Sunday, 06 May 2012 14:20

ሳይጠገብ የተጠናቀቀው የማኪራ ጉዞ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

“ቡናን ለዓለም ያስተዋወቀው ካሊ አዲ እንጂ ካልድስ አይደለም”

የ“ገመና” ተዋናዮች በማኪራ ተደምመዋል

ልጅ አዋቂ ሳይባል ሁሉም በክትና ባህላዊ ልብሱ አምሮና ደምቆ፣ በማይጠገብ ባህላዊ ዜማ፣ ዘመናዊነት ባልነካውና ባልተበረዘ ንፁህ የብሔረሰቡ ማራኪ ውዝዋዜና ጭፈራ ይጠብቀናል ብሎ ያሰበ ቀርቶ የጠረጠረ እንኳ በመኻላችን አልነበረም፡፡

የኦሮሚያና የካፋ ዞን አዋሳኝ የሆነውን የጐጀብ ወንዝ ድልድይ እንደተሻገርን ከወንዙ ጐን ባለችው ጐጀብ ከተማ የጠበቀን ትዕይንት ለማመን የሚከብድ ነበር፡፡ የዚያን ዓይነት ከልብ የመነጨና በፍቅር የተሞላ አቀባበል ለመሪዎች እንኳ ሲደረግ ማየት የተለመደ ስላልሆነ በጣም ነው የተደነቅነው፡፡

በስፍራው የደረስነው ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ነበር፡፡ የቦንጋና የጐጀብ ከተሞችና የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ከተማዋን በባንዲራና በአበባ አሸብርቀው ዝግጅታቸውን አጠናቀው፣ እንግዶቻቸውን በዘፈንና በባህላዊ ዳንኪራ ለመቀበል፣ ሙዚቃና ጭፈራውን የጀመሩት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት እንደነበር ተረዳን፡፡ ጊዜው እየመሸ ስለሄደ፤ ራቅ ካለ አካባቢ የመጡ በርካታ ሰዎች መመለሳቸውን ስንሰማ ብዙዎቻችን “ምነው ቀደም ብለን ደርሰን ቢሆን ኖሮ፣…”በማለት ተቆጨን፤ የጥፋተኝነት ስሜትም ተሰማን፡፡

የካፋ አስተዳደርና ማንኪራ የፕሮሞሽን ሥራዎች ኃ.የተ.የግ.ማ በጋራ ያዘጋጁት ጉዞ ሁለት ዓላማዎች አሉት፡፡ አንደኛው፣ ብዙዎች ቡናን ለዓለም እንዳበረከተች በሚገምቷት በካፋ ዞን በዴቻ ወረዳ የእናት ቡና መገኛ (ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ እንደበቀለባት በሚነገርላት) ማኪራ ቀበሌ ተገኝቶ ማንም ሳይነካው ለበርካታ ዘመናትና ትውልድ ተጠብቆ የቆየውንና የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለልማትም ሆነ ለሌላ አገልግሎት እንዳይውል በማለት አምና የመዘገበውን የተፈጥሮ ቡና የሚበቅልበትንና ጥቅጥቅ ያለ የተፈጥሮ ደን (የአካባቢው ሳንባ) የሆነውን ስፍራ መጐብኘት ለሌሎችም ማሳወቅ ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት የቡና ሙዚየምና ዓለምአቀፍ የቡና መረጃ ማዕከል በቦንጋ ከተማ እንዲሠራ በወሰነው መሠረት፣ ግንባታው ተጀምሮ በ2005 ሥራ እንደሚጀምር የሚጠበቀው ሙዚየም አሁን በምን ደረጃ ላይ እንዳለ አይቶ ለሌሎችም ማሳወቅ ነው፡፡ የጉብኝቱ ታዳሚዎች፣ ከተለያዩ ክፍሎች የተውጣጡ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ በርካታ አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ደራሲዎች፣ ጸሐፍት፣ ዘፋኞች፣ ሙዚቀኞች፣ ፊልም ፀሐፊ፣ አዘጋጅ…በአጠቃላይ ሦስት መለስተኛ አውቶቡሶች የሞሉ የጥበብ ሰዎች ናቸው፡፡

ማክሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2004 የደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ይዘን ጉዟችንን እንደጀመርን፣ የምናየው ስፍራ ሁሉ አረንጓዴ የለበሰ ነው፡፡ እየራቅን በሄድን ቁጥር አረንጓዴነቱ ቢጨምርም የተፈጥሮ ማራኪነቱ ማየል የጀመረው ጐጀብ ልንደርስ 19 ኪ.ሜ ሲቀረን ነው፡፡ ተፈጥሮን እያደነቅን ጉዟችንን ቀጠልን፡፡

ጐጀብ ቀድሞ የደረሰው ጋዜጠኞችን፣ አርቲስት አብራር አብዶና አርቲስት ችሮታው ከልካይን የያዘው አውቶቡስ ነበር፡፡ አስተናጋጆቻችን መድረሳችንን ሲሰሙ ተስፋቸው ለምልሞ፣ ድካማቸው ጠፍቶ ከበሯቸውን እየመቱ ሆታ፣ እልልታና ጭፈራቸውን አቀለጡት፡፡ አርቲስት አብራር የተቀመጠው ከፊት - ለፊት ስለነበር በቀላሉ ይለያል፡፡ አስተናጋጆቻችን (ተቀባዮቻችን) የሚያውቁት ሰው በማየታቸው እየተጠቋቆሙ በደስታ ፈነደቁ፡፡ ከመኪናው ስንወርድ እንደ እቅፍ አበባ የቡና ችግኝ ተበረከተልን፡፡ ስለመሸ ሁለቱ አርቲስቶችና አንዲት ጋዜጠኛ፣ ለችግኝ መትከያ ወደተዘጋጀው መደብ ሄደው በባትሪ እየተመሩ ችግኙን ተከሉ፡፡

ከዚያም ወደተዘጋጀልን ድንኳን ገብተን አጭር ንግግር ከተደረገ በኋላ የእራት ግብዣው ቀጠለ፡፡ በዚህ በመኻል የዘገዩት ሁለቱ መኪኖች ሲደርሱ ዳግመኛ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ተጀመረ፡፡ አስተናጋጆቻችን በቲቪ መስኮት የሚያውቋቸው የገመና 2 አርቲስቶች በገሃድ ፊታቸው ቆመው ሲያዩዋቸው ማመን አቃታቸው፡፡ “እገሌ፣ …እገሌ…” እያሉ በሚያውቁት የድራማው ገፀ - ባህሪ ስም እየጠሩ ጨበጡዋቸው፣ አቀፏቸው፡፡ አርቲስቶቹም ታዲያ የአድናቂዎቻቸውን አያያዝ ስለሚያውቁ አፀፋውን ከመመለስ አልቦዘኑም፡፡ የጐጀቡ ዝግጅት እንዳበቃ በበርካታ መኪኖች ታጅበን ጉዞ ወደ ቦንጋ ተጀመረ፡፡ ትንሽ እንደተጓዝን ስላካፋ የመንገዱ ጭቃ ጉዟችንን ከመፈታተኑም በላይ አንዳንዱን መኪና አላላውስ ብሎ በሌላ መኪና ተጐትቶ ወጣ፡፡ ቦንጋ ከተማ ስንገባ ከምሽቱ 6፡00 ነበር፡፡

በማግስቱ እንግዶችና በርካታ የከተማዋ ነዋሪ ከቦንጋ 17 ኪ.ሜ ወደምትርቀው የእናት ቡና ምድር ማኪራ ጉዞ ጀመርን፡፡

ምናልባት 10 ኪ.ሜ ያህል በመኪና እንደተጓዝን ጥርጊያው መንገድ አያስኬድም ስለተባለ ብዙ መኪኖች ባሉበት ሲቆሙ፣ አንዳንድ ጠንካራ የገጠር መኪኖች በጥቅጥቁ ደን ውስጥ የወጣው ጥርጊያ መንገድ ቁልቁለት፣ ዳገትና ጭቃ እየበጣጠሱ፣ እየተጐተቱና እየተገፉ ውጡና ከዚያ በላይ በላይ መሄድ ስለማይቻል ለመቆም ተገደዱ፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው መንገድ የጋማ ከብትና የእግር ነው፡፡

አሁን ማኪራ ለመድረስ 4 ኪ.ሜ ያህል ይቀረናል፡፡ መንገዱ ጥቅጥቅ ባለው የተፈጥሮ ደን ውስጥ ከመሆኑም በላይ ዳገትና ቁልቁለት ስላለው በሁሉም ሰው ፊትና በአንዳንዶች ጀርባ ነጭ ላብ ይንቆረቆራል፡፡

ያልተነካ ድልብ መሬት ስለሆነ ሲረግጡት፣ ስርጉድ ስርጉድ ይላል፡፡ ደኑ ጥቅጥቅ ባለበት ስፍራ ከአንድ ሜትር በላይ አሻግሮ ማየት ይከብዳል፡፡ አንዳንዱ ዛፍ ስር ሆነው ሽቅብ ሲመለከቱ፣ በጣም ረዥም ከመሆኑ የተነሳ ጫፉን በትክክል መለየት አይቻልም፡፡ የአንዳንዱ ዛፍ ስር ምናልባት ከ10-20 ሜ ሊሰፋ፣ ወገቡን ደግሞ 10 ሰዎች ተያይዘው ላይሞሉት ይችላሉ፡፡

አብዛኞቹ ዛፎች ከቅርንጫፎቻቸው ቁልቁል ሐረግ ያበቀሉ ሲሆን፤ ሐረጉ ራሱ መሬት ደርሶ ሥር አፍርቶና ወደ ጐን ደርጅቶ እንደገና ሽቅብ ይወጣል፡፡ በርካታ ዛፎች ቅርፊታቸው የተላቀቀ ሲሆን ጥገኛ ተክሎች በቅለውባቸው ምግባቸውን ይሻሟቸዋል፡፡ ሁሉንም ዘርዝሮ መዝለቅ ስለማይቻል ለአብነት ያህል ይበቃል፡፡ እናት ቡና ጋ ለመድረስ አንድ ኪ.ሜ ያህል ሲቀር ወጣት ሴቶችና ወንዶች ተሰብስበው እየዘፈኑ በሚጨፍሩበት አካባቢ አንድ አዛውንት አየሁና ስለቦታው የሚያውቁትን እንዲነግሩኝ ጠጋ አልኳቸው፡፡

አቶ አሰፋ ገ/ማርያም የቦንጋ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ የ60 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡

ቡና የት ነው የተገኘው?

በደቻ ወረዳ እዚህ ማኪራ ቀበሌ ነው የተገኘው፡፡

ማነው ያገኘው?

ካሊ የተባለ እረኛ ፍየል ሲጠብቅ ነው ያገኘው፡፡ አንዲት ፍየል ብዙ ጊዜ የቡና ፍሬ እየበላች ስትቅበዘበዝ ያያል፡፡ ምን ዓይነት ፍሬ እንደምትበላ ተከታተለና የቡና ፍሬ መሆኑን ተረዳ፡፡ ፍሬው ጐጂ እንዳልሆነ ስለተረዳ ራሱም ሞከረውና ፍየሏ የተሰማት ስሜት ስላደረበት ወደ ቤት ወስዶ አስተዋወቀው፡፡

ይህ ብቻ ካፋ የቡና መገኛ መሆኗን ያረጋግጣል?

አያረጋግጥም፡፡ ሌሎች የሚጠቀሱ ማስረጃዎች አሉ፡፡ በዘጠነኛው መቶ ክ.ዘ አካባቢ ቦንጋ አካባቢ ፒፋ የሚባል ትልቅ ገበያ ነበር፡፡ ያ ገበያ ጂማን አቋርጦ በሦስት አቅጣጫ ይሄዳል፡፡ አንደኛው በጐንደርና መተማ በሱዳን በኩል፣ ቡና ለውጭ ገበያ የሚቀርብበት ነው፡፡ ሌላው በአድዋ በኩል የሚወጣው ነው፡፡ በምሥራቅ ሶዶ በኩል፣ በሐረር በጅቡቲ በርባራ ወደብ ወደ ዐረብ አገሮች የሚወጣም ነበር፡፡ ከ15 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ፀሐፍት ካፋን የቡና መገኛ አድርገው ጽፈዋል፡፡

አረቦች ወደ ካፋ የመጡት በንግድ ነው፡፡ 700 ዓመት ያስቆጠረ ቶንጐላ የተባለ መስጊድ አለ፡፡ ያ መስጊድ የተቋቋመው ቴፋ በተባለ የገበያ አካባቢ ነው፡፡ እስልምናን ወደ ካፋ ያመጡት አረቦች ከመሆናቸውም በላይ ከካፋ ቡና እየወሰዱ በምትኩ ከመካከለኛው ምሥራቅ ሐር እያመጡ ይነግዱ ነበር፡፡

አቶ በድሩ ጀማል አብደላ የቦንጋ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ የ53 ዓመት ጐልማሳ ናቸው፡፡ በሙያ ኢኮኖሚስትና የከፊቾ ብሔረሰብ ተወላጅ ናቸው፡፡

የቡና መገኛ የት ነው?

ማንኛውም የከፊቾ ብሐረሰብ ተወላጅ በዘር ሐረጋችን ሁሉ ከአያት ቅድመ አያቶቻችን ጀምሮ ያለው ሁሉም ትውልድ፣ ካፋ ዞን በተለይም ማኪራ የቡና መገኛ መሆኗን ነው የምናውቀው፡፡ ይኼ በእኛ በተወላጆቹ በኩል ያለው ሐቅ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ብዙ የውጭ አገር ፀሐፍት ካፋ የቡና መገኛ መሆኗን ይመሰክራሉ፡፡ ለምሳሌ አሌክሳንደርን፣ ሃዋርድን፣ ማክስዌልን፣… መጥቀስ ይቻላል፡፡

ለምሳሌ አሌክሳንደር ሩሲያዊ ሲሆን፣ አፄ ምንሊክ የጂማውን ንጉሥ አባጅፋር በማስገበር አንዲት ኢትዮጵያን ለመመሥረት ጦር በላኩ ጊዜ፣ አሌክሳንደር ከጦሩ ጋር ዘምቶ የነበረ የጦር አማካሪ ነው፡፡ አሌክሳንደር ስለጦርነቱ በጻፈው መጽሐፍ፡- “የጂማ ነዋሪዎች የአካባቢው (የካፋን) ብቸኛና አንጡራ ሀብት የሆነውን ቡና በሌላ ምርት ለውጠው ወደ ጂማ በማምጣት፣ ዱቄቱን በጦርነቱ ለተጐዳው ሕዝብ ያጠጡ ነበር” በማለት ገልጿል፡፡ ሌሎች በርካታ የውጭ ፀሐፍትንም መጥቀስ ይቻላል፡፡

ካፋ የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን ቡና ላኪም (ኤክክስፖርተር) ነበረች፡፡ ያኔ የካፋ መንግሥት በነበረበት ወቅት (የወደቀው በ1897 ዓ.ም ነው) በንግድ የሚታወቁት አረቦችና ካፋ ነበሩ፡፡ እስከ አውሮፓና ቻይና ድረስ ቡና ይነግዱ ነበር፡፡

ቡናን ለዓለም ያስተዋወቀው ማነው?

አቶ በድሩ “ቡናን ለዓለም ያስተዋወቀው ካልድስ የተባለ የየመን እረኛ ነው” መባሉ፣ “በጣም አሳዛኝ ታሪክ ነው” በማለት በኅዘንና በቁጭት ይናገራሉ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ቡና አነቃቂ ነገር እንዳለው ለዓለም ሕዝብ ያስተዋወቀው የካፊቾ ተወላጅ የሆነ ካሊ አዲ የተባለ እረኛ ነው ብለዋል፡፡

ታዲያ እንዴት ካልድስ ነው ተባለ?

ካሊ አዲ የሚለውን በእንግሊዝኛ ጻፍና አንብበዋ!

አርቲስቶችንና ጋዜጠኞችን መጋበዝ ለምን አስፈለገ?

የአገሪቷ ዜጐች ቀርቶ፣ የውጭ አገር ጸሐፍትም ቡና ካፋ (ኢትዮጵያ) ለዓለም ያበረከተችው ሀብት መሆኑን መስክረዋል፡፡

ኢትዮጵያዊው የሆነ ሁሉ እውነታውን ተረድቶ የአገሩን አንጡራ ሀብት በየሙያው ማስተዋወቅ ግዴታው ነው፡፡ ያኔ ነው የአቀባባዩ ጥቅም ቀንሶ የቡና ገበሬ ጥቅም ማደግ የሚችለው፡፡ ለዚህ ነው የተፈለጋችሁት፡፡

ዩኔስኮ የአካባቢው የተፈጥሮ ደን የአካባቢው የአየር ንብረት ተጠብቆ እንዲቆይ የተፈጥሮ ሳንባ ስለሆነ ለኢንቨስትመንትም ሆነ ለሌላ ልማት ሳይውል ተጠብቆ ይቀመጥ ብሎ መዝግቦታል፡፡ ነገር ግን ከካርቦን ሽያጭ ባለሀብቷ ኢትዮጵያ ምንም ጥቅም አላገኘችም፡፡ እየተጠቀሙ ያሉት ያው አውሮፓውያን ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ መለወጥና ደኑን ጠብቆ ያቆየው ሕዝብ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት አለበት፡፡

ይህ የተፈጥሮ ደን በዩኔስኮ ተመዝግቧል እንዴ?

አዎ! በዞናችን አንድ ሚሊዮን 100,000ሺ ሄክታር መሬት ነው ያለን፡፡ ከዚህ ውስጥ 74 በመቶ ያህሉ በጥብቅ የተፈጥሮ ደንነት አምና ተመዝግቧል፡፡ የዚህ አካባቢ በተፈጥሮ መመዝገብ ያለው ጥቅም ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም የዚህን አካባቢ ስም ይዞ ለአውሮፓ ገበያ የሚቀርብ ማንኛውም ምርት የተፈጥሮ (ኦርጋኒክ) መለያ ስለሚኖረው ከሌላ አካባቢ ከሚቀርቡት ምርቶች ጋር በተመሳሳይ ዋጋ አይሸጥም - ይጨምራል፡፡

የካፋ ቡና ከሌላው አካባቢ በምን ይለያል?

የእኛ ቡና ከተቆላ በኋላ ቅባት አለው፡፡ ስትቆረጥመው የመጮህ ድምፅ አለው፡፡ የእኛ ቡና ሲቆላ መጠኑ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ሌላውና ዋነኛው የጣዕሙ ልዩ መሆን ነው፡፡ ይኼ የጀርመን ሳይንቲስቶች ባደረጉት ጥናት ተረጋግጧል፡፡ የጥናት ውጤቱንም ከአስተዳደሩ ቢሮ ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

ዘንድሮ መንግሥት 170 ሚሊዮን ችግኝ እንዲዘጋጅ አዟል፡፡ ከዚህ ውስጥ እስካሁን 126 ሚሊዮን ችግኝ የበቀለ ሲሆን፣ ችግኙ ሲደርስ በየገበሬው ማሳ ይተከላል፡፡

አቶ ኩራባቸው አበበ በቦንጋ ከተማ ተወልዶ ያደገ ሲሆን በሙያው ፋርማሲስት ነው፡፡

የካፋ ቡና መተዋወቅ ምን ጥቅም አለው?

በአሁኑ ወቅት ጥራቱ የተጠበቀ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ለገበያ እየቀረበ ነው፡፡ ከይርጋጨፌና ከሲዳማ ቀጥሎ በጥራት የሚታወቀው የካፋ ቡና ነው፡፡ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ልዩ ጣዕም ያለው ቡና በብዛት የሚያቀርበው የካፋ ቡና ነው፡፡

አርቲስቶች የቡና መገኛ እንደሆነች በሚነገርላት የእናት ቡና ምድር ማኪራ ተገኝተው ችግኝ ተክለዋል፡፡ ምን ተሰምቷቸው ይሆን?

አርቲስት ሳምሶን ታደሰ (ቤቢ)፡-

በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ እንዲህ ዓይነት ቦታ በሕይወቴ አይቼ ስለማላውቅ በአገሬ በጣም ኮርቻለሁ፡፡ በዚህ ስፍራ አንድ ችግኝ በመትከሌም በጣም ተደስቻለሁ፡፡

ያሬድ ስሜ፡- የተሰማኝን ስሜት መናገር አልችልም፡፡ ከአዲስ አበባ ተነስቼ እዚህ እስክደርስ ድረስ እንዲህ ዓይነት ለምና አረንጓዴ አካባቢ ማየት ትልቅ እርካታ ነው የሰጠኝ፡፡ በአገሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለሁት፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ላይ እንዲህ ዓይነት ለምና አረንጓዴ አካባቢ የትም አታገኝም፡፡

አገራችን በቡና የታወቀች ናት፡፡ እኔ በዚች የቡና መገኛ በሆነችው ማኪራ ተገኝቼ ቡና በመትከሌ ትልቅ ደስታ ነው የሰጠኝ፡፡ አክብረው የጋበዙኝን ሰዎች በጣም አመሰግናለሁ፡፡ አሁን የተከልኳትን ቡና ምትኬ ብያታለሁ፡፡ መጀመሪያ ላይ ካሊ አዲ ያገኛት ቡና ምትክ ስለሆነች እየመጣሁ እንከባከባታለሁ ብያለሁ፡፡

አርቲስት ትዕግሥት ግርማ፡- በጣም በጣም ልዩ ሕዝብ ነው ያጋጠመኝ፡፡ የሕዝቡ ፍቅር ሲገርመኝ የአካባቢው ውበት፤ ከነአፈር ለምነቱ በጣም ያምራል፡፡ ወደዚህ ስትመጣ አረንጓዴ አካባቢ አያለሁ ብለህ ልታስብ ትችላለህ፡፡ አሁን ያየነው ግን ከማስበው በላይ በጣም አስደስቶኛል፡፡

የተከልኳትን ችግኝ እዚህ ላለ ሰው አደራ ሰጥቼ በየዓመቱ እየመጣሁ ከዚያች ቡና ፍሬ የምለቅም ይመስለኛል - (በቀልድ ሳቅ፡፡)

አቶ ክፍለ ገ/ማርያም የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ናቸው፡፡

ቡና፣ ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ገጸ-በረከት ነው፡፡ ዓላማው ይህቺን የቡና መፍለቂያ ስፍራ ለዓለም ማስተዋወቅ፣ አሁን በዞኑ ከተጀመረው የቡና ልማት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምርትና የግብይት ማዕከል ለመሆን የሚያነሳሳ በመሆኑ የዕለቱ ጉብኝት በጣም ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብለን እናምናለን፡፡

ይህን ያህል በርካታ ቁጥር ያለው አርቲስት ይመጣል የሚል ግምት አልነበረንም፡፡ ነገር ግን አርቲስቱ ሕዝቡንና አካባቢውን ለማየት ወደዚህ መምጣቱ የተጀመረውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ለማስቀጠል ከፍተኛ ሚና ስለሚጫወት በጣም ደስተኛ ነን፡፡ አርቲስቱና ጋዜጠኞች ከቡናው መገኛ በተጨማሪ በቦንጋ ከተማ እየተሠራ ያለውን የቡና ሙዚየምና ዓለም አቀፍ የቡና መረጃ ማዕከል በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ሚና እንድትጫወቱ አደራ እንላለን፡፡

አርቲስት አብራር አብዶ፡-

ያየሁትን ለሌላ ሰው ማሳየት ወይም ማግለጽ በጣም ይከብዳል፡፡ በሥራ አጋጣሚ ቦንጋን ባውቅም ማኪራን ግን አላውቃትም፡፡ ዛሬ ያየሁት አምልጦኝ ቢሆን ኖሮ በሕይወቴ አንድ ትልቅ ነገር እንዳመለጠኝ ነበር የሚሰማኝ፤ አሁን በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ዛሬ በኪነ-ጥበብ ሰዎችና በጋዜጠኞች ላይ የተጣለው ኃላፊነት በጣም ከባድ እንደሆነ ይሰማኛል - የቤት ሥራችንንም ለመወጣት ተግተን መሥራት ይኖርብናል፡፡

አርቲስት ችሮታው ከልካይ፡- በሕይወቴ እጅግ የተደሰትኩበት ቀን ቢኖር የዛሬዋ ዕለት ናት፡፡ በተለያየ የሥራ አጋጣሚ ብዙ ጊዜ ወደ ቦንጋ (ካፋ) መጥቻለሁ፡፡ ነገር ግን የቡና መገኛ መሆኗን አላውቅም ነበር፡፡ ዛሬ የቡና መገኛ በሆነችው ማኪራ ቀበሌ ተገኝቼ እናት ቡናን በማየቴ የተሰማኝ ደስታ ወደር የለውም፡፡ አገራችንን በሰው ዘር (በሉሲ) መገኛነት ብቻ ነበር የምናውቃት፡፡ የአረንጓዴው ወርቅ መገኛም መሆኗ በጣም የሚያኮራ ስለሆነ የዓለም ሕዝብ ማኪራን (ካፋን) በስፋት ማስተዋወቅ ይጠበቅብናል፡፡ እኔ ማስተዋወቁን ከቤቴ ነው የምጀምረው፡፡ በአጠቃላይ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡

ወ/ሮ ዓለምፀሐይ የሚኖሩት ፈረንሳይ ሲሆን ሰዓሊ ናቸው፡፡ በማኪራ ጉብኝት ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ ምን እንደተሰማቸው ሲናገሩ፤

ከአሁን ቀደም ብዙ ደስታዎችን አሳልፌአለሁ፡፡ ነገር ግን በማኪራ ያገኘሁትን ደስታ ወደፊትም የማገኝ አይመስለኝም፡፡ ቦንጋ ማለት የኢትዮጵያ ሕይወትና እስትንፋስ ናት ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም፣ የተጠበቀ የተፈሮ ቡና የተፈጥሮ ደን የተፈጥሮ ውበት ለመጀመሪያ ጊዜ ማየቴ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሕዝቡ የዋህነትና ለሰው ልጅ ያላቸው ክብር እጅግ ማርኮኛል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያንና ብዙ የውጭ አገር ጸሐፍት በቡና መገኛነት የሚያውቁትና የጠቀሱት ካፋን ቢሆንም፣ የቡና መገኛ በኦሮሚያ ክልል ከጂማ ከተማ በቅርብ ርቀት የምትገኘው ጨጮ ናት የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡

የቦንጋ ብሔራዊ ሙዚየምና ዓለም አቀፍ የቡና መረጃ ማዕከል ግንባታ 99 በመቶ መጠናቀቁ፣ በፋይናንስ ረገድ ደግሞ 75 በመቶ ወጪ መደረጉ በጉብኝቱ ወቅት ተነግሯል፡፡ የሚቀረው ነገር የሙዚየሙን የቅርስ ክምችት አሳድጐና ኤግዚቢሽን አዘጋጅቶ ማስመረቅ እንደሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ሙዚየም ቺፍ ኩሬተር ዶ/ር ሐሰን ሰዒድ ገልጸዋል፡፡

 

 

Read 4233 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 16:08