Sunday, 13 May 2018 00:00

የጠ/ሚኒስትሩ ጉዞዎችና ፋይዳቸው?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

 ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ጋር እውነተኛ ድርድር ማድረግ ያስፈልጋል
      አሁን የሚያስፈልገው አስቸኳይ የሃገር ውስጥ የፖለቲካ መፍትሄ ነው
      ገዥው ፓርቲ ብቻ አይደለም የተዳከመው፤ ተቃዋሚዎችም ነን

   ወደ መንበረ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከመጡ ዛሬ 40 ቀን የሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እስከዛሬ ያደረጋቸው እንቅስቃሴዎች የሃገሪቱን ፖለቲካዊ ችግሮች ከመቅረፍ አንፃር ምን ያህል አጋዥ ናቸው? የውጭ ሃገራት ጉብኝታቸውስ ፋይዳ ምንድን ነው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አንጋፋውን ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌውን እና ዶ/ር መረራ ጉዲና አነጋግሯል፡፡

           “ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት”
               አቶ ልደቱ አያሌው

   የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ የአንድ ወር የሥራ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
እንግዲህ አንድ ወር ቀላል ጊዜ አይደለም፤ ብዙ ሥራ ሊሰራበት የሚችል ነው፡፡ እሳቸው ወደ ስልጣን የመጡበት መንገድ በቀውስ ምክንያት ነው፡፡ ያንን ቀውስ ሌት ተቀን ሰርቶ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ከአንድ ወር በላይ ሆኗቸዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት በተለያዩ ቦታዎች ህዝባዊ ስብሰባዎች ማድረጋቸው ተገቢ ነው፡፡ ከህዝቡ ጋር እየተገናኙ ተስፋ ሰጪ ንግግር አድርገዋል፡፡ ህዝቡም ንግግራቸውን ወድዶ ተስፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ አንፃር ሃገር ውስጥ ያደረጓቸው ውይይቶች ተገቢ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ህብረተሰቡ ደግሞ ያንን መነሻ በማድረግ፣ ተጨባጭ የሆነ ተግባራዊ እርምጃ እየጠበቀ ነው ያለው፡፡ ምናልባት ሃገር ውስጥ የጀመሯቸውን ህዝባዊ ስብሰባዎች ከጨረሱ በኋላ ወደ ተግባር ይገባሉ ብሎ ህዝቡ እየጠበቀ ነው፡፡
በዚህ መሃል ነው እንግዲህ ወደ ጎረቤት ሃገር ጉብኝታቸውን የቀጠሉት፡፡ በእኔ እምነት፤ ሃገሪቱ ከጎረቤቶቿ ጋር በጎ የሆነ ግንኙነት ያስፈልጋታል፡፡ በጣም ውስብስብ ችግር ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ከዚያ አንፃር ብዙ ጠንካራ ስራ ሊሰራበት የሚገባ ቀጠና ነው። ነገር ግን አሁን ዶ/ር አብይ፤ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያበቃቸው ምክንያት በዋናነት፣ በሃገር ውስጥ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ነው፡፡ ስለዚህ ከምንም ነገር በላይ በቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው ለመፍታት መረባረብ ያለባቸው የሃገር ውስጥ ጉዳይን እንጂ ውጪ ያለውን አይመስለኝም፡፡
ህዝቡ ተጨባጭ የሆነ መፍትሄ ከዛሬ ነገ ይመጣል እያለ እየተጠባበቀ ባለበት ሁኔታ፣ ተዘዋውረው የሚያደርጉት ስብሰባ፣ ከሃገር ውስጥ አልፎ ወደ ጎረቤት ሃገራት መሸጋገሩ ተገቢ መስሎ አልታየኝም፡፡ ሰው ምናልባት ይሄን ጉዳይ እንደ ጊዜ መግዣ አድርጎ እንዳይወስድባቸው እሰጋለሁ፡፡ ሀገሪቱ ከነበረችበት ፖለቲካዊ ቀውስ አንፃር፣ ጠ/ሚኒስትሩ በከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት፣ አስተማማኝ መፍትሄ ለማምጣት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ መንገድ የተወሰኑ ስራዎች ከሰሩ በኋላ የውጭው ጉብኝት ቢቀጥል ይሻል ነበር፡፡ ከቅደም ተከተል አንፃር አካሄዳቸው ትክክለኛ ነው ብዬ አላምንም፡፡
በሀገር ውስጥ የሚያደርጉት ጉብኝትና ህዝባዊ ስብሰባ፣ ሰላምና ፖለቲካዊ መረጋጋትን በመፍጠር  ረገድ አስተዋጽኦው ምን ያህል ነው?
ጠቀሜታው አጠያያቂ አይደለም፡፡ ግን አሁንም በርካታ ቀሪ ስራዎች አሉ፡፡ ቀሪ ስራዎች አሉ ብቻ ሳይሆን ገና አልተጀመረም ማለት ይቻላል፡፡ እውነቱን ለመናገር በኦሮሚያ ከተሞች ላይ ስብሰባ ማድረጋቸው ምክንያታዊ ነው፡፡ ጅግጅጋም በተመሳሳይ፣ ከዚያም በአማራ ክልል እና በትግራይ  ስብሰባ ማካሄዳቸውም ምክንያታዊ ናቸው ማለት እንችላለን፡፡ ነገር ግን በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የግድ ስብሰባ ማድረግ ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ ከዚህ በኋላ ቢሮአቸው ተቀምጠው፣ ወደ ዋናው ተጨባጭ የመፍትሄ እርምጃ መሄድ አለባቸው፡፡
እነዚህ ተጨባጭ የመፍትሄ እርምጃዎች ምንድናቸው?
በመጀመሪያ ደረጃ ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ጋር እውነተኛ ድርድር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በድርድሩ የህግ ማሻሻያዎች ማድረግ ያስፈልጋል፤ ተቋማት መሻሻል አለባቸው፡፡ የትኞቹ ተቋማት? በምን መልኩ ይሻሻሉ? በሚለው ላይ ከፍተኛ ስራ ይጠብቃል። እነዚህ ሁሉ ተግባር የሚጠይቁ ስራዎች ናቸው፡፡ ገና አልተጀመሩም፡፡ ከአሁን በኋላ ቢሮአቸው ቁጭ ብለው፣ ይሄን ትርጉም ያለው ስራ መስራት አለባቸው። ያለበለዚያ ግን ህዝቡ ንግግራቸውን ትርጉም እያሳጣው ይሄዳል፡፡ ጥንቃቄ ካልተደረገ፣ ሰው ተመልሶ ወደ ተስፋ መቁረጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ወደ ግርግርና አመፅ የማንመለስበት ዋስትና የለም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ወደ ተጨባጭ ስራ በአስቸኳይ መግባት አለባቸው፡፡
አሁን እኮ በአንዳንድ አካባቢዎች በጎ ያልሆኑ ነገሮችም እያየን ነው፡፡ አንዳንዴ እንደ መንግስትም እንደ ህዝብም የመርሳት ችግር ያለብን ይመስለኛል። በአንፃራዊነት ያገኘነውን ፋታ እንደ ዘላለማዊ ሰላም እንቆጥረውና እንዘናጋለን፡፡ ከዚያ ተመልሶ ችግሩ ሰፍቶ ይመጣል፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ ያየነውና የሆነው ይሄ ነው፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተወሰነ መረጋጋት ሲመጣ ህዝቡም መንግስትም የነበርንበትን ረሳነው፡፡ መንግስት የተለመደ ተግባሩን ቀጠለ … በቃ ተረጋግቷል በሚል ተዘናጋ፡፡ ትኩረታችን ወደ ልማት፣ ወደ ከፍታ መሆን አለበት ተባለ፤ ግን ተመልሶ ችግር ውስጥ ተገባ። አሁንም ይሄን ነገር እየረሳነው ነው፡፡ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ምን አይነት አስጨናቂ ሁኔታ ላይ እንደነበርን፣ እንደ ህዝብም እንደ መንግስትም እየረሳነው ነው። የፖለቲካ አልዛይመር አለብን፡፡ የመርሳት በሽታ። እንዲህ አይነት ችግር አውሮፓ ተከስቶ ቢሆን፣ መንግስቱም ህዝቡም፣ ሁለተኛ እንዳይደገም በሚል ለስር ነቀል ለውጥ ይተጉ ነበር፡፡ እኛ ሀገር ግን የመዘናጋት ችግር አለብን፡፡ ዶ/ር አብይ በዚህ አንድ ወር ውስጥ በርካታ ስብሰባዎች አድርገዋል፡፡ ነገር ግን አንድም ቀን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አድርገው አያውቁም፡፡ እራት መጋበዝና ውይይት ማድረግ አይገናኝም፡፡ አሁን የሚያስፈልገው አስቸኳይ የሃገር ውስጥ የፖለቲካ መፍትሄ ነው፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በጎረቤት ሀገራት ጉብኝታቸው የታሰሩ ኢትዮጵያውያንን አስፈትተዋል፡፡ ሌሎች ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶችም ተገኝተዋል፤ እስቲ ከዚህ አንፃር ይመልከቱት?
ዲፕሎማሲ አያስፈልግም አላልኩም፡፡ ጥያቄው የቅደም ተከተል ጉዳይ ነው፡፡ በአገር ውስጥ አስተማማኝ ሰላም እስካልተፈጠረ ድረስ በውጭ ሃገር ዲፕሎማሲያዊ ድል የትም መድረስ አይቻልም፡፡ በመጀመሪያ የውስጥ ቤት ነው መጥራት ያለበት፡፡ ቤት ሳይጠራ ወደ ውጪ ማተኮር ትክክል አይመስለኝም። ጎረቤት አካባቢ ችግር የለብንም እያልኩ አይደለም። ከዚያ የባሰ፣ ሀገር ውስጥ አታካች ችግር አለ ማለቴ ነው፡፡ በመጀመሪያ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ እንዳይደገም አድርገን መፍትሄ መስጠት አለብን፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ለምን ጉዳዮች ነው ቅድሚያ ሊሰጡ የሚገባው?
ከፓርቲዎች ጋር መደራደር ነው ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው፡፡ ሀገሪቱን ለፖለቲካ ቀውስ የዳረገው መሰረታዊ ምክንያት ምንድን ነው በሚለው ላይ ውይይት አድርጎ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ በችግሮቹ ላይም ከህዝብ ወኪሎች ጋር መተማመን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ሳናደርግ መፍትሄ መስጠት ግራ መጋባት ነው የሚሆነው፡፡ ይሄን ችግር ለመፍታት ምን እናድርግ? ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ እዚህ ጥያቄ ላይ ሲደርስ ጉዳዩ ወይም የለውጥ ሂደቱ የኢህአዴግ ብቻ ስለማይሆን አንድ ሃገር አቀፍ ተቋም መቋቋም አለበት፡፡ የሃገር ጉዳይ ስለሆነ ምናልባት የሪፎርም ኮሚሽን ልንለው እንችላለን፡፡ ሁሉንም ወገን በማሳተፍ ነው መቋቋም ያለበት፡፡ ይህ ኮሚሽን የሚሰራቸው ተግባራት፣ የቆይታ ጊዜው ተወስኖ በአዋጅ መቋቋም አለበት፡፡ በኔ አመለካከት ይህ ኮሚሽን ለሁለት አመታት የሚሰራ መሆን አለበት፡፡ የኮሚሽኑ የመጀመሪያ ተግባር፣ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ መድረክ መፍጠር ነው፡፡ ህዝቡ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ማዕከል ድረስ ተሳትፎ የሚያደርግበት፣ እስከ አሁን የነበርንበትን የፖለቲካ ቁርሾ፣ ቂም በቀል አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ፣ እኛ ላይ አቁሞ፣ ለቀጣይ ትውልድ እንዳይተላለፍ የሚያደርግ የብሔራዊ እርቅ መደረግ አለበት፡፡
በሃገር ውስጥ የሚገኙ፣ በውጭ ያሉ ማናቸውም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች ሁሉ ጥሪ ተደርጎላቸው ውይይት መደረግ አለበት፡፡ ከተቻለ ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ በመንግስት ኃላፊነት የሰሩ፣ በፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥ የነበሩ ሰዎች መድረክ እየተሰጣቸው፣ ጥናታዊ ፅሑፎች እየቀረቡ ውይይት እየተደረገ፣ ይቅርታ እየጠየቁ፣ ህዝቡም ይቅር እያለ፣ ይሄን አዙሪት የምናቆምበት የብሔራዊ እርቅ መድረክ ያስፈልጋል። አንዱ የኮሚሽኑ ስራ መሆን ያለበት ይሄ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛው መሰራት የሚችለው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አካሂዶ፣ የኔ የሚለውን መንግስት መምረጥ ሲችል ነው፡፡ ሌላኛው የዚህ ኮሚሽን ተግባር በሚቀጥለው ሁለት ዓመት ውስጥ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ መሻሻል ያለባቸውን ህጎች መፈተሽ፣እንዲሁም ተቋማትን መለየት መቻል ነው፡፡
ፓርቲዎች ተጠናክረው ወጥተው ከህዝብ ጋር በደንብ ተገናኝተው፣ የፖለቲካ ስራ የሚሰሩበት ምቹ ሁኔ መፈጠር አለበት፡፡ ህዝቡም ሳይሸማቀቅ፣ ማንኛውንም ፓርቲ ብደግፍ የሚደርስብኝ ነገር የለም ብሎ ከልቡ አምኖ፣ የፖለቲካ ተሳትፎው ማደግ አለበት፡፡ እነዚህን ነገሮች ካደረግን በኋላ በሁለት ዓመት ውስጥ ብሔራዊ ምርጫ መካሄድ አለበት፡፡ በዚያ ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ የፈለገውን ፓርቲ መርጦ፣ የሚረካበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ሁለት አመት ሰፊ ጊዜ አይደለም፡፡ በሩጫ መስራት ያስፈልጋል። የዶ/ር አብይ ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚለየውም በእነዚህ ሁለት ዓመታት በሚሰሩት ሥራ ነው፡፡ ዋነኛ ስራቸውም ብሔራዊ እርቅና መግባባት ማምጣት፤ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የሚካሄድበትን መድረክ መፍጠር ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ተማምነን፣ ተደራድረን መፍታት ያለብን ችግር ካለ መፈተሽ አለብን፡፡ ለምሳ እኔ ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን የምንከተለው የፌደራል አደረጃጀት መፈተሽ አለበት፡፡ የህግ እና የመዋቅር ችግሮች ናቸው ለቀውስ የዳረጉን፤ ስለዚህ መፈተሸ አለባቸው፡፡ የፓርቲዎች አደረጃጀትም መሻሻል አለበት፡፡ ሌላው ከፍተኛ የሆነ የፕሮፓጋንዳ ስራ፣ ቅኝት ማሻሻያ መደረግ አለበት፡፡ ከፋፋይ የሆነ ፕሮፓጋንዳ ሲነዛ ነው የኖረው፤ ይሄ መስተካከል አለበት፡፡ አንድነታችንን ሊያጎለብቱ የሚችሉ ስራዎች መሰራት አለባቸው፡፡ ይሄም በጥልቀት መፈተሽ አለበት። መገናኛ ብዙኃን ያለባቸው መሰረታዊ ችግር መፈተሽ አለበት፡፡ ጥልቀት ያለው ውይይት መደረግ አለበት፡፡ አለበለዚያ ህዝቡ እና መንግስት የሚገናኙበት ሁነኛ ሚዲያ አጥተው፣ የሃገሪቱን እጣ ፈንታ የሚወስነው ማህበራዊ ሚዲያ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ችግሮች በአመፅ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት የሚቻልበት መንገድ ሊፈጠር ይገባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለባቸው አንዱ ኃላፊነት ይሄ ነው፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ከተቃዋሚዎች ምን ይጠበቃል?
እውነቱን ለመናገር አብዛኛው ተቃዋሚ፣ የዶ/ር አብይን ወደ ስልጣን መምጣት በበጎና በተስፋ ነው ያየው፡፡ ንግግራቸውን አበረታትቷል፤ ደግፏል። ተቃዋሚው ከዚህ አንፃር መመስገን አለበት፡፡ ድሮ ያደርግ እንደነበረው ኢህአዴግ ስለሆኑ ብቻ ጥላሸት ሊቀባቸው አልፈለገም፤ ደስ ብሎታል ግን ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየጠበቀ ነው፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚው ማድረግ ካለበት አንዱን ተግባር አከናውኗል ማለት ነው፡፡ ሌላው ተቃዋሚው ለድርደር በቂ ሃሳብ እየያዘ፣ ለሰፊ ተሳትፎ መዘጋጀት አለበት፡፡ ሰፊ ሃሳብ ይዞ ለመደራደር ጫና መፍጠር አለበት፡፡ ድርድሩ ተካሂዶ የሚፈለገው ውጤት ከመጣ በኋላ፣ ህዝቡ ውስጥ ገብቶ የማንቃት ስራ ይጠብቀዋል፡፡ ለዚያም ሰፊ ዝግጅት ማድረግ አለበት፡፡ በሁለት አመት ውስጥ ይሄን ማድረግ ቀላል ስራ አይደለም፡፡ ከባድ ነው፡፡ ግን ተቃዋሚዎች የተቻለውን ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡
ህዝቡ ውስጥ ገብተው የተደራጀ ስራ መስራት አለባቸው፡፡ ራሳቸውን መገምገም አለባቸው፡፡ ከእርስ በእርስ ቁርሾ መውጣት ይገባቸዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ብቻ አይደለም የተዳከመው፤ ተቃዋሚዎችም ነን፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የማንጠቅም ሆነናል፤ እንዴት ሆንን? ለምን ሆንን? ብለን መጠየቅ አለብን። በህዝቡ ትግል ውስጥ ተጨባጭ የሆነ ሚና የለንም። ይሄን አምነን ለህዝቡ አሳውቀን፣በሌት ተቀን ስራ፣ ጠንክረን መወጣት አለብን፡፡

--------------

         ”ተስፋችን ጥንቃቄ የተሞላበት ነው”
           ዶ/ር መረራ ጉዲና

• በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ሆኖ፣ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የለም
• ህዝቡ በየጊዜው፣ ለዶ/ር ዐቢይ እያነሳ ያለው ጥያቄ ቀላል አይደለም
• ጠ/ሚኒስትሩ እስካሁን ከፖለቲካ ኃይሎች ጋር ድርድር አልጀመሩም


    ጠ/ሚኒስትሩ በጎረቤት ሃገራት ያደረጓቸው ጉብኝቶች ፋይዳ ምን ያህል ነው ይላሉ?
በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወዳጅ ማፍራትን ታሳቢ ያደረገ ነው። እንቅስቃሴው ምን ያህል የሀገሪቷን ጥቅም ያስከብራል፣ ያሳድጋል የሚለውን ለመገምገም፣ ስምምነቶቹ ነገ ከነገ ወዲያ ምን እንደሚያመጡ ማወቅ አለብን፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን እንደ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ከሀገሪቱ ዜጎች ጋር መወያየትም ሆነ ከአካባቢ መንግስታት ጋርም የዲፕሎማሲ ስራ መስራት ያለና የሚኖር ነው፡፡
ከዚህ በፊት ከነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተለየ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ነው ማለት ይቻል ይሆን?
አዎ! እንቅስቃሴው ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየ ነው፡፡ ለምሳሌ አቶ መለስ በጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ዘመን፣ ህዝብን በዚህ አግባብ፣ ተዘዋውረው ያነጋገሩ አይመስለኝም፡፡ እንደውም አንዳንድ አካባቢዎች አለመሄዳቸው ያሳማቸው ነበር፡፡
እኚህኛው ሙከራቸው ጥሩ ነው፡፡ ግን የሳቸው ጉዞ ለኢህአዴግና ለፖሊሲው ዝምድና ለመግዛት ነው? ወይስ የህዝቡን ጥቅም ለማስከበር ነው? የሚለውን ውሎ አድሮ የምናየው ይሆናል፡፡ ግን አዲስ መሪ፤በተመረጠ ሰሞን በሃገር ውስጥም በውጪም ጉብኝት ማድረግ የተለመደ ፖለቲካዊ አካሄድ ነው፡፡
ለጉብኝት የመረጧቸው ሃገራትስ---ፖለቲካዊ አንድምታቸው ምንድን ነው?
የሃገራት ምርጫ እንኳ እንደ ግብዣው ነው። ለምሳሌ ወዲያው እንደተመረጠ “ና ጎብኝ” ብሎ የሚጋብዝ አለ፡፡ ስለዚህ ጉብኝቱ የሚካሄደው እንደቀረበለት ግብዣ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ጉብኝቱ ለህዝብ ምን ያህል ጥቅም አለው ነው ጉዳዩ፡፡ ለምሳሌ ጅቡቲና ሱዳን ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች በራቸው ዝግ ነው፡፡ እንቅስቃሴያቸው ተቃዋሚዎችን የሚጎዳ ነው፡፡ ከዚህ ከሞትም ከእስርም ሸሽተው የሄዱት ሰዎችን፣ መልሰው አሳልፈው የሚሰጡ አገራት ናቸው። አሁን ያደሱት ወዳጅነት ከኢህአዴግ ጋር ነው ወይስ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር? የሚለውን በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡
የሀገር ውስጥ ጉብኝቶችና ህዝባዊ ውይይቶች ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶችን ለመፍታት አስተዋጽኦዋቸው ምን ያህል ነው?
ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ብዙ ጊዜ ነው ቃል ሲገባ የኖረው፡፡ እሳቸውም ከሰማይ በታች  ብዙ ነገር ቃል እየገቡ ነው፡፡ ዋናው ነገር ይሄን ቃል ወደ ተግባር ማውረድ ነው፡፡ ይሄ ነው ትልቁ ፈተና፡፡ ኢህአዴግ ለመለወጥ ምን ያህል ዝግጁ ነው? የሚለውም ውሎ አድሮ የሚታይ ነው፡፡ በጉብኝታቸው፤ ህዝቡ እያነሳ ያለው ጥያቄ ቀላል አይደለም፡፡ በጣም ብዙ ችግር ነው እየተነሳላቸው ያለው፡፡ ድርጅታቸውን አሳምነው፣ ምን ያህል ምላሽ ይሰጣሉ የሚለው በቀጣይ የሚታይ ነው። አሁንም ከእስር መፈታት እያለባቸው፣ ያልተፈቱ አሉ። ለምሳሌ በእነ በቀለ ገርባ መዝገብ የተከሰሰ፣ ደረጀ መርጋ የሚባል አባላችን፣ ተነጥሎ ተፈርዶበት በእስር ላይ ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ሆኖ፣ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የሚባል ነገር የለም። በዚህ መሃል ደግሞ በተለይ በኦሮሚያ ሞያሌ፣ ሻኪሶ አካባቢዎች ሁኔታዎች ጥሩ አይደሉም። የህዝብን ልብ ለመግዛት ለሚንቀሳቀስ አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና እነዚህ ሁኔታዎች እንቅፋት ናቸው፡፡
ለምሳሌ በሻኪሶ፣ ከአላሙዲ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ጋር የተፈጠረው ችግር፣ ከ15 ዓመታት በፊት የሚታወቅ ነው፡፡ ይሄን ለመመለስ ዛሬም ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡ ብዙ ነገሮች ሊታዩ የሚችሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለእነዚህ ሁሉ የህዝቡ ጥያቄዎች፣ ምላሽ መስጠት ሲጀምሩ ነው፡፡ ሌላው ዋና ጉዳይ፣ ጠ/ሚኒስትሩ እስካሁን፣ የህዝብ ድጋፍ አላቸው ከሚባሉ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ምንም አይነት ድርድር አልጀመሩም፡፡ ከሃገር ውስጥም ከሃገር ውጪም የሚንቀሳቀሱ የህዝብ ድጋፍ ያላቸው ኃይሎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ጋር ድርድር መጀመር አለበት፡፡
የጠ/ሚኒስትሩን የእስካሁን ሥራዎች እንዴት ነው የሚገመግሙት?
እኛ ተስፋ የምናደርገው ከጥንቃቄ ጋር ነው። በጣም ጥንቃቄ በበዛበት ሁኔታ ነው ተስፋ የምናደርገው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም ማድረግ አይችሉም ብለን እግራቸውን መጎተት አንፈልግም። አሁን ያለውን ኢህአዴግን ለውጠው፣ የኢትዮጵያን ህዝብ በአግባቡ ይመራሉ ወይ? የሚለውን እኛም ህዝቡም እንጠይቃለን፡፡ ዋናው የእሳቸው ፈተና ይሄ ነው፡፡
ኢህአዴግን ለለውጥ ካዘጋጁ፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መስራት አይከብዳቸውም፡፡ ለ27 ዓመታት የተጋፈጥናቸው በርካታ የታሪክ ፈተናዎች አሉ። ስለዚህም እኛ ተስፋ የምናደርገው፣ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ነው፡፡   


Read 5293 times