Saturday, 18 August 2018 09:42

“ኢትዮጵያ፤ ትወልዳለች እንጂ አታሳድግም”

Written by 
Rate this item
(18 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ በኑሮው የደላው፤ ሀብቱ የተመቸው፣ እጅግ ቀብራራ ሰው፣ ነበረ፡፡ የሰፈር ሰው ሁሉ ደግና ለተቸገረ ደራሽ ነው ይለዋል፡፡ ወደ ቤተ - ዕምነት ሄዶ ሰባኪው የሚሉትን ይሰማል፡፡
ሰባኪው - በሀልዮ በነቢር በገቢር የተሰራ ሐጢያትን እግዚሐር ይፍታን
ምዕመናን - አሜን!
ሰባኪው - ለተቸገረ እርዱ!
      - በሽተኛ ጠይቁ!
      - ለደሀ መጽውቱ!
      - ሁለት ያለው አንዱን አንድ ለሌለው ይስጥ!
      - የላይኛው ቤታችሁን እምድር ሳላችሁ አብጁ!
      - ፁሙ! ፀልዩ!
      - ትምህርታችሁን ይግለጥላችሁ!
ምዕመናን - አሜን!
ሰባኪ - ከእናንተ የተሻለ የሚኖር ማን አለ?
ምዕመናን - ማንም!
ሰባኪ - ከእናንተ መካከል ሳይበላ የሚያድር ማን አለ?
ምዕመናን - ማንም!
ሰባኪ - ትሰጡት አትጡ!
ምዕመናን - አሜን!
ሰባኪ - በየመንገዱ የወደቁትን ለማሰብ ልቦና ይስጣችሁ!
ምዕመናን - አሜን!
ሰባኪ - የሰማነውን በየልቦናችን ያሳድርብን!
ምዕመናን - አሜን! አሜን!
ሁሉም ወደ የቤታቸው ሄዱ፡፡ ያም ሀብታም ሰው ወደ ቤቱ ለመሄድ መንገድ ጀመረ፡፡
ወደ ቤቱ መሄጃው ላይ አንድ ድልድይ አለ፡፡ እድልድዩ ላይ በግራና በቀኝ በኩል ተቀምጠው የሚለምኑ ሁለት ዓይነ - ሥውር ለማኞች አሉ፡፡ መካከላቸው ሲደርስ ከኪሱ በርካታ ሳንቲሞች አወጣ!
ለማኞቹ - “ጌታዬ አትለፈን! ካለህ አይጉደልብህ! ትሰጠው አትጣ! ትመፀውተው አትጣ! እጅህ እርጥብ ይሁን!” ይሉታል፡፡
ሀብታሙ ሰው ከኪሱ ያወጣቸውን ሳንቲሞች በሁለት እጆቹ ይዞ አንኳኳቸው፡፡ ሿ! ሿ! ሿ! አደረጋቸው፡፡ ሁለቱ ዐይነ - ስውር ለማኞች በጣም ጎመጁ፡፡ ከአሁን አሁን መጥቶ ይሰጠናል ብለው ሲጠብቁ, ሳንቲሞቹን መልሶ ኪሱ ከቶ፤
“ተካፈሉ!” ብሎ ሄደ፡፡
በወዲህ ወገን ያለው ለማኝ; “ያኛው ተቀብሏል፤ ያካፍለኛል” አለ፡፡
በወዲያ በኩል ያለውም ለማኝ፤
“እሱ ተቀብሏል፣ ያካፍለኛል!” አለ፡፡
ሁለቱም ምንም ሲያጡ ተነስተው አንዱ; “ስጠኝ! የሰጠንን አካፍለኝ!` ሌላውም; “ላንተ ነው የሰጠህ አካፍለኝ!”
`አንተ ወስደሃል … አንተ ወስደሃል” እየተባባሉ፤ ድብድብ ጀመሩ፡፡
ሀብታሙ ሰው; ከሩቅ ሆኖ ከት ብሎ ሳቀባቸውና ወደ ቤቱ ሄደ!
***
እኛ ኢትዮጵያውያን ደግ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ለተቸገረ ደራሽ፣ ተዛዛኝ … እንባላለን፣ እንጂ ጭካኔያችን ለከት የለውም! ውስጣችን አልተፈተሸም፡፡ አልተመረመረም! በሰብአዊነት ሽፋን የምንኖር ኢ-ሰብአዊዎች ነን! ፈዋሽ ሀኪም አልተገኘልንም እንጂ የውስጥ ደዌ አለብን - ጭካኔ! እንዋደዳለን እንላለን እንጂ ውስጣችን በጭካኔ አባዜ የተሞላ ነው! የመሀይምነታችንና የአረመኔነታችን (Barbarism) መጠን ገና አልታወቀም - አልተጠናንም! እርግጥ ሁላችንም ላንሆን እንችላለን እንጂ የክፋታችን ልክ ይህ ወሰንህ፣ ይህ ዲካህ የሚባል አይደለም፡፡ አያምጣው እንጂ ክፉ ጊዜ ቢመጣ፣ እርስ በርስ ሊያበላላን ይችላል! ነፃነት ይከብደናል! መከራ ከመልመዳችን የተነሳ ነፃነት ሸክም ይሆንብናል፡፡ ድህነታችን የሀብት ብቻ ሳይሆን የአዕምሮም ነው! የልቡናም ነው! ደግ ጊዜ ያምጣልን እያልን፣ ደጉን ጊዜ ገፍተን እንጥላለን! ይሄ ኃይለኛ የልቡና ቀውስ ነው! አዎንታዊ ነገር የማይጥመን ከሆነ፣ አሉታዊው ነገር በደም ጎርፍ ያስተጣጥበናል!
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በቴያትሩ እንዳስቀመጠው፤
“ሞትን ለሚሻ ሞትን ነው መንፈግ! ህይወትንም አለመቸር! እማህል ቤት ነው የሰው ልጅ ጥቅም የሚሰጥ! ሰው ሆኖ ካሹት፣ ጥቅም የማይሰጥ የለም!” ይለናል፡፡ ለዚህ ፀሐፊ፣ የአበሻ ውስጠ ነገር ዱሮ ነው የገባው ማለት ነው!
ያም ሆኖ “በርኩቻው ማህል ፀጥ ብለህ ለመጓዝ ሞክር” ይላል፤ የጥንቱ የጠዋቱ የዴዚዴራታ ምክር! ምክሩ ከገባን ዓለም በውካታ የተሞላች ናት - አንተ ግን ተረጋግተህ ተጓዝባት ማለት ነው፡፡ መረጋጋት፣ ማረጋጋት፣ ሁኔታዎችን በሰከነ ዐይን ማየት፤ የበሳል ሰው መርህ ነው፡፡ “በካፊያው ከተረበሽክ የዶፉ ዝናብ ጊዜ ምን ይውጥሃል?” ይላሉ አበው፡፡ ህዝባችንን ማሳወቅና ማስተማር፣ መሰረታዊ ጉዳያችን መሆን አለበት፡፡ በክፋት፣ በጭካኔና በአረመኔያዊነት (Barbarism) እና በህዝባዊ እምቢተኝነት (Civil disabidience) መካከል፤ የገደል ያህል ልዩነት አለ፡፡ የፊተኛው የኃላ ቀርነት፣ የኋለኛው የአዋቂነት አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ በመሰይጠንና በመሰልጠን መካከል ያለውን አደጋ እናስተውል፡፡ የዱሮ ፍልስፍናም ቢሆን “ህግ የማይገዛውን ነፃነት፣ ኃይል ይገዛዋል” የሚለውን አባባልም እንደገና ማውጠንጠን ግዴታ ሊሆን እንደሚችል አንዘንጋ፡፡ “ጥንቃቄ ሲጠብቅ ፍርሃት ይሆናል” የሚለውንም አንርሳ፡፡ ዞሮ ዞሮ የሚመለከተውና ኋላፊነቱ የሚሰማው ክፍል የሚያደርገውን ያውቃል ብለን እንገምታለን - “እኔ ተጎድቼ ባመጣሁበት ውሰደው” ይላል ጮሌ ነጋዴ፡፡
ሀገራችን ሾተላይ ያለባት ይመስል ፅንስ ይጨነግፍባታል፡፡ ማስወረድ ልማድ ሆኖባታል፡፡ አሮጊው እንቅፋት አዲስ እንቅፋት እየፈለፈለ ያሽመደምዳታል፡፡ “እኔ ስወለድ ነው የሳቅ ጀምበር የጠለቀችው” የሚል ኢትዮጵያዊ እንዳይበዛ፤ ልባም ልባሞቹ ሰዎች መመካከር አለባቸው፡፡ “ገዢ እንጂ መሪ አያምርብንም” እንዳለው አፍሪካዊው ፀሐፊ፤ በግድ የገዢ ያለህ እያልን እንዳንፀልይ ምህረቱን ይላክልን፡፡ ውድቀትን ማቀድ አልፎ አልፎ ያዋጣል ብንልም፣ መነሻችን ጨለምተኝነት ከሆነ፣ ከ“ሁሉም ይውደም ፍልስፍና” (nhilism) አባዜ አይተናነስም! “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው እንስሳም፤ የአገር ጨለማን መባጀት ክፉ እርግማን ነው! የየዓይነቱን እርግማን በበቂ አይተናልና አዲስ እርግማን ፍለጋ መባቸር ከንቱ መላላጥ ነው፡፡ “ከመርገምት ሁሉ የከፋው መርገምት፤ ቋንቋ ለቋንቋ መጠፋፋት ነው!” ይላል ገጣሚው፡፡ መግባባት እንዳይጠፋብን አሳቢዎቻችንን (Thinkers) እናዳምጥ እንሰማማ!! እርስ በርስ እንናበብ፡፡ መናበባችንን ይባርክልን ዘንድ ቀና እንሁን፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ከእንግዲህ “ትወልዳለች እንጂ አታሳድግም” መባሏ መቆም አለበት፡፡ የበቀሉ ዕድሎች እንዳይጠወልጉ እንንከባከባቸው! እውቀታችንንና አቅማችንን ሁሉ አፍንጫችን ሥር ባለው ጉዳይ ላይ ሳይሆን ትልቁን ስዕል አገርን (The Bigger Picture) ማየት ላይ እናውለው፡፡ የግለሰቦችን ምንነት ከአጠቃላዩ ህዝብ ህልውና ለይተን እንይ! ዛሬም ትምህርታችንን ይግለጥልን!!  

Read 9059 times