Sunday, 29 April 2018 00:00

“ቄሮን እዚህ ያደረስነው እኛ ነን”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

 · “ኦህዴድ የታችኛው መዋቅር ላይ ሙሉ ለውጥ ማምጣት አለበት”
 · “ኢትዮጵያዊነት ብሔር ብሔረሰቦችን ያቀፈ እንጂ ባዶ ቅል አይደለም”
 · “ያለፈውን ሥርዓት ሁሉ መውቀስ የለብንም

       በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሰሞነኛ እንቅስቃሴዎችና ንግግሮች ዙሪያ የመድረክና ኦፌኮ አመራሩ የቀድሞ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባልና የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባል የተከበሩ አቶ ገብሩ ገ/ማሪያም ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ አካባቢዎች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጉትን ስብሰባ እንዴት ይመለከቱታል?
ንግግሮቹ እንደተባለው ተስፋ ጫሪ ናቸው። ተስፋ ጫሪ የሚያደርገው ሰውየው ወደ ስልጣን የመጡት ሃገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ ባለችበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የሁሉንም ህብረተሰብ ልብ የነካ ንግግር ማድረግ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የህዝብን ተስፋ ያለመልማል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በንግግራቸው ስለ ፍቅር፣ አንድነት፣ ይቅርታ ስለ ኢትዮጵያዊነት አንስተዋል፡፡ እነዚህ የሰው ልብ ውስጥ የራሳቸውን ቅሪቶች ፈጥሯል። ግን አካሄዱ ጥንቃቄ የሚያስፈልግ ነው፡፡ ጠንካራ የህዝብ እንቅስቃሴና ችግሮች በነበረባቸው አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ፣ ከህዝብ ጋር መገናኘት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ እኔ በበኩሌ ወድጄዋለሁ። ለመሪ ህዝብን በቀጥታ የማግኘት ያህል ጠንካራ ስራ የለም፡፡ ክልሎችን በማናገር ሂደት ውስጥ ጊዜም ቢወስድ ያለ ልዩነት ሁሉንም ማዳረስ ያስፈልጋል፡፡
አንዳንድ ወገኖች ጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄ ያለውን ህዝብ ጋር በቀጥታ አላናገሩም፤ በስብሰባዎቹ እንደቀድሞው የፓርቲ አባላት ናቸው የተሳተፉት ሲሉ ይተቻሉ …
በአንድ ጊዜ ሁሉንም ለውጥ ስለማልጠብቅ በአሁኑ አካሄድ ብዙም ችግር የለብኝም፡፡ በሚሊኒየም አዳራሽ 25 ሺህ ህዝብ ነበር፡፡ ሁሉም የፓርቲ አባላት አይመስሉኝም፡፡ ዋናው ጉዳይ ጠ/ሚኒስትሩ ቀጥሎ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባር ሲገቡ ዋና ፈተና የሚሆንባቸው ምንድን ነው ይላሉ?
ድርጅቱ አንዱ ኢህአዴግ ራሱ ነው፡፡ ዶ/ር መረራ እንዳለው፤ ትልቁ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈተና ኢህአዴግ ነው፡፡ የኢህአዴግን “ከኔ ወዲያ ላሳር” ባይነት “ሌላውም ኢትዮጵያዊ ለዚህች አገር ያስባል” የሚል የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት በሚያደርጉት ጥረት ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን ቁርጠኛ ከሆኑ ብዙም የሚቸግራቸው አይመስለኝም፡፡ ንግግሮቻቸው በራሱ የአንጋፋዎቹ የፓርቲ አመራሮች መቀስ ያገኘው አይመስለኝም፡፡
ኢህአዴግ ውስጥ የለውጥ አብዮት እየተፈጠረ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
በዚያ ደረጃ ባይሆንም እንደሚታወቀው አንድ መንግሥት ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል። ይህ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ አንድ መንግስት ለመውደቅ ሲቃረብ ደግሞ ሶስት ምልክቶች ይታያኩ። አንደኛው የፓርቲ የውስጥ መከፋፈል ነው፡፡ ይሄ በኢህአዴግ ውስጥ ተፈጥሯል፡፡ ሁለተኛው መመሪያዎች፣ ደንቦች፣ ትዕዛዞች በበታች ሹማምንት አለመከባር ነው፡፡ ሶስተኛው የህዝብ አልገዛም ባይነት ነው። እነዚህ ሁሉ በኢህአዴግ መንግስታዊ አስተዳደር ውስጥ በሚገባ ታይተዋል፡፡ በኋላ የመጣው እንግዲህ የወጣ ቶቹ የእነ አቶ ለማ እንቅስቃሴ ነው። በሌላ በኩል የኢህአዴግ ፈጣሪዎች የሆኑት የእነ አቶ ስብሃት ነጋ አቶ ስዩም መስፍን ከአካባቢው ዞር አንልም የሚል ችክ ያለ አካሄድ ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች መተካታቸውን እያዩም አሁንም አለንበት እያሉ ነው፡፡ ትልቁ ልዩነት ግን እነ አቶ ለማን እነሱ ሳይሆኑ የህዝብ ትግል ያመጣቸው መሆኑ ነው። በህዝብ ትግል የመጡ በመሆናቸው ምናልባት ድርጅቱን ለመቀየር እድልና ድፍረቱ ሊኖራቸው ይችላል። እርግጥ ነው እነሱም ቢሆኑ የኢህአዴግ ሽታ አላቸው፡፡ ነገር ግን በህዝብ ግፊት ወደ ፊት መስመር የመጡ እንደመሆኑ ለህዝብ የመስራት ኃላፊነት በጫንቃቸው ላይ ተጭኗል፡፡ ይሄን ጭነት እንዴት ይወጡታል የሚለው በቀጣይ የሚታይ ይሆናል፡፡
የለውጡ ማዕከሎች ኦህዴድ እና ብአዴን ናቸው ተብሎ ብዙዎች ይናገራሉ እርሶ ኦህዴድን በቅርበት ያውቁታልና ተጠናክሯል፣ ጠንካራ ድርጅት ሆኗል ማለት ይቻል ይሆን?
ጠንካራ ድርጅት ነው ማለት ፈፅሞ አይቻልም። ኦህዴድ ትልቁ ተቀናቃኙ ኦነግ ነበር። ኦነግን ይፈራዋል፡፡ ነገር ግን በህውሓት ቆራጥ አጋርነት ነው መቆየት የቻለው፡፡ ኦህዴድ በውስጡ ትግል አካሄደ እና አቶ ለማን የመሰሉ መሪዎች ቢያወጣም የእነሱን ፍላጎት የሚያስፈፅሙለት የታችኛው የአመራር እርከን ላይ ያሉ ብቁ መሪዎችን መፍጠር ገና አልቻለም፡፡ ካቢኔው ያው ነው አልተቄረም፣ የፖሊስ መዋቅሩ ያው ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ነው ተሃድሶ ብለው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው፡፡ የእስካሁኑ ተሃድሶ ቀልድ ነበር ከዚህ በኋላ ግን እነ አቶ ለማ ድርጅቱን ማደስ ይችላሉ። አሁን በህውሓት ሲመሩ የነበሩት የሞግዚትነት ጊዜ ያበቃ ይመስለኛል ስለዚህ እነ አቶ ለማ እና እነ ዶ/ር አብይ ላይ ያለው ስልጣን ላይ ተኝጠልጥለው ታች ያለው ካድሬ እነሱ ወዴት ሊሄዱ እንዳሰቡ ካልገባው ዝም ብሎ መደናቆር ይሆናል ማለት ነው፡፡ የታችኛው መዋቅር ላይ ሙሉ ለውጥ ማምጣት አለባቸው፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰሞኑ ንግግሮች የእርሶን ቀልብ የገዛው የቱ ነው?
አንደኛው ያለፈን ነገር መውቀስ ብቻ የለብንም ያሉት ነው፡፡ ፖለቲከኞቻችን ብዙ ጊዜ ዘለው ሚኒልክን ያብጠለጥላሉ፡፡ መንግስቱ ኃ/ማሪያምን መውቀስ ነው የሚቀናቸው፡፡ ምኒልክ በሶስት ወራሪ ኃይሎች ተወጥረው ነበር ለሀገሪቱ አንድነት ዘመናቸው በፈቀደላቸው አስተሳሰብ ልክ ሲሰሩ የነበረው፡፡ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ የእሳቸው ድርሻ አለበት፡፡ አንዳንዶች መንግሥቱ ኃ/ማሪያምን እንደ እኩዮቻቸው አድርገው ሲሰድቧቸውና ሲዘልፏቸው እሰማለሁ፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም። ይብዛም ይነስም ይህቺን ሃገር መርተዋል። ለሃገር አንድነት ሰርተዋል፡፡ እርግጥ ነው ብዙ ሰው በሳቸው ዘመን በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳቢያ ተገድሏል። ይሄ ትክክል አልነበረም። እንደዛሬው ግና ጎሳና ዘር ልዩነት አልነበረም። የፖለቲካ አመለካከት ነበር የሚያገዳድለው፡፡ ግን በጎ አስተዋፅኦዋቸውን መደፍጠጥም ተገቢ አይሆንም፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በንግግራቸው ለአገራዊ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ብዙ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ ይሄን እንዴት ይመለከቱታል?
ትኩረት ማድረጋቸው የሚወደድ ነው። ጥሩ ነው። ስጋቴ እሳቸው የሚሉት “ኢትዮጵያዊነት” በሌላ እንዳይተረጎም ነው። የአሃዳዊነት አቀንቃኞች ይህን አባባላቸውን ወደ ሌላ እንዳይተረጉሙባቸው ስጋት አለኝ፡፡ አሁን የሚቦርቁት ኢትዮጵያዊነት የሚሉ ቃላት ስለገነኑ ይመስለኛል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያዊነት ግን አሃዳዊነትን የሚደግፍ እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ብሔር ብሔረሰቦች ያቀፈ ነው እንጂ ባዶ ቅል አይደለም። ኢትዮጵያ ባዶ ቅል አይደለችም፡፡ ደጋግመው ኢትዮጵያዊነትን መናገራቸው የብሔር ብሔረሰቦች መብት የለም ለማለት አይደለም ኢትዮጵያዊነት የብሔር ብሔረሰቦች መብትን ያከበረ መሆን አለበት። የጎሳ ፖለቲካ፣ የብሔር ፖለቲካ እያሉ የሚያጣጥሉ ወገኖች ይሄን መገንዘብ አለባቸው። እውነቱን ለመናገር ይሄ ንግግራቸው ወዳልሆነ አቅጣጫ ሊወሰድ ስለሚችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይሄን ለውጥ ያመጣው የቁቤ ትውልድ፣ ባለፉት 25 ዓመታት ስለ ብሔሩ ማንነት ተነግሮት ያደገ ነው። አሁን ለመላው ኢትዮጵያ የሚበጀውን ለውጥ አምጥቷል፡፡ አሁን ይሄን መቀልበስና ወደ አሃዳዊነት መቀየር አይቻልም፡፡ ቄሮ፣ ፋኖ የሚባለው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ የአዲሱ ትውልድ ፍላጎት መገለጫዎች ናቸው፡፡ ይህን አውቀን ነው ፖለቲከኞች ትግላችንን መፈተሽ ያለብን፡፡ አሃዳዊነትን የሚያቀነቅኑ ወገኖችም ይሄን ፍተሻ ማድረግ ቢችሉ መልካም ነው፡፡
ሌላው ዶ/ር አብይ በንግግሮቻቸው ቀደም ሲል በተቃዋሚዎች ይቀርቡ የነበሩ ትችቶችን መንግስታቸው እንደተቀበለ የሚያመለክቱ ጉዳዮችን አንስተው፣ እንደሚያስተካክሉ ቃል ገብተዋል። ለምሳሌ አፋን ኦሮሞን የፌደራል ቋንቋ ማድረግ አንዱ የእናንተ ትግል አጀንዳ ነበር። ኦህዴድም ይሄን ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሰራ ገልጿል፡፡ ይህ መሆኑ የትግል አጀንዳችሁን እንድትፈትሹ አያሳስባችሁም?
እርግጥ ነው አፋን ኦሮሞ የፌደራል ቋንቋ እንዲሆን መጀመሪያ ጥያቄ ያነሳነው እኛ ነን። አሁን ኦህዴድ ከተቀበለው በደስታ ነው የምንወስደው፡፡ የኛ አጀንዳ ደግሞ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ዲሞክራሲ፣ እውነተኛ ፌደራሊዝም፣ የፍትህ ጥያቄ፣ የህገ መንግስቱ መከበር፣ ነፃና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ፣ ነፃ የምርጫ ቦርድ መቋቋም ወዘተ በበለጠ አጠናክረን የምንቀጥልባቸው አጀንዳዎች ናቸው። የእነዚህን ተግባራዊ እንቅስቃሴ መከታተል አንዱ የትግላችን ማጠንጠኛ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ጠ/ሚኒስትሩ ህገ ወጥ እስር መፈፀም የለበትም ብለዋል፤ ነገር ግን ዛሬም ኦሮሚያ ውስጥ ሰዎች እየታሰሩ ነው፤ ለምን? ቃላችሁ የታለ? የሚለው ጥያቄ፤ የኛ የትግል ጥያቄ ይሆናል ማለት ነው፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ትግል አሁን ውጤት አግኝቷል ማለት ይቻላል?
አንድ ከኢህአዴግ ውስጥ የመጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለተሾመ፣ የኦሮሞ ህዝብ በልኩ የሚሆን ጃኬቱን አግኝቷል ማለት አይቻልም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትክከል ስልጣኑን የመጠቀሙ ጉዳይም መታየት አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣኑን ወደ ተግባር ለውጦ የህዝቡን ጥያቄ መመለስ ከቻለ ብቻ ነው የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ውጤት አግኝቷል ሊባል የሚችለው፡፡
በድርድር ውስጥ የማትሳተፉ ተቃዋሚዎች ወደ ድርድሩ እንዲመለሱ ጠ/ሚኒስትሩ ጠይቀዋል፡፡ ይሄን ጥሪ እንዴት ያዩታል?
መልዕክቱ የተላለፈው ለኛ ለመድረክ ይመስለኛል። እኛ ደግሞ ድርድር በደቦ አይካሄድም የሚል አቋም ነው የያዝነው፡፡ አሁንም ይሄ አቋማችን አልተቀየረም፡፡ ድርድሩ እኛ በምንፈልገው መንገድ ሲዘጋጅ ለድርድር የማንቀመጥበት ምክንያት የለም። ለቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ስለ ድርድር ከአራት ጊዜ በላይ በደብዳቤ ጠይቀናል። ግን ምላሽ አላገኘንም። የምናደርገው ድርድር ለሀገሪቱ የሚበጅ ነው መሆን ያለበት፡፡
መደረክ ምን ዓይነት ድርድር ነው የሚፈልገው?
ድርድሩ አስፈላጊ የሚሆንባቸው አንዱ ነፃና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ ማቋቋም እንዲቻል ነው። የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት አለበት፣ ሚዲያ ለሁሉም በእኩል ማገልገል አለበት፣ የፍትህ ስርአቱ ከፖለቲካ ነፃ መሆን ይኖርበታል፡፡ እነዚህ አቋሞቻችን ናቸው። ይሄን አቋም የያዝነው በሀገሪቱ ስላልተተገበሩ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲተገበሩ እንደራደርባቸዋለን፡፡
ተቃዋሚዎች አሁን በመጣው ለውጥ ውስጥ ድርሻቸው ምንድን ነው?
አንዳንዶች ምን ውጤት አመጣችሁ ይሉናል። መቼም ትግል በገንዘብ ስለማይተመን ምን ተብሎ ይገለፃል፤ ባለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያን ህዝብ ማንነት ተናግረን፣ የኦሮሞ ህዝብን ማንነት ተናግረን፣ ቄሮን አንቅተን መንገዱን አሳይተን እዚህ ያደረስነው እኛ ነን፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና በ2007 ምርጫ በኦሮሚያ ያልረገጠው ወረዳ የለም። ተዟዙሮ ቅስቀሳ አድርጎ ነው ቄሮን ያነቃው። ቄሮ እንዲሁ ከሰማይ የወረደ አይደለም። እኛ ነን አስተምረን ቀስቅሰን እዚህ ያደረስነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ ቄሮን ያመጣነው እኛ ነን፡፡ ቄሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በበጎ የተቀበለው የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ስለተመለሰ ሳይሆን የለውጥ ጭላንጭል ስላየ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምቦ በሄዱበት ወቅት እኔ አምቦ ነበርኩ። ከአቀባበሉ በኋላ ሰልፈኞች ሲያወሩ እንደሰማሁት፤ “ዛሬ አጨብጭበን ተቀብለነዋል፤ ዛሬ ለኛ የተናገረውን ካልፈፀመ ነገ ወጥተን እንዲሁ እንፎክርበታን” ሲሉ ነው የሰማኋቸው፡፡ ስለዚህ ዶ/ር አብይ የተደረገለትን አቀባበል ተንከባክቦ መያዝ አለበት፡፡ 

Read 6287 times