Saturday, 12 May 2012 10:31

የሔዋን ልጆች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

ስለ ሔዋን ዘሮች ሥናስብ ብዙ ወንዶች ጌጠኛ ጥቅስ አለችን፡፡ “አቴናዊያን ዓለምን ይገዛሉ፤ እኔ አቴናዊያን እገዛለሁ፤ ሚስቴ ደግሞ እኔን ትገዛለች፡፡” የሚለው ነው፡፡ … ይህ ሀሣብ ዞሮ ዞሮ የሚወሥደን ዓለም የምትሽከረከረው በራሷ ዛቢያ ሣይሆን በሴቶች እጅ ነው ወደሚል ድምዳሜ ነው፡፡ በያዝነው ዓመት ያነበብኩት የሚኻኤል ጐርባቾሆቭ የሕይወት ታሪክም የዚህ ዓይነት ጣዕም አለው፡፡ ጐርባቾቭና ባለቤታቸው በአንድ ዩኒቨርሲቲ ነበር የሚማሩት፡፡ ግን በተለያየ ክፍለ ትምህርት፡፡ ይሁንና ጐርባቾቭ የአሁንዋ ባለቤታቸው አፍቃሪ ብቻ ሣይሆኑ አድናቂም ነበሩ፡፡ ደሞም በፍልስፍና ዲፓርትመንት ሠቃይ ተማሪ ሚስታቸው ነበሩ፡፡ ብስለታቸውም የትናየት! … እናም ተጋብተው ባልና ሚስት ከሆኑ በኋላ ሰውየው ሲጠየቁ የሰጡት መልስ አንዳች ነገር ለሚስታቸው ሣያማክሩ እንደማይወስኑ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የሀገሪቱ ወሣኝ ጉዳይ እንኳ ቢሆን! … ይህ ማለት፣ ጐርባቾቭ ሶቭየትንና ዓለምን ሲመሩ፣ ባለቤታቸው ራይሣ እርሳቸውን ትመራለች፡፡ ጐርባቾቭ በእንዝርት ላይ ያሉ ልቃቂት ናቸው፡፡ እንዝርቷ ደ’ሞ …

ዛሬ በሔዋኖች ጉዳይ የምፅፈው ወይም ሀሣብ የማቀርበው የሴቶችን አቅም በተመለከተ አይደለም፡፡ ባህርይ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ታላላቅ አንበሳ ሴቶች እንዳሉ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ፅፌያለሁ፡፡

በንባብ ከማውቃቸው ሴቶች የጆን ቡንያን ሚስት … አንድዋ ነች፡፡ ራስዋን ለባል የሰጠች፤ ከባልዋ ይልቅ መከራን የተቀበለች፡፡ ሲታሠር አብራ የተንገላታች፡፡ እያዘነች ለርሱ ስትል ሀዘንዋን ውጣ የሣቀችና ሰው ያደረገችው ሴት ነበረች፡፡ የስኬቱ ችቦ አቀባይም ናት፡፡

ሴቶች በበጐ መልኩ ጥሩ እናት ጥሩ ሚስት የሆኑበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ለምሳሌ ጥበብ ከሚወድዱ ሴቶች በመወለዳቸው ለዓለም ብርቅ የጥበብ ሥራ ካፈለቁ ሰዎች መካከል ቲ.ኤስ ኢሊየትንና ዎልፍ ጋንግ ቮን ገተን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ሁለቱም በግጥምና ዜማ፤ በድራማና በጥበብ እሽሩሩ ስላሣደጉዋቸው ታላላቅ ሆነዋል፡፡ በአብዛኛው የልጆች ሕይወት ከእናቶች ጋር በመሆኑም ጥሩ መልክ ይዘው  አድገዋል፡፡

በፍቅርም በኩል ቢሆን ዝናና ሥልጣን አሣብዶዋት የተንጠለጠለች ሴት ናት ተብላ የታማችው የሞሰሎኒ ፍቅረኛ ፔታቺ የዝናና የሥልጣን ጥገኛ ሣትሆን የፍቅር ጥመኛ መሆንዋን “ካንተ በፊት!” በማለት ደረትዋን ለጥይት በመስጠት ብዙዎችን አስደምማለች፡፡

ጄኔቫ የተወለደው ዣን ዣክ ሩሶ፤ ለታላቅ ፈላስፋነት ለትልቅ ሙዚቃ አቅምና ለሌላ ስኬት ያበቃችው በስደት ዘመኑ “አይዞህ!” ብላ ያሣረፈችው ማዳም ዴ. ሞረንስ ነበረች፡፡ ያ ባይሆን ግን ዓለማችን ያንን ታላቅ ሰው ሜዳ ላይ እንደተጣለ ፍሬ ተረግጦ ላታገኘው ትችል ነበር፡፡ የሕይወቱ ታዳጊ፣ የጥበቡ አሣዳጊ እርሷ ናት፡፡

የኖርዌይ ተወላጁ ፀሐፌ ተውኔት ሄኔሪክ ኢበሰን ሱዛናን ባያገኝ ኖሮ በሸለቆ ውስጥ ደርቀው እንደተቀሩት የእሥራኤል አጥንቶች ሕልም ሆኖ ይቀር ነበር፡፡ ግና … የፍቅር እስትንፋስዋን እፍፍ ብላ ሕይወቱን ያለመለመች እርሷ ናት፡፡ … ታዲያ እርሱም በጭጋግ ከተሞላ ዋሻ ወደ ፀሐይ ብርሃን፣ ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ብሩህ ፀዳል ያወጣችኝ ሱዛና ናት ይላል፡፡

ወላጅ አልባ የነበረው የዓለማችን ታላቅ ገጣሚና የልቦለድ ደራሲ አላንፓ፣ በአሣዳጊ አባቱ ክፋት ሲሠቃይ፣ አምጣ ከወለደች እናት ይልቅ ትዳርዋን እያናጋች ሲያለቅስ እያለቀሰች ካላት እየቆረሰች ያሣደገችው እናትም ሴት ናት፡፡

እስካሁን ይዤ የመጣሁትን ሀሣብ በጥቂቱ ከተመሳሰሉ በሚል “የዕድሜ መንገድ” ከሚለው መጽሐፌ አንዲት ግጥም መዝዣለሁ፡፡

አንተ አዳም ራስ ነህ ይላል ቅዱስ ቃሉ፤

አንቺ ሔዋን አንገት ነሽ ብለው ያወራሉ፣

እንግዲህ ተስማሙ አንቺ ራስ እርሱ አንገት፣

ብታሽከረክርህ ታዲያስ ምናለበት? … የሚለውን!

ብዙ ወንዶች ይህንን አይቀበሉትምና የጦፈ ሙግት አለ፡፡ እኔም ራሴ ቀደም ሲል የማስበውን ያህል ቅንነት ለሔዋኖች ያለኝ አይመሥለኝም፡፡ ምክንያቱም በተጨባጭ የማያቸው ገጠመኞች በልቤ ውስጥ የኖረውን እውነት እየሸረሸረብኝ ይመሥለኛል፡፡ በርግጥም ይህንን መጣጥፍ ከመፃፌ በፊት “የሴቶች ጉዳይ እንዴት ነው?” ብዬ እራሳቸውን ለመጠየቅ ሞክሬያለሁ፡፡ የአብዛኛዎቹ መልስ ዥንጉርጉር ነው፡፡ የእኔም ልብ አሁን ተዥጐርጉሯል፡፡ ቀደም ሲል ስለ ሔዋኖች የምከራከርበትን አቅም እያጣሁ መጣሁ፡፡ ቢሆንም እጅግ የማከብራቸው ሴቶች መኖራቸውን ግን አልክድም!

ለሴት ወገኖቼ ወይም ለሁሏም ሴት ቀለምና ፆታ ሣይለይ ፍቅር እንዲኖረኝ ያደረገኝ በብዙ እህቶቼ መካከል ማደጌ ይመሥለኛል፡፡ ለእህቶቼ ያለኝ ፍቅርም ሠፍቶ ለሴቶች ሁሉ ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ እህቶቼ ላይ ያየሁት ፍቅርና ንቅሳት በአብዛኛው የለም፡፡ ምናልባትም እህቶቼ ለወንድማቸው እንጂ ለባላቸው አይሆኑ ይሆን? ወደ ሚል ጥያቄ መጥቻለሁ (ጥያቄ ማለት ድምዳሜ እንዳልሆነ አሥምሩልኝ)

በቅርቡ የማያቸው ገጠመኞች ደግሞ ይህንን የሚያፀኑ እየሆኑብኝ ተቸግሬያለሁ፡፡ ለምሳሌ አንድ የቅርብ ወዳጄ የገጠመው ገጠመኝ ብዙ ጊዜ አጋጥሞኛል፡፡ ወዳጄና እኔ ለሴቶች የተሻለ ፍቅርም አክብሮት አለን፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ የእርሱ ሚስት አበባ ልብ ያላት አበባ ናት፡፡ ርግብ!

ታዲያ ልክ እኔ እንደማደርገው እርሱም በታክሲ ግፊያ መሀል ገብቶ (ጡንቻ ቢጤም ስላለው) ቦታ ይይዝና ግፊያ የበረታባትን ሴት ይጠራታል፡፡ ይሄኔ ገላምጣው አረፈች፡፡ ይታያችሁ! … ይህቺ ሴት ያሰበችው ካንገት በላይ ባለው አእምሮ ነው ወይስ ከወገብ በታች ባለው ሥጋ? … ወዳጄ በጣም አዘነ፡፡

እኔ እንደርሱ ጡንቻ ባይኖረኝም አንዳንዴ እርጉዝ ሴቶች ሲኖሩ የምጠላውን ግፊያ አይኔን ጨፍኜ ባልጋፋም ሾልኬ አስገባቸውና ወርጄ ታክሲ እጠብቃለሁ፡፡ ይህንን የማደርገው ሕሊናዬ ስለሚረካ ነው፡፡ ምናልባትም እህቶቼ ስለሚታዩኝ! …ከዚህም ሌላ በዕድሜ ቢያንሱኝም ታክሲ ውስጥ ባብዛኛው ሴቶች በፀሐይ ወገን እንዳይቀመጡ ራሴ በፀሐዩ በኩል እሆናለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ (አልፎ አልፎ ካልሆነ) በደግ አይተረጉሙትምና አሮጊት ካልሆኑ ይህንን ማድረጌን ትቻለሁ፡፡ እርጉዝ ሴቶች ከሆኑ ግን ለክፉም ያስቡናል ስለማይሉ ቅንነት አይባቸዋለሁ፡፡ ባላይባቸውም ወደፊትም ይህንን በጐነት አደርጋለሁ! ብዬ አስባለሁ፡፡

ታዲያ ስንት ውበት ያላቸው የሔዋን ልጆች ለምን እንደዚህ ሆኑ? አልልም፡፡ ምክንያቱም ወንዶችም የበዛ ኮተት አለብንና! ግን ሁላችንም አንድ አይደለንም፤ ያለ ፆታዊ ምላሽና ሌላ ፍላጐት ለሴቶች ደግ ነገር ማድረግ የምንወድ፣ ለሴቶች የምንሳሳ፣ የምንሟገት ወንዶች እንዳለን ሴቶቹ ሊያውቁልን የሚገባ ይመሥለኛል፡፡ በወንዶች ለሚፈፀምባቸው ማንኛውም ጫና ዕገዛ ለማድረግ እናስፈልጋቸዋለን ብዬ አምናለሁ፡፡ እነርሱ ለእኛ እህት እናትና ሚስት እንደሆኑ ሁሉ እኛም ለእነርሱ ወንድም፣ አባት እና  ባል መሆናችን ሊዘነጋ አይገባም፡፡

ቀደም ሲል በጅማሬዬ ካነበብኳቸው ታሪኮች የሴቶችን ሠናይነት እንደተናገርኩ ሁሉ  ከዚህ በተቃራኒ የቆሙ ወንዶች የሚሉትን ደግሞ በጥቂቱ ብናይ የሚል ምኞት አለኝ፡፡ ምናልባትም አንዳንዶቹ አባባሎች ከዚህ በፊት ስለ ሴቶች ከማውቀው ውጭ የሆነ አገር ስላሣየኝ ሴት ወገኖቼ አንዳች ነገር በእውነተኛ ቅንነት ፅፈው ቢያረጋጉኝ ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም ያስደነብራልና! ደንብረህ ቅር ካሉኝም ራሴን የማሥርበት ገመድ አላጣም!

ለምሣሌ ፍሬዴሪክ ኒች የተናገረውን ነገር ከመጽሔት ላይ ሳነብብ እንዴት? በሚል ጠይቄያለሁ፡፡ እንዲህ ነበር ያለው “ስለ ሴቶች እውነተኛውን ነገር የምናገረው አንድ እግሬ መቃብር ውስጥ ሲገባ ነው!” ይህንን ሲል ካልሞትኩ በስተቀር ምን ቆርጦኝ? ብሎ ፍርሀቱን መግለጡ ነው፡፡

ይህ የኒች ንግግር ሚስቱ ማታ ማታ የምትደበድበው ባል “እኔ የመታሁሽ እንዲመሥል እባክሽ ጩሂ!” ያለውን ያስታውሰናል፡፡

ሌላው ሊዮ አን ቶልስቶይ ነው፡፡ የቶልስቶይ ሚስት በቅናት ያበደችና የባልዋን ግንባር በሽጉጥ ለማፍረስ የምትቋምጥ ነበረች፡፡ ታዲያ ቶልስቶይ ከኒች በባሰ እንዲህ ብሏል፤ “ስለሴት እውነቱን ለመናገር ወደ ሬሣ ሣጥኔ ዘልዬ እገባለሁ፡፡ የሳጥኑን ክዳን ከዘጋሁ በኋላ ካሁን በኋላ የፈለግሽውን ማድረግ ትችያለሽ እላለሁ፡፡…”

ይሁን እንጂ የቶልስቶይ ሴት ልጅ ደግሞ ነፍሱ ነበረች፡፡ … ወንድ ልጁ ሲያላግጥበት እምባ እየረጨች ከቤት ሲወጣ የተከተለችው እርሷ ሔዋንዋ ናት፡፡

በሕይወት ዘመኔ በታሪክ ላይ ከማውቃቸው ሴቶች እንደ ሜሪ ቶድ የምትገርመኝ ሴት የለችም፡፡ ወፈፌ ናት፡፡ አስቸጋሪና አዋራጅ ናት፡፡ የገሀነም ማንፀሪያ መሆንዋንም ብዙ ሰዎች ፅፈዋል፡፡ ባልዋን በቢላዋ ያባረረች፤ ቡና ፊቱ ላይ የደፋች፤ በሰዎች ፊት የምትሣደብ፣ ዋይት ሀውስ እየገባች በባለሥልጣኖች ፊት የምታንጓጥጠው ሴት ነበረች፡፡ የሚገርመው ግን የእርሷ እሳትነት ብቻ አይደለም - የሊንከን በረዶነት ነው፡፡ ያንን ሁሉ ስታደርግ አንድም ቀን ስለርሷ ክፉ ተናግሮ አያውቅም፡፡ በሁለተኛ ዙር ምርጫ ውድድር እንኳ የተበደረችው ገንዘብ ቢታወቅ የተቃዋሚዎቹ ማላገጫ ልታደርገው ነበር፡፡ ፈጣሪ አዳነው፡፡ እዚህ ቦታ ሊንከን አሜሪካን ሲገዛ እርሷ ሊንከንን ገዝታለች፡፡

የዳዊት ፀጋዬ ግጥም ለእነቶልስቶይ የምትወግን ትመሥላለች፡፡ እንዲህ፡-

“አምላኬ ሆይ!

የሰጠኸኝ ሴት

ወደብ አልሆን ብላ፤

ነፍስና መንፈሴ፣

ሥጋዬም ተጉላላ፤

ወተት ሁኚ ብላት

ሆነችብኝ ውጋት፣

ብሎ ቢያሳቅላት፣

አምላክ መለሰለት፡፡

“ታዲያ ይህቺ ሴት

ምንድነው ስህተቷ?

ምንድነው ጥፋቷ?

ቀድሞም አጥንት ናት

መዋጋት ነው መብቷ!”

እናት ወላጅ ስትሆን የምታደርገውን በጐነት ሣሥብ፣ ልጅሽ ደደብ ነው ወደ ቤት ይዘሽ ሂጂ የተባለችው የቶማስ ኤዲሰን እናት ትዝ ትለኛለች፡፡ ቆፍጣና ሴት ነበረች፡፡ እናም “ልጄ ደደብ አይደለም” ብላ አምጥታ ፊደል አሥቆጥራ ወገብዋን ታጥቃ አስተምራ፣ ለዓለም ኮከብ ያደረገችውና የኮከቡ ብርሃን ተጠቃሚ ያደረገችን እርሷ ናት፡፡ እርሷ ደግሞ ሴት ናት!

ሌላ የሚያሣዝነኝ ሰው አለ፡፡ እርሱም ታላቅ ሰው ነው፡፡ ሉድ ዊንግ ቤትሆቨን! … የሙዚቃ ቀማሪ ታላቅ ጠቢብ ነው፡፡ ግና ወላጅ አባቱ ሰካራምና ከልጆቹ ጉሮሮ  እየነጠቀ የሚጠጣ ስለነበር በልጅነት ወንድሞቹን እንጀራ ለማብላት ፒያኖ ለመጫወት ያለ ጊዜው ወጥቶ ነበር፡፡ ይህም ወንድ ነው፣ አባት ነው፡፡ ግን … ሚስቱን “የሴት ነገር!” ብሎ ያማርር ይሆናል፡፡ ታዲያ ወዳጆች ሆይ፤ ሴት ሁሉ የዋህ ርግብ፣ ወይም ተናዳፊ እባብ ናት ማለት ይቻል ይሆን? … ወይንስ? … ወንድ በሴት የተጠቃ፣ ለሚስቱ አንገቱን የደፋ ነው? …

ወደ ማጠቃለያ ለመምጣት የሜሮን ጌትነት አሽሟጣጭ ግጥም ልውሰድ መሠለኝ፡፡ ሜሪ እንዲህ ትላለች፡-

“ባልና ሚስት ከአንድ ባህር ይቀዳሉ ብሎ

ተመሳስሎን ወ’ዶ

ልዩነት አጉድሎ

እኔ ካለሁበት ጨው - አልባ ባህር ላይ

እሱም ተጨልፎ

እንኖረው ጀመር

ጣዕም ያጣ ሕይወት

በማር አልባ ቀፎ!!

የሜሮን ሽሙጥ አንድ አይነት ነን አትበሉ፡፡ እንለያያለን የሚል ድምፀት አለው፡፡ በልዩነት ግን አንድነት! … ልዩነት ቢኖርም ግን ተከባብረን ተፋቅረን መኖር እንችላለን፡፡ ሴቶች ባሎቻችሁን ለቀቅ አድርጉ! ወንዶች የሚስቶቻችሁን ሥጋ አትብሉ እላለሁ! መደምደሚያዬንም አንድ አሜሪካዊ የነገረ መለኮት መምህር በተናገሩት ሀሣብ አደርጋለሁ፡፡ “እግዚአብሔር ሔዋንን ሲፈጥር እንድትረግጠው ከጭንቅላቱ፣ ወይም አዳም እንዲረግጣት ከእግሩ ሥር አልፈጠራትም፡፡ ይልቅስ የልቡ እንዲያደርጋት ከልቡ ጐን ከአጥንቱ ሠራት እንጂ”

 

 

 

Read 2243 times Last modified on Saturday, 12 May 2012 10:41