Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Sunday, 06 May 2012 14:14

ሚሼል ለኦባማ ቅሰቀሳ እያደረጉ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በመጪው ዓመት በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ አሸንፈው ዋይት ሃውስ ለመቅረት ወገባቸውን ታጥቀው ዱብ ዱብ እያሉ ነው፡፡ ባለቤታቸው የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማም ከጐናቸው ሆነው መራጩ ህዝብ ለኦባማ ድምፁን እንዲሰጥ እየቀሰቀሱ ነው - በምርጫ ዘመቻ ንግግሮቻቸው፡፡ ሚሼል ባለቤታቸው ምርጫውን አሸንፈው ከዋይት ሃውስ ላለመውጣት ሲሉ የ74 ዓመት እናታቸው ዋይት ሃውስ ውስጥ እንደማይኖሩ አስተባብለዋል፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሚሼል እናት ማርያን ሮቢንሰን በዋይት ሃውስ ከኦባማ ቤተሰብ ጋር እንደሚኖሩ ቢታወቅም ባለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ቀዳማዊት እመቤትዋ በገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር እናታቸው በዋይት ሃውስ እንደማይኖሩ ተናግረዋል - ለዲሞክራት ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች፡፡

“እኔና ቤተሰቤ በደቡባዊ ቺካጐ በአክስቴ ትንሽዬ አፓርትመንት ውስጥ ነበር የምንኖረው፡፡ እናቴ አሁንም ድረስ እዛ ቤት ውስጥ ነው የምትኖረው” ሲሉ እናታቸው አብረዋቸው እንደማይኖሩ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፤ ሚሸል ይሄን ሁሉ መናገር ያስፈለጋቸው መራጩን ህዝብ እኔና ቤተሰቦቼ እንደናንተ መካከለኛ መደብ የህብረተሰብ ክፍል ነን የሚል መልዕክት በማስተላለፍ መራጩ ድምፁን ለኦባማ እንዲሰጥ መማረካቸው ነው፡፡

ሆኖም የሚሼል ቤተሰብ ወደ ስፔን፣ ሃዋይና ሌሎች አገራት ላደረገው ጉዞ ያወጣው ከፍተኛ ወጪ በአሜሪካውያን ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ ከ2008 እ.ኤ.አ ጀምሮ በአንድ በኩል ገቢያቸው እያሽቆለቆለ በሌላ በኩል የነዳጅ፣ የጤናና የትምህርት ወጪ እያሻቀበ የመጣባቸው አሜሪካውያን በቤተሰቡ የጉዞ ወጪ ቅሬታ ቢያድርባቸው አይፈረድባቸውም ይላሉ - ተንታኞች፡፡

የቀዳሚዋ እመቤት የ2010 የስፔን ጉዞ ግብር ከፋዩን ለ487ሺ ዶላር ወጪ የዳረገ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ በጉዞው የተካተተው የቤተሰቡ ብዛት የጥበቃና ደህንነት ወጪውን ስላናረው ነው ተብሏል፡፡ በቀጣዩ ዓመት ሚሼል ወደ ደቡባዊ አፍሪካ ላደረጉት ጉዞ ደግሞ 424ሺ 142 ዶላር እንዳስወጣ ተጠቁሟል፡፡ የእነዚህን ከፍተኛ የጉዞ ወጪዎች ያጋለጠው መቀመጫውን በዲሲ ያደረገው “ጁዲሽያልዎች” የተባለ መንግስትን በዓይነ ቁራኛ የሚከታተል ቡድን ነው፡፡

“መራጩ ህዝብ ማንኛውንም ነገር ከራሱ የግል ሁኔታ አንፃር ነው የሚያየው፡፡ እነሱ ለማድረግ አቅማቸው የማይፈቅድ ከሆነ ሊያስደስታቸው አይችልም፡፡ ኦባማ በግብር ከፋዩ ገንዘብ ራሳቸውን ሲጠቅሙ ማየት አይወዱም” ብሏል አንድ የምርምር ተቋም፡፡

ከእነዚያ መራጮች መካከል አንዱ “ሚሼል ኦባማ ልጆቻቸውን ሃዋይ ለመውሰድ 1ሚ. ዶላር አውጥተዋል” ሲል ቀዳሚዋ እመቤትን አሳጥቷቸዋል፡፡ ሌላው መራጭ ደግሞ “በጣም ብዙ ጉዞዎችን በማድረግ ኦባማ ብቸኛው ፕሬዚዳንት ናቸው” በማለት ቅሬታውን ገልጿል፡፡

እነዚህ ሁሉ ቅሬታዎችና ትችቶች የሚዘንብባቸው ኦባማ ሆኑ ባለቤታቸው ራሳቸውን የመካከለኛው መደብ ህብረተሰብ አባል አድርገው ለማቅረብ መሞከራቸው አልቀረም፡፡

“እስካሁን መቼም ስለ እኔ ታሪክ ታውቃላችሁ … አባቴ በከተማዋ የውሃ ፋብሪካ የጉልበት ሠራተኛ ነበር… እናም እዚያ ዕድሜውን በሙሉ ነው የሰራው … ከወላጆቼ አንዳቸውም ኮሌጅ የመግባት ዕድል ገጠማቸውም … ያላቸውን በሙሉ ግን እኛ ላይ አፍስሰዋል፤ ምክንያቱም እኔና ወንድሜ ተጨማሪ ነገር እንድናገኝ ፈልገው ነበር” በማለት በአሪዞና የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ለተገኘው ታዳሚ ገልፀዋል - ሚሼል፡፡

የቀዳማዊት እመቤትዋ አባት በአካባቢያቸው የሚገኘው የዲሞክራት ፓርቲ ዕውቅ አባል የነበሩ ሲሆን ሚሼል በፕሪንስተንና በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማም ተመሳሳይ ቃና ያለው ነገር ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ኦባማ በ1981 ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ፣ ከዚያም በ1988 ሃርቫርድ ከመግባታቸው በፊት አያቶቻቸው በሃዋይ የግል ት/ቤት እንዳስተማሯቸው ይታወቃል፡፡

ባለፈው ወር አፕሪል 25 ኦባማ በአዮዋ ለተማሪዎች ባደረጉት ንግግር፤ “እናቴ ላጤ ነበረች፤ አባቴ አብሮን አልነበረም፤ ሁለት ልጆችን ከአያቶቼ ጥቂት ድጋፍ እየተደረገላት ለብቻዋ ነው ያሳደገችን … እኔም ሚሼልም ዛሬ እዚህ ለመገኘት የበቃነው ስኮላርሺፕና የተማሪዎች ብድር የላቀ ትምህርት የመማር ዕድል ስለሰጠን ነው” ብለዋል፡፡ ባራክ ኦባማና ባለቤታቸው ምርጫውን በድል ለመወጣት የቀየሱት ስትራቴጂ ያዋጣቸው ይሆን? አብረን እናየዋለን፡፡

 

 

 

 

Read 3057 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 14:18