Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Sunday, 06 May 2012 14:14

ጋዳፊን ማድነቅና ማወደስ በህግ ያስቀጣል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በሊቢያ የቀድሞውን የአገሪቱን መሪ ሙዓመር ጋዳፊ ከስልጣን ለማውረድ ሲዋጉ ለነበሩ አማፅያን ያለመከሰስ መብት የሚያጐናፅፍ አዲስ ህግ ባለፈው ሐሙስ የወጣ ሲሆን በማንኛውም መልኩ ጋዳፊን ወይም አገዛዛቸውን ማወደስ ወንጀል እንደሆነና በህግ እንደሚያስቀጣም ባለፈው ሐሙስ የወጣው ህግ ይደነግጋል፡፡ብሄራዊ የሽግግር ም/ቤት ድረገፅ ላይ የሰፈረው የህግ አንቀፅ “ለፌብሩዋሪ 17 አብዮት ሲባል የተወሰዱ እርምጃዎች በህግ አያስቀጡም” የሚል ሲሆን፤ ያለመከሰስ መብቱ “የአብዮቱን ስኬትና ግብ ለማረጋገጥ በአብዮተኞቹ የተወሰዱ ወታደራዊ፣ የደህንነት እና የሲቪል እርምጃዎችን” እንደሚያካትት ታውቋል፡፡

ፌብሩዋሪ 17 ባለፈው ዓመት የቀድሞውን የሊቢያ መሪ ሙዓመር ጋዳፊ ከስልጣን የገረሰሰው ህዝባዊ አመፅ የተጀመረበት ቀን እንደሆነ ይታወቃል፡፡የጋዳፊን መያዝና መገደል ተከትሎ ብሄራዊ የሽግግር ም/ቤቱ፣ ኦክቶበር 23 ቀን 2004 ዓ.ም የሊቢያን ነፃ መውጣት ማወጁ የሚታወቅ ሲሆን ህጉ ከዚያ በኋላ የተፈፀሙ ድርጊቶችን ያካትት እንደሆነ በግልፅ አልታወቀም ተብሏል፡፡

አምና በጋዳፊ ደጋፊዎችና በኔቶ በሚደገፈው የአማፂ ቡድን መካከል በነበረው ግጭት በሁለቱም ወገኖች የጦር ወንጀል መፈፀሙን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች የጠቆሙ ሲሆን ከቀድሞ አማፅያን በተውጣጡ ሚሊሺያዎች በሚመሩ የእስር ቤት ማዕከላት ድብደባና ግርፋት ይፈፀማል ሲሉ ቡድኖቹ አስጠንቅቀዋል፡፡

ብሄራዊ የሽግግር ም/ቤቱ የቀድሞውን የአገሪቱን መሪ ጋዳፊን ወይም አገዛዛቸውን ማወደስ ወንጀል ነው ብሏል - በአዲሱ ህግ ላይ፡፡

“ሙዓመር ጋዳፊን፣ አገዛዙን፣ ሃሳቦቹን ወይም ልጆቹን ማወደስ ወይም ማድነቅ በእስር ያስቀጣል” ይላል - ለሪፖርተሮች የተነበበው የህግ አንቀፅ፡፡

“የዜና ዘገባዎች፣ አሉባልታዎች ወይም ፕሮፓጋንዳዎች በመንግስት ላይ ማንኛውንም አይነት ጉዳት ካደረሱ የእድሜ ልክ እስር ያስቀጣል” የሚለው የም/ቤቱ ህግ፤ “የፌብሩዋሪ 17ቱን አብዮት የነቀፈ፣ የእስልምና ሃይማኖትን፣ የመንግስት ባለስልጣንን ወይም ተቋማቱን ስም ያጐደፈ” የእስር ቅጣት እንደሚጠብቀው ይደነግጋል፡፡

አዲስ በወጣው ህግ መሰረት ሊቢያ አሁንም በጦርነት ሁኔታ ውስጥ ያለች ሲሆን አገሪቱ በጦርነት ውስጥ ባለችበት ሁኔታ ጦር ሃይሉ አገሩን ለመከላከል የሚያደርገውን ዝግጅት የሚያደናቅፍ መረጃና አሉባልታ የሚያሰራጭ፣ የዜጐችን ሞራል የሚያዳክም ሽብር የሚነዛ ማንኛውም ሰው በእስር እንደሚቀጣ ተጠቁሟል፡፡

በሽግግር ም/ቤቱ የወጣው ሌላ ህግ ደግሞ የጋዳፊ ዘመዶችን ጨምሮ የቀድሞ አገዛዝ መሪዎች ሃብትና ንብረት በመንግስት እንደሚወረስ ያመለክታል፡፡

ብሄራዊ የሽግግር ም/ቤቱ በመጪው ሰኔ ወር የወረዳና የአውራጃ ምርጫ ለማካሄድ ቃል መግባቱን ያስታወሰው አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ፤ ይሄ አደገኛ ህግ የወጣው ምርጫው ሊካሄድ ጥቂት ሳምንታት ሲቀሩት እንደሆነ አክሎ ዘግቧል፡፡

 

 

 

Read 3500 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 14:16