Monday, 07 May 2018 09:01

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝና የሚፈጸሙ ጥሰቶች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

  (በህግ ባለሙያዎችና በፖለቲከኞች ዕይታ)

  • የሰብአዊ መብት ጥሰትና የስቃይ ምርመራ፣የህንፃ ዲዛይኖችም ውስጥ ገብቷል
  • ዜጎችን ነጥሎ ጭለማ ክፍል ውስጥ ማሰር የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው
  • ከ97 ወዲህ የወጡ ህጎች፣ ለሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸም ምክንያት ሆነዋል
  • የሰብአዊ መብት እንዲከበር የመጀመሪያው እርምጃ ለሰው ልጅ ዋጋ መስጠት ነው
  • ከብሔር ግጭት ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶች በስፋት ይታያሉ

   የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ አል ሁሴኒ ባለፈው ሰሞን በኢትዮጵያ ባደረጉት የሦስት ቀናት ጉብኝት፤ከእስር ከተፈቱ ፖለቲከኞች፣የሃይማኖት መነኮሳት፣አባ ገዳዎችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን የሃገሪቱን የሰብአዊ መብት ይዞታ ለማሻሻል መንግስት ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅበት አስታውቀዋል - ማናቸውንም ድጋፍ እንደሚያደርጉ በመግለጽ፡፡ የኮሚሽኑን ቅርንጫፍ ፅ/ቤት በአዲስ አበባ ለመክፈትም ከመንግስት ጋር ተስማምተዋል፡፡ የፅ/ቤቱ በአዲስ አበባ መከፈት ለአገሪቱ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ይኖር ይሆን ? ለመሆኑ የኢትዮጵያዊ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ምን ይመስላል? በሀገሪቱ የሚፈጸሙ
የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ባህሪያትና መገለጫዎች ምንድን ናቸው? ሰብአዊ መብቶችን እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤የህግ ባለሙያዎችንና የፖለቲከኞችና ሃሳብና ምልከታ አሰባስቦ እንደሚከተለው አጠናቅሮታ


         “የፍትህ አካላት የሰብአዊ መብት ተሟጋች መሆን አለባቸው”
             አቶ ቁምላቸው ዳኜ
         (የህግ ባለሙያና የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

    ሰብአዊ መብት የሞራል መብት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሰው ልጅ ሰብአዊ ክብር የሚመነጭ ነው። የሰው ልጅ በሰውነቱ ብቻ የራሱን እድል በራስ መወሰን ሲችል ነው ሰብአዊ ክብሩ ተጠብቋል ሊባል የሚችለው፡፡ ይህን መብቱን ለማረጋገጥ ደግሞ ነፃነቱ ሊከበር ይገባዋል፡፡
ብዙ ጊዜ በኛ ሃገር ሁኔታ ሰብአዊ መብት ሲባል ከፖለቲካ ጋር ብቻ የተያያዘ ሆኖ ነው የሚቀርበው። ነገር ግን ሰብአዊ መብቶች ከሲቪልና ፖለቲካ መብቶችም የሰፋ በርካታ ጉዳዮችን የሚያካትቱ ናቸው፡፡ የመልማት መብት፣ የአካባቢ ጥበቃ መብት፣ የህፃናት መብት፣ የሴቶች መብት፣ የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝ ዜጎች መብት የመሳሰሉትን ሁሉ ያካተተ ነው -ሰብአዊ መብት፡፡
በኛ ሀገር በስፋት የሚታዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በአራት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛ በተለይ በህይወት ከመኖር መብት፣ ከመንቀሳቀስ፣ ከአካላዊ ነፃነት መብት ጋር የተያያዙ ጥሰቶች ይፈጸማሉ። በተለይ ከዜጎች በብሔራቸው ምክንያት መፈናቀል ጋር ተያይዞ እነዚህ ጥሰቶች ጎልተው ይታያሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ፣ ከመምረጥና መመረጥ፣ ከመደራጀት ጋር በተያያዘ የሚፀሙ ጥሰቶች አሉ፡፡ በህግ ጭምር ገደብ እየተደረገባቸው የሰዎች መብት ይጣሳሉ፡፡ እነዚህ ጥሰቶች የሚፈፀሙት መንግስትን ይቃወማሉ ተብለው በሚታሰቡ ግለሰቦች ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ የፀረ ሽብር ህጉ አጠቃቀምና አተረጓጎም በዚህ ረገድ ከፍተኛ ጥሰት እንዲፈፀም ምክንያት ሆኗል። በሌላ በኩል የሲቪክ ማህበራት አዋጁ በመደራጀት መብት ላይ ገደቦች አስቀምጧል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ የሚታዩት ጥሰቶች ከኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ከትላልቅ የመንግስት የልማት እቅዶች ጋር በተያያዘ ዜጎች ተገቢውን እንክብካቤና ካሳ ሳያገኙ እንዲፈናቀሉ ይደረጋል፡፡ ከስኳር ፕሮጀክት፣ ከመብራት ኃይል ማመንጫዎች፣ ለግል ባለሀብቶች ከሚሰጡ መሬቶች ጋር በተያያዘ በሰፊው ይህ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈፀማል፡፡ በጅምላ በኃይል ቤቶችን ከማፍረስ ጋርም በተያያዘ የመብት ጥሰቶች ይፈፀማሉ፤ ሲፈፀሙም ተመልክተናል፡፡ በአራተኛ ደረጃ ከፆታ አድሎአዊነት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ ከጠለፋ፣ ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶችም አሉ፡፡ አካል ጉዳተኞች ላይም የሚፈፀሙ አድሏዊ መገለሎችና የመብት ጥሰቶች አሉ፡፡
እነዚህ ሁሉ በሀገሪቱ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ በእኛ (የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ) ተቋም ሪፖርትም በስፋት የሚታየው ግን ከብሔር ግጭት ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙት የመብት ጥሰቶች ናቸው፡፡ እነዚህን የመብት ጥሰቶች ለማስቀረት ወይም ለመቀነስ አንደኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያለው ዲሞክራሲያዊ ስርአት ያስፈልጋል፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ ለዲሞክራሲዊ ስርአት መኖር አስፈላጊ የሆኑ ተቋማት መሟላት አለባቸው፡፡ ገለልተኛ የሆኑ የፍትህ ተቋማት፣ ለህግ የሚገዛ ህግ አስፈፃሚ መኖር አለበት፣ የህዝብ ውክልና ያለው የህግ አውጪ መኖር አለበት፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠው ጉዳይ በአግባቡ ስራ ላይ መዋል አለበት፡፡ የፍትህ አካላት ከምንም በላይ የሰብአዊ መብት ተሟጋች መሆን አለባቸው፡፡ መብትን መጣስ ኃላፊነት እንደሚያስከትል እያረጋገጡ መሄድ አለባቸው፡፡ በተለይ ዳኞች ይሄን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው፡፡
ሁለተኛ መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምንጭ የእውቀት ክፍተት ነው፡፡ ስለዚህ ማህበረሰቡን ስለ መብቱ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ በህብረተሰባችን ውስጥ የተለያዩ አይነት ጭቆናዎችን እንደ ባህል አድርጎ የመመልከት ባህሪ አለው፡፡ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም እንደሚሉት፤ ህብረተሰባችን ጨቋኝን እንጂ ጭቆናን አይደለም የሚቃወመው፡፡ እሱም ነገ ጨቋኝ ነው መሆን የሚፈልገው፡፡ ይሄ ነገር በትምህርት ታሽቶ በአስተሳሰብ ለውጥ መስተካከል አለበት፡፡ ህብረተሰቡ እነዚህን የአስተሳሰብ ለውጦች ባመጣ ቁጥር የመብት ጥሰቶችን በራሱ መጋፈጥና ለመብቱ መሟገት ይጀምራል፡፡ በሌላ በኩል ከብሔር ግጭትና መፈናቀል ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ ጥሰቶችን ለማስቆም የመንግስት ድርሻ ወሳኝ ነው፡፡ የህግ እና ተቋማዊ አደረጃጀቶችን እስከ ማስፋት የሚጠይቅ ነው ጉዳዩ። ድርጊቱን የሚፈፅሙ አካላት ላይ በግልፅ እርምጃ የሚወሰድ ከሆነና በዳኝነት ፍትህ የሚገኝ ከሆነ ችግሩ እየቀነሰ ነው የሚሄደው፡፡ ህብረተሰባችን ከሰብአዊ መብት ጋር በተያያዘ ከፍ ባለ ሞራል ላይ እንዲገነባ የሃይማኖት ተቋማት፣ ምሁራን፣ (ፈላስፎች የሉንም እንጂ ፈላስፎች) መሰረታዊ ድርሻ አላቸው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰሞኑን በሃገር ቤት ተገኝተው መጎብኘታቸው ለሀገሪቱ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች የሰጡትን ትኩረት የሚያሳይ ከመሆኑ አንፃር በመልካም የሚታይ ነው፡፡ ከዚህ በመለስ ተቋሙ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱን አዲስ አበባ ለመክፈት መስማማቱ ለሰብአዊ መብቶች አለመጣስ በራሱ ዋስትና አይደለም፡፡ በመሰረቱ መንግስትና ተቋሙ በምን ጉዳይ ተስማምተው እንደተፈራረሙ አናውቅም፡፡ የተቋሙ ቢሮ ኃላፊነቱ ምን ድረስ ነው? በሀገሪቱ ሲንቀሳቀስ ምን ያህል ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት ይዞታ የመመርመር ስልጣን  አለው? የሚለውን አናውቅም፡፡   

Read 4946 times