Saturday, 28 April 2012 14:52

ወርቃማው ሕግ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(1 Vote)

“ራሱን የሚያከብርና የሚወድ ለሌሎች የሚተርፍ ፍቅር ይኖረዋል”

በዓለም ላይ ባሉ አገራትና ሕዝቦች ውስጥ ከሚገኙ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች ተመርጠው “ወርቃማው ሕግ” የተሰኙት አባባሎች ሠላምና መግባባት በምድር ላይ ለማስፈን እንደሚጠቅሙ ስለታመነበት የወርቃማው ሕግ ቀን በየዓመቱ ይከበራል፡፡ “ተለውጦ ማየት የምንሻው ዓለም ለውጡ የሚጀምረው ከራስ ነው” በሚል መርህ በአገራችን ኢትዮጵያ የወርቃማው ሕግ ቀን ለአምስተኛ ጊዜ የተከበረው መጋቢት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ነበር፡፡

በሀገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ የቀረበውን ዝግጅት ያሰናዳው “የተለያዩ ሃይማኖቶች ለሰላም ማህበር” (ኢንተርፌይዝ ፒስ ቢዩልዲንግ ኢኒሽዬቲቭ) ሲሆን ተቋሙ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ በፍትሕ ሚኒስቴር የተመዘገበና ዕውቅና የተሰጠው ነው፡፡ ሰላም ለአንድ ወገን ብቻ የማይተው የሁሉም የጋራ ጉዳይ መሆኑን የተረዱና ከተለያዩ ሃይማኖቶች የተውጣጡ ግለሰቦች ያቋቋሙት ማህበርም ነው፡፡

“በሕዝቦች መካከል የመከባበርና የመተባበር፤ መልካም ግንኙነት የመፍጠርና በተለያየ አጋጣሚዎች ሊከሰቱ የሚችሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፤ የሰላም ባህል ይበልጥ ለማዳበር፣ የወርቃማው ሕግ አስተምሮት ወደ ሕብረተሰቡ እንዲሰርጽ ለማድረግና በተለያዩ እምነት ተከታዮች መካከል ጥሩ የመግባባት መንፈስ ለመፍጠር” ታስቦ በኢትዮጵያዊያን የተቋቋመው ማህበር፤ ለሠላም የሚያደርገውን ጥረት በብሔራዊ ደረጃ አጠናክሮ ለመሥራት በክልል ከተሞችም ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ከፍቷል፡፡

ከማህበሩ ዓላማዎች አንዱ በተለያዩ ሃይማኖቶች መንፈሳዊ መፃሐፍት ውስጥ የሚገኙና ለሰላምና መቻቻል አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ወርቃማ ሕግና መርሆችን ለሕብረተሰቡ ማሳወቅ በመሆኑ በአገር ውስጥ የሚታወቁ ብቻ ሳይሆኑ ብዙም በማይታወቁ ሃይማኖቶች ወስጥ ያለ ወርቃማ ሕግ ሕዝብ እንዲያውቀው ጥረት ያደርጋል፡፡

ከማንኛውም ፖለቲካዊ አመለካከትም ሆነ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ነፃ የሆነው ማህበር፤ በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ልዩነት ያከብራል፡፡ ሃይማኖቶች ለሰላም የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ያበረታታል፡፡ አርአያነት ያለው ሰላማዊ ተግባር ላከናወኑ ግለሰቦችና ተቋማት በየዓመቱ ሽልማት ይሰጣል፡፡

በዕለቱ መድረክ ይመራ የነበረው አርቲስት ሽመልስ በቀለ፤ “ዓለም ሦስት አራተኛ ክፍሏ በውሃ የተሸፈነ ነው፡፡ አንድ አራተኛው በክፋት የተሸፈነ ነው ይባላል” ብሎ የምድር ላይ ነዋሪ የሆኑት ሰዎች በተለያየ ምክንያት እርስ በእርስ እንደሚጐዳዱ አመልክቷል፡፡ “የተለያዩ ሃይማኖቶች ለሰላም ማህበር” የቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሙሴ ኃይሌ ስለ ወርቃማው ሕግና ስለ በዓሉ ንግግር ካደረጉ በኋላ፣ የተጠሩ የክብር እንግዶች መልዕክት እንዲያስተላልፉ ጋብዘዋል፡፡

“ወርቅ፤ በማንኛውም ሰው እጅ ቢገባ ተከብሮ የሚያዝ ውድ ዕቃ እንደሆነው ሁሉ ወርቃማው ሕግንም መመሪያችን ብናደርገው እንከበርበታለን” ያሉት የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን፤ “እያንዳንዳችን ራሳችንን ለመለወጥ በመጀመር ነው ለውጥ የሚመጣው፡፡ ሁላችንም ስንፈጠር ልባችን ንፁህ ነው፡፡ ሌላውን የምንጠላውና የምንጐዳው በሆነ አጋጣሚ በደረሰብን ጉዳት ምክንያት ነው፡፡ ራሱን የሚያከብርና የሚወድ ሰው ለሌሎች የሚተርፍ ፍቅር ይኖረዋል፡፡ ውስጡ በሰላም የተሞላ ውጪውም በሰላም ያበራል፡፡ በምድር ላይ ያለን ዕድሜ አጭር ስለሆነ የወርቃማውን ሕግ እየተከተልን አኗኗርና አስተሳሰባችን ሰላማዊ እንዲሆን እንጣር” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው በለጠ በበኩላቸው፤ “ወርቃማውን ሕግ በየዕለቱ ኑሯችን ላይ ተግባራዊ ማድረግ የሚኖርብን እኛ የእኛ ብቻ ስላልሆነ ነው፡፡ ዛሬ ያለን ማንነት፣ ዕውቀት፣ ችሎታ…አገሪቱ፣ ሕብረተሰቡ፣ ሠፈሩ፣ ጐረቤቱ፣ ትምህርት ቤቶች፣ አስተማሪዎች፣ የመንደራችን ባለኪዮስኮች ሳይቀሩ ተባብረው የፈጠሩትና የቀረፁት ነው፡፡ ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለዚህ እንድንበቃ በተለያየ መልኩ የረዳንን ሕብረተሰብ ሰላም ለማስጠበቅ ወርቃማው ሕግ መፍትሔ ነው” ብለዋል፡፡

የአእምሮ ዝግመት ተጠቂ በሆኑ ዜጐች ላይ ትልቅ ሥራ በመሥራት የሚታወቁት ወ/ሮ ዛሚ የኑስ ደግሞ፤ ሕይወታችን በብዙ ትግል ተወጥሮ የምናየው ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ምክንያት እንደሆነና በየቤታችን፣ በየመንደሩና በሕብረተሰብ ደረጃ የሚታዩ ችግሮች የወርቃማውን ሕግ መልዕክት ካለመረዳት የመነጩ ናቸው ብለዋል፡፡ “በተለያየ ችግር ሰው፣ ጓደኛ፣ ፍቅረኛ አጥተን፤ የፀሐይ ብርሃን ናፍቆን ቤት ተቆልፎብን ብንውል፤ አገር፣ ዓለም ዞር ብሎ ሊያየኝ ያልቻለው ሰው እኔ ነኝ ብላችሁ አስቡ እስቲ … ከባድ ነው፡፡ የወርቃማውን ሕግ መልዕክት የተረዳ ሰው ሌላውን አያገልም፡፡” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ወርቃማው ሕግ በተለይ በትዳር ውስጥ በተደጋጋሚ ሲጣስ እናያለን በማለት የተናገረችው በፋና ሬዲዮ የ”እርቅ ማዕድ” በማዘጋጀት የምትታወቀው ወ/ት ትዕግስት ዋልተንጉሥ፤ ስለ ወርቃማው ሕግ ጠቃሚነት ባሏን በተግባር ስላስተማረች ሴት ታሪክ ተናግራለች፡፡

ባሏ አምሽቶ የመምጣቱ ልማድ በመደጋገሙ የተጨነቀች ሚስቱ፣ ስለተቸገረችበት ጉዳይ ጓደኞቿን ስታማክር አንቺም እያመሸሽ ለምን አትገቢም ይሏታል፡፡ በአንዱ ዕለት ባል አምሽቶ ሲመጣ ሚስቱ በቤቱ የለችም፡፡ ባል ተናደደ፡፡

ከጥቂት ቆይታ በኋላ ሚስቱ መጣች፡፡ በንዴት ፀጉሩ የቆመው ባል በማግስቱ ሽማግሌ ሰበሰበ፡፡ የሚስቱ ውጭ ማምሸት ካናደደው የእሱም  ማምሸት ለሚስቱ ምን ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል ተጠየቀ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ትዳራቸው ጠፍቶበት የነበረው ወርቃማው ሕግ ተፈልጉ ተገኘላቸው” ያለችው ወ/ት ትዕግስት፤ መጪው ትውልድ የተሻለ ህይወት እንዲመራ በትዳር፣ በቤተሰብና በሕብረተሰቡ ውስጥ መልካም ተግባሮች መዳበር እንዳለባቸው አስገንዝባለች፡፡

 

 

 

Read 3147 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 15:01