Sunday, 03 June 2018 00:00

የፖለቲከኞች ከእስር መፈታትና ህጋዊ አንደምታው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

  “ፓርላማው የሽብርተኝነት ፍረጃን ማንሳት አለበት ተባለ”

   ከሰሞኑ የፌደራል አቃቤ ህግ በሙስና ተከስሰው የነበሩ ባለሥልጣናትና ባለሃብቶች እንዲሁም የአርበኞች ግንባር ግንቦት 7፣ ዋና ፀሃፊ
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጨምሮ 700 ያህል የተለያዩ እስረኞችን በይቅርታ ፈትቷል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሣ በበኩላቸው፤ በክልላቸው እስካሁን 40 ሺህ ያህል እስረኞች መፈታታቸውን ሰሞኑን ገልፀዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች የመፈታታቸው አንድምታ፣ የአርበኞች ግንቦት 7 ዋና ፀሃፊ ፍቺ እና ቀጣይ ሊፈጠሩ የሚችሉ የህግ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ጉዳይ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ
አለማየሁ አንበሴ የህግ ባለሙያዎችንና ፖለቲከኞችን አነጋግሯል፡፡

      “ፓርላማው የሽብርተኝነት ፍረጃን ማንሳት አለበት
         አቶ ተሾመ ወ/ሐዋሪያት (የህግ ባለሙያ)


    በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ተቀብለን ያፀደቅናቸው ዓለማቀፍ ስምምነቶች ላይ እንደተጠቀሰው፣ ሃሳብን በነፃ በመግለጽ፣ በመደራጀት፣ በአጠቃላይ የፖለቲካ ስራ በመስራት ሂደት ውስጥ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ቅጣት የሚያስከትል ህግ፣ ህገ መንግስቱን የሚፃረር ነው። ለዚህ ነው ፀረ ሽብር ህጉ ተቃውሞ የሚገጥመው። መንግስት፤ ይሄን ነገር መፈተሽ ባለመቻሉ፣ በህዝቡና በዓለማቀፍ ማህበረሰብ ጫና ስር ነበር፡፡ ዛሬ ያ ጫና ውጤት አምጥቶ ነው፣ የፖለቲካ እስረኞች እየተፈቱ ያሉት፡፡ ይሄ ደግሞ ዲሞክራሲውን ከመገንባት፣ የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታ ከመወሰን አንፃር ጠቃሚ ነው፡፡ ህዝቡ በነፃነት ሃሳቡን ለማራመድ ይህ እርምጃ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ለፖለቲካውም የመድኃኒት ያህል  ጠቃሚ ነው፡፡
አቶ አንዳርጋቸው የሚመሩት ድርጅት በመጀመሪያም ቢሆን በሽብር ሊፈረጅ አይገባም ነበር፡፡ በህዝቡ ውስጥ ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች የሚመሩትን ድርጅት፤ ሽብርተኛ ብሎ መፈረጅ ነው ስህተቱ፡፡ አሁን ደግሞ ሽብርተኛ የተባለው ድርጅት መሪ፣ አቶ አንዳርጋቸው ተፈትተው፣ ድርጅቱ ሽብርተኛ ተብሎ እንደተፈረጀ ነው ያለው፡፡ ዋናው ጥያቄ፣ ይሄ ተቃርኖ እንዴት ይታረቅ የሚለው ነው፡፡ በመጀመሪያ ፓርላማው ፍረጃውን ማንሳት አለበት፡፡ ያን ጊዜ ነው ፍቺው ሙሉ መተማመን የሚፈጥረው። ለምሳሌ ከኦነግ የወጣውን ኦዴግን ተቀብለዋል፡፡ ይሄ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የዚህ ድርጅት አመራሮች ይመሩት የነበረው ድርጅት ሽብርተኛ የተባለ ነው። እነዚህ ተቃርኖዎች፣ ህጉ ተፈትሾ መታረቅ አለበት። የእነ ዶ/ር ብርሃኑ ክስ መነሳትም ከዚሁ አንፃር ነው የሚታየው፡፡

-------------

            “ዛሬ የተፈቱ ነገ የማይታሰሩበት ዋስትና የለም”
                አቶ አመሃ መኮንን (የህግ ባለሙያ)

    እነዚህ እየተፈቱ ያሉ ሰዎች፣ በአመለካከታቸው በሚያደርጉት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ምክንያት ነው ታስረው የነበሩት፡፡ ሲፈቱ ደግሞ በፊት ሲሳተፉ በነበሩበት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሊሳተፉ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ለዚህ ጠቃሚው ዜጎች የበለጠ ሃሳባቸውን የሚገልፁበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡ እኔ በጥብቅና ሳገለግል ካለኝ ግንዛቤ፣ አብዛኞቹ የታሰሩ ሰዎች አንድም፣ ከኦነግ ጋር ሁለትም፣ ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር አባል ሆናችኋል፣ ደግፋችኋል፣ አላማ አራምዳችኋል ተብለው ነው የሚከሰሱት፡፡ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ደግሞ በፓርላማ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ናቸው። ስለዚህ ይህ ፍረጃ እስካለ ድረስ እነዚህ ዛሬ የተፈቱ ሰዎች፣ ተመልሰው የሚታሰሩበት እድል ሰፊ ነው። ነገር ግን መንግስት፣ እነዚህን እስረኞች ለመፍታት የወሰነው፣ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር እስከሆነ ድረስ እስረኞቹን መፍታት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ በተለይ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች በፓርላማ አሸባሪ የተባሉበት ሁኔታ መጤን አለበት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም ወደ ሃገር እንዲመጡ እየጠየቁ ባለበት ሁኔታ፣ ይህ ሁኔታ መፍትሄ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ የተፈቱ ሁሉ በቂ ዋስትና አይኖራቸውም ማለት ነው፡፡
የኢህአዴግ መሪዎች፣ መጀመሪያ የፖለቲካ እስረኞችን እንፈታለን ባሉባት መግለጫቸው፣ የተወሰኑ መስፈርቶችን ከማስቀመጥ ውጪ፣ እነማን ይፈታሉ የሚለው አልተቀመጠም፡፡ ከዚህ አንፃር የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት በጣም የሚያስደንቅ አይደለም፡፡ አቃቤ ህግ ካስቀመጠው መስፈርት አንዱ፣ ሰው ያልገደለ የሚል ቢሆንም ሰው የገደሉም ሲፈቱ ነበር፡፡ ስለዚህ የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ እስካሁን መዘግየቱ ካልሆነ በቀር፣ አሁን መፈታታቸው የሚያስገርም አይሆንም፡፡ ነገር ግን በሳቸው ድርጅት ስም የታሰሩ ሰዎች በእስር ቤት ያሉ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንፃር የመንግስት ውሳኔ በሁሉም ላይ ተፈፃሚ መሆን አለበት፡፡ ይሄ የአሰራርና የአፈፃፀም ችግር ነው። መሪዎች ተፈትተው “ከእነሱ ጋር ግንኙነት አላችሁ” የተባሉ ያልተፈቱበት ሁኔታ እኔም እታዘባለሁ፡፡ ይሄ ስራን በጥራትና በብቃት የመስራት ችግር ይመስለኛል። እነዚህ ሰዎች በእስር ቤት የሚቆዩበት ሁኔታ በየትኛውም መንገድ ተገቢ አይሆንም፡፡
እርግጥ ምን ያህል ሰው በፖለቲካ አመለካከቱ ሳቢያ በዚህ ሃገር ታስሯል የሚለው የሚታወቅ አይመስለኝም፡፡ ይሄን ለማወቅ ጥረት ያደረገም ያለ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚረሱ ሰዎች ሊኖሩም እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ ይሄ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል፤ አሰራሩ ግልፅ ሆኖ፣ በጥብቅና የተሳተፍን ሰዎች እገዛ ብናደርግ፣ ክፋት ያለው አይመስለኝም፡፡ ይሄ ቢሆን ጉዳዩን የበለጠ የተቀላጠፈ ሊያደርገው ይችላል፡፡

-------------

          “ይሄ ሁሉ ሰው ለምንድን ነው እስር ቤት የገባው?”
              አቶ ተመስገን ዘውዴ (ፖለቲከኛ)

     እኔ ፖለቲከኞች በመፈታታቸው ደስተኛ ነኝ። ግን አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ይሄ ሁሉ ሰው እስር ቤት ለምንድን ነው የገባው? በኦሮሚያ ብቻ እስከ 40 ሺ የሚደርስ ህዝብ እስር ቤት ገብቶ እንደነበር ማሰብ ይከብዳል። ሰላማዊ ሃገር እየመራን ነው፣ ኢትዮጵያ ሰላም ነች እየተባለ፣ 40 ሺህ ህዝብ ከእስር ቤት መውጣቱ የሚጠቁመው ነገር አለ፡፡ ህዝቡ ምን አይነት ስቃይ ውስጥ እንደነበር በዚህ ማየት ይቻላል፡፡ አሁንስ ሁኔታው ምን ያህል እየተቀየረ ነው? የሚለው ለእኔ አጠያያቂ ነው፡፡ ሰዎች በአሉባልታ ብቻ ሲታሠሩ ነበር የከረሙት፡፡ ይሄ ሁኔታ አሁን ለዓለም ህዝብ በሙሉ የታየ ይመስለኛል፡፡ ይህ ሁሉ ሰው መፈታቱ፣ የኢትዮጵያን የሠብአዊ መብት ጥበቃና የፍትህ ስርአት፣ ለአለም ፍንተው አድርጎ ያጋለጠ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ሰው እስር ቤት ምን ሲያደርግ ነበር? በምን አይነት ሁኔታ ነው ታስሮ የነበረው? የሚሉ ጥያቄዎችን ያስነሣል፡፡
አሁን ዶ/ር አብይ የድርጅቱን አመለካከት የሚቀይሩ ከሆነ፣ ሁነቱ ለታሪክ ሊቀመጥ የሚገባው ነው፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያለውን ነገር ያየነው፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ነው፡፡ ይሄ ሁኔታ ኢትዮጵያ የነበረችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለማየት እድል የሰጠ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ የምንረዳው፣ አሁንም የበለጠ ትግል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው ፡፡
በውጭ ሃገር እየታገሉ ያሉ ፓርቲዎች አሉ፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ስለ ኢትዮጵያ የተለየ ሃሳብ አለን እያሉ ነው። እነዚህ ፓርቲዎች እድል ሊሠጣቸው ይገባል፡፡ ዶ/ር አብይ ጥሪያቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት ብዙ ጥቅም አለው፡፡ እሳቸው በውጪ ባሉ ኢትዮጵያውያን ሰፊ ተቀባይነት አላቸው፡፡ ስለዚህ ፖለቲካችን በውጪ ሃገር የተቃና እንዲሆን ሊያግዙ ይችላሉ፡፡ አሁንም ግን ዳያስፖራው አካባቢ ያሉ ፖለቲከኞች፣በሃገራቸው ጉዳይ ሰፊ ተሣትፎ እንዲያደርጉ  መጠራት አለባቸው፡፡
ዶ/ር አብይ ጀምራቸው ጥሩ ነው፡፡ የምንፈልገውን የአመራር ብልጭታ እያየን ነው፡፡ አጀማመራቸው ከዚህ በፊት ሃገሪቱ ከነበራት የፖለቲካ ልምድ የተለየ ነው፡፡ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡ ግን አሁንም መታወስ ያለበት፣በዚህ ሃገር ፖለቲካ ውስጥ ያገባናል የምንል ሰዎች አለንና፣ ወደ ሁሉም የሃገሪቱ ክፍል ወርደን፣ ሃሣባችንን እንድናስረዳ፣ እድሉ እንዲኖረን ሊያደርጉ ይገባል፡፡

------------

           “ፖሊከኞች ከይቅርታ ይልቅ በምህረት ቢፈቱ ጥሩ ነበር”
                አቶ ሽብሩ በለጠ (የህግ ባለሙያ)


    እነዚህ ፖለቲከኞች የሚፈቱት ከይቅርታ ይልቅ በምህረት ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡ በምህረት ሲሆን ከወንጀል ሪከርድ ላይ እስከመነሳት ይደርሳል፡፡ ክስ ማቋረጥ፣ ጥፋተኛ የሚለው ነገር ስላልመጣ፣ ወንጀለኛ የሚለው ነገር አይኖርም፤ ነገር ግን የክስ ማቋረጥ እንጂ ሙሉ ምህረት አይደለም፡፡ መንግስት በመጀመሪያ ምህረት ነበር ያለው፡፡ ቀጥሎ ነው ይቅርታ የሚለው ነገር የመጣው፡፡ በኋላ ስንሰማ፣ ብዙዎች ተፀፅቻለሁ ብለው የይቅርታ ፎርም መፈረም አለባቸው የሚል አቋም የተያዘ ይመስላል፡፡ ብዙዎች የተከሰሱት ደግሞ በሽብር ነው፡፡ ዋነኛው የክስ ሰነድም የፀረ ሽብር አዋጁ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ መነሻ ደግሞ ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ ኦብነግ ተፈርጀዋል፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች በተጨማሪ ያልተፈረጁ ድርጅቶችና ግለሰቦችም በሽብር ሲከሰሱ አይተናል፡፡
በፀረ ሽብር አዋጁ ላይ አንድ ድርጅት፣ ሽብርተኛ ነው የሚባለው፣ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተፈረጀ እንደሆነ ወይም በሽብር ተግባር የተሳተፈ እንደሆነ ነው ይላል፡፡ ይህ ማለት በሽብር ለመክሰስ፣ያልተፈረጀ የተፈረጀ አይልም ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን ሽብርተኛ ተብለው የተፈረጁ ድርጅቶችን መሪዎች መፍታት ይሻላል ወይስ ፍረጃውን አንስቶ የዚያ አካል ናቸው ተብሎ የታሰሩትን በሙሉ በምህረት መልቀቅ ይቀላል? አሁን ባየሁት መንገድ ግን የተወሰኑ ሰዎችን እየነጠሉ ክስ ማቋረጡ፣ ከግንቦት 7 ጋር ሊደረግ የሚጠበቀውን ለማመቻቸትና የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር ከማሰብ ይልቅ ግለሰቦችን በታዋቂነታቸው ብቻ መፍታት ነው የተያዘው፡፡ እርግጥ እንደ ጅምር ጥሩ ነው፡፡ አሁን በኢሳት፣ ኦኤምኤን፣ አቶ ጃዋር መሃመድ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ላይ የተመሰረተው ክስም ተነስቷል፡፡ የብርሃኑ ነጋና የጃዋር መሃመድ ክስ ተነሳ ተብሎ፣ እነሱ የሚመሩት ድርጅት የሽብር ፍረጃ ካልተነሳ ትርጉም የለውም፡፡ ለህግም አስቸጋሪ ነው፡፡ አቶ አንዳርጋቸውን መፍታት ጥሩ ሆኖ፣ ድርጅታቸው ግን አልተፈታም። ፍረጃው እስካለ ድረስ ሁኔታው አስቸጋሪ ነው፡፡ ክስ ማቋረጥ ብቻውን ለሚታሰበው የፖለቲካ አውድ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል የሚል እምነት የለኝም፡፡
እርምጃው በበቂ መጠን መተማመን መፍጠር አይችልም፡፡ ድርጅቶቹ፤ በፓርላማ፣ በህግ፣ ሽብርተኛ ተብለዋል፡፡ በዚያው ልክ እነዚህን ፍርደኞች ተከታትሎ፣ ለማረሚያ ቤት ያስረክብ የሚል ትዕዛዝ የተሰጠው አካል አለ፡፡ ያ አካል፤ ሌላ ተለዋጭ የፍ/ቤት ትዕዛዝ አልተሰጠውም፡፡ ክሱ ተነስቷል፣ የእስር ትዕዛዙ ሁሉ አያስፈልግም፣ የሚል ትዕዛዝ፣ “ተይዘው ይታሰሩ” ካለው ፍ/ቤት አልተሰጠም፡፡ በዚህ ሁኔታ መተማመን ይፈጠራል ማለት የዋህነት ነው፡፡   

Read 3592 times