Sunday, 06 May 2012 15:11

የሀያሲ ነፍስ በየምናምንቴው ብናኝ ካደፈ፣ የብእሩን እድፍ ከቀለሙ መለየት ያስቸግራል

Written by  በድሉ ዋቅጅራ
Rate this item
(3 votes)

ወንድሜ አለማየሁ ገላጋይ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ፣ በዚሁ አምድ ስር “ከተስፋ ቀብር መልስ...” በሚል ርእስ የጻፍከውን አነበብኩት፡፡ ስለተናገርከው እውነት ደስ አለኝ፡፡ የተስፋህን መቀበር ብጠራጠርም፣ በተስፋ ስም ስለቀበርከው እውነት ግን መደነቄ አልቀረም፡፡ ካስደሰተኝ እውነትህ ብጀምርስ! እውነትም አንተ ደካሞች ብለህ የጠቀስካቸው ሶስት ግጥሞች በግጥሜ ውስጥ ካካተትኩዋቸው 56 ግጥሞች ጋር ሲነጻጸሩ በደረጃ ዝቅ ያሉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የራሳቸው ተደራሲ አላቸው፡፡ ለምሳሌ፣ “አበሻና ትዝብት” የሚለውን ግጥም አንብቦ የተደነቀ አንባቢ አጋጥሞኛል፡፡ ቢሆንም ወንድሜ ሙት ልክ ነህ! ሶስቱ ግጥሞች ከሌሎቹ አንጻር ዝቅ ያሉ ናቸው፤ ከአንተ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ስለመድበሉ በዚሁ አምድ ስር የጻፈው ደረጀ በላይነህም፣ “ምነው ባልገቡ ያልኩዋቸው ጥቂት ግጥሞች አሉ” ያለው እነዚህን ሳይሆን አይቀርም፡፡

አንተም ልክ ነህ! አየህ ሂስ ማለት እንዳንተ ነው! ድክመትን መንገር! አመሰግናለሁ፡፡ ወደፊት ግጥም ካሳተምኩ እንደነዚህ አይነት “ተራ ጉዳዮች ላይ በተራ አቀራረብ የሚባዝኑ” ግጥሞችን ላለማስገባት እጥራለሁ፡፡ ወንድሜ አለማየሁ፣ በተስፋ ስም ስለቀበርከው እውነት ከመናገሬ በፊት አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፡፡ አንድን የኪነ ጥበብ ስራ ስንሄስ፣ መሰረታችን ምንድን ነው? እንዳንተ በልምድ ለደረጀ ደራሲና ሀያሲ፣ ይቺ ቀላል ጥያቄ መሆንዋ ይገባኛል፡፡ ሂስ መሰረት ማድረግ ያለበት፣ ስራውን ነው፡፡ ግን ልብ በል! ስራው በእጄ ገባ ብሎ፣ ማንም ኪነ ጥበብን ሊሄስ አይችልም፡፡ የሂስ ስራ፣ መጀመሪያ ሙያዊ እውቀትን ይሻል (እውቀቱ አንድም በትምህርት፣ አንድም በልምድ ሊገኝ ይችላል)፡፡ ዋናው ግን ይህ አይደለም፡፡ ዋናው፣ በየትኛውም አስገዳጅ ሁኔታ፣ እውነትን ለመናገር የሚደፍር ቅን ነፍስ ነው፡፡ ወንድሜ አለማየሁ፣ ከልምድም አግኘው ከትምህርት፣ እውቀቱ እንደሚኖርህ  አልጠራጠርም፡፡ እውነትን ለመናገር ጋት ፈቀቅ የማይል የሀያሲ ነፍስ እንዳለህ ግን እጠራጠራለሁ፡፡ መቼም ለምን ማለትህ አይቀርም፤ መጠየቅ አይገድ! ለምን እንዲህ እንዳልኩህ በሁዋላ ላይ መልሱን ታገኘዋለህ፡፡እኔ የምልህ አለማየሁ፣ እውን “ፍካት ናፋቂዎች”ን ያን ያህል የምታደንቀው ከሆነ፣ ምነው እንዲህ በፍጥነት “አዲሱ የበድሉ የግጥም መጽሀፍ የፍካት ናፋቂዎች ብርቁ ገጣሚ ተስፋ ማክተም ልፋፌ ነው” ብለህ የብእሬን መንጠፍ ተመኘህ? ለምን ስብራቴን አሽተህ ልታቆመኝ አልሞከርክም? ይህ ከእንዳንተ ያለ ታላቅ ሀያሲ ካልተገኘ ከየት ይገኛል፡፡የተስፋህን ቀብር ያነበበ አንድ ተማሪዬ፣ “አለማየሁ የጻፈው ስላንተ ግጥሞች እንዳይመስልህ። እሱ፣ መግቢያውን የጻፈልህን ገዛኸኝን ያገኘ መስሎት ነው” አለኝ። “አይ! በፍጹም! አንድ በልምድ የዳበረ ደራሲና ሀያሲ እንዲህ ተራ ነገር አይሰራም” ብዬ ተከራከርኩት፡፡ ተማሪዬ ግን ሞገተኝ፤ “ገዛኸኝ ጌታቸው የአለማየሁን ‘ህይወትና ክህሎት...’ አስመልክቶ በተከታታይ በዚሁ አዲስ አድማስ ላይ ሂስ ሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህም ጽሁፍ፣ አለማየሁ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የግንዛቤ እጥረት እንዳለበትና በዚህም የተነሳ የተለያዩ ጽንሰ ሀሳቦችን አጣሞ መተርጎሙን፣ ደራሲ ስብሀትን የአማርኛ ዘመናዊ ስነ ጽሁፍ ጀማሪ ለማድረግ ሲል ደራሲ ሀዲስ አለማየሁንና በአሉ ግርማን ማኮሰሱን፣ በማስረጃ አስደግፎ ጽፎአል፡፡ በተጨማሪም በርካታ ሊያሻሽላቸው የሚገቡ ነጥቦችን ጠቁሞት ነበር፤ ካላመንክ ጋዜጣውን ልስጥህና አንብበው” አለኝ፡፡ “ማንበብ ወደፊት አነበዋለሁ፤ እኔ ግን አንድ እንደ አለማየሁ በልምድ የዳበረ ደራሲና ሀያሲ፣ እንዲህ ‘ለምን ሂስ ተሰጠኝ’ ብሎ፣ ቂም ቋጥሮ አይብሰከሰክም” ብዬሞገትኩት፡፡እንዲያውም ይህ ጉደኛ ተማሪዬ፣ “አለማየሁ፣ በህይወት እያለ ‘እብድ ነው’ ይለው የነበረውን ብርሀኑ ገበየሁ አሁን ታላቅ ሀያሲ አድርጎ ማቅረቡ ገዛኸኝን ለማኮሰስ ሆን ብሎ ያደረገው ነው” ቢልም አልተቀበልኩትም፡፡ መቼም የአንተን ታላቅነት የሚያውቅ ለዚህ ተራ አሉባልታ ጆሮ አይሰጥም፡፡ እስቲ ደግሞ የችግሩ ምንጭ ወዳልከው ጉዳይ እንመለስ፡፡ አንዱ ችግር “አሁን ያሳተማቸው ግጥሞች፣ ብርሀኑ ገበየሁ ከፍካት ናፋቂዎች ውስጥ መርጦ ያስወጣቸውን ነው” ማለትህ ደነቀኝ፡፡ እኔ የምልህ፣ አንድ የመግቢያ ጸሀፊ፣ መጽሃፉን አንብቦ ሙያዊ አስተያየቱን ከመጻፍ ባሻገር፣ “ይህ ይውጣ ይህ ይግባ” ብሎ በቀረበለት ስራ ላይ የመሰልጠን ስልጣን አለው ወይ? እንደኔ የለውም፡፡ አንተ ከዚህ ቀደም ብለርብ ለጻፉልህ ሰዎች ያንን ስልጣን ሰጥተህ ከነበር አላውቅም፡፡ ሌላው የችግር ምንጭ ያልከውና በጣም ያበሳጨህ የሀያሲ አብደላ እዝራን አስተያየት አለመቀበሌ ነው፡፡ እንዳልከው አብደላ እዝራ ታላቅ ሀያሲ ነው፡፡ ለዚህ ነው እኔም በተዋወቅን ማግስት፣ ግጥሞቼን ከመታተማቸው በፊት ቢያያቸው እንደሚወድ ሲገልጽልኝ በደስታ ፈንድቄ የሰጠሁት፡፡ እሱም ጊዜውን ሰውቶ፣ እውቀቱን አጣቅሶ፣ ደክሞበታል፡፡ በጥሞና አይቶ፣ እንዳልከው በደረጃ ከፋፍሎ ሰጥቶኛል፡፡ ይህን ያደረጋችሁት ግን አብራችሁ መሆኑን አልነገረኝምና አላውቅም፡፡ ይህን ቀደም ብዬ ባውቅ ኖሮ አንተንም ላመሰግንህ ይገባ ነበር፤ ወንድሜ ሙት ይቅርታ! ለመሆኑ አንተ እንዴት በእያንዳንዱ ግጥም ላይ የተሰጠውን አስተያየት ልታውቅ ቻልክ? መቼም እንደ አብደላ  እዝራ ያለ ታላቅ ሀያሲ ከጸሀፊ የተቀበለውን ስራ ሸንጎ አቅርቦ በደቦ ያስገመግማል ብሎ ማመን ይከብዳል፡፡ይሄም ሆኖ አብደላ ከ56ቱ ግጥሞች መካከል፣ 27ቱን እጅግ በጣም ጥሩ፣ 25ቱን በጣም ጥሩ፣ 4ቱን ደግሞ ከሌሎቹ ጋር ሲተያዩ የማይመጥኑ ብሎ በመከፋፈል መልሶልኛል፡፡ ከዚህም በላይ በርካታ ግጥሞች ላይ ከፊደል ግድፈት ባሻገር፣ ከቃላት መቀየር እስከ ስንኝ መተካት የደረሰ ስራ ሰርቷል፡፡ ከገዛኸኝ ጌታቸው መግቢያ ውስጥ ቀንጭቤ በመጽሀፉ ጀርባ ላይ ያስቀመጥኩትን ጽሁፍ አይቶም፣ “የግጥሞቹን ታላቅነት አይገልጽም፤ ይቅር” ብሎ ሌላ ብለርብ ጽፎ ሰጥቶኛል፤ አብደላ፡፡ እኔ ግን አንተ እንዳልከው ተራ ገጣሚ በመሆኔ፣ ይህንን እድል ሳልጠቀምበት ቀርቻለሁ፡፡ የራሴ በሆነ ምክንያት ከፊደል ግድፈት ማስተካከያው በስተቀር፣ ከአብደላ ተቀብዬ ተግባራዊ ያደረግኩት አንድም አስተያየት የለም፡፡ ለዚህ ነው በምስጋናዬ ውስጥ ስለፊደል ግድፈቱ ብቻ ማመስገኔ፡፡ በርግጥ ተሳስቻለሁ፤ ባልቀበለውም ስለሁሉም አስተያየት ማመስገን ነበረብኝ፤ ይቅርታዬ ለአብደላ እዝራ ይድረስህ፡፡ወንድሜ አለማየሁ በተስፋ ስም የቀበርከው እውነትን ነው ያልኩት ለምን እንደሁ መጨረሻ ላይ እገልጣለሁ ብዬ ነበር፡፡ አለማየሁ፣ አብደላ እዝራ ግጥሞቼን በደረጃ እንደከፋፈለ አውቃለሁ ብለሀል፡፡ ይህ ከሆነና 27ቱን እጅግ በጣም ጥሩ፣ 25ቱን በጣም ጥሩ፣ 4ቱን ደግሞ ከሌሎቹ ጋር ሲተያዩ የማይመጥኑ ብሎ እንደከፋፈለ የምታውቅ ከሆነ፣ ስለምን ስለ 52ቱ ግጥሞች አልጻፍክም? ስለምንስ የማይመጥኑ ከተባሉት 4 ግጥሞች ውስጥ 3ቱን መርጠህ አተኮርክባቸው? በእውነት እልሀለሁ፣ ስለ 52ቱ ግጥሞች በርታ እንድትለኝ ጠብቄ ነበር፡፡ እንዳንተ ካለ በልምድ የዳበረ ሀያሲ ማን ይህን ላይጠብቅ ይችላል! አየህ ቀበርከው ያልኩህ ጥሩ መባላቸውን ስለምታውቀው 52 ግጥሞች ያለውን እውነት ነው፡፡ ለዚህም ነው፣ የቀበርከው ተስፋህን ሳይሆን እውነትን ነው ለቴ፡፡ ለዚህ ነው፣ ሀያሲ በጥቃቅን ቂምና ሽኩቻ ነፍሱን ማሳደፍ የለበትም የምለው፤ የሀያሲ ነፍስ በየምናምንቴው ብናኝ ካደፈ የብእሩን እድፍ ከቀለሙ መለየት ያስቸግራል፡፡

 

 

 

 

Read 5405 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 15:19