Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 May 2012 10:28

ሰሚ ያጣ ጩኸት . . .

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ ቤት ተከራይቼ ከገባሁ አንድ አመት ከመንፈቅ ሆኖኛል፡፡ ከአከራዮቼ በተጨማሪ በጊቢው ውስጥ ላጤና ባለትዳር ተከራዮችም አሉ፡፡ በርካታ ህጻናትም ጊቢው ውስጥ ወዲህ ወዲያ ይላሉ፡፡የስራዬ ሁኔታ ሆኖ ማልጄ ወጥቼ በውድቅት የምገባባቸው ቀናት ስለሚበዙ አከራዮቼን ሆነ ሌሎች በጊቢው ውስጥ ያሉ ነዋሪዎችን አብዛኛውን ጊዜ አላገኛቸውም፡፡ ሆኖም ዘወትር ጠዋት ስወጣ እድሜዋ ከ10 ዓመት ያልበለጠች ህፃን፣ በአንደኛው የኪራይ ቤት በር ላይ ቁጭ ብላ ስራ ስትሰራ ወይም ህፃን አዝላ ስትንቆራጠጥ በተደጋጋሚ ታጋጥመኝ ነበር፡፡ሁኔታዋንና አለባበስዋን ሳየው የተከራዮቹ ልጅ ወይም የቅርብ ዘመድ እንዳልሆነች ገብቶኛል፡፡ በዚህ ለጋ እድሜዋ በስራ መወጠሯ አስገርሞኛል፡፡ እኔ ወደ ስራ በማቀናበት ቀዝቃዛ ማለዳ የህፃኗ ፋታ ማጣት ሲደጋገም ግን ያንገበግኝ ጀመር፡፡

እናም ከእለታት በአንዱ ቀን ላናግራት ወሰንኩ፣

“ስምሽ ማን ነው?” ስል ጠየኳት

“መስታወት”  አለች ዘዬ ባለው አማርኛ

“አብረውሽ የሚኖሩት ዘመዶችሽ ናቸው?”

ደገምኩ ጥያቄዬን

“ቀጣሪዎቼ” አጭር ነበር መልሷ

“ትማሪያለሽ?” ነበር ቀጣይ ጥያቄዬ

“ከትምህርት ቤት ደርሼም አላቅ!”

መስታወት የመጣችው ከገጠሪቱ ሰሜን ኢትዮጵያ ከምስራቅ ጎጃም ሲሆን ከቀጣሪዎቿ ጋር እ-ድትገናኝ ያደረጓት ዘመዶቿ መሆናቸውን ተረዳሁ፡፡ የሚጎራበቱኝ ተከራዮች ጋር የምትኖረውም በእድሜ ይነሳት እንጂ የሷንም ህጻንነት የሚጋራትን ጨቅላ ለመንከባከብ መሆኑን እጅግ ዝግ በሚል ድምጽ አወጋችኝ፡፡ ከዚህ በላይ ግን ከኔ ጋር ሽርፍራፊ ደቂቃዎችን ለማውራት አልቻለችም፤ የማለዳ ስራዋ ገና መጀመሩ ነበር፡፡

አሁንም ድረስ ያለ ዕድሜያቸው በመኖሪያ እንዲሁም በንግድ ቤት ከዛም ሲያልፍ በሴተኛ አዳሪነት የሚሰሩ ህፃናት በአፍሪካይቱ መዲና አዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የክልል ከተሞች እንደሚገኙ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ እነዚህ ጨቅላ ህፃናት አብዛኞቹ በፍላጎታቸው (ዋነኛ መንስኤ ሆኖ ለዚህ ህይወት የሚያስገድዳቸው ድህነትና እሱን ተከትሎ የሚመጣው የቤተሰብ ሃላፊነት በጨቅላ ጫንቃቸው መጫኑ እንደሆነ በርካታ ጥናቶች ይስማማሉ) ወይም በወላጆችና ዘመዶች ነን ባዮች አስገዳጅነት ከገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ወደ ከተማ የሚመጡ ሲሆን እንደ ጥናቶች ገለፃ፤ ህፃናቱ ለሚሰሩት ከአቅም በላይ ስራ ክፍያ የማይሰጣቸው ወይም አነስተኛ ክፍያ የሚያገኙ፤ በተጨማሪ ደግሞ ትምህርት የማግኘት እድላቸው እጅጉን የመነመነ ነው፡፡በምኖርበት በዛው ቦሌ አካባቢ በጫት ማስቃሚያ ቤቶች፣ ጫት በማመላለስ ህይወቱን የሚገፋው፤ በ11 ዓመቱ ከደቡቧ ወላይታ ዞን የመጣው አክሊሉ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡

እሱንና አራት ታናናሾቹን ጉርስ መሸፈን በተሳናቸው ወላጆቹ ከግፊት ባልተናነሰ ፍቃደኝነት ከ4 ዓመት በፊት ወደ አዲስ አበባ የመጣው አክሊሉ፤ አሁን በሚሰራበት ቦታ ደሞዝ ተቀብሎ አያውቅም ፡፡

“ጫት የማድረስ ስራውን የማከናውነው ደንበኞች በሚሰጡኝ ቲፕ (ጉርሻ) ብቻ ነው” የሚለው አክሊሉ፤ ከአገሩ ከመጣ አንስቶ ወደ ትምህርት ቤት ሄዶ አያውቅም፡፡ መንገድ ላይ የትምህርት መሳሪያዎችን የያዙ ህጻናትን ሲያይ ውስጡ በአምሮትና በምኞት ከመቃጠል በቀር፡፡

ከአገሩ ሲመጣ ለሽመና ስራ ወደ ሽሮ ሜዳ አቅንቶ የነበረው አክሊሉ፤ አሁን ያለበት የስራ መስክ በእጅጉ እንደሚሻል ይገልፃል፡፡ እዛ እያለ ቀኑን ሙሉ የአሰሪዎቹን ትዕዛዝ ለማሟላት የልጅ እግሮቹን ጉድጓድ ውስጥ ቀብሮ፣ መጣሁ እያለ ከሚያዳፋው እንቅልፉ እየታገለ ጥበብን ቢሸምንም ከልፋት ባለፈ በቂ ምግብ እንኳን አላገኘበትምና የሽመና ስራውን ጥሎ እግሩ እንደመራው ወደ ቦሌ ኮበለለ፡፡ “ምንም እንኳን ትምህርትና ክፍያ ባይኖረኝም እዚህ የስራ ሰአቴ እረፍት ያለው በመሆኑ ይኸየኛውን ስራ ወድጄዋሁ” ይላል የህይወትን ጣዕም ሳይቀምስ ነገው የጨለመበት ጨቅላው አክሊሉ፡፡

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ አክሊሉ ወይም መስታወትን መሰል በርካታ ወንድና ሴት ህፃናት አሁንም በህገ ወጥ መንገድ ድህነት ክፉኛ ከተጫናቸው የአገሪቱ የገጠር ክፍል ወደ ከተማ እየጎረፉ ነው፡፡

የክፋትም ክፋት

የእነ መስታወትን አነሳን እንጂ እንደ ሔለን ያሉ ዕድሜያቸው ገና 15ኛ ዓመትን ያልተሻገሩ ሴት ህፃናት የሚኖሩበት የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት፤ ህጻናት በማይገባቸው የስራ መስክ ስር በሰደደ መልኩ እየተዘፈቁ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

ዕድሜዋ 15 ዓመት እንደሆነ የምትገልፀው ሔለን፤ የሴተኛ አዳሪነት ህይወቷን ለቅፅበት ማሰብ አትፈልግም፡፡

“ከጎንደር ከቤተሰቦቼ ጠፍቼ ስመጣ ቢያንስ የቤት ውስጥ ስራ እንደምሰራ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡” የምትለው ሔለን፤ በደላሎች አማካኝነት ማሰብ ከማትፈልገው የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ከገባች 1ዓመት እንዳለፋት ሳግ በተናነቀው ስሜት ታስረዳለች፡፡

በከተሞች አካባቢ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ በየሴተኛ አዳሪነት ህይወት ውስጥ ያሉ ህፃናት በርካታ እንደሆኑና ቁጥራቸውም ከዕለት ወደዕለት በአሳሳቢ መልኩ እየጨመረ ለመሆኑ ከጥናቶች ባለፈ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ሊረዳው የሚችል ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ለህፃናቱ በዚህ አስፈሪ የስራ መስክ መሰማራት ከገጠር ማስመጣት ጀምሮ የደላሎች ሚና ከፍተኛውን ቦታ ይወስዳል፡፡ ይሁን እንጂ በህፃናቱ አቅራቢያ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦችም ለህፃናቱ ወደዚህ ያላሰቡት ህይወት መግባት ድርሻ አላቸው፡፡

ከጭለማ ወደ ተስፋ

ዕድሜያቸው 14 ዓመትን ያልተሻገረ ህፃናት በማንኛው የስራ መስክ ማሰማራት ያልተፈቀደ መሆኑን የኢትዮጵያ አሰሪና ሰራተኛ ህግ ይደነግጋል፡፡ ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 18 የሆኑ ታዳጊዎችንም ቢሆን በቀን ከ7 ሰዓታት ላልበለጠ ጊዜ እንዲሰሩ ነው ህጉ የሚፈቅድው፡፡ ያም ሲባል የዕረፍትና የበዓላት ቀናትን ጨምሮ ታዳጊዎቹን በአደገኛ የስራ መስክ ማሰራት በህግ የተፈቀደ አይደለም፡፡ የመስታወት አሰሪ የሆኑት ጎረቤቶቼም ሆነ የአክሊሉ ቀጣሪዎችን የመሰሉ በርካታ ግለሰቦች የሀገሪቱን ህግ ወደ ጎን በመተው፣ ህፃናትን ያለክፍያ ወይም በዝቅተኛ ደሞዝ ለረጅም ሰዓታት እያሰሩ ይገኛሉ፡፡

በህፃናት ላይ እየደረሰ ያለውን ህገ ወጥ የጉልበት ብዝበዛ ለመቅረፍ መንግስትና አንዳንድ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እርምጃዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡  ሆኖም የህብረተሰቡ ጣልቃ ገብነት አስተዋጽኦ ወሳኝ ሚና እንዳለው የጉዳዩ ባለቤቶች ያስረዳሉ፡፡ ጥናቶች ህገወጥ የህጻናት ዝውውር የተደራጀ መልክ ይያዝ እንጂ የጉልበት ብዝበዛው በአብላጫው ቤት ለቤት የሚካሄድ መሆኑን ነው የሚጠቁሙት፡፡ እናም እያንዳንዱ ቤተሰብ ይህን አሳፋሪ ማህበራዊ ቀውስ ከተዋጋ ትርጉም ያለው ለውጥ ይመጣል፡፡

“ማናችንም በአካባቢያችን የህፃናት ጉልበት የሚበዘብዙ ግለሰቦችን ለህግ አካላት ብንጠቁም በዘርፉ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እንችላለን፡፡” የሚሉት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ባለስልጣን፤ መንግስት እ.ኤ.አ በ2014 የህፃናትን ህገ ወጥ ዝውውር እና ህገ ወጥ ጉልበት ብዝበዛ ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ ያወጣውን ዕቅድ ለማሳካት የህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚጠበቅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 

 

Read 2171 times Last modified on Saturday, 12 May 2012 10:35