Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Sunday, 06 May 2012 14:05

ኑሮ የከበደው፣ እኔ ላይ ብቻ ይሆን እንዴ?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

መንግስት፤ በየገጠሩ በርካታ ሚሊዬነሮች እየተፈጠሩ እንደሆነ ይናገራል።

ከብት የሌላቸው የገጠር ቤተሰቦች፣ ቁጥራቸው በ18% ጨምሯል (በ4 አመት)

የበግ፣ የፍየልና የዶሮ ቁጥር፤ የእንቁላል፣ የወተትና የማር ምርት ከምናው ያንሳል

መንግስት፤ በየከተማው የስርጭት እንጂ የምርትና የአቅርቦት ችግር የለም ይላል።

የስኳር ሽያጭ፤ የሲሚንቶ ፍጆታና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ከአምናው ያንሳል

በየሳምንቱና በየወሩ ከሚንረው የገበያ ዋጋ ጋር፤ የአዳሜ የኑሮ ውጋት እየጨመረ እንደመጣ አያጠራጥርም። ወይስ ያጠራጥራል? ውሸት ምን ያደርጋል! አንዳንዴ እጠራጠራለሁ። ምናልባት፤ የኔ ኑሮ ብቻ ይሆን እንዴ እንደ ብረት ከባድ የሆነው? የብረት ክብደቱን ብቻ ሳይሆን ቅዝቃዜውንም አስቡት።

“በየገጠሩ እልፍ ገበሬዎች ሚሊዬነር እየሆኑ ናቸው” እየተባለ በመንግስት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሲወራ እልፍ ጊዜ ሰምቻለሁ። ሰምታችኋል። በየከተማውም፤ እልፍ ወጣቶች በ”ጥቃቅንና አነስተኛ” እየተደራጁ፤ ኑሯቸው እንደተደላደለ፤ ዘወትር ይነገረናል። ኑሯቸውን ከማደላደል አልፈው ቱጃር እየሆኑ ነው ተብለናል - ብዙ ብዙ ጊዜ።

የአገሪቱ ኢኮኖሚ በየአመቱ ከ10 በመቶ በላይ እያደገ እንደሆነ፤ “ልማታዊ የምስራች” መስማትም ለምደናል። ለስምንት አመታት፤ በተከታታይ ከአስር በመቶ በላይ እድገት ማስመዝገብ ማለትኮ፤ በነዚያ አመታት ውስጥ የአገሪቱ የአመት ምርት ከእጥፍ በላይ ጨምሯል ማለት ነው። ይህ መልካም ዜና እውነት ከሆን፤ የዜጎች ኑሮም በዚያው መጠን በእጥፍ እንዳደገና እንደተሻሻለ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ምን ያጠራጥራል?

እንዲያውም፤ ብዙዎቻችን የምንማረርበት የኑሮ ውድነት ራሱ፤ የእድገት ምልክት የልማት ምስክር እንደሆነ ተነግሮናል። አዳሜ፤ ኑሮው ተሻሽሎ ብዙ ስንዴና ስጋ መብላት፤ ብዙ ልብስና እቃ መግዛት፤ ሰፋፊ መኖሪያ ቤትና ቢሮ መከራየት ሲጀምር፤ የሸቀጦች ዋጋ ተወደደ። “ብዙ በላተኛና ብዙ ገበያተኛ ካለ፤ ዋጋዎች ይወደዳሉ” ... ይሄ አባባል አሳማኝ ይመስላል አይደል?

በእርግጥ፤ እድገት ማለት በቁንፅል “ብዙ መብላትና መግዛት” ብቻ ሳይሆን፤ “ብዙ ማምረትና ብዙ መሸጥ”ም ነው። “እድገት ካለ፤ ማለትም ብዙ አምራችና ብዙ ሻጭ ካለ፤ ዋጋዎች ይረክሳሉ” ብለን ብንናገርምኮ አሳማኝ ነው። መንግስት ግን ይህንን ሲናገር ሰምተን አናውቅም።

እድገት እንደተመዘገበና የዋጋ ንረቱም የእድገት ምልክት እንደሆነ አዘውትሮ የሚነግረን ልማታዊ መንግስት፤ በከተማና በገጠር የዜጎች ኑሮ እንደተሻሻለ፣ ሳያስና ታከተኝ ደከመኝ ሳይል የብስራት ዜማውን ያንቆረቁርልናል። ደግሞም ዜማው ያጓጓል። በእድገት ላይ የልማት ዜና፤ በልማት ላይ የእድገት ብስራት ... ደጋግመው ሲሰሙት ደስ ስለሚል፤ “ማመን ማመን” ያሰኛል። ልማታዊውን የምስራሽ፣ በእልልታ መቀበልና መቦረቅ ያሰኛል። እንዲያው፤ የዋጋ ንረቱ፤ የኑሮ ውጋት እየሆነ ቀን ከሌት እረፍት ባይነሳኝ ኖሮ፤ በእምቢልታና በነጋሪት የልማት ምስክርነት ለማወጅ የወረፋ ግፊያ ውስጥ መግባቴ አይቀርም ነበር።

ግን ምን ያደርጋል? ይሄ የኑሮ ውድነት አላንቀሳቅስ አለ። የካቻምናው የዋጋ ንረት፤ ጫናው ቢከብደኝ፤ የኑሮውን ቁልቁለታማ ደረጃ ወርጄ ከአዲስ የኑሮ ውጋት ጋር እንደተዋወቅኩ አስታውሳለሁ። ያንኑን ከተለማመኩ በኋላ፤ እንደገና የአምናው የዋጋ ንረት፤ ሌላ ክፉ ውጋት ደርቦ አመጣው። እሱንም በመከራ ተለማምጄ ሳልጨርስ፤ ዘንድሮም ተጨማሪ ውጋት። ታዲያ፤ እንዴት ብዬ የልማት ዜናውንና የብስራት ዜማውን ተቀብዬ ላስተጋባ?

እንዲያም ሆኖ፤ ዜናው በየእለቱ ሲደጋገም፤ ይፈታተናል፤ ህመምን ያረሳሳል። የእድገት ብስራቱን ለማመን ካለኝ ጉጉት የተነሳም፤ “ምናልባት ኑሮ የከበደው እኔ ላይ ብቻ ይሆን እንዴ?” ብዬ ራሴን እሞግታለሁ። መሞገት ብቻም ሳይሆን፤ ሙሉ ለሙሉ ራሴን ለማሳመን የሚረዱ መረጃዎችን ባገኝ ብዬ መመኘቴ አልቀረም። ከመመኘት በመነሳትም ነው፤ አንድ ሁለት ሪፖርቶችን ማንበብ የጀመርኩት።

 

ስጋ ፍለጋ

የመጀመሪያው ሪፖርት፤ አዳሜ በየጊዜው ስንቴ በግ እያረደና ምን ያህል ስጋ እየበላ እንደሆነ ለማወቅ የሚረዳ ነው። አበሻ ነሮው ተሻሽሎ፤ ስጋ መብላት ስላዘወተረ ይሆን የበሬና የበግ ዋጋ የተወደደው? መልሱን የምናገኘው፤ የስታትስቲክስ ኤጀንሲ በየአመቱ ከሚያሳትማቸው የጥናት ሪፖርቶች ውስጥ ነው። መቼም የገበሬ ኑሮ ከተሻሻለ፤ የበሬዎቹና የላሞቹ ቁጥር በጣም ይጨምራል። የዘንድሮውን (እስከ ህዳር ወር ድረስ የነበረውን አመት) እና የአምናውን (ከአመት በፊት የነበረውን ተመሳሳይ ጊዜን) የሚሸፍኑ ሁለት ሪፖርት ይዤ አነፃፀርኳቸው። በጣም የገረመኝ፤ የከብቶች ቁጥር ከመጨመር ይልቅ ቀንሷል። የገጠር የህዝብ ብዛትና የቤተሰቦች ቁጥር በየአመቱ ቢጨምርም፤ የከብቶች ቁጥር ግን ከአምናው በ1.3 ሚ. እንደቀነሰ ሪፖርቶቹ ያሳያሉ። የበሬዎች ቁጥር ደግሞ በግማሽ ሚሊዬን ቀንሷል።

ምናልባት፤ ብዙ ገበሬዎች ከከብት እርባታ ይልቅ ወደ በግ እርባታ ገብተው እንደሆነስ? አይ፤ የበጎች ቁጥርም አምስት በመቶ ያህል ወርዷል - ከ25.5 ሚ ወደ 24.2 ሚ ቀንሷል (በ1.3 ሚ.)። የፍየሎች ብዛትም እንዲሁ በሁለት መቶ ሺ ከአምናው ያንሳል። ሪፖርቶቹን እያነፃፀርኩ ስመለከት፤ መፅናኛ የሚሆን ነገር ለማግኘት ተቸገርኩ። የገጠር ኑሮ እየተሻሻለ መሆኑን የሚያረጋግጥ መረጃ አጣሁ። ምን አለፋችሁ! ከአህያ ቁጥር በስተቀር፤ ያልቀነሰ ነገር የለም ማለት ይቻላል። በሪፖርቱ የተካተቱት፤ የበሬና የላም፤ የበግና የፍየል፤ የፈረስና የበቅሎ፤ የግመል ቁጥር ሳይቀር ከአምናው ያንሳል።

ምን ይሄ ብቻ! የዶሮዎች ቁጥር ከአምናው በዘጠኝ በመቶ ቀንሷል። አምና 49.3 ሚ. ዶሮዎች ነበሩ፤ ዘንድሮ 45 ሚ. ብቻ። የንብ ቀፎም ከአምናው እንደሚያንስ የኤጀንሲው የጥናት ሪፖርት ያመለክታል። ከዚሁ ጋርም፤ የእንቁላል ምርት በአራት በመቶ፤ የማር ምርት በ25 በመቶ ቀንሷል። ያው፤ የከብት ቁጥር ሲወርድ፤ የወተት ምርትም አብሮ በሃያ በመቶ ቀንሶ የለ?

እንዲያም ሆኖ፤ የገጠሬው ኑሮ አልተሻሻለም ብዬ አልደመደምኩም። ያን ሁሉ የልማትና የእድገት ዜና እየሰማሁ በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ አልችልም። ምናልባት፤ የበሬና የበግ፤ የፍየልና የዶሮ ቁጥር የቀነሰው፤ ገበሬው ኑሮው ተሻሽሎ ብዙ ስጋ መብላት ስለጀመረ ሊሆን ይችላል ብዬ ጠረጠርኩ። የስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሪፖርቶች፤ ለዚህኛው ጥያቄም መልስ ይዘዋል።

አምና፤ በገጠር ገበሬዎች ዘንድ ለእርድ የዋሉ የከብቶች ቁጥር 417ሺ እንደሆኑ የዚያው ሪፖርት ይገልፃል። ዘንድሮ ለእርድ የዋሉት ከብቶችስ ስንት ይሆኑ? 407 ሺ ብቻ። ይሄ ምን ማለት መሰላችሁ? በገጠር የሚኖሩ ቤተሰቦች ወደ 15ሚ. የሚጠጉ መሆናቸውን ልብ በሉ። እና፤ በአማካይ በአመት አንድ በሬ ለ37 ቤተሰብ ታርዶ ይበላል። በቃ። ከአራት አመት በፊት የወጣው የኤጀንሲው ሪፖርት ላይ የምናየው ሪፖርትም ተመሳሳይ ነው፤ በአማካይ በአመት አንድ በሬ ለ38 ቤተሰብ ነበር የሚታረደው።

ለነገሩ፤ በገጠር አካባቢ በሬ የሚታረደው ለሰርግ ወይም ለልዩ አመት በአል እንጂ፤ “ስጋ መብላት አማረኝ” በሚል አይደለም። እንዲሁ ስታስቡት፤ ስጋ መብላት ያሰኘው ቤተሰብ፤ በግ ወይም ፍየል ነው የሚያርደው። ግን የተመኘሁት አይነት መረጃ አላገኘሁም። ገበሬዎች ኑሯቸው እየበለፀገ ብዙ የበግ ስጋ መብላት እንደጀመሩ የሚያረጋግጥ መረጃ ለማየት ነበር የጓጓሁት - አልተሳካልኝም እንጂ። ዘንድሮ በገበሬ ቤተሰቦች ውስጥ ለእርድ የዋሉት በጎችና ፍየሎች ቁጥር ከአምናው በመቶ ሺ ያንሳሉ። አምና 5.19 ሚ. በጎችና ፍየሎች ለምግብነት ውለዋል - ዘንድሮ ግን 5.08 ሚ. ብቻ። በአማካይ፤ በአመት ውስጥ አንድ በግ ወይም ፍየል ለሶስት ቤተሰቦች እንደማለት ነው።

በእርግጥ፤ የበሬና የላም፤ የፍየልና የበግ ቁጥር በቀነሰበት አመት፤ ገበሬዎች ብዙ ስጋ እንዲበሉ መጠበቅ ያስቸግራል። እንዲያውም፤ ገበሬዎቹን ይበልጥ የሚያስጨንቃቸው፤ ስጋ አለመብላታቸው ሳይሆን፤ የከብቶቻቸው ቁጥር መመናመን ነው።

የበሬ ያለህ፤ የበግ ያለህ

እንደምታውቁት፤ የገበሬው ትልቅ ካፒታል (ጥሪት)፤ የቤት እንስሶቹ ናቸው - በሬዎቹና ላሞቹ፤ በግና ፍየሎቹ። ታዲያ የእነዚሁ ቁጥር እየቀነሰ፤ የገበሬዎች ኑሮ እንዴት ሊሻሻል ይችላል? ሚሊዬነር ሊሆኑ ይቅርና ኑሯቸው ወደ ታች እየወረደ ይመስላል። “ይመስላል” ያልኩት፤ ድህነታቸው ተባብሷል ብዬ ማመን ስለከበደኝ ብቻ አይደለም። ደግሞም የሁለት አመት ሪፖርት ብቻ በማየት ስለ ኑሮ መሻሻልና መውደቅ መናገር ተገቢ እንዳልሆነ አውቃለሁ። ቢያንስ፤ የሶስት የአራት አመታት ሪፖርቶችን ማገናዘብ ያስፈልጋል በሚል ሃሳብ፤ አፅናኝ መረጃ አገኝ እንደሆነ አፈላልጌያለሁ።

መቼም የህዝብና የቤተሰብ ቁጥር ከአመት አመት እየጨመረ ነው። የገበሬዎች ህይወት ባይሻሻል እንኳ፤ እዚያው ባለበት ደረጃ እንዲቀጥል፤ የቤት እንስሶቹ ቁጥርም ከህዝብ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ እድገት ሊኖረው ይገባል። የስታትስቲክስ ኤጀንሲ የጥናት ሪፖርቶች ምን ይላሉ?

የዛሬ አራት አመት የወጣው የጥናት ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ መቶ የገጠር ቤተሰቦች ውስጥ በአማካይ 355 ከብቶች፤ 180 በጎች፤ 160 ፍየሎች ይገኙ ነበር። የዘንድሮው ሪፖርትስ ምን ያሳያል? የከብቶቹ ቁጥር ወደ 345፤ የበጎቹ ቁጥር ወደ 160፤ የፍየሎቹ ቁጥር ወደ 150 እንደወረደ የኤጀንሲው የዘንድሮ ሪፖርት ያመለክታል። በቤተሰብ ደረጃ ከታየ፤ የገበሬዎች ጥሪት ባለፉት አራት አመታት ወደ ታች ወርዷል ማለት ነው። መረጃውን በሌላ አቅጣጫ ስንመለከተውም ወደ ተመሳሳይ ድምዳሜ ያደርሰናል።

ምንም ከብት የሌላቸው ቤተሰቦች፤ ባለፉት አራት አመታት፤ ቁጥራቸው በግማሽ ሚሊዬን ያህል ጨምሯል። የዛሬ አራት አመት፣ 2.7 ሚ. ቤተሰቦች ምንም ከብት አልነበራቸውም። ዘንድሮ ጥናት ሲካሄድ ደግሞ፣ 3.2 ሚ. ቤተሰቦች ምንም ከብት እንደሌላቸው ተረጋግጧል። ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የበሬ እርሻ፣ እጅግ ኋላቀር በመሆኑ ወደ ዘመናዊነት እንዲሸጋገር ስንጠብቅ፤ ጭራሽ በበሬ ማረስም ለበርካታ ሚሊዬን ገበሬዎች ብርቅ እየሆነባቸው ነው።

በግ የሌላቸው ቤተሰቦች ደግሞ እጅግ ብዙ ናቸው። የዛሬ አራት አመት 8.5 ሚ. ቤተሰቦች፣ ለምልክት ያህል እንኳ በግ የሚባል ነገር አልነበራቸውም። ዘንድሮ ግን በግ አልባ ቤተሰቦች እጅግ በዝተዋል፤ ከሶስት የገጠር ቤተሰቦች መካከል፤ ሁለቱ በግ የላቸውም። ከአስር ሚሊዬን በላይ ቤተሰቦች በግ አልባ ናቸው።

የፍየል ነገርማ የባሰ ነው። ከአራት አመት በፊት፤ ፍየል የሌላቸው ቤተሰቦች አስር ሚሊዬን የነበሩ ቢሆንም፤ ዘንድሮ ቁጥራቸው ከአንድ ሚሊዬን በላይ ስለጨመረ 11.2 ሚ. ሆነዋል። ከአራት የገጠር ቤተሰቦች መካከል፤ ሶስቱ ፍየል በአጠገባቸው ዝር አይልም።

አልቆርጥም ተስፋ

በዚህም በዚያም ብዬ የአራቱን አመታት ሪፖርቶች ስመለከት፤ የገጠር ድህነት እንደተባባሰ እንጂ እንደተሻሻለ የሚጠቁም መረጃ ላገኝ አልቻልኩም። በየገጠሩ ሚሊዬነሮች እንደአሸን እየፈሉ እንደሆነ የሚገልፁ ታላላቅ ልማታዊ ዜናዎችን በየእለቱ መስማቴ ባይቋረጥም፤ ለማመን መማለሌ ባይቀርም፤ ዜናውን ደጋግፎ የሚይዝ የመረጃ ምርኩዝ ጠፋ፤ በሪፖርቶቹ ውስጥ አልተገኘም።

ቢሆንም... ቢሆንም... በግል፤ ኑሮ ቢከብደኝም፤ ከመንግስት ሚዲያዎች በየእለቱ የሚዥጎደጎዱትን የልማት ዜናዎችንና የእድገት ብስራቶችን ለማመን ጥረት እያደረግኩ እንደሆነ እይሉኝ። ነገር ግን፤ የገጠሩን ኑሮ በሚመለከት፤ “ልማታዊ ዜናዎችን” የማመን ጥረቴ አልተሳካም። ምናልባት፤ መንግስት እንደሚያወራው የገጠር ኑሮ ባይሻሻልም፤ የከተሜዎች ኑሮ ተሻሽሎ ሊሆን ይችላልኮ ብዬ ከማሰብ ወደኋላ አላልኩም። ሃሳቤን ለማረጋጋጥም፤ የተወሰኑ መረጃዎችን ከዚህም ከዚያም ለማየት ሞክሬያለሁ።

የመጀመሪያው መረጃ፤ የስኳር ገበያውን የሚያሳይ ነው። እዚህ ላይ፤ ምንም አዲስ መረጃ ልነግራችሁ እንደማልችል ትገምቱ ይሆናል። የስኳር ምርት፤ ከከተሜነት የኢኮኖሚ እድገት ጋር አብሮ እንደሚያድግ ግልፅ ቢሆንም፤ ኢኮኖሚዋ በከፍተኛ መጠን እያደገ ነው በሚባልላት በአገራችን ግን፤ ስኳር አልተትረፈረፈም። ወይ መትረፍረፍ! ከስኳር እጥረት ጋር መኖር ከጀመርን አመታት ተቆጥረዋል - ታውቁታላችሁ።

ከመንግስት የምንሰማቸው ምላሾች፤ ከአመት አመት፤ ከወር ወር ተመሳሳይ እንደሆኑም ታውቃላችሁ። “የስርጭት ችግር እንጂ የስኳር አቅርቦት እጥረት የለም” የሚል የመንግስት ባለስልጣናት ምላሽ፤ መቼም ቀርቶብን አያውቅም። እንዲህ አይነት ምላሽ የሚያረካን ከሆነ፤ እድለኞች ነን፤ “የምላሽ አቅርቦት ላይ እጥረት የለም”። ስኳሩን በአይን ለማየትና በእውን ለመግዛት ባንችልም፤ “የስኳር እጥረት አለመኖሩ” ደስ አይልም?

የስርጭት ችግር እንጂ የስኳር እጥረት የለም የሚል ምላሽ፤ ጣፋጭ ነው - ስኳርን የሚተካ። በእርግጥ፤ ስኳር የማከፋፈልና የማሰራጨት ቢዝነሱን፣ ራሱ መንግስት ከነጋዴዎች ነጥቆ እንደተቆጣጠረው በየጊዜው የምናስታውስ ከሆነ፤ እርካታችን ሊቀንስ ይችላል። “የስርጭት ችግር እንጂ የአቅርቦት እጥረት የለም” የሚል ምላሽ ስንሰማ፤ “ደሞዝ ከፋይ የለም እንጂ፤ ደሞዝ አለ” እንደማለት አይሆንብንም?

ቢሆንም ግን፤ “የስኳር እጥረት እንደሌለ” መስማት፤ የከተሜ ነዋሪዎች የኑሮ ደረጃ እንደተሻሻለ እንደሆነ የሚጠቁም አባባል ስለሆነ... ያማልላል። ይህንኑን ለማረጋገጥ ነበር፤ በመንግስታዊው የስኳር ኮርፖሬሽን የቀረቡ የዘንድሮና የአምና ሪፖርቶችን ለማነፃፀር የሞከርኩት። “የመንግስት ኮርፖሬሽን”? የደርግ ጊዜ አባባል ይመስላል አይደል? መንግስት የንግድ ቢዝነሶችን የሚቆጣጠርበት የሶሻሊዝም ነገር!

የሆነ ሆኖ ኮርፖሬሽኑ አምና በሚያዝያ ወር ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት፤ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ሁለት ሚሊዬን ኩንታል የሚጠጋ ስኳር እንደተመረተ ጠቅሶ ነበር። በዚሁ ምርት ላይ፤ ከውጭ ተገዝቶ የመጣ ተጨምሮበት፤ በአጠቃላይ ለገበያ የዋለውና የተሸጠ የስኳር መጠን 3.25 ሚሊዬን ኩንታል ገደማ እንደሆነ የአምናው ሪፖርት ይገልፃል። ዘንድሮ በተመሳሳይ ሚያዝያ ወር የቀረበው ሪፖርትም ስለ ስኳር ምርትና ሽያጭ ጥቂት መረጃዎችን ይዟል። የዘንድሮው ምርት ከአምናው በስምንት በመቶ ያንሳል - የስኳር ምርት በ160ሺ ኩንታል ቀንሷል ማለት ነው። ለገበያ የዋለውና የተሸጠው የስኳር መጠንም ከአምናው በሁለት በመቶ ያንሳል (በ75ሺ ኩንታል)።

የስኳር ብቻ ሳይሆን የሲሚንቶ ፍጆታም ባለፉት ወራት ቀንሷል - ከአምናው ጋር ሲነፃፀር። በዚያ ላይ የአገር ውስጥ የግል ኢንቨስትመንትም ዝቅተኛ እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሪፖርት ያመለክታል... እንግዲህ እንደተመለከታችሁት፤ የመንግስትን የእድገት ዜናዎችና የልማት ብስራቶችን ለማመን በመጓጓት ያየኋቸው የመንግስት ሪፖርቶች፤ እድገትንና ልማትን የሚያበስሩ መረጃዎች አልያዙም። ግን፤ በዚህ ተስፋ የምቆርጥ እንዳይመስላችሁ። ሌሎች ብዙ ሪፖርቶችን ለማየት አስቤያለሁ።

 

 

 

Read 3363 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 14:09