Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 May 2012 10:10

ዳኞች ከመፍረስ ያዳኑት የ50 አመት ትዳር

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ወ/ሮ አልማዝ አስፋው እና አቶ ዘመረ ጀማነህ የትዳር ህይወት የጀመሩት የዛሬ 50 ዓመት ገደማ ነበር፡፡ ወ/ሮ አልማዝ የ19 አመት” አቶ ዘመረ የ23 አመት ወጣቶች ሳሉ፡፡ ያኔ አባት የባንክ ሰራተኛ ሲሆኑ እናት አየር መንገድ ነበር የሚሰሩት፡፡ ከ27 ዓመት የትዳር ህይወት በሁዋላ አባት የንግድ ስራ ጀመሩ፡፡ በፍቅር የተሞላው ትዳራቸው አምስት ልጆቻቸውን በስርአት አንፀው ለማሳደግ እንደጠቀማቸው የሚናገሩት ወ/ሮ አልማዝ” ከንግድ ስራው ጋር በተገናኘ ባለቤታቸው እያመሹ መግባታቸው ለጠብ መነሻ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ባለቤታቸው የመንግስት ሰራተኛ እያሉ ከስራ መልስ እቤት ሲያገኙዋቸው ይደሰቱ እንደነበር የሚናገሩት ሚስት” ባለቤታቸው እያመሹ ሲመጡ መነጫነጭ እንደጀመሩያስታውሳሉ፡፡ ንጭንጩ ወደ ጭቅጭቅ እየተካረረ ሲመጣ ባለቤታቸው አቶ ዘመረ” ከሚስታቸው ተለይተው ለብቻቸው መኖር ጀመሩ - ሌላኛው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ፡፡ ለአራት ዓመት ተለያይተው ቢኖሩም ግን ከልጆቻቸው በቀር ማንም አያውቅም ነበር ይላሉ - ወ/ሮ አልማዝ፡፡ አምስት የልጅ ልጆች ያዩት ባልና ሚስቱ” በተለያየ ቤት ውስጥ ቢኖሩም የቤት ወጪ የሚሸፍኑት አቶ ዘመረ ነበሩ፡፡

አንድ ቀን ወ/ሮ አልማዝ 3500 ብር ይፈልጉና ባላቸው ጋ ሰው ይልኩባቸዋል፡፡ ባል ግን አሜሪካ ልጆቹዋ ጋ መሄድ ለምዳ ነው በሚል ሰበብ ገንዘቡን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ፡፡ በዚህ የተናደዱት ሚስት” የፍቺና የንብረት ክፍፍል ጥያቄ ያነሱና ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ያመራል፡፡ በ2001 ዓ.ም ህጋዊ ፍቺ ፈፀሙና በንብረት ክፍፍል ዙሪያ በፍ/ቤት ክርክር ጀመሩ፡፡ በመጨረሻ ፍ/ቤት በጉዳዩ ላይ የሰጠውን ውሳኔ ያልተቀበሉት ሚስት” ይግባኝ እንደጠየቁ ይናገራሉ - በከፍተኛ ፍ/ቤት፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ ወላጆቹ ፍቺ ከፈፀሙ በሁዋላ ከአባቱ ጋር መኖር የጀመረው አምስተኛ ልጃቸው ዳዊት” አባት ከአዋሽ ኢንሹራንስ በስሙ የገዙትን የ500ሺ ብር አክሲዮን  ይገባኛል በሚል ክስ ይመሰርታል፡፡ የአባትና ልጅን የአክስዮን ይገባኛል ጉዳይ እልባት ሳያገኝ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይደርሳል፡፡ ፍ/ቤትም እናት ቀርበው  በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ያዝዛል፡፡ ወ/ሮ አልማዝ ፍርድ ቤት ቀርበው ሲናገሩ ያደመጡት ዳኞች” ከያዙት ጉዳይ ወጥተው የአቶ ዘመረ ጀማነህና የወ/ሮ አልማዝ የ50 አመት ጋብቻ መፍረስ የለበትም ብለው መነጋገር ጀመሩ፡፡ የቤተሰብ ህይወት ፈረሰ ማለት ህብረተሰብ ፈረሰ ማለት ነው ያሉት ዳኞቹ” ፍቺ ተፈፅሞ የንብረት ክፍፍል ላይ መድረሱን ቢያውቁም ጉዳዩ እንደገና በሽማግሌ መታየት አለበት የሚል ሃሳብ ለቀድሞዎቹ ባልና ሚስት አቅርበዋል፡፡የታች ፍ/ቤት የሽምግልና ሂደት አለመሳካቱ ተነግሮዋቸው ነበር - ዳኞቹ፡፡ ሆኖም ሽማግሌዎች የቻሉትን ያህል እንዲጥሩ ይጠይቁዋቸዋል - የፍ/ቤቱን ቤተመፃህፍት እንዲጠቀሙበት  በመፍቀድ ጭምር፡፡ ወ/ሮ አልማዝ  በነገሩ ተስፋ ቆርጠው ስለነበረ “ሁሉ ከንቱ ንፋስን እንደመከተል ነው”በማለት ሽምግልናውን ቸል እንዳሉት ይናገራሉ፡፡ ከሶስት ወር ድካም በሁዋላ የሽምግልና ሂደቱ  በስኬት ይጠናቀቅና” ባልና ሚስቱ ጉዳያቸውን በእርቅ መፍታታቸውን በመግለፅ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ባስገቡት ደብዳቤ መሰረት” ከትላንት በስቲያ የክስ መዝገቡ ተዘግቶ ፋይሉ ወደመዝገብ ቤት እንዲገባ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቱዋል፡፡ በእርቁ መደሰታቸውን የተናገሩት ወ/ሮ አልማዝ” በውስጤ የሻከረ ነገር የለም ሁሌም አምላኬን አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡ “ቤቴ ሙሉ ነው” አምላክ በደግነቱና በቸርነቱ ሁሉንም ነገር አስተካክሎታል” ሲሉ የተሰማቸውን ገልፀዋል - ወ/ሮ አልማዝ፡፡ ሠላም የሠፈነበት ብቸኝነት ያከተመበት” አዲስ ህይወት በመምጣቱ መደሰታቸውን የተናገሩት  አቶ ዘመረ ጀማነህ በበኩላቸው” ቀድሞውኑም የእሳቸውን መከፋት ከማይፈልጉት ባለቤታቸው ጋር በፍቅር እንደሚኖሩ ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡ “ያለፈው ጊዜ ቅጣት ነው” ያ ዘመን ይብቃ” ብለዋል - አቶ ዘመረ፡፡ ስንት ውጣ ውረድ የነበረበትን ሽምግልና የተቀበሉበት አንዱ ምክንያት ልጆቻቸው ከአሜሪካ በላኩት በምስል የተደገፈ መልዕክት የተነሳ እንደሆነ የገለፁት አቶ ዘመነ” ምስሉ የሚያሳየውን ሲያብራሩ” “ወተት ያጋተች ላምን ባል ቀንዷን” ሚስት ጭራዋን ትጐትታለች፡፡ ጠበቃ ደግሞ የላሟን ጡት እየጠባ ወተት ይጠጣል፡፡ ዛሬ ግን ወተቱን እኛ ነን የምንጠጣው” የሚል ነው ብለዋል፡፡ የአነአቶ ዘመነን የእርቅ ጉዳይ ይዘው የነበሩት አምስቱ ሽማግሌዎች” ሁለቱ የረጅም ዘመን ጥንዶች ዳግም አብረው መኖር እንዲችሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ዳኞች አመስግነዋል፡፡ መላ ቤተሰቡም ለዳኞቹ በጋራ ምስጋናውን አቅርቦዋል፡፡ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ያሰሙት ዳኛ ደስታ ገብሩ “ህጉ ለቤተሰብ ልዩ ከለላ ይሰጣል” የዘመናት ትዳር ቀልድ አይደለም” ቤተሰብከህብረተሰብ የሚመሠረት ነውና እናንተ ለሌላው አርአያ መሆን አለባችሁ”  ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል፡የእርቅ ስምምነት ሚያዝያ 24 2004 ዓ.ም የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት 1 ፍትሐብሔር ችሎት በአንደኛ በወ/ሮ አልማዝ እና በአቶ ዘመረ እና በጣልቃ ገብ ወ/ሮ ፂዮን ዘመረ” በሌላ በኩል በአቶ ዘመረ እና በአቶ ዳዊት ዘመረ መካከል ያለውን ክርክር” ፍ/ቤቱ ባዘዘው መሠረት የሽምግልና ጉባኤውና የፈጣሪው ሃይል ተጨምሮበት ቅሬታቸውን ሙሉ በሙሉ አስወግደው እንደሚመለከተው የእርቅ ስምምነት አድርገዋል፡፡ አንደኛ- አቶ ዘመረ ጀማነህ እና ወ/ሮ አልማዝ አስፋው ቀደም ሲል ትዳራቸው ወይም ጋብቻ በፍርድ ቤት ፍቺ ሰጥቶ የነበረ በመሆኑ እንደገና አዲስ ጋብቻ ለማድረግ ሙሉ ፈቃደኝነትና ስምምነት አድርገዋል፡፡ ሆኖም በፍርድ ቤት ከፈረሰ በኋላ የባልና የሚስት የንብረት ክፍፍልን አስመልክቶ የሁለቱን ንብረት በማጣመር አብሮ ለመኖር ወስነዋል፡፡ ፍ/ቤቱ የወሰነውን ውሳኔ ሁለቱም ወገኖች ተቀብለውታል፡፡ በመሆኑም በፌደራል ከ/ፍ/ቤት 12ኛ ወንጀል ችሎት የይግባኝ ክርክር እንዲዘጋ በዚህ ታዟል፡፡ ሁለተኛ- በአቶ ዘመረ ጀማነህና በአቶ ዳዊት ዘመረ መካከል ያሉት የፍትሐብሔር ክርክሮች” አቶ ዳዊት በወላጅ አባቱ ላይ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ላደረሰባቸው ጉዳት እግራቸው ስር በመውደቅና በማልቀስ ይቅርታ በመጠየቁ” ወላጅ አባቱ ይቅርታውን ተቀብለዋል፡፡ አቶ ዘመረ እና ወ/ሮ አልማዝ ልጃቸው አቶ ዳዊት ከእስር በሚፈታበት ወቅት እራሱን ችሎ ከቤተሰቦቹ ተለይቶ እንዲኖር ተስማምተዋል፡፡ አቶ ዳዊት እራሱን ችሎ መኖር ያስችለው ዘንድ በእሱ ስም ተመዝግቦ የሚገኝ 549 ሺህ ብር የሚያወጣ የአዋሽ ኢንሹራንስ ሼር እና የሼሩ የተጣራ ትርፍ (ዲቪደንት) ከ250 ሺህ ብር በላይ የተጠራቀመለት ገንዘብ” በበቂ ሁኔታ ሊያቋቁመው እንደሚችል ተስማምተዋል፡፡ በተጨማሪ አቶ ዘመረ ጀማነህ” በአቶ ዳዊት ላይ የመሠረቷቸውን የፍትሐብሔር ክርክሮች በዚህ የእርቅ ስምምነት እንደሚያቋርጡ ፈቃደኝነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ አቶ ዳዊት የተሠጠውን ስጦታ በመቀበል” ከወላጆቹ ቤት በመውጣት የራሱን ህይወት እንደሚመራ በዚህ የእርቅ ስምምነት አረጋግጧል፡፡ ሦስተኛ- በሙሉ ፍቃደኝነትና ሁነኝነት ከልብ በመነጨ ይቅር ባይነት የእርቅ ስምምነት የተደረገ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉት የቤተሰቡ አባላት በሚገኙበት አንድ የቤተሰብ ጉባኤ ጉዳዩን ወደነበረበት የሚመልስ አንድ የቤተሰብ ጉባኤ እንደሚኖር ተስማምተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የእርቅ ስምምነቱን ተመልክቶ ውሳኔ ሠጥቷል፡፡ ትዕዛዝ ይግባኝ ባይና መልስ ሰጪ አባትና ልጅ እንደመሆናቸው መጠን” በመሀከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት በእርቅ ወይም በስምምነት እንዲፈቱ ከችሎት ተጠይቀው” ችግሩ ይሄ ብቻ ሳይሆን ይግባኝ ባይና ባለቤታቸው ወ/ሮ አልማዝ  ወደ ሀምሳ አመት የሚጠጋ ትዳራቸው በፍቺ ፈርሶ” አቶ ዘመረ ጋር በተለያዩ ክርክሮች በስር ፍ/ቤቶች በመሆናቸው” አቶ ዘመረና አቶ ዳዊትም የተለያዩ ክሶች እንደመሠረቱ”  አቶ ዘመረ አቶ ዳዊትን በወንጀልም እንደከሰሷቸው እና ችግሩ በቤተሰቡ ውስጥ ስር እየሰደደ መሄዱ ስለተገለፀ” ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ወደ ሠላም መንገድ እንዲመጡ ፍ/ቤቱ የሰጠውን ምክር በመቀበል” ከችሎት ተገኝተው መቀበላቸውን በማረጋገጣቸው” በርካታ አመታት በትዳር የኖሩ በመሆኑና ለህግና ለሞራልም ተቃራኒ ባለመሆኑ” በህግ ቁጥር በፍ/ብሔር አንቀጽ 277/2/ መሠረት ተቀብለን” በእርቅ ስምምነቱ መሠረት ይፈፀም ተባብለን ወስነን” እግዶቹን አንስተን ጉዳዩ ለሌላም አርአያ በመሆኑ በመገናኛ ብዙሀን እንዲገለጽ አዘናል፡፡

 

 

 

 

 

Read 19804 times Last modified on Saturday, 12 May 2012 11:23