Saturday, 28 July 2018 15:27

“ትላንት ማታ ቤትህ ስትገባ የመታህ የድንጋይ እንቅፋት ዛሬም ከደገመህ፤ ድንጋዩ አንተ ነህ”

Written by 
Rate this item
(9 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ይጭነው አጋሠሥ፣ ይለጉመው ፈረስ የነበረው፣ ለምድር ለሰማይ የከበደና ባለሙያ የሆነ፤ ትልቅ ጌታ፤ በአንድ አገር ይኖር ነበር፡፡
አሽከሮቹ፣ ባለሟሎቹ፣ ጋሻ- ጃግሬዎቹ ሥፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ከአሽከሮቹ መካከል ሁለት በጣም የሚተሳሰቡ፣ በጣም የሚግባቡ፣ ስራ ከመሥራታቸው አስቀድመው የሚመካ ኩሩ ቅንና ታታሪ አሽከሮች አሉ፡፡
አንድ ቀን አንደኛው፤ ለሁለተኛው፤
“እንደዚህ ያለ አስተዳደሪ ጌታ ስላለን ዕድለኛ እንደሆንን ይገባሃል?” ሲል ጨዋታ ያነሳል፡፡
ሁለተኛው፤
“እጅግ በጣም ዕድለኞች ለመሆናችን ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ እንዲያውም እስከ ዛሬ ለዋለልን ውለታ ምን ልንከፍል እንችላለን? እያልኩ ሁልጊዜ እጨነቃለሁ፤ እጠበባለሁ፡፡”
አንደኛው፤
“ዕውነትም አንድ ነገር ለማድረግ መቻል አለብን፡፡ እስቲ አንተም አስብበት፤ እኔም ላስብበትና አንድ መላ እንፈጥራለን” አለ፡፡
ሁለቱ ታማኝ አሽከሮች ለውለታው ምላሽ ምን ለማድረግ እንደሚችሉ ማሰላሰላቸውን ቀጠሉ፡፡
የሁለቱ አሽከሮች ወዳጅነት የሚያስገርመው የጎረቤት ሰው፤ አንድ ቀን ወደ ጌትዬው ይመጣና፤
“እኔ እምልህ ወዳጄ፤ አንድ ነገር ልጠይቅህ እፈልግ ነበር” አለው፡፡
ጌትዬውም፤
“ስንትና ስንት ዘመን አብረን የኖርን ጎረቤታሞች ሆነን ሳለን፤ ጥያቄህን በሆድህ ይዘህ እስከዛሬ  መቆየት የለብህም ነበር፡፡ አሁንም የፈለከውን ጠይቀኝ” አለና መለሰለት፡፡
ጎረቤትዬውም፤
“እነዚህ ሁለት ታማኝ አሽከሮችህን፤ ምን ዘዴ ተጠቅመህ ነው እንደዚህ ተዋደውና ተሳስበው እንዲያገለግሉህ ያደረግሃቸው? መቼም በዚህ አገር እንዳንተ ያለ ዕድለኛ ሰው ያለ አይመስለኝም!” አለው፡፡
ጌትዬው የመለሰው መልስ በጣም አስገራሚ ነው፡፡
“ወዳጄ! እርስ በርስ ተጣጥመው እንዲያገለግሉኝ ለማድረግ የተጠቀምኩበት ምንም ጥበብ የለም፡፡ ይልቁንም ሌት ተቀን የምጠበብ የምጨነቅበትን አንድ ነገር ልንገርህ፡-
ለእኔ የሚጠቅመኝ ከሚዋደዱ ይልቅ ቢጣሉ ነበር!”
ጎረቤትዬው በጣም ደንግጦ፤
“ለምን? እንዴት?” ሲል ጠየቀው፡፡
ይሄኔ ጌትዬው፤
“አየህ ወዳጄ! ለእኔ የሚበጀኝ ቢጣሉና አንዱ አንዱን ቢጠብቅልኝ ነበር!” አለው ይባላል፡፡
* * *
“የአልጠግብ ባይ..” አስተሳሰብ፤ ሰው ወደ ጠብ፣ ወደ ጠላትነት፣ ወደ መናቆር፣ ወደ መሰላለል፤ እንዲሄድ የሚያደርግ ነው!
ሰው ከተፋቀረ፣ ከተሳሳቀና ደስ ብሎት ካደረ ይከፋዋል፡፡ ስለዚህም እንቅልፉን አጥቶ ሲያሴር፣ ነገር ሲጠመጥም ያነጋል፡፡ ደግ እንዳይበረክት ይመኛል፡፡ መመኘት ብቻ አይደለም ጥፋት ጥፋቱን ያጎለብታል፡፡ ሰላም ይበጠብጠዋል፡፡ የማሪያም መንገድ ሲታይ ዐይኑ ይቀላል! ወገን ከወገኑ ሲለያይ፣ ዘር ከዘር ሲደማማ፣ ሲቋሰል፤ ህልውና ይረጋገጥለት ይመስለዋል፡፡ እየዘረፈ፣ እየመዘበረ የገነባው ፎቅ ውሎ አድሮ ይነካበት አይመስለውም፡፡ የድሀ ዕንባ ጎርፍ ሆኖ ይወስደው አይመስለውም፡፡ ዘላለም እያባላሁ፣ እያናከስኩ እኖራለሁ፤ ይላል! እንደ ሁልጊዜው፤ ረዥም ጊዜ መኖርን ከዘለዓለማዊነት ጋር ያምታታዋል (He mistakes longevity for eternity)፡፡ የማታ ማታ ግን ተመናምኖ ተበትኖ ያበቃል! ይህ በታሪክ የታየ፣ ነገም የሚታይ ገሀድ ዕውነት ነው፡፡ “ሞት ቢዘገይ የቀረ ይመስላል” ነው ጉዳዩ!
አንድ፤ ጃንሆይ (ቀዳማይ ኃይለ ሥላሴ) ተናገሩት የሚባል መሠረታዊ አባባል አለ፡፡ አቃቤ- ሰዓት ተሰጥቶት ጉዳዩን በቅጥፈት ላስረዳቸው ሚኒስትር ያሉት ነገር ነው ይባላል፡-
“…ያልተሠራውን ሠርቻለሁ እያሉ መደለልና ወደፊትም እሠራለሁ እየተባለ ሐሳብን በሸምበቆ መሠረት ላይ መገንባት፣ ታላቅ ጉዳት የሚያስከትል ስለሆነ፤ የሠራኸውንም ሆነ ወደፊት ለመሥራት የምታስበውን እየለየህ በጥልቀት አጥናው…”
ይህ ዛሬም ላገራችን ባለሥልጣኖች የሚሠራ መሆኑን ልብ እንበል!
ሀገራችን ወደፊት ትራመድ ዘንድ የተደቀኑባትን አንዳንድ ጥያቄዎች በጥንቃቄ መመለስ ይገባታል፡፡
እነዚህ ጥያቄዎች በመሪዎች ጫንቃ ላይ ብቻ የምንጭናቸው ሳይሆኑ የሁላችንንም እርዳ-ተራዳ የሚሹ ናቸው፡፡ ተነጣጥለን የምንታገልባቸው ሳይሆኑ አንድነታችንን ልንፈትሽባቸው ግድ የሚሉ ናቸው፡፡ እነሆ፡-
ምን ዓይነት ዲሞክራሲ እንዲኖረን እንፈልጋለን? ቀጣዩን ሥርዓት ለመገንባት የእስካሁኑን በምን መልክ ብንገላገለው፣ ብንጠግነው ወይም ብናድሰው ይሻላል? ህገ-መንግስቱ ላይ ያየናቸው እንከኖች የቶቹ ናቸው? ምን ቢደረጉ ይመረጣል? ዕውን የሽግግር መንግሥት ያስፈልጋል? በኢትዮ-ኤርትሪያ ዙሪያ የተጀመረው መልካም ጉርበትና እንዴት ይቀጥል? በዝርዝር ጉዳዩን ማን ያውጠንጥን? ቀድሞ በ1983 ዓ.ም ከምናውቀው ግንኙነታችን የተለየ ምን መልክ ይያዝ? ኮንፌዴሬሽን አዋጭ አካሄድ ነው ወይ? የህወኃት እና የአዲሱ ጠ/ሚኒትር አቅጣጫ ግንኙነት ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ሚና ምን መሆን አለበት? ከህገ መንግሥት ማሻሻልና ከምርጫው የቱ ይቅደም? ለመሆኑ ፕራይቬታይዤሽን ያዋጣል? የምሥራቅ አፍሪካን መሪነት ማን ይይዛል? ያልተረጋጋውና የማይረጋጋው (ever volatile) የአፍሪካ ቀንድ ዕጣ-ፈንታ ምን ይሆን? በኢትዮጵያ ጉዳይ ዕውነተኛ ህዝበ- ተሳትፎ እንዴት ለማምጣት ይቻላል? ኢህአዴግ ከግንባር ወደ ውህደት ሊመጣ ይቻለዋልን? ህወኃት እና የትግራይ ህዝብ እንዴት ይታያሉ? ዕውነት ህወኃት የመሰነጣጠቅ አደጋ ላይ ነው? የግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ተቋማዊ የሆነን ጥንካሬ እንደምን ማምጣት ይቻላል? ሙስና በማስፈራራት ይቆማል? እስካሁን የወጡ ህጎች የፕሬስ፣ የፀረ ሽብር፣ የብሮድካስት ወዘተ እንዴት ይሻሻሉ? ያለው መንግሥት የህዝብ አመፅ የወለደው ነው? አለመረጋጋቱ ተገቷል ወይስ ሊቀጥል ይችላል?...
ጥያቄዎቻችን በርካታ ናቸው፡፡ የሚመለከተው አካል በአግባቡ ሊመልሳቸው ይገባል፡፡ ከእንግዲህ ማድበስበሱም ሆነ ቆይ-ነገ- ማለቱ (Procrastination) ለማንም አይጠቅምም፡፡ ሳንፈታቸው መጓዝና እርምጃ አለመውሰድ ስህተት ነው!! ይህን ስህተት ደግመን ከሠራን “ትላንት ማታ ቤትህ ስትገባ የመታህ የድንጋይ እንቅፋት ዛሬም ከደገመህ፤ ድንጋዩ አንተ ነህ” የሚለው የቻይናዎች አባባል እኛ ላይ ሠራ ማለት ነው፡፡ ሰብሰብ፣ ጠንቀቅና ጠበቅ እንበል! ሁሉንም ደበላልቀን አንድ ላይ ከመፍጨት፣ በየከረጢቱ አስቀምጠን መቋጠር በመልክ በመልኩ ለመፍት ያመቻል፡፡ (From smashed potato to potato-sacks እንደሚሉት መሆኑ ነው)

Read 9104 times