Saturday, 12 May 2012 10:45

ማን ያስታምመኛል ብሎ ጭንቀት ቀረ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ገጠር የሚኖሩት አባትዎ ወይም እናትዎ አሊያም ወንድምና እህት ወይም በጣም የሚወዱትና የሚቀርቡት ሰው (ዘመድ) በጠና ስለታመመ እርስዎ ጋ አርፎ ለመታከም መጥቷል እንበል፡፡ እርስዎም ሆኑ ባለቤትዎ በምትሠሩበት መ/ቤት ባላችሁ ኃላፊነት ሥራ በጣም ይበዛባችኋል እንበል፡፡ ወይም ደግሞ በምትመሩት የግል ቢዝነስ ባለው የሥራ ውጥረት ትንሽ ዞር ስትሉ ብዙ ነገር ይበላሽ ይሆናል፤ ማን እንደባለቤት! ልጆች እንኳ እንዳይተኩ ት/ቤት የሚውሉ ትናንሽ ልጆች ናቸው፡፡ ምንም እንኳ ያለዎት ጊዜ በጣም የተጣበበ ቢሆንም፤ ወላጅና የቅርብ ዘመድ ታሞ ሲመጣ ማሳከም ኢትዮጵያዊ ግዴታ ስለሆነ እንደምንም ብለው ታማሚውን ሆስፒታል ወስዶ ማስመርመር ያለና የሚገባም ነወ፡፡ ሐኪሞቹ የምርመራ ውጤቱን አይተው በአስቸኳይ ተኝተው እንዲታከሙ አዘዙ፡፡

ይኼኔ ነው እንግዲህ ጭንቁ፡፡ ሕመምተኛው ሆስፒታል ሲተኛ አጠገቡ ሆኖ የሚያስታምመው ሰው የግድ ያስፈልገዋል፡፡ እርስዎም ሆኑ ባለቤትዎ ረዥም ፈቃድ ወስደው ማስታመም አትችሉም፡፡ “እገሌ ያስታምምልኛል” የሚሉት ቤተሰብም ሆነ ጓደኛ የለዎትም አንበል፡፡ ታዲያ ምን ተሻለዎት?

በቅርቡ ቤተሰብን ተክቶ በሠለኑ ባለሙያዎች በሽተኛውን የሚያስታምም “ቤተሰብ የአስታማሚዎች ማዕከል” የተሰኘ ድርጅት ተቋቀሟል፡፡ አቶ አምባቸው አራጌ፤ እህቱ ታማ ሆስፒታል በተኛችበት በ1998 ዓ.ም የቤተሰቡ የኢኮኖሚ አቅም ደካማ ስለነበር ቀን እየሠራ፣ ማታ ኮሌጅ ማርኬቲንግ ይማር ነበር፡፡ ወንድምና እህቶቹ  ትናንሽና ተማሪ ስለነበሩ እህቱን የማስታመም ኃላፊነት በእሱ ላይ ወደቀ፡፡ ስለዚህ ብዙ ጊዜ ከሥራና ከትምህርት ይቀር እንደነበር ያስታውሳል፡፡ “እህቴን ለማስታመም ነው የቀረሁት” ሲል ሰዎች እንደማያምኑት የገለጸው አምባቸው፤ “እንዲህ ያለ ችግር ሲያጋጥም ምናለ ገንዘብ እየተከፈለው የሚያስታምም ሰው ቢኖር” እያለ ማሰብ መጀመሩን ይናገራል፡፡

ከዚያ በኋላ በሐሳቡ ዙሪያ ከባለሙያዎች ጋር ሲመካከር፣ መጻሕፍት ሲያገላብጥ፣ ኢንተርኔት ሲፈትሽ ቆይቶ፣ ሐሳቡን ካዳበረና መስመር ካስያዘ በኋላ ፕሮጄክት ቀርፆና ፈቃድ አውጥቶ በዚህ ዓመት አጋማሽ ወደተግባር እንደገባ ገልጿል፡፡

ድርጅቱ (ቤተሰብ የአስታማሚዎች ማዕከል) ምን አገልግሎት ነው የሚሰጠው?

በመንግሥትም ሆነ በግል ሆስፒታሎች እንዲሁም ቤት ለቤት እየተዘዋወረ በሠለጠኑ ባለሙያዎች በሽተኞችን ማስታመምና ቀልጣፋና አስተማማኝ የ24 ሰዓት የእንክብካቤ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡

የሠለጠኑ ባለሙያዎች ስትል እነማን ናቸው?

ነርሶችና በጤና ኤክስቴንሽን ሙያ የሠለጠኑ ባለሙያዎች ማለቴ ነው፡፡ ሕመምተኛው የመክፈል አቅም ካለውና “ነርስ እፈልጋለሁ” ካለ ነርስ፤ አቅሙ ደከም ካለ ደግሞ የጤና ኤክስቴንሽን ይመደብለታል፡፡ ቀን አንድ ሌሊት ደግሞ ሌላ አስታማሚ ተመድቦለት፣ የ24 ሰዓት አገልግሎት ይሰጠዋል፡፡

አንድ ሰው ታሞ ረዥም ጊዜ ሆስፒታል ሲተኛ የቤተሰብ አባላት የሚያስታምሙት ከትምህርት፣ ከሥራ ፣…እየቀሩ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ታማሚ ደግሞ አስታማሚ ቤተሰብ ላይኖረው ይችላል፡፡ ከቤተሰብ አባላት ሰው ሲታመም ተማሪው፣ ይማር ሠራተኛውም ይሥራ፡፡ እኛ እነሱን ተክተን እናስታምማለን፡፡ አስታማሚ የሌለውንም ጥሩ ቤተሰብ ሆነን እንንከባከበዋለን፡፡

አንዳንድ ሕሙማን ደግሞ ከሆስፒታል ወጥተው ቤት ከገቡ በኋላ፣ ብዙ ጊዜ አልጋ ላይ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ቤተሰብ ሊሰላች፣ አስታማሚ ሊጠፋና ችግር ሊከሰት ይችላል፡፡ እኛ የዚህ ዓይነቱን ክፍተት ሸፍነን እንሠራለን፡፡

የእናንተ አስታማሚዎች ስለሚሰለቹ እንደቤተሰብ የሚሆኑ አይመስለኝም

እንደሱ አይደለም፡፡ የቤተሰብ አስታማሚነት የውዴታ ግዴታ ስለሆነ በሽተኛ ብዙ ጊዜ አልጋ ላይ ሲቆይ በተለያዩ ምክንያቶች ሊሰለች ይችላል፡፡ የእኛ አስታማሚዎች አንደኛ ገንዘብ ተከፍሏቸው ነው የሚሠሩት - ልክ እንደማንኛውም ሥራ፡፡ ሁለተኛ የሕክምና ሙያ ተምረው ሲመረቁ፣ በሽተኛን ሳይፀየፉና ሳይሰለቹ ያለ አድልዎ፣ በሐቅ ለማገልገል ቃል ገብተው ነው የሚመረቁት፡፡ ያ የሥራ ሥነ ምግባር ስላላ ሳይሰለቹ በቅንነት ያገለግላሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ታካሚው አገልግሎቱ የሚሰጠው በነፃ አይደለም ከፍሎ ነው፡፡ ስለዚህ ያልተመቸውና ያልተስማማው ነገር ካለ ተናግሮ እንዲስተካከልለት ማድረግ ይችላል፡፡ አስታማሚዋ ደሞዝ የሚከፈላት ደንበኛችንን በደንብ ስትንከባከብ ስለሆነ ጥፋት ከሠራች ስህተቷን እንድታርም ትደረጋለች፤ ካልሆነም ከፍ ያለ ቅጣት እንደሚጠብቃት ስለምታውቅ የተጠቀሰው ስጋት አይኖርም፡፡

በሆስፒታልም ሆነ ቤት ለቤት አስተማሚዎች ምንድነው የሚሰጡት አገልግሎት?

በሐኪም የሚሰጡ ትዕዛዞችን እናስፈፅማለን፡፡ ለምሳሌ ለተለያዩ ሕመሞች የተለያዩ መድኃኒቶች ይታዘዛሉ፡፡ እነዚያ መድኃኒቶች በሽተኛው እንደታዘዘለት፣ ከምግብ በፊትና በኋላ፣ በተባለው ሰዓትና መጠን እንዲወስድ እናደርጋለን፡፡ ምግቡንም እንደዚያው፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ ጠያቂዎች፣ ለበሽተኛው ከታዘዘው ምግብ ውጭ (ቅባት፣ ጨው፣ … የበዛበት ሊሆን ይችላል፣ እያመጡ በሽተኛውን ሲያጨናንቁ ይታያል፡፡ እኛ ይህን ችግር እናስቀራለን፡፡

ሌላው ደግሞ የሕመምተኛውን ንፅህና እንጠብቃለን፤ መፀዳጃ ቤት መሄድ የማይችል ከሆነ ዳይፐሩን እንቀይራለን፤ መራመድ የሚችል ከሆነ ደግፈን ሽንት ቤት እንወስዳለን፣ ገላውን ማጠብ፣ ፀጉሩን ማበጠር፣ አልጋ ማንጠፍ፣ … ልክ እንደስሙ፣ ከቤተሰብ የበለጠ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡

ለምን ያህል ባለሙያዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ማዕከሉ?

ሥራ ከጀመርን ቅርብ ጊዜ ቢሆንም ስምንት ቋሚ ሠራተኞች አሉን፡፡ ሌሎቹ አገልግሎት ፈላጊው ሲደውልልን የምንጠራቸውና በኮንትራት የሚሠሩ ናቸው፡፡

ወደፊት ይህ አገልግሎት በኅብረተሰቡ ዘንድ በደንብ ሲለመድ የአገልግሎት ጥራቱ ከፍ እንዲል የሚጠይቁ ሰዎች እንደሚመጡ እርግጠኞች ነን፡፡ በሠለጠነ የሰው ኃይል በኩል ችግር አይገጥመንም፡፡ ምክንያቱም ከተለያዩ የጤና ተቋማትና የጤና ኮሌጆች ተመርቀው ያለ ሥራ የተቀመጡ ስላሉ፣ እነሱን ለመጠቀም ከአንዳንድ የጤና ኮሌጆች ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡

ዋጋችሁ እንዴት ነው?  መቼም ውድ መሆን አለበት፡፡

ኧረ አይደለም፤ ከምንሰጠው አገልግሎት አንፃር በጣም ቀላል ነው፡፡ ለአንድ በሽተኛ ከአጠገቡ የማትለይ ቀን አንድ ሌሊት ሌላ፣ በአጠቃላይ ለ24 ሰዓት ሁለት አስታማሚ መድበን የምናስከፍለው ዋጋ ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የማይባልና የኅብረተሰቡን አቅም ያገናዘበ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

አሁን ቤት ለቤት ሄዳችሁ የምታስታምሙት ሰው አለ?

በሆስፒታልም በቤትም ያስታመምናቸው አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአሜሪካ የመጣች ሴት ቤቷ ሄደን እያስታመምን ነው፡፡ አካሏ ፓራላይዝ ስላደረገ እንደልቧ መንቀሳቀስ አትችልም፡፡ ቤት ውስጥ ደግሞ በተለያየ ምክንያት አስታማሚ አልነበራትም፡፡ ገንዘብ ስላላት፣ ይህን አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት መኖሩን ስለሰማች ጠራችን፤ ሄደን እያስታመምናት ነው፡፡

ኅብረተሰቡ የሚሰጣችሁ ምላሽ ምን ይመስላል?

በጣም ጥሩ ነው፡፡ ትላልቅ ሰዎችና ባለሥልጣናት ሳይቀሩ እየደወሉ እስካሁን ያልተዳሰሰ ትልቅ ክፍተት ነው ያገኛችሁት በርቱ! ይሉናል፡፡ አንድ ሰው በቁጭት፣ “እንደዚህ ዓይነት አገልግሎት ቢኖር ኖሮ፣ እህቴ አስታማሚ አጥታ አትሞትም ነበር” በማለት አበረታተውናል፡፡

አገልግሎቱን ለማስተዋወቅ ምን እየሠራችሁ ነው?

በአንዳንድ ኤፍ ኤም ራዲዮኖችና ጋዜጦች ኢንተርቪው ሰጥቻለሁ፡፡ አሁን ደግሞ በየሆስፒታሉ ካሉ ሐኪሞችና ነርሶች ጋር ለመሥራት እያነጋገርናቸው ነው፡፡ አንዳንዶቹ “ይህማ ሆስፒታሉንም የሚያግዝ ነው፡፡ ያልሠለጠነ አስታማሚ ምን ማድረግ እንዳለበት እንኳ አያውቅም፡፡ ይህማ የሆስፒታሎችን ችግር የሚያቃልል ነው፡፡ …” ይሉናል፡፡

አንዳንድ የግል ሆስፒታሎች ደግሞ ዓላማችንን ባለመገንዘባቸው የእነሱን ሥራ የምንጋፋባቸው መስሏቸው ደስተኛ ያልሆኑ አሉ፡፡ ስለዚህ “እኛ በሽተኛ የምናስተኛበት ቦታ የለንም፡፡ ከእናንተ ጋር ነው የምንሠራው፡፡ ያለባችሁን የሠለጠነ የሰው ኃይል በመቅረፍ እናንተንም የሚጠቅም ነው፡፡ …” በማለት እያስረዳናቸው ነው፡፡

 

 

 

Read 3085 times Last modified on Saturday, 12 May 2012 11:29