Sunday, 01 April 2018 00:00

ኢህአዴግ አቅቶታል፤ እስቲ እኛ ቤቱን እናጽዳለት!

Written by  ማርቆስ ረታ
Rate this item
(7 votes)


     “--ዛሬ ስለ ኢህአዴግ ስናስብ ይኸው አዲሱ የአንድነት፥ የፍቅርና የኢትዮጵያዊነት ኃይል ሊዘነጋ አይችልም። በአዲሱ
ኃይል ምክንያት የኢህአዴግ ማንነት ተዥጎርጉሯል፤ በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ይወከል የነበረው ወጥ አቋሙ/ማንነቱ፣
አሁን ቢያንስ ብቸኛ አማራጭ መሆኑ ቀርቷል።--”
     ማርቆስ ረታ

    (ካለፈው የቀጠለ)
2. የኢህአዴግ መሠረታዊ ድርጅት ነክ ችግሮች
ኢህአዴግ ራሱ በሚያደርስብን በደል መሰቃየታችን ሳያንስ ጭራሽ እሱ ደረሰብኝ የሚለው ቀውስ በሚጎትተው ጦስም ስንጨነቅ ኖረናል። በእውነቱ ቢያንስ በውስጡ የሚፈጠር የድርጅት ጉዳይ ሊያሳስበን አይገባም ነበር። ሆኖም ‘የራሱ ጉዳይ፥ እኛን ምን አገባን’ ብለን እንዳንተወው ችግሩ በአገር ላይ የመጣ ነው ተብሎ፥ ያገር ሰላም በሚያደፈርሱ ግጭቶች ታጅቦ ይቀርብልናል። ኢህአዴግ በረዥም የስልጣን ዘመኑ ባራመደው ልዩነት ተኮር አጀንዳ የተፈጠረው እውነታ እንዲሁ የሚተዉት አይደለም - የድርጅቱን ብተና ያገር አስመስሎ በማቅረብና በግጭት በማጀብ የሚያስጨንቀን የህዝቡን ያገር ፍቅር አውቆ አይደለም? በሌላ በኩል ለረዥም ጊዜ የተዘነጋውን በማስታወስ አንድነትና ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩ መሪዎች ከኢህአዴግ መካከል ዛሬ ብቅ ማለታቸውን ተመልክተናል። ዛሬ ስለ ኢህአዴግ ስናስብ ይኸው አዲሱ የአንድነት፥ የፍቅርና የኢትዮጵያዊነት ኃይል ሊዘነጋ አይችልም። በአዲሱ ኃይል ምክንያት የኢህአዴግ ማንነት ተዥጎርጉሯል፤ በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ይወከል የነበረው ወጥ አቋሙ/ማንነቱ፣ አሁን ቢያንስ ብቸኛ አማራጭ መሆኑ ቀርቷል። ስለሆነም ድርጅቱ ወደፊት ችግሮቹን ለመፍታት የሚጓዝበት መንገድና የሚያራምደው ዓላማ ምንም ቢሆን ከቀድሞ የተለየ ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለ ለማለት ይቻላል። ጥናንጥ ምልክቶችም ታይተዋል።
ኢህአዴግ የፌዴራል መንግሥት ስልጣን ለመያዝ የሚያስችል ህብረ-ብሄራዊ አደረጃጀት በመሆኑ አባል ድርጅቶቹንና በነሱም አማካይነት የክልል መንግስታትን በአንድ የእዝ ሰንሰለት ሥር በማስገባት በተለይ ለመሪው በአገሪቱና በፓርቲዎቹ ላይ ፍጹም ስልጣን ያስጨበጠ አስተማማኝ መንገድ ሆኖ ቆይቷል። ግንባሩ በዚህ ቁመናው እንዳለ ነበር አቶ ኃይለማሪያም መሪነቱን የተረከቡት። ከዚያ በኋላ ጥቃቅንም ቢሆኑ አንዳንድ ለውጦች ታይተዋል። ለምሳሌ በአቶ መለስ ጊዜ ኢህአዴግ ከሹመኞቹ የሚፈልገው ከችሎታ ይልቅ ታማኝነትን ነበር፤ በአቶ ኃይለማርያም ጊዜ ግን ችሎታ ያለው ባለሙያ አባልም ባይሆን ሊሾም እንደሚችል በ2008 ዓ.ም ታይቷል። በተጨማሪ ኢህአዴግ ‘ብሔራዊ መግባባትን’ በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የሚመኙ ተቃዋሚዎች የሚያቀርቡት ሃሳብ ነው ብሎ ሲያጣጥለው እናስታውሳለን፤ አሁን ግን ቢያንስ አስፈላጊነቱን ሳይገነዘብ አልቀረም። እንዲያውም ለዚሁ መግባባት ሲባል የፖለቲካ እስረኞች “የሉም” ብሎ በመሸምጠጥ ፋንታ “አሉ፤ እንፈታማለን” በማለት እነሆ ፕ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ ከመቶ በላይ፥ በክልሎችም በሺ የሚቆጠሩ ታሳሪዎች ነጻ ወጥተዋል። አባል ድርጅቶቹ በመግለጫዎቻቸው፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የአብረን እንስራ ጥሪ አስተላልፈዋል። ይህም ሁሉ ሆኖ አሁንም እውነተኛ ብሄራዊ መግባባት አልተፈጠረም። እንግዲህ ኢህአዴግ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ጤናማና በመርሕ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ሊኖረው የሚችለው ቅድሚያ የራሱን ድርጅታዊ ጤንነት መጠበቅ ሲችል ነው። በዐበይት አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚፈጠሩ የሐሳብ/አቋም ልዩነቶች የአባል ድርጅቶችን ግንኙነትና በተለይም አንድነቱን የሚፈትኑበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል እሙን ነው። በዚያን ጊዜ ልዩነቶችን ይዞ አንድ ላይ ለመጓዝም ሆነ ሌሎች የግንኙነት አማራጮችን ለመወሰን የቆመባቸው መርሆች በሁሉም አባላት ዘንድ የተከበሩና ልዩነት ባለበትም ቢሆን አስፈላጊውን ሥራ ከመስራት የማይከለክሉ ሊሆኑ ይገባል።
ከዚህ አንጻር ኢህአዴግ በአባል ድርጅቶቹ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመራበት ከፌዴራል ሥርዓቱ የተስማማና ደጋግሞ በሚያነሳው የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ የሚፈቅድለት የግንኙነት መርሕና አሠራር ማበጀት ያስፈልገዋል።
2.1 የኢህአዴግ አሐዳዊ መዋቅርና ፌደራላዊ የብዝኃነት ሥርዓት
ኢህአዴግ አራት ብሄራዊ ድርጅቶችን ያቀፈ እንደመሆኑ ህብረ - ብሄራዊ ድርጅት ሊባል ቢችልም አባል ድርጅቶችን በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ በአንድ የእዝ ሰንሰለት ማስገባቱና በድርጅቱ መዋቅር የበታቹ ለበላዩ ታዛዥ እንዲሆን ግድ ማለቱ የህብረ - ብሄራዊነት መገለጫ የሆነውን ብዝኃነትን እንዳያስተናግድ አስቸጋሪ ያደርግበታል። ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በሐሳብ ብዝኃነት   ፋንታ አንድ ሐሳብ፥ ለያንዳንዱ ችግርም የየራሱ መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ ሁሉንም በአንድ የመፍትሔ ሐሳብ ማስተናገድ፥ ባልተማከለ አስተዳደር ፋንታ ስልጣን በአንድ ድርጅት ብቻ ሳይሆን በአንድ ግለሰብ/ቡድን እንዲከማችና ውሳኔዎችም ከዚያ ብቻ እንዲመነጩ የሚያደርግ መርህ በመሆኑ ሲተች ኖሯል። ሆኖም የሐሳብ ብዝኃነትን እንዲያስተናግድ፣ ለተለያዩ ችግሮች ልዩ ልዩ የመፍትሄ አማራጮችን ለማበጀት በሚችልበት መልኩ ለማሻሻል ይቻል ይሆናል። አሁንም ቢሆን ‘እህ’ት ድርጅቶቹ የግንባሩን የፖሊሲ መርሆች ለያካባቢያቸው እንዲስማማ አድርገው ሊተገብሩ እንደሚችሉ በድርጅቱ ፕሮግራም ተደንግጓል። ሆኖም ያልተማከለውን የፌዴራል - ክልል - ዞን መዋቅር በተማከለ ሥልጣን ለመምራት የሚደረግ ጥረት ብዝኃነትና ተለያይነት ከሚጠይቁት ስልጣንን በውክልና የመስጠት ሁኔታ ጋር ተጣጥመው መሄዳቸው ያጠራጥራል፤ ከታሰበበት ግን የማይቻል አይደለም። ለጊዜው ግን ተጣረሶቹን መመልከት ግድ ነው።     
የአባል ድርጅቶች አንድነት በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ እስከተመራ ድረስ ዛሬ ባለው ሁኔታ እያንዳንዱ እህት ድርጅት ክልላዊ መንግሥትን እንደሚመራ ድርጅት በክልሉ ባለሙሉ ስልጣን ሲሆን እንደ አባል ድርጅት ደግሞ የኢህአዴግ የበታች መሆኑ ነው። ባንድ በኩል የፌዴራል ሥርዓቱ ለክልል መንግሥታት ከፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብነት ውጭ የሆነ ስልጣን ሲያጎናጽፍ፥ በሌላ በኩል የኢህአዴግ አሐዳዊ አደረጃጀት ሕገ መንግስቱ በግልጽ የሰጠውን ስልጣን አባል ድርጅቶቹን በሚመራው የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርሕ አማካይነት ከጀርባ ገብቶ ከፈቃዴ እንዳትወጡ ቢል፣ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የክልል መንግሥት በሚመሩበት ጊዜ ከእነ ሥልጣናቸው ለድርጅቱ የበላይ ተገዢ መሆን ሊኖርባቸው ነው። ዛሬ ከብሄራዊ ፓርቲ መሪነት ጋር የክልል ርዕሰ መስተዳድርነትን የደረቡት ፕሬዚደንቶች ባንድ በኩል ክልላዊ መብትና ስልጣናቸውን ለማስከበር፥ በሌላ በኩል አባል ለሆኑበት ፓርቲ የበላይ አካል ተገዢነታቸውን ለማረጋገጥ ሲጣጣሩ በተጣርሶሽ መወጠራቸው አይቀርም። ከዚህ አንጻር ባንድ በኩል የበታች አካል ለበላይ አካል እንዲገዛ በሚያስገድደው ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ ላይ በቆመው አሐዳዊና የተማከለ አደረጃጀቱ፣ በሌላ በኩል የፌዴራል ሥርዓቱን በሚቃኘው የብዝኃነት መርህና ያልተማከለ አስተዳደር መካከል ያለው ቅራኔ ኢህአዴግን መቼም የማይፋታው ዐቢይ ፈተና ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም። ምን ማድረግ ይቻላል?
አንዱ አማራጭ ስልጣን እንዳይማከል ተደርጎ የተዋቀረውን የፌዴራል ሥርዓት በመጻረር በድርጅቱ መዋቅር አማካይነት የድርጅት ብሎም የመንግሥት ስልጣን እንዲማከል የሚያደርገውን ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ማሻሻል አልያም መቀየር ነው። ሌላው አማራጭ ፓርቲውን ከመንግሥት መነጠል ሲሆን ይህም ማለት ለምሳሌ የአባል ድርጅት መሪዎች የክልልና የፌዴራል ባለስልጣናት ሆነው ሲሾሙ ለፓርቲው የሚኖራቸው ተጠሪነት በፓርቲ ጉዳዮች ብቻ የተወሰነና በተለይም የመንግሥትን ሥራ የማያካትት እንዲሆን አድርጎ ማሻሻል ነው። ይኸውም ከሥር እንደምንመለከተው፣ አንድነቱን በማይጎዳበት መልኩ ማከናወን የሚቻል ቢሆንም የአባል ድርጅቶች አንድነት ፋይዳም ራሱ ቢፈተሽ ምናልባት ለአንድነቱ የተሰጠው ቦታና ድርጅት የሚበትን ተግባር ሊፈጸም ይችላል የሚል ጥርጣሬ የሚፈጥረውን ጭንቀት በአግባቡ ለመረዳት ማገዙ አይቀርም።
 2.2 አባል ድርጅቶች ከኢህአዴጋዊ ‘አንድነት’ ሌላ አማራጭ የላቸውም?
የአባል ድርጅቶችን “አንድነት” በቦታው መኖሩን ለማረጋገጥ ሲል ነበር፣ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው ታህሳስ የመንግሥት ሥራ ሁሉ ትቶ ስብሰባ የተቀመጠው። በአንድነቱ ላይ የተነሳው ጥርጣሬ በኢህአዴግ ህልውና ላይ የተደቀነ አደጋ ተደርጎ በመቆጠሩ፣ የአባል ድርጅቶቹ የጭንቀት ምንጭ ከመሆኑም ባሻገር የመንግሥትን ባለስልጣናት፥ ከዚያም አልፎ ሕዝብን ሲያሸብር ተመልክተናል። ምናልባት ለአንድነቱ የተሰጠው ቦታ እጅግ ሳይጋነን አልቀረም። [ድርጅቱ ትጥቅ ያልፈታ መሆኑ የሚፈጥረውን ጫና ዝቅ ብለን እንመለከተዋለን።] ‘አንድነቱ’ በአባል ድርጅቶቹ ፍላጎትና ፈቃድ የተመሠረተ እስከሆነ ድረስ ፍላጎትና ፍቃድም ሊለወጥ የሚችል እንደመሆኑ መጠን አንድነቱ ሁሌም ባለበት ከመቀጠል ውጪ አማራጭ የሌለው ተደርጎ ሊታሰብ አይገባም። ምክንያቱም አንድነቱ ዓላማ ያለው እስከሆነ ድረስ ለምሳሌ ዓላማው ግቡን ከመታ አልያም ግቡን የማይመታ መስሎ የታየ እንደሆነ አንድነቱ ላይቀጥል ይችላልና ነው። ይልቁንም የግንባሩ አንድነት አባል ድርጅቶቹን እንዲያገለግልና በተናጠል የማያገኙትን ጥቅም/አገልግሎት የሚያገኙበት መድረክ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስችሉ አሠራሮችን ለመዘርጋት ጥረት ቢደረግ ፍሬያማ ሊሆን ይችላል።
ለምሳሌ አባል ድርጅቶቹ ለጋራ ግንባሩ ያለባቸው ግዴታ በተናጠል ሙሉ ሕጋዊ ሰውነት የሚያጎናጽፋቸውን ድርጅታዊ መብትና ስልጣን በብቃት ከመጠቀም የማይከለክል፥ [የክልላዊ መንግሥት ሥልጣን በሚይዙበት ጊዜም] የህዝብን ችግር ለመፍታት፥ ወይም በምርጫ ጊዜ ለመራጩ የገቡትን ቃል ለመፈጸም የሚያስፈልጉ እርምጃዎችን ለመተግበር የሚያስችላቸውን ሕገ መንግሥታዊ ስልጣን በአግባቡ ከመጠቀም የማይገድብ መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ የግንባሩን አወቃቀር ማስተካከል ይቻላል። ኢህአዴግ የብሄራዊ ድርጅቶች ጥምረት እንደመሆኑ፣ የድርጅቱን ዓላማ በፌዴራል መንግሥት በኩል በአገር ደረጃ ለመተግበር የሚያስችል ሥልጣን የሚገኝበት አንድ መንገድ እንደመሆኑ መጠን መንገዱ ለሁሉም እህት ድርጅቶቹ ክፍት መሆኑን ማረጋገጥ ለአንድነቱ መጎልበት ትልቅ አስተዋጽዖ ሊኖረው ይችላል። ስለሆነም አባል ድርጅቶቹ የጋራ ግንባሩን ሊቀ መንበርነት እንዲሁም [ምርጫ ባሸነፉ ጊዜ] ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን በዙር ለመቀባበል ሊስማሙ ይችላሉ። ይህም ከአባል ድርጅቶች መካከል ማንም የበለጠ ወይም ያነሰ ተጠቃሚ እንዳይሆን ከማድረጉም ባሻገር እያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት በፌዴራል መንግሥት ከመሳተፉም በተጨማሪ የየክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉ [የፓርቲም ሆኑ የመንግሥት] ሥራዎችን ለማከናወን ያስችለዋል።
በአንጻሩ አባል ድርጅቶቹ ዛሬ እንታገልለታለን የሚሉትን ፍትሐዊ ያልሆነ ሥርዓት መገንባትን የመሰለ አውቆ አጥፊነት ወይም የገበሬውን ብሎም ያገራችንን የምግብ ዋስትና በዋዣቂነቱ ከሚታወቀው የዓለም ገበያ ጋር ማቆራኘትን የመሰለ የፖሊሲ ዕዳ ለመሸከም መገደድ የለባቸውም። በሌላ በኩል የያንዳንዱ አባል ድርጅት እህትነት የሚነሳው በኢህአዴግ ሥር በሚሆኑበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን የየክልሎቻቸውን መንግሥታት በሚመሩበት ጊዜም ጭምር መሆኑን በመገንዘብ፣ ሁለትም ሦስትም ክልሎች ለጋራ ክልላዊ መደጋገፍና ብሎም ለጋራው አገራዊ ሰላም፥ ልማት፥ ፍቅርና አንድነት የሚበጁ ሥራዎችን ለማከናወን ያስችላቸዋል። ዝምድና መፍጠሩና ማዳበሩ መብታቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ኢህአዴግ አባላት እህት የተሰኙት ድርጅቶች፣ እንደ ክልል መሪዎች እህት/ወንድም ቢሆኑ የሚጠበቅ [ሊጠበቅም የሚገባ] በመሆኑ ነው።
ሆኖም ፓርቲዎቹ በኢህአዴግ አባልነታቸው የሚያደርጓቸው የርስ በርስ ግንኙነቶችን የሚመለከቱ መርሆችና ደንቦችን በማውጣት የተከለከሉና የተፈቀዱ፥ ያልተከለከሉና ለያንዳንዱ ድርጅት ምርጫ የተተዉ ጉዳዮችን በግልጽና በዝርዝር በማስቀመጥ፥ የሁሉን ይሁንታ ካገኙ በኋላም በጋራ መመሪያነት ተቀብሎ ማጽደቅ ቢቻል የአባል ድርጅቶቹ ግንኙነት ተቋማዊ መሠረት እንዲኖረው ያደርጋል። ለምሳሌ የኢህአዴግ መሪዎች ከግምገማው በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ የአመራር ችግር ተብለው ከተነሱት አንዱ መርሕ አልባ ግንኙነት ነው። ሆኖም “መርሕ አልባ ግንኙነት” ማለት ለምሳሌ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች መሪዎችና ሕዝቦች መካከል የተደረገው ዓይነት አለመሆኑን አቶ ደመቀ አስረድተዉናል። እሳቸው እስኪናገሩ ድረስ ግን መርሕ አልባ ሲባል ያንን ለመግለጽ የተጠቀሙበት ነበር የሚመስለው። ስለሆነም የአመራር አባላትን ግንኙነት መርሕ አልባ በማለት በቀላሉ የመፈረጅ አደጋን ለመከላከል ግልጽ የሆነ ትርጉምና የግንኙነት መርሆችን መዘርዘር አስፈላጊ መሆኑ አይቀርም። ሌላው የተነሳው ችግር ‘የኔ ወገን ለሚሉት ማድላት’ ነው ተብሏል። ሆኖም ‘የኔ ወገን ለሚሉት ማድላት’ በምን ይገለጻል? በህግና ደንብ፥ መመሪያ ወይም አሠራር ወይስ ሕገ ወጥ በሆነ ተግባር? በሕግ/ደንብ የሚገለጽ አድልዎ ለማረም አያስቸግርም፤ በዚያው ልክ የአመራር አባላትን ድርጊቶችና ግንኙነቶችን የሚመለከቱ መርሆችን በማስቀመጥ ተገቢና “መርህ አልባ” የሚሰኙትን ለመለየት፥ መልካሙን እያበረታቱ ጎጂውን ለማረም የሚያስችልና ሁሉንም የሚያግባባ መንገድ ለመቀየስ ይቻላል። በአመራሩ መካከል የሚኖረው ግንኙነትም የጋራ ግዴታውን ያልዘነጋና ሁሉም የተስማማባቸው መርሆችና ደንቦችን የተከተለ እስከሆነ ድረስ አባል ፓርቲዎች የሚያከናውኑት ሥራ ዞሮ ዞሮ፣ ከጋራ ድርጅታቸው ዓላማና ጥቅም ውጭ የመሆን ዕድሉ ጠባብ ነው። ይሁንና ከእህት ድርጅቶቹ አንዱ የፈጸመው ተግባር ከድርጅቱ ዓላማ ውጭ ነው/አይደለም የሚል ክርክር ቢነሳም በግልጽ የተቀመጡ መርሆችና ደንቦች መኖራቸው ለመካሰስና ለመዋቀስም ሆነ ለመማማር፥ ባጠቃላይ ለሚተላለፍ ውሳኔ ሁሉ ሕጋዊ መሠረት ተበጀለት ማለት ነው።
ከዚህም ባሻገር ከላይ እንደተጠቀሰው ወደፊት በአገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ ተዘርግቶ ጠንካራ ፓርቲዎች ተፈጥረው በክልልና በፌዴራል ምክር ቤቶች ፉክክሩ ጦፎ፥ ማንም ድርጅት ለብቻው መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል የወንበር ቁጥር የማያገኝበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል፥ በዚያን ጊዜም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመደራደርና በመዋሐድም ጭምር መሥራት አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ነው።
2.3 በመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ውስጥ የአባል ድርጅቶች ግንኙነት
በአገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እውን በሆነበት ሁኔታና እንዲሁም በግንባታው ሂደት አራቱ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች በግንባሩ ጥላ ሥር ሆነው በአንድነት፣ ለአንድ ዓላማ ቢሰለፉ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ከተፎካካሪዎች ጋር በሚያደርጓቸው ውድድሮች እርስ በርስ በመደጋገፍ አሸንፎ የመውጣት ዕድላቸውን ሊያሰፉ እንደሚችሉ ግልጽ ነው። በተፎካካሪዎች ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት የአንድነቱ አስፈላጊነት ባያከራክርም አንድነቱ ብቻውን አባል ድርጅቶች በየክልላቸው እንዲመረጡ ዋስትና አይሆናቸውም፤ አባል ድርጅቶቹ አንድ የጋራ ዓላማ በማራመዳቸው ምክንያትም በድልም ሆነ በሽንፈት ዕጣ ፈንታቸው የግድ አንድ አይሆንም። ለምሳሌ አንዱ የኢህአዴግ አባል ድርጅት በሚወዳደርበት ክልል በተፎካካሪ ፓርቲ ተበልጦ ቢሸነፍና በፌዴራል ም/ቤትም ጥቂት ወንበሮችን ብቻ ቢያገኝ፤ በአንጻሩ የተቀሩቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የየክልሎቻቸውንና የፌዴራል ም/ቤቶችን ወንበሮች ቢያሸንፉ፤ ግንባሩ ኢህአዴግ በሦስቱ አማካይነት የፌዴራል መንግስቱን ስልጣን ይይዛል፤ ሦስቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ደግሞ የየክልሎቻቸውን መንግሥታት ሥልጣን ይይዛሉ። የክልሉን መንግሥት ምክር ቤት ወንበሮች ለማሸነፍ ያልቻለው አራተኛው አባል ድርጅት በበኩሉ፤ የግል ዕጣ ፈንታው ለቀጣዩ ምርጫ መዘጋጀት መሆኑ አይቀርም።
እንዲሁም አራቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ያሸነፏቸው የፌዴራል ም/ቤት ወንበሮች ቁጥር መንግሥት ለመመስረት ከሚያስፈልገው በታች ሆኖ ቢገኝ፥ ኢህአዴግ መንግሥት ለመመስረት ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር መደራደርና አብሮ ለመስራት መስማማት ይኖርበታል። የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ያገኙት የክልል ም/ቤት ወንበር ቁጥርም እንዲሁ መንግሥት ለመመስረት በቂ ካልሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወክለው ም/ቤት ከገቡት አባላት ጋር በተናጠል መደራደር አማራጭ አይኖረውም። ከዚህ አንጻርም ሲታይ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች በአላማ እና/ወይም በአደረጃጀት አንድ ቢሰኙም ዕጣ ፈንታቸው የግድ አንድ ይሆናል ማለት አይደለም።
በተጨማሪ በአገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እውን በሚሆንበት ጊዜ እህት ድርጅቶቹ በክልል ደረጃ ሲወዳደሩም ሆነ በጋራ የፌዴራል መንግሥት ለማቋቋም ሲተባበሩ የእያንዳንዱ ድርሻ የተለያየ መሆኑ አይቀርም። እንዲያውም ሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች እንደመሆናቸው መጠን አንዱ ለሌላው ወሳኝ አስተዋጽኦ ሊያደርግ መቻሉ ያጠራጥራል። ከስልጣን አንጻርም የአባል ድርጅቶቹ መለያየት በራሱ በተናጠልም ሆነ በጋራ የሚያስከትልባቸው ጉዳት ለማየት ያስቸግራል። ለምሳሌ አራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ተለያይተው ለፌዴራል ም/ቤት ወንበሮች በጋራ ሳይሆን በተናጠል ተወዳደሩ እንበል። ከምርጫው በኋላ እያንዳንዱ ያሸነፈውን ወንበር ይዞ ሁሉም በፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መገናኘታቸው አይቀርም። [በክልል እንደሆነ አሁንም አይገናኙም።] ታዲያ በፌዴራል ምክር ቤት ተገናኝተው መንግሥት ለመመሥረት የግድ መደራደርና መስማማት ይኖርባቸዋል - ማለትም የዛሬዎቹ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ቢለያዩም እንኳ ተለያይተው አይለያዩም፤ የሚገናኙበት የጋራቸው የሆነው የፌዴራል ም/ቤት አለና። እንዲያውም ከዚህ አኳያ ሲታይ አራቱም እህት ድርጅቶች እርስ በርስ የሚፈላለጉበትና ሁሉም አንድነቱን የሚንከባከቡበት ምክንያት ሊያገኙ ይችሉ ይሆናል።
በዚህ መሠረት ‘አንድነት የህልውና ጉዳይ ነው’ እያሉ ተሳቆ ማሳቀቅ ሳያስፈልግ በነጻነትና ያለ ምንም ፍርሃት የሚያዳብሩት መቀራረብና አንድነትም ቀጣይና ምናልባትም ዘለቄታዊ የመሆን ዕድሉ ሰፊ እንደሚሆን ለማየት አይቸግርም።
3. የኢህአዴግ አደረጃጀት በመንግሥት ሥራና በሕዝብ ላይ የሚያደርሳቸው ችግሮች
የኢህአዴግ ድርጅታዊ የውስጥ ችግሮች ለብልሹ አስተዳደር መንሰራፋትና ለመልካም አስተዳደር መጥፋት ምክንያት መሆናቸውን ከአመራሩ ኑዛዜ ተገንዝበናል። በዚህ ክፍል በድርጅቱና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት የሕግ የበላይነት እንዳይከበር ለማድረግ ያለውን አስተዋጽኦ እንመለከታለን።
ኢህአዴግ ሐሳብ ብቻ የታጠቀ ጠመንጃ አልባ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ አያውቅም። በተለይ ተቃዋሚ ፓርቲነትንማ  የት አይቷት። በረኸኛ ሆኖም መንግሥት ተሰኝቶም ሲፋጅ በጠበንጃ፣ ሲቀዘቅዝ በቃል ሲያዝ የኖረ ድርጅት ነው። ሁሌም አዋቂ ነው፤ ሰዉ - ሕዝቡም ሆነ ተቃዋሚ ድርጅቶች - ኢህአዴግ ያቀረበላቸውን ሐሳብ ለመቀበል ቢያንገራግሩ ችግሩ ከነሱ ነው። ሕዝቡ ችግሩ ከራሱ መሆኑን ውሎ አዱሮ እስኪገነዘብ ድረስ በስብሰባ ይጠምዱታል፤ ተቃዋሚ ፓርቲውን በድርድር፤ እምቢ ካሉ ሁለቱንም አሳራቸውን የሚያበሉበት ኃይል አያጡም።
የታህሳሱን ግምገማ ተከትሎ ማብራሪያ ከሰጡት መሪዎች መካከል ሕገ መንግሥቱን የነቀፈ አንድም አልነበረም። ሁሉም ችግሩ ሕገ መንግሥቱ ሳይሆን የሕገ መንግሥቱ አለመተግበር ነው ብለዋል። ግን ያልተተገበረበትን ምክንያት አልነገሩንም። ኢህአዴግ እንዲያ የሚመካበትን ሕገ መንግሥት እንዳያከብር ማን ከለከለው? አንደኛው ምክንያት ኢህአዴግ አሁንም ትጥቁን ያልፈታ ታጋይ ድርጅት እንጂ መንግሥት ለመሆን አለመቻሉ ሲሆን፥ ሁለተኛው ምክንያት የፓርቲው አመራር ከአገሪቱ ሕጎች ሁሉ በላይና ከፍተኛው የስልጣን አካል ሊሆን መቻሉ ነው። አራት አባል ድርጅቶችንና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባላትን የያዘው ኢህአዴግ፤ አደረጃጀቱን በሚመራበት ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ አማካይነት የበላዩ የበታቹን እየታዘዘ፣ በተዋረድ አባላቱ በደረሱበት ሁሉ ውሳኔዎቹ እንዲተገበሩ ለማድረግ የሚያስችል አቅም ያለው ድርጅት መሆኑ ይታወቃል። ገዢ ፓርቲ እንደመሆኑም አቋሞቹን ሕግ በማድረግ በመላ አገሪቱ እንዲተገበር ለማድረግ ይችላል። ችግሩ ፓርቲውንና መንግሥቱንም የሚመራው ያው የኢህአዴግ አመራር ሲሆን እንደ ፓርቲ የፓርቲ ሥራ፥ እንደ መንግሥት ደግሞ የመንግሥት ሥራ ሲሠራ በሁለቱም መካከል ያለውን ሕጋዊ ድንበር ለማክበር አልቻለም። በመንግስትና በፓርቲ መካከል ሊኖር የሚገባው ድንበር ባለመጠበቁ፣ በመንግሥት ብቻ ሊታዘዝ የሚገባው ጦር በፓርቲው ይታዘዛል።  በሌላ አባባል፤የፓርቲ/መንግሥት ድንበር ባለመጠበቁ፣ ኢህአዴግ አሁንም ትጥቁን አልፈታም። አሁንም ታጣቂ፥ አሁንም ታጋይ ነው። ብቸኛው ባለ ትጥቅ ፓርቲ በመሆኑም በአመራሩ መካከል የሚፈጠረው ችግር በፓርቲው ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር አድርጎታል። በኢህአዴግ አመራር መካከል ችግር ሲፈጠር የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር የተነገበ ጠመንጃ፣ የውስጠ-ድርጅት የቡድን ወይም የግለሰብ አመራር ጥቅም፥ ስልጣን ወይም ሙግት ለመደገፍ አልያም ለማጨናገፍ በማስፈራሪያነትና በማሸበሪያነት ጥቅም ላይ ይውላል። ጠመንጃ ባይኖረው ኖሮ ያ ሁሉ አይሆንም። የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራር አባላት ተጣሉ ሲባል ስንሰማ ኖረናል። ሆኖም ምርጫ ቦርድ ላንዱ ማኅተም፣ ለሌላው የድርጅት ስም ሲሰጥ ሲነሳ፥ ሁሉም የተሰጠውን ተቀብሎ፣ የተቀማውን ባይዋጥለትም ይሁን ብሎ ይኖራል። ጸቡ አገር ሳያሸብር የቀረው ነገሩ ጦር የማያማዝዝ ሆኖ አይደለም። ኢህአዴግ ግን በፖለቲካ ሕይወቱ ሁሉ ጠመንጃ ተለይቶት አያውቅም። ስለሆነም በአመራሩ መካከል የሚፈጠር የግንኙነት መሻከር የድርጅቱን ህልውና ከመፈተን አልፎ የአገርን ሰላም ያደፈርሳል፤ ሕይወት ያጠፋል፥ ንብረት ያወድማል።
በሌላ በኩል፤ ያው አመራር ድርጅትና መንግሥትን እንደሚመራ ሁሉ ለድርጅትና ለመንግሥት ሥራም የሚያሰማራቸው እነዚያኑ አባላቱን ነው። በተለይ የአባላቱን ሥራ ሲገመግም፥ ጥፋቶቻቸውንም ሲመዝንና የእርምት እርምጃ ሲወስድ፣ የመንግሥት ሰራተኝነታቸውን ትቶ አባልነታቸውን ብቻ መመልከቱ አልቀረም። በመንግሥት ሥራ ኃላፊነት የሚሰሩትንም ጥፋት ጨምሮ ድክመቶቻቸውን ቁርጠኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ፥ የተዛባ አመለካከታቸውን በቀናው በማስተካከል ለመፍታት ይሞክራል። በዚህ ምክንያት ራሳቸው እንደሚሉት፣ የድርጅት አባልነት ወደ መንግሥት ሥልጣን መወጣጫ መሆኑን የተረዱ ሰዎች ድርጅቱ ውስጥ ገብተዋል። በአገሪቱ ሕግ ወንጀል ተብለው ቅጣት የተቀመጠባቸው ድርጊቶች በአባላት ሲፈጸሙ ከመቅጣት ማስተማርን ባስቀደመ ሆደ ሰፊነት ይታለፋሉ። ይህን ማድረግ በመቻሉ ድርጅቱ እንደ ድርጅት ከሕግ በላይ ሆኗል። የፓርቲው ባለስልጣናት ይህን ማድረግ እንደሚችሉ የተገነዘበ አባል፤ የመንግሥት ሕጎችን ከማክበር ይልቅ ለድርጅቱ ኃላፊዎች ትዕዛዝ ቅድሚያ መስጠቱ አይቀርም። ቅድሚያ አልሰጥም ካለም፣ ምንም ሕግ ከፓርቲው እርምጃ እንደማያስጥለው ያውቃል።
የፓርቲው አባላት የመንግሥትን ስልጣን ይዘው በሚሠሩት ሥራ ተጠያቂነታቸው ለፓርቲ ብቻ በሆነበት ሁኔታ ፓርቲው በወንጀል መጠየቅ የሚገባቸውን አባላቱን በፓርቲ ደረጃ በተግሳጽ እንዲታለፉ ማድረጉ ስለማይቀር ፓርቲው የዘራፊዎች ምሽግ እንደሆነ ይቀጥላል። ባለስልጣኖች ለሰሩት ሥራ በአባልነታቸው በፓርቲ መድረክ እንዲገመገሙና ወንጀሉ የዲሲፕሊን ጉድለት ተሰኝቶ እንዲቀርብ በማድረግ፥ በግምገማ ሽፋን [አባላት] ከተጠያቂነት ውጭ እንዲሆኑ ከማድረጉም ባሻገር የመንግሥት ተቋሞችን ገለልተኝነት በማጥፋት፣ የፍ/ቤቶችንና ሌሎች ተቋሞችን ሥራ በድርጅት ግምገማ ልተካ ባይ ይሆናል።
የፓርቲው ስልጣን የበታች ለበላይ መታዘዝ አለበት በሚለው የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ አማካይነት ያልተማከለውን የመንግሥት መዋቅር ተሻግሮና ምንም ሕግ ሳያደናቅፈው፣ ከኢህአዴግ አመራር መንጭቶ፣ በፌዴራልና በክልል ለሚገኙት አባሎቹ በተዋረድ የሚፈስ ሆኖ ይገኛል። ሆኖም በህጎችና የአስተዳደር ክልሎች ሳይገደብ በዘረጋው መዋቅር፣ ገሸሽ ባላቸው ህጎችና አስተዳደራዊ ወሰኖች ልክ አባላቱ በየደረጃው የሚጥሷቸውን ሕጎች እንዲያከብሩ የማድረግ አቅሙን አጥፍቶታል።
ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ በሕገ መንግሥታዊ ተቋሞች ብቻ ሊጠበቅ ሲገባው ጭራሽ የሥርዓቱ ህልውና ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አንድነት መቀጠል አለመቀጠል ጋር በማያያዙ፥ የግንባሩንም ህልውና በአመራሩ መግባባት/አለመግባባት የሚወሰን አድርጎ በመተው፥ አውቆም ይሁን ሳያውቅ የኢህአዴግ አመራር ለድርጅቱ የሚሰጠው ቦታ ከሕገ መንግሥቱ በላይ ሲሆን አመራሩ ለራሱ የሚሰጠው ቦታ ደግሞ ከድርጅቱ ኢህአዴግ በላይ መሆኑ አልቀረም። ስለሆነም ኢህአዴግ ከሕግ በታች መሆን እስካልቻለ ድረስ አመራሩ/አባላቱም ሕግ እየጣሱ መቀጠላቸው አይቀርም።
3.1 የመበስበስ ግርሻን ለመከላከል ተቋማዊ
አሰራር መዘርጋት
የኢህአዴግ አመራር ዛሬ እንደ ድክመት የሚያነሳው መቧደንና መርህ አልባ ግንኙነት አብሮት የኖረ የቤት ጣጣው ሲሆን፥ በዚያው ልክ ግለሰብና ቡድን ተሻጋሪ ለሆነው ተቋማዊ አስተሳሰብ እንግዳ ነው። ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ደጋግሞ ሲያነሳ እንሰማለን። ሆኖም ሥርዓቱ ሕግ አክብሮ ከመሥራት ጋር፥ የተቋሞችን ገለልተኝነት ከማረጋገጥ ጋር፥ ከዜጎች መብት ጋር ያለው ግንኙነት አይታየውም። በግንባር ደረጃም ያለው ችግር ተቋማዊ አሠራር ካለማበጀት/ካለመከተል፥ ተቋማዊ አስተሳሰብ ካለመልመድ የመነጨ ሊሆን እንደሚችል ከአመራሩ ማብራሪያ ብቻ ለመገንዘብ ይቻላል። ድርጅቱ በየጊዜው የአመራር ቀውስ ውስጥ ሲገባ፥ ሲገማገምና ተከፋፍሎ፥ ተለያይቶ ታድሼ መጣሁ ሲል የኖረበት አንዱ ምክንያት ተቋማዊ ዓላማዎቹና መርሆቹ ተለዋዋጭ ከመሆናቸውም በተጨማሪ የድርጅቱን ደንብና አሠራር ገሸሽ ከማለትና ከተቋማዊ አስተሳሰብ ያለማዳበር ጋር መያያዙ አይቀርም።
ከግምገማው በኋላ የኢህአዴግ የቀድሞ አመራር አባላት ድርጅቱን በዚህ ሁኔታ ጥለን አንሄድም በማለት አስቀድመው ያቀረቡትን የስንብት ጥያቄ በማንሳት ወደ ፓርቲው መመለሳቸውን ሰምተናል። ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ያገኙት መብቶች ተጥሰው፥ የተዘረጋው ሥርዓት ፈርሶ እነሱ የታገሉለትና በርካቶች የተሰዉለት ድል ተቀልብሶ መና እንዳይቀር በማለት ነው ተብሏል። ታዲያ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ቀጣይነት ሊረጋገጥ የሚችለው ዛሬ በተለይ ኢህአዴግን ጨምሮ በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ታውቆ የታመነበትና በሁሉም የሚከበር የፖለቲካ ፉክክር ሥርዓት ለመሆን ሲችል ብቻ ነው። ለዚህም ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጥበቃ/ጥገኝነት ነጻ ወጥቶ ተቋማዊ ሕልውና ሊጎናጸፍ ይገባል። ነባር ታጋዮቹ ያቀረቡትን የመልቀቂያ ጥያቄ አንስተው ወደ ሥራ ለመመለስ ግድ ያላቸውም ለመብቶቹም ሆነ ለሥርዓቱ ቀጣይነት የሚያስፈልገውን ተቋማዊ ሥራ ሳይሰሩ በመቆየታቸው ነው። አሁንም ወደ ድርጅቱ ተመልሰው የሚሰሩት ሥራ ምንም ይሁን ምን ተቋማዊነትን ካልተላበሰ እንደ ጓዶቻቸው ሁሉ እነሱም ሲያልፉ አብሯቸው ማለፉ አይቀርም።
ቀደምቱም ሆኑ የትናንቱ ታጋዮችና ሰማዕታት የፈጸሙት ገድል፥ ሞተው የጠበቁት አገርም ሆነ ታግለው ያመጡት ድል ሁሉ ለሁሉም ያገር ልጅ እኩል የሚደርሰውን ያክል፤ እንደ ውለታቸው ሁሉ ዝምድናቸውም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ነው። ሕይወት ከፍለው የጠበቁለትን መልካሙን ሁሉ እንደተጠበቀ እንዲዘልቅ የሚተጋውና ዘመኑ የሚጠይቀውን ኃላፊነት ለመወጣት በሚደረግ ጥረት ሁሉ የነሱን ጽናት የሚመጥን ወኔ ታጥቆ የሚሰራው ሁሉ የአደራቸው ጠባቂና አክባሪያቸውም ነው። ጋዜጠኛው፥ ጦማሪው፥ ተፎካካሪ ፓርቲው ሁሉም የዚያው ጥረት ተዋናዮች ናቸው። የሥጋ ዘመዶቻቸውን ጨምሮ ለታጋይ/ሰማዕታቱ የተለየና የበለጠ ቀረቤታ አለኝ የሚል ሁሉ ወገንተኝነቱ የሚለካበት ለፍትሕ፥ እኩልነትና ነጻነት፥ ለፍቅርና ለአንድነት የሚደረግ ጥረት ሊሆን ይገባል። ከዚህ አንጻር ኢህአዴግ ራሱ በኢኮኖሚው ረገድ ኢ-ፍትሐዊ የሚለውን ሥርዓት በመገንባት ላይ መሆኑና ፍትሕንም ለመበየን አለመቻሉ፥ ጭራሽ ራሱ ባመነው ስልጣንን ለዝርፍያ መጠቀሙ ብቻ አደራ በሊታነቱን የሚያረጋግጥ ሲሆን እረፍት ይቅርብን ብለው ወደ ሥራ የተመለሱት ነባር ታጋዮችም የሚደክሙት አሁን ያለው ሁኔታ እንዲቀጥል ለማድረግ ከሆነ ትርፉ ድካም ነው። አንጋፋዎቹ ታጋዮች ዛሬ ኢህአዴግን ጨምሮ ማንም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅት ሊደክምለት የሚገባው ዓላማ ከአንዳች ኢትዮጵያዊ አመለካከት አልያም ከተጨባጭ የአገራችን ልዩ አቋሞችና ችግሮች የሚንደረደርና የወደፊቱን አገራዊ መዳረሻ የሚያመላክት ሆኖ፣ ሕዝብንና አገርን ከነጣቂዎች ጠብቆ፣ አገራዊ አቅምን የሚገነባና አገራዊ እሴቶችን የሚያጎለብት ሊሆን እንደሚገባ አያጡትም።
4. የእርምት እርምጃ ከየት ይጀመር?
የፖሊሲ ችግሮችን ለመፍታት ቅድሚያ በአመራሩ መካከል በየጊዜው የሚቀሰቀሰውን መጠራጠር በድርጅት ሕልውናና በአገር ሰላም ላይ አደጋ እንዲደቅን ሊፈቀድለት አይገባም። መቼም ኢህአዴግ ትጥቁን እስካልፈታ ድረስ ይህን ለማረጋገጥ አይቻልም። ሆኖም ከላይ ለማስረዳት እንደተሞከረው፤ የአባል ድርጅቶቹ አንድነት የሞት ሽረት ጉዳይ አለመሆኑን ከመገንዘብ ቢጀመር፥ የኢትዮጵያ አንድነትም የአራቱ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች አንድነት— ያውም በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ላይ የቆመ አንድነት —  በቦታው ሲኖር ብቻ የሚረጋገጥ አለመሆኑን መረዳት ቢቻል ይጠቅማል። የዝርፊያውን መፍትሄ ለማለት ያክል እነሱም ይሉታል። አዎን የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ነው የሚፈታው። ሆኖም የመንግሥትና የፓርቲ መዋቅር በተቀላቀሉበት ሁኔታ የሕግ የበላይነት ማለት ምን ማለት ይሆናል? የኢህአዴግ አባል የሆነ የመንግሥት ሠራተኛ/ባለስልጣን፤ በሕግና በህግ ብቻ ይስራ ማለት ነው? ፓርቲው የሚሠጠውን መመሪያ ከተቀመጠለት ህጋዊ አሠራር ጋር የሚጋጭ ቢሆን አልቀበልም ይበል ነው? ፓርቲው ቀድሞ ነገር የመንግሥትን ሕግ የሚጥስ መመሪያ/ትዕዛዝ ለአባላቱ ማውረድ የለበትም ነው? አውርዶስ ቢገኝ ምን ይደረጋል? ፓርቲው ራሱን ከሕግ በታች ለማድረግ ቆረጠ ሊባል የሚችለው የመንግሥት ሰራተኛ/ባለስልጣን የሆኑት አባሎቹ በሕግና በሕግ ብቻ እንዲሰሩ፥ ሕግ ጥሰው ቢገኙ ግን እያንዳንዱ በስራው ተጠያቂ እንዲሆን ለማድረግ ሲፈቅድ ነው።
አሁን ያለው እውነታ ግን ባንድ በኩል፣ የፓርቲ አባልነት ለመንግሥት ስልጣን መወጣጫ መሰላል ሲሆን ፓርቲውም የመንግሥትን ስልጣን ተጠቅሞ፣ የራሱን ሕገ ወጥ ፍላጎቶች ለማራመድ ሲል፣ ያንኑ ባለስልጣን መረማመጃ የሚያደርግበት ነው። ስለዚህ በስልጣን አላግባብ ተጠቃሚው ግለሰብ ባለስልጣኑ ብቻ ሳይሆን ድርጅቱም ጭምር በመሆኑ ማን ማንን ሊቀጣ ይችላል? ስለዚህ እያንዳንዱ ጥፋተኛ በሥራው ልክ በተናጠል እንዲጠየቅ ካልተደረገ በቀር የፓርቲው መሪዎች ቢፈልጉም ችግሩ አይጸዳም። ከዚህ አንጻር በተለይ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ችግር ኢህአዴግ ራሱን በራሱ በማረም ሊፈታው አይችልም። በርግጥ ጠንከር ባሉ ደንቦች አማካይነት የአባላቱን ሥነ ምግባር ደረጃ ከፍ ለማድረግ ሊጣጣር ይችላል። በመንግሥት ሥራ ውስጥ የሚሳተፉ አባላቱን በሚመለከት ግን እያንዳንዱ ሰራተኛ ለሚፈጽመው ጥፋት በግሉ ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ፥ ይህንንም ለማረጋገጥ ገለልተኛ የመንግሥት መ/ቤት ማቋቋም ወይም ካሉት መካከል መርጦ ገለልተኝነታቸውን በሚያጠናክር መልኩ እንዳዲስ በማደራጀት ሥራውን መስጠት ነው።    
(ይቀጥላል)

Read 2930 times