Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Sunday, 06 May 2012 15:54

በመስጊዶች አካባቢ የታየው ጥበቃና የኮሚቴው መግለጫ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሐሙስ እለት ባወጣው መግለጫ፤ “የሙስሊሙን ማህበረሰብ የማይወክሉ ፀረ የልማት ሃይሎች በሃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ” ካለ በኋላ፤ በአወሊያ ት/ቤት ሽፋን ለቀረቡ ተገቢ ምላሽ እንደሰጠ ጠቅሶ፤ ከውጪ ሃይሎች ጋር በቅንጅት የሚያካሂደው ተግባር ህገወጥ ነው ብሏል፡፡ጥያቄውን በኮሚቴ አማካኝነት ካቀረቡት መካከል አንዱ እንደሆኑ የገለፁት አቶ አህመዲን ጀበል፤ በመግለጫው እንደማይስማሙ አመልክተዋል።

ከኮሚቴው ጥያቄ ጋር በተያያዘ፤ የእስካሁኑ እንቅስቃሴ ህገወጥ እንደነበረ የጠቆመው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ አወሊያ ለ11 ሳምንታት ሲካሄድ የነበረው እንቅስቃሴ ህግና ስርአትን ማክበር ያልፈለጉ ወገኖች የሚያካሂዱት ነበር ብሏል። ኮሚቴው ወደ ህጋዊና ሠላማዊ መንገድ እንዲመለስ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ጫና ያድርግ ብሏል ሚኒስቴሩ።

የኮሚቴው አባል አቶ አህመዲን ጀበል በበኩላቸው፤ መግለጫውን ተከትሎ በአዲስ አበባ አራት መስጊዶች እና በደሴ መስጊድ ጥያቄ ቀርቧል ብለዋል። ቀደም ብለው ለቀረቡ ጥያቄዎች ለአራት ወራት ያህል መልስ አልተሰጠም የሚሉት አቶ አህመዲን፤ አንዱ ጥያቄ አወሊያ ተቋም እንደቀድሞው ከእስልምና ጉዳዮች ምክርቤት ነፃ ይሁን የሚል ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክርቤት አመራር ህዝቡ አልመረጣቸውም በማለት ሁለተኛውን ጥያቄ የጠቀሱት አቶ አህመዲን፤ ማህበረሰቡ ላይ የግድ ጫና ይቁም በማለት ሶስተኛውን ጥያቄ አቅርበናል ብለዋል። የአሩሲው የግድያ ሁኔታ ከኛ ጥያቄ ጋር ግንኙነት የለውም የሚሉት አቶ አህመዲን፤ ግንኙነት እንዳለው አድርጎ ማቅረብ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

አርብ ሰላማዊ ሰልፍ እንወጣለን በሚል የተሰራጩ መልእክቶች እኛን አይወክሉንም፤ በእነዚህ መልእክቶች ምክንያት ስጋት በመፈጠሩም መግለጫ ለመስጠት ተገደናል ብለዋል። በመስጊዶች አካባቢ ጥበቃ ተጠናክሮ መዋሉ የሚታወቅ ሲሆን፤ ሰላማዊ ሰልፍ እንወጣለን በሚል የተሰራጨው መልእክት እኛን እንደማይወክለን መግለጫ የሰጠነው ስጋቱን ለማስወገድ ነው ብለዋል - አቶ አህመዲን።

 

 

Read 14820 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 15:57