበት መንገድ እንዲሄዱ ማድረግ ቢቻል ጥሩ ነው፡፡ ብዙ ሰው ሀገሪቱ ትበታተናለች የሚል ስጋት አለው። ለኔ እዚህ ጫፍ ላይ የደረስን አይመስለኝም፡፡ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች በጊዜ ካልተስተካከሉ ግን ወደዚያው ማምራታችን አይቀርም፡፡
ምንድን ናቸው እነዚህ መስተካከል ያሉባቸው ጉዳዮች?
አንዱና ትልቁ ጉዳይ ለወጣቱ እድል መስጠት ነው፡፡ ሌላው ባለፉት ዓመታት አፈንግጠው የወጡ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮች መስመር ካልያዙ፣ ጠቅላላ ሃገሪቱን ወደ ውድቀት ነው የሚወስዱት፡፡
ኢህአዴግ ራሱ ህገ መንግስቱን የመተግበር ችግር እንዳለበት ጠቁሟል፡፡ ከሦስቱ የመንግሥት አካላት አሰራር አንጻርስ ምንድን ናቸው ጉድለቶቹ? ለወደፊትስ ምን መደረግ አለበት?
የኢህአዴግ አሰራር ለሦስቱ የመንግስት አካላት (ህግ አውጪ፣ ተርጓሚ፣ አስፈፃሚ) ያመቻል ወይ የሚለው በራሱ ጥያቄ ነው፡፡ በኔ አተያይ ለእነዚህ ሦስቱ የመንግስት አካላት፣ የኢህአዴግ አሰራር የተመቸ አይደለም፡፡ እነዚህን አካላት ለያይቶ ለማየት የቻለም አይመስለኝም፡፡ በአሰራርም በአስተሳሰብም አንድ የማድረግና የፓርቲው አካል አድርጎ የመመልከት ነገር ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህገ መንግስቱ እነዚህ አካላት የተለያዩ እንደሆኑ ያስቀምጣል፤ ስለዚህ ለእነዚህ ጉዳዮች ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ጉዳይ፣ ወዴት ነው የምንሄደው? የሚለው ነው። መድረሻችንን ካሰብን፣ እነዚህን ከፓርቲው ነፃ ማድረግ አያዳግትም። ሚዲያውን መክፈት፣ የሲቪክ ሶሳይቲውን ማጠናከር ይህን ተከትሎ የሚመጣ ነው፡፡ የእነ ለማ ቡድን ይህን ሀገር ወዴት ነው የሚወስዱት? ፍልስፍናቸው ከቀድሞ የኢህአዴግ አሰራር የተለየ ነው ወይ? የሚለውን ማወቅ ነው ወሳኙ፡፡ ይሄንን ደግሞ በቀጣይ የሥራ ጊዜያቸው የምናየው ይሆናል፡፡
በኢህአዴግ የተደረገው የአዲስ ጠ/ሚኒስትር ምርጫ በአገሪቱ ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?
በስብሰባቸው ምን ተነጋግረው ይህን ለውጥ እንዳደረጉ አናውቅም፡፡ ኢህአዴግ እንዴት ለዚህ በቃ የሚለውን ከእነሱ ነው መረዳት የሚቻለው፡፡ የልማቱ ጉዳይ ላይ የተለየ አዲስ ሃሳብ ሲያቀርቡ አልሰማንም ወይም የዲሞክራሲና የመብት ጉዳይ አሁን ካለበት ወዴት ሊወስዱት እንዳሰቡ አልነገሩንም፤ አዲስ የትምህርት አቅጣጫ አላስቀመጡልንም፡፡ ኦህዴድ የያዘው የኢህአዴግን አቋም ነው፡፡ በመሰረቱ ትግሉ የነበረው ማን ጠቅላይ ሚኒስትር ይሁን የሚለው ላይ ይመስለኛል። አደገኛ የሚሆነውም ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ብቻ ስናተኩር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለብቻው ብዙም የሚያመጣው ነገር የለም፡፡ ለብቻው ለውጥ ማምጣት ከፈለገ ከኢህአዴግ መውጣት የሚጠበቅበት ይመስለኛል፡፡ ወይም ኦህዴድ ከኢህአዴግ መውጣት ይኖርበታል። ለዚህ የተዘጋጁ ግን አይመስለኝም፡፡
አገሪቱን ከፖለቲካ ቀውስ ለማውጣት ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ምን ይጠበቃል?
እንደ ቀድሞው ተሃድሶ አድርገናል ምናምን እየተባለ መቀጠል አስቸጋሪ ነው፡፡ በመጀመሪያ ሰላም ያስፈልጋል። ሰው የህግ የበላይነት እንዲኖር ይፈልጋል፤ ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት አለበት፡፡ ይሄ በአጭር ጊዜ ውስጥ መሆን አለበት። ህዝቡ በህግ መመራት አለበት፡፡ አሁን በህግ እየተመራን አይደለም፤ በአዋጅ ነው የምንመራው፡፡ ሁለተኛው፤ መሰረታዊ የሆኑ ለውጦችን ለማምጣት የተጠያቂነት ደንቦችን፣ ህጎችን ማውጣት አለበት። መንግስት ተጠያቂ መሆን አለበት፡፡ ሙስና የተስፋፋው የሚወጡት ህጎች እርስ በእርስ የማይስማሙ፣ ሩቅ የማይጓዙ በመሆናቸው ነው። ይሄን አሰራር መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ ሦስተኛው፤ የፖለቲካ መድረኩን ማስፋት ነው፡፡ ጋዜጦች ነፃ መሆን አለባቸው፤ ሰው እንደፈለገ መሰብሰብ መቻል አለበት፡፡ በቀጣይ ሁለት ዓመት ውስጥ መንግስት ህዝብን መፍራት መጀመር አለበት፡፡ አሁን መንግስትን የሚፈራው ህዝብ ነው፡፡ ውጤት መምጣት የሚችለው መንግስት ህዝብን መፍራት ሲችል ነው፡፡ መዋጋት ያለብን መንግስት ጉልበቱን እንዲቀንስ ነው፡፡ ህዝብ የራሱን መብት ማስከበር አለበት፡፡
እርስዎ በግልዎ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተስፋ ያደርጋሉ?
አዎ በጣም አደርጋለሁ፡፡ ኢህአዴግ ጠንካራም ደካማም ጎን አለው፡፡ ለኔ ኢህአዴግ የማይጥመኝ ኪራይ ሰብሳቢነቱ ነው፡፡ ለሙስና የሚያዘጋጅ መንገድ መክፈቱ ነው የማይጥመኝ፡፡ ከዚህ በመለስ በልማት ጠንካራ ስራ ሰርቷል፡፡ ውጤት ያመጡ ጠንካራ ፖሊሲዎች አሉት። ነገር ግን ፖሊሲዎች ዘላለማዊ መሆን የለባቸውም። ከወቅቱ ጋር ታይተው መፈተሽ አለባቸው፡፡ ዘመናዊ ሀገር መፍጠር መቻል አለብን፡፡ እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ አማራ ነኝ፣ ትግራዋይ ነኝ ከሚለው አመለካከት መውጣት አለብን፡፡ ኢትዮጵያዊነት ነው ወይስ ብሄር መቅደም ያለበት? ለሚለውም ምላሽ መስጠት መቻል አለብን። ይሄን ለመመለስ ውይይቶች መካሄድ አለባቸው፤ ጥናቶች መጠናት አለባቸው። የተቃዋሚዎች ድምፅ መሰማት ይገባዋል፡፡ የኢንተርኔት ሀገር መፍጠር መቻል አለብን፡፡ ወጣቶች በሁሉም ዘርፍ የሚሳተፉበትን መንገድ መሻት ይኖርብናል፡፡ ይሄ ሃገር ነፃ ሆኖ የሌላ ዓለም ዜጋ ለመኖር የሚጓጓለት መሆን አለበት፡፡    

Read 2418 times