Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 May 2012 10:37

“እንጀራ በአቋሯጭ…”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ክረምቱ አንደኛውን መግባቱ ነው እንዴ! ኧረ ትንሽ ብልጭ ይበልልን! ብዙ ነገር እኮ ‘ትንሽ ብልጭ’ አልልን ብሎ ነው የተቸገርነው፡፡ስሙኝማ…ይሄ የ‘አቋራጭ’ ነገር እኮ ‘በይ’ና ‘የበይ ተመልካች’ እያደረግን ነው! አብዛኛው ሰው ቀጥተኛውንና የቀለበት መንገዱን ተከትሎ ሲሄድ፣ የዘመኑ ጨዋታ ህጎች የገባው ደግሞ በውስጥ ለውስጥ ‘አቋራጭ መንገድ’ እያጦፈው…አለ አይደል… ነገርዬው ሁሉ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡እናላችሁ… ኮሚክ ነገር ነው፡፡ አርባ ምናምን ኪሎ ሜትር ማራቶኑን  እኩል ትጀምራላችሁ፡፡ ነጭ ላብ እስኪያልባችሁ ሮጣችሁ በ‘ጥሩ ሰዓት’ መጨረሻው ትደርሳላችሁ፡፡ ምን ይሆናል መሰላችሁ… ሪባኑ ቀድሞ ተበጥሷል! ያውም በደቂቃዎች! አንዳንዴማ… አይደለም አብሯችሁ መነሻው መስመር ላይ ሊገኝ፣ ተመልካች መሀል ያልነበረ ሰው “ስታንድ አፕ ፎር ዘ ሻምፒዮን” ሲዘፈንለት ታገኛላችሁ፡፡

እናማ አስቸጋሪ ነው…ልምምድ የለ፣ ምን የለ… ከመጨለጫው ቤት በቀጥታ ወደ አሸናፊ ሳጥን የምንወጣ እየበዛን ስንመጣ… “ኧረ እንዴት ነው ነገሩ!” ማለት አሪፍ ነው፡፡

‘ቦተሊከኛ’ መሆን ለአቋራጭ እንዴት አሪፍ መሰላችሁ! ልክ ነዋ… በአንዱ ወገን ሲሆኑ ቪታራ፣ በሌላ ወገን ሲሆኑ ቪዛ በ‘አቋራጭ’ ይገኛላ!  ምን ችግር አለው… በኋላ ነገርዬው አልሆን ካለ ‘ሂስን መዋጥ’ ነው፡፡ (እኔ የምለው…ሂስና ግለ ሂስ ምናምን የሚሉት ነገር ምነው ከዲክሺነሪ ጠፋሳ! ‘ዋጩ’ ነው የጠፋው ‘አስዋጩ!’ ቂ…ቂ…ቂ…) “ልጆቼን ላሳድግ ብዬ ነው እንጂ ፖለቲካውን አምኜበት አይደለም፡፡” “እኔ የአሜሪካ ቪዛ ታገኛለህ ስላሉኝ ነው እንጂ ፖለቲካ ውስጥ የለሁበትም…” ምናምን ማለት ይቻላል፡፡

“በሁለት ወር እንግሊዝኛ አቀላጥፈው እንዲናገሩ እናደርጋለን…” ምናምን የሚል ማስታወቂያ አያስደነቃችሁም! ይሄን የመሰለ ጥበብ እኮ፣ አይደለም እኛ፣ እነ ዩ.ሲ.ኤል.ኤ. ቢያገኙትም አይጠሉም፡፡ አሥራ ምናምን ዓመት ቀን ተሌት ተለፍቶ አልሳካ ያለ ነገር በሁለት ወር! የምር “ውሻና ሚዷቋ አብረው ኖሩ…” ምናምን ከማለት ይልቅ… የእውነት ‘ድንቃ ድንቅ’ ማለት በሁለት ወር የ‘ፈረንጅ አፍ’!

ስሙኝማ… መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…‘ቦትልድ ወተር’ ምናምን መያዝ እኮ የሰውነትን የውሀ ‘ባላንስ’ የመጠበቅ ሳይሆን… አለ አይደል… በአቋራጭ ስልጡን የመምስል አይነት ነገር ሆኗል፡፡ በአቋራጭ ‘ሞደርን’ ለመሆን በሚደረገው ጥረት ስንት ኮሚክ ነገር ይታይ መሰላችሁ! እውቀትና፣ የአእምሮ መጎልበት ዋና መለኪያዎች መሆናቸው ቀርቶ ነገርየው ሁሉ በ‘አሳባሪ መንገድ’ ሲሆን በቋፍ ያለች ተስፋችንን ጭራሽ እንዳያወድማት መስጋት ነው፡፡

እናላችሁ… ሁሉም ነገር ‘አቋራጭ’ ሆኖ ለእውቀት የሚጓጓ ትውልድ፣ በ‘ግንባሩ ወዝ’ ለመብላት የሚታትር ትውልድ መገንባት ካልተቻለ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ነገ እየተረሳ ሁሉም ነገር “እዛው ፈላ እዛው ሞላ” ሲሆን ነገራችን ሁሉ እንደምናያቸው ‘ልብ ወለድ ተች ዶኪዩሜንተሪ’ ፊልሞች ሆኖ ይቀራል፡፡

ዋናው ነገር ምን መሰላችሁ… ‘የኔትወርክ ጉዳይ፡፡’ አዎ… ‘ኔትወርክ’ አዘረጋጉን የሚያውቁበት አቋራጯን አገኟት ማለት ነው! “እንትን መሥሪያ ቤት የምታውቀው ሰው አለህ?” ምናምን እያልን ደጅ የምንጠናው እኮ ‘ኔትወርክ’ አዘረጋጉን ስለማናውቅበት ነው፡፡

የምር እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ለሌላው እንደ ጂብራለታር ቋጥኝ አልንቀሳቀስ ያለውን ሁሉ በቀላሉ እንደ ሚጢጢ ጠጠር ገፋ ማድረግ የምትችሉት ነገርዬው እንዴት ነው! ልክ ነዋ… የምትጠቀሙበትን ‘ሰርቨር’ አይነት ንገሩንና እኛም ከእፍታው ባናገኝ እንኳን ከ‘ድስት ጥራጊዋ’ ይድረሰና! አሀ… “መረቋንም ደረቋንም ለእኛ…” ማለት አሪፍ አይደለማ!

እናላችሁ… አንዳንዱ ሰው ቀላል አቆራርጦ ይሄዳል እንዴ! እኛ “ዳይል አፕ አልከፍት አለን…” “ሲ.ዲ.ኤም.ኤ. ተንቀረፈፍብን…” ምናምን ስንል ሰዉ ምን አይነቱን ‘ብሮድባንድ’ ቢጠቀም ነው እንዲህ የመከፈት፣ የመንቀርፈፍ ችግር የማይገጥመው አያሰኛችሁም! ግራ ገባና!

እኔ የምለው…ዘንድሮ ዲታነት በአቋራጭ ሆኗላችኋል፡፡ ልክ ነዋ… የዛሬ ዓመት “ለሳሙና ብር አበድረኝ…” ሲል የነበረው ዛሬ በሌክስስ ‘ውሀ ረጭቶባችሁ’ ሲያልፍ…ከዚህ የባሰ ‘ሾርት ከት’ ከየት ይመጣል! (እነ እንትና… ኽረ ብላክ ሌብሉን እንዲህ አትጨልጡት! በኋላ፣ አምና “አረፋውም ቢሆን ተከፍሎበታል…” እያላችሁ የጨለጣችሁት ድራፍት ጡር ጉድ እንዳያደርጋችሁማ!

እናማ… የድሮ ዲታነት እኮ “ቄጤማ ስሸጥ ኖሬ…”  “የቡና ቤት አሳላፊ ሆኜ…” ምናምን የሚባልበት ነበር፡፡ ዘንድሮ ዋናው የተሮጠበት መንገድ ሳይሆን የሪባኑ መበጠስ ነው፡፡ (“አዲስ የአቋራጭ ሀብታምን ለማወቅ የውስኪ ብርጭቆ አያያዙን ተመልከቱ…” ያልከን ወዳጃችን… ውስኪ ማለት ምን ማለት ነው! ቂ…ቂ…ቂ…)

እናማ…ዘንድሮ ሩጫው መጀመሪያ መስመር ላይ ያልነበረው ሁሉ ሜዳሊያ ሳጥኑ ላይ ወጥቶ እጆቹን ሲያውለበልብ…አለ አይደል…“እኔ ወደ ኋላ ቀርቼ ነው ወይስ እነሱ ጥለውኝ ሄደው ነው!” ምናምን ነገር ያሰኛችኋል፡፡

ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ድሮ እንትናዬ ለማግኘት… አለ አይደል… የምትመላለስበት አውቶብስ የሚቆምበት ፌርማታ ላይ መቆም፣ እሷ መኖሯ ከታወቀ የማያውቁት ሰው ተዝካር መሄድ ምናምን አይነት ዘመቻ ነበር፡፡ አይደለም እንደ ዛሬ ‘ከመቀመጥ መጋደም’ በቀለለበት ዘመን… በአራዶቹ ቋንቋ… ‘ኪሲንግ ለማጦፍ’ እንኳን ስለት ቢጤ አይጠፋም ነበር!

ስሙኝማ…ካነሳነው አይቀር ይቺን ስሙኝማ፡፡ ሰውየው አንዷን የእኔ ቢጤ ሞኝ የሆነች ምን ይላታል መሰላችሁ… “እንወራረድ፣ እንዲች አድርጌ ጫፍሽን ሳልነካሽ ልስምሽ እችላለሁ፡፡” እሷም ሆዬ “እሺ እንወራረድ፣” ትልና በአምስት ብር ይወራረዳሉ፡፡ እሱም ግጥም አድርጎ አቅፎ ደጋግሞ ይስማትና ሲበቃው ይለቃታል፡፡ እሷም “ይኸው ነክተኸኝ አይደል የሳምከኝ!” ስትለው ምን አለ መሰላችሁ… “በቃ ውርርዱን ተሸንፌያለሁ፡፡ ያውልሽ የበላሽው አምስት ብር…” ብሎ ሰጥቷት ሄደ፡፡ በልመና ያልሆነ በአምስት ብር ውርርድ! (እንትናዬ ሦስት ብር ከሽልንግ አለኝማ…!)

ሌላ ደግሞ… አንዱ ለጓደኛው ምን ይለዋል፣ “እንትና እኮ ሚስቱ ከሳመችው አሥር ዓመት ሆኖታል፡፡” ጓደኝየው ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ… “ባሏ ወይ በህይወት የለም፣ ወይም በስሟ የባንክ ደብተር አላት ማለት ነው፡፡” እና ሚስቶች ባሎቻቸውን የሚስሙት ፍራንክ ሲፈልጉ ብቻ ነው ለማለት ነው! እስቲ በዚህ ጉዳይ ላይ ያላችሁን አስተያየት ኤስ.ኤም.ኤስ. አድርጉልን፡፡ (ማን ከማን ያንሳል!)

እናላችሁ የዘንድሮ ‘አቋራጭ’ መንገድ የጨዋታው ህግ ለገባቸው መአት ነው! እንትናዬን ለማግኘት ‘ፊሲቢሊቲ ስተዲ’  ‘ቴክኒካል ፕሮፖዛል’ ምናምን  አይነት  ቀርቷል፡፡ የአቋራጭ ዘመን ነዋ!  ልጄ ዘንድሮ አብዛኛውን ነገር ‘ሴም ዴይ ሰርቪስ’ ሆኗል፡፡ ነገርዬው… ‘አድሮ ሲነጋ ምን እንደሚፈጠር ይታወቃል!’ አይነት ስለሆነ…ባለሱቆቹ…እጅ በእጅ ሽያጭ የሚሉት አይነት ነው..

ሌላ ደግሞ…በ‘አቋራጭ’ ቀለባችንን የምናሟላ አለንላችሁ፡፡ ሰርግ አይቀረን፣ ሰንበቴ አይቀረን፣ አድባር አይቀረን…ብቻ የሚታኘክ፣ የሚዋጥ ያለበት ቦታ ሁሉ ከች ነው፡፡ ልጄ… ቀላል በጀት መደጎሚያ ‘አቋራጭ’ ነው እንዴ!

ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ዝናቡን እኛ ብንወደውም የውጪ ሠርጎችን አበላሸሳ! እናማ… የሠርግ ነገር ካነሳን… አለ አይደል… በነጻ የምንበላ ይመስለናል እንጂ ‘በአይነት’ እኮ እንከፍላለን፡፡ ልክ ነዋ… “እየበሉ እየጠጡ ዝም የጋን ወንድም…” ማለት “የበላችሁባትን ቁጭ አድርጓት ማለትም አይደል!”

ለነገሩማ… እኛም ሠርግ እየበላን ለከርሞ ሪዘርቭ እናስይዛለን፡፡ ለበላንበት ካጨበጨብን በኋላ… አለ አይደል… “ለክርስትና እንመጣለን ገና…” ምናምን እያልን ‘እንዳትረሱን’ አይነት መልእክት እናስተላልፋለን፡፡ ለነገሩ…ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…ከተጋባዡ ዘጠኝ አሥረኛው አፉ እንደ ደረቀ “እየበሉ እየጠጡ ዝም…” አይነት ነገር የሆነ ስታንድ አፕ ኮሜዲ ይመስላል፡፡ ግጥሞቹ ይከለሱልንማ!

ስሙኝማ… አዲስ ተዋናይ ነው አሉ፡፡ እናላችሁ… የመጀመሪያውን ቀን መድረክ ላይ ከወጣ በኋላ ጓደኛውን “አጅሬ አየኸኝ አይደል! ያውም እኮ በመጀመሪያው ትዕይንት በጥይት ተመትቼ ባልሞት ኖሮ ጉድ ነበር የማሳየው፡፡ አንተ እንዳየኸኝ እንዴት ነበርኩ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኛው ምን ብሎ መለሰለት መሰላችሁ… “በአንደኛው ትዕይንት ከምትሞት ይልቅ ትያትሩ ከመጀመሩ ፊት ብትሞት ይሻልህ ነበር፡፡” “ባይበላስ ቢቀር…” ብሎ ተዋናይነት መተው ይሄኔ ነው!የትወናን ነገር ካነሳን አይቀር… እንደምንሰማው በተለይ ለእንትናዬዎች የ‘ፊልም ስታር’ነት በአቋራጭ ሆኗል አሉ፡፡ እናማ… “ዳይሬክተሩ እንዴት ካስት አደረገሽ?” ሲባል መልሱ… “በቃ፣ ድርሻውን ወስዷሏ!” ሆኗል አሉ፡፡ ታዲያማ…ፊልም ላይ ለምናየው ቅሽምና የ‘አቋራጭ’ ምልመላ እንዳለ ልብ ይባልልንማ! (ጭራሽ ወደ ‘ድርሻ’ ወረደና አረፈው!)

እናላችሁ…በፊት “እንጀራ በአቋሯጭ በምላስ በሰለ…” ምናምን የሚል ግጥም ነበር፡፡ ልጄ አሁን ግሎባላይዜሽን፣ ፌስቡክ፡ ፓልቶክ…ምናምን የሚሏቸው ነገሮች መጡና ምላስ ሥራው ቀሎለታል፡፡እነ እንትና… እንዲህ ነገሩ ሁሉ የሚሳካላችሁ… ‘ሰተላይት ፎን’ ምናምን ነው እንዴ የምትጠቀሙት?

እስቲ ‘አላፊ አግዳሚ’ መስዬ የውስኪውን ብርጭቆ እንደ ጃምቦ ድራፍት ብርጭቆ የሚይዙትን ሰዎች ልመልከትማ!

ደህና ሰንበቱልኝማ!

 

 

 

Read 2575 times Last modified on Saturday, 12 May 2012 10:41