Sunday, 14 October 2018 00:00

የፕሬዚዳንቱ ንግግር - በምሁራንና በፖለቲከኞች እይታ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

ባለፈው ሰኞ የ2011 የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ም/ቤት መክፈቻ ሥነ ስርዓት ላይ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፤
የመንግስት የትኩረት አመላካች ንግግር ላይ ምን አንኳር ጉዳዮች ተነሱ? በሚለውና ተያያዥ ጉዳዮች የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ
አለማየሁ አንበሴ ምሁራንና ፖለቲከኞችን አነጋግሯል፡፡

• ሁሉም የሚጋጩ ህልሞችን ይዞ ነው እየነጎደ ያለው
• ተስፋ የሚፈነጥቅና የሚያነሳሳ ንግግር አላደረጉም
• ወጣቱ ነፃነቱን ካገኘ በኋላ ጥያቄው የዳቦ ይሆናል      

 “የሚጋጩ ህልሞችን ይዘን መሄዱ አደጋ አለው”
ዶ/ር መረራ ጉዲና (የኦፌኮ ሊቀ መንበር)

     በዋናነት ትኩረት ይሰጠዋል ብዬ የጠበቅሁት የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ነበር፡፡ ነገር ግን ይሄን ከፕሬዚዳንቱ ንግግር ማግኘት አልቻልኩም፡፡ የሀገራችን ፖለቲካ ትልቁ ችግር፤ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ጋራ ስምምነት፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ወደ የጋራ አጀንዳ መቅረፅና ለውጡ የጋራ እንዲሆን በጋራ ወደ መምራት እየሄድን አይደለም፡፡
ኢህአዴግ በራሱ መንገድ የራሱን ማሻሻያዎች እያደረገ ነው፡፡ በተለይ ማሻሻያዎቹ ከብሔራዊ መግባባት ስምምነት የመነጩ አለመሆናቸው ደግሞ ሌላው ድክመት ነው። በተለይ የኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ ፈንታ ላይ፣ ቀጣይ ምርጫ ላይ፣ የፖለቲካ ኃይሎች እንዴት ተቻችለው አብረው ይንቀሳቀሳሉ፣ የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ በምን ፍጥነት ሊቀርፁ ይችላሉ---የሚሉት ጉዳዮች ቀን ተቆርጦላቸው ለውይይት መቅረብ አለባቸው።
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ላይ ካልደረስን፣ ሰፊ ችግር የሚጠብቀን ይመስለኛል፡፡
የምርጫ ህግ፣ የፀረ ሽብር ህግ የመሳሰሉትን ማሻሻል ከብሔራዊ መግባባት በኋላ በሚኖር የድርድር ሂደት ሊፈፀሙ የሚችሉ ናቸው፡፡ ከብሔራዊ መግባባት በኋላ ሊመጡ የሚገባቸው ናቸው፡፡ መጀመሪያ የሚያስፈልገው በሀገር፣ በታሪክ፣ በወደፊቱ ኢትዮጵያ ላይ ብሔራዊ መግባባት ነው፡፡
ብሔራዊ መግባባቱ ባለመኖሩ በአሁኑ ወቅት የተቋጠረ ነገር የለንም፤ አደጋው ይሄ ነው፡፡ በየቦታው የሚነሱ ግጭቶች መጥፎ አዝማሚያ ናቸው፡፡ በተወሰነ ደረጃ ብሔራዊ መግባባት በመጥፋቱ የሚመጡ ችግሮች እየታዩኝ ነው። ሁሉም የሚጋጩ ህልሞችን ይዞ ነው እየነጎደ ያለው፡፡ ሀገሪቱ እንደ ሀገር፣ ህዝቦቹ እንደ ህዝብ፣ የመቻቻል ፖለቲካን መፍጠር እንዴት እንችላለን? የሚለውን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ የሚጋጩ ህልሞችን ይዘን መሄዱ አደጋ አለው፡፡ ህልሞቹ ቢያንስ መቀራረብ አለባቸው፡፡
   
====================

“ትልቁ ትኩረት የምርጫው ጉዳይ መሆን አለበት”
ዶ/ር አለማየሁ ረዳ (ምሁርና የፖለቲካ ተንታኝ)

የፕሬዚዳንቱ አቅጣጫ ማመላከቻ ንግግር የኢህአዴግን ፍላጎት ያመላከተ ነው፡፡ ነገር ግን የኢህአዴግ ብቻ ነው ወይ አሁን ላለንበት ሁኔታ ወሳኝ የሚሆነው? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፣ አሁን ወደ ዲሞክራሲ የምንሸጋገርበት፣ ለውጦቹ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የሚካሄዱ ናቸው እየተባለ ነው፡፡ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የሚደረግ ማናቸውም ለውጥ መነሳት ያለበት ከዲሞክራሲ ተልዕኮ ነው፡፡ የዲሞክራሲ ዋነኛ ተልዕኮ ደግሞ ነፃነትንና እኩልነትን ተቋማዊ ማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም ነፃነትና እኩልነት በግለሰቦች በጎ ፍቃድ ልክ እየተሰፈረ አይደለም መሰጠት ያለበት፡፡
ፕሬዚዳንቱ ሲናገሩ የነበረው፤ ተቋም የሚለውን ነገር የሚገልፅ አልነበረም፡፡ ተቋም ማለት በመጀመሪያ አካሉ ሳይሆን ተቋሙ ራሱ የቆመበት ህግና ስርአት ማለት ነው፡፡ የድርጅቱ የአሰራር ባህል ዲሞክራሲያዊ መሆን አለበት፡፡ የሰው ኃይሉ ጉዳይ በሌላ በኩል አለ፡፡ ስለዚህ ሶስቱም ናቸው ተቋምን ተቋም የሚያደርጉት፡፡ ህግ እናሻሽላለን እንቀይራለን ተብሏል፡፡ ህግ ብቻውን መቀየሩ ግን ዋጋ የለውም። ለምሳሌ የንግድ ህጉ ይሻሻላል ተብሏል፡፡ በእርግጥ የንግድ ህጉ መቀየር ያለበት ነው፡፡ ነገር ግን በመጀመሪያ የንግድ ህጉን ለማሻሻል የኢህአዴግን የኢኮኖሚ ፖሊሲ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ፖሊሲውንና የንግድ ህጉን ማጣጣም እንዴት ነው የሚቻለው? ኢህአዴግ እኮ ርዕዮቱን እንኳ ገና አልወሰነም፡፡ ስለዚህ የንግድ ህጉን የሚያሻሽለው ቴክኒካዊ በሆነ መንገድ ነው ማለት ነው፡፡ የንግድ ህጉን ቴክኒካዊ በሆነ መንገድ ለማሻሻል ሲታቀድ፣ እነማን ናቸው የሚሳተፉት? የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ ይሄ ግልፅ መሆን አለበት፡፡ የንግድ ህጉም ሆነ ሌሎች ህጎች ይሻሻላሉ መባሉ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን የሚያሻሽለው አካል፣ አሁን ያለው ፓርላማስ ይሄን ለማድረግ ብቁ ነው ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምናልባት ተፎካካሪ መባላቸው ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ምንድን ነው? መደመር ምንድን ነው በሚለው ላይ አባሎቻቸውን ሲያወያዩ አልሰማንም፡፡ እንዴት ብለው ነው የምርጫ ህጉ ማሻሻል ላይ የሚሳተፉት? የትኛውን ማህበረሰብ ነው ወክለው የሚነጋገሩት? እንዴት ነው የፖለቲካ ማሻሻያዎች የሚተገበሩት? ነፃ የዜጎች መድረክ ለማዘጋጀት ምን ታስቧል? እነዚህ ሁሉ መታየት አለባቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በጎ ፍቃድ ነው ሀገር እየመራ ያለው፤ ተቋማት የሉም፡፡ ህብረተሰቡ በነፃ ስሜት እየተወያየ ሲሄድ ነው ለውጥ የሚመጣው። ፕሬዚዳንቱ የነገሩንን አቅጣጫ፣ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን አልነገሩንም፡፡ ለኔ ወሳኙ ከሁለት አመት በኋላ የሚደረገው ምርጫ ነው፡፡ ይህ ምርጫ ነፃ እና ግልፅ ሆኖ በሚካሄድበት ጉዳይ ላይ ግልፅ አቋም መወሰድ አለበት፡፡ ትልቁ ትኩረት የምርጫው ጉዳይ መሆን አለበት፡፡

======================


“የፕሬዚዳንቱ ንግግር አዳዲስ ሃሳቦችን ያቀረበ አይደለም”
አቶ ግርማ ሰይፉ (የቀድሞ የፓርላማ አባል

ፕሬዚዳንቱ ያደረጉት ንግግር እንደጠበቅሁት፣ አዳዲስ ሃሳቦችን ያቀረበ አይደለም፡፡ አቀራረቡም አሰልቺ ነበር፡፡ ተስፋ የሚፈነጥቅና የሚያነሳሳ ንግግር አላደረጉም፡፡ በንግግራቸው ካነሷቸው ሚዛን ያላቸው ነጥቦች አንዱ፣ መንግስት እቅዶቹን ማሳካት አለመቻሉን መግለጻቸው ነው፡፡ ይሄ ትልቅ እመርታ ነው፡፡ መንግስት ብዙ ጊዜ “እድገት በእድገት ሆኛለሁ” ሲል ነበር የሚደመጠው፡፡ ዘንድሮ ግን እውነታውን አልሸሸገም፡፡ በይፋ እድገት ማስመዝገብ ያልተቻለበት ሁኔታ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ በደንብ ያሰምሩበታል፣ ትኩረት ሰጥተው ያቀርቡታል ብዬ ያሰብኩት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ ነበር፡፡ ሆኖም በእግረ መንገድ ዓይነት ነገር በዋዛ ነው ያለፉት፡፡ የተድበሰበሰ አቅጣጫ ነው ያመላከቱት፡፡ ልክ የፀረ ሽብር፣ የሲቪክ ማህበራትና የሚዲያ ህጉ እንደሚሻሻል ሁሉ፣ የምርጫ ህጉ ተሻሽሎ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጠናከረ ፓርቲ ምስረታ ይካሄዳል የሚለውን፣ በተደጋጋሚ ጠ/ሚኒስትሩ ሲናገሩ የቆዩትን ነገር፣ ትኩረት ሰጥተው፣ የእቅድ ማመላከቻ ንግግራቸው ውስጥ ማስገባት አልቻሉም፡፡ ይሄን ሳስብ፤ ኢህአዴግ አሁንም ባልጠራ አካሄድ ውስጥ መሆኑንና ሌሎቹ ባልተጠናከሩበት ሁኔታ ብቻውን ሮጦ ለማሸነፍ እቅድ እንዳለው ያመላክተኛል፡፡ ተቃዋሚዎች ይሄን ነገር ተረድተው፣ ከመንግስት ድጋፍ ከመጠበቅ በራሳቸው መንገድ ተሯሩጠው ጠንካራ የሆነ ድርጅት ማሰብ እንዳለባቸው አመላካች ነው፡፡ ሚዲያ ነፃ ካደረግንላችሁ፣ የመጫወቻ ሜዳው ከተከፈተላችሁ ይበቃል የሚል አንድምታ ነው ያለው፡፡ በአመዛኙ የተነገረው፣ የተድበሰበሰ ነገር ነው፡፡  
በኢኮኖሚው በኩል አንዳንድ ሰዎች፣ አስቸኳይ የኢኮኖሚ ሪፎርም ይደረግ ሲሉ ይደመጣል፤ ነገር ግን አሁን መደረግ ያለበት ማረጋጋት ነው፡፡ ዘላቂ የሆነ የኢኮኖሚ ሪፎርም የሚመጣው ግልፅ በሆነ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት፣ የፖለቲካ ሁኔታውን የተሻለ የማድረግ ስራ ነው መሰራት ያለበት፡፡ የወጣቱን ስራ አጥነት የሚቀንሱ እርምጃዎች መቀየስ አለባቸው፡፡ ከዚህ በፊት በተለያየ መንገድ ኢኮኖሚውን የማደናቀፍ ስራ ይሰራ ነበር፡፡ ይሄ እንዲቆም መንግስት አቅጣጫ በማስያዝ፣የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረግ ይገባዋል፡፡ መቼም ዳቦ ሳንበላ ልንሰራ ስለማንችል፣ ኢኮኖሚው በትክክል መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ዛሬ ወጣቱን ድንጋይ ያስወረወረው የነፃነት ጥያቄ ሊሆን ይችላል፤ በኋላ ደግሞ የዳቦ ጥያቄ ድንጋይ ሊያስወረውረው ይችላል፡፡ ነፃነትህን ሰጥተንሃል፤ ዳቦ ምን ያደርጋል መልስ አይሆንም፡፡ ወጣቱ ነፃነቱን ካገኘ በኋላ ጥያቄው የዳቦ ነው የሚሆነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጠንካራ ምላሽ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ፕሬዚዳንቱ ያመላከቷቸው ጉዳዮች መልካም ናቸው፡፡
======================


“የህግ የበላይነት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል”
ዶ/ር ንጋት አስፋው (ምሁርና ፖለቲከኛ)


የዘንድሮው የፕሬዚዳንቱን ንግግር፣ በዋናነት በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ እኔ መመልከት የምፈልገው፣ ባለፈው ዓመት ምን አቅጣጫ አመላክተው የትኛው ተፈፀመ? ዘንድሮስ የሚለው ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት፣ ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠሪያ 10 ቢሊዮን ብር ይመደባል ብለውን ነበር፡፡ ይሄ ምን ያህል ተፈፀመ? ምን ውጤት አመጣ? ይሄ መነገር ነበረበት። በሌላ በኩል፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት በሀገሪቱ ላይ ያጋጠሙ ከፍተኛ የፖለቲካ ችግሮች ነበሩ፡፡ በርካታ ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ ቤት ንብረታቸውን አጥተዋል። የጠፋው የሰው ህይወትና ንብረት ቀላል አይደለም። ፕሬዚዳንቱ እነዚህ ነገሮችን መጥቀስ ነበረባቸው፡፡ መሰራት ስላለባቸው ጉዳዮችም አቅጣጫ መጠቆም ይገባቸው ነበር፡፡ እንደኔ ከሆነ፣ ዋናው መሰራት ያለበት የሰላምና ማረጋጋት ጉዳይ ነው፡፡ የህግ የበላይነት ጉዳይ በፕሬዚዳንቱ ንግግር መካተት ነበረበት፡፡ ይሄን በበቂ መጠን አላገኘሁትም፡፡ በሀገሪቱ የህግ የበላይነት ጠፍቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መጎዳታቸውን የዘነጋ ንግግር ነው፡፡ በቀጣይም የህግ የበላይነት እንዴት ይከበር በሚለው ላይ አቅጣጫ መጠቆም ነበረባቸው፡፡
በምጣኔ ሃብት በኩል ነፃ ገበያን እንተገብራለን ብለዋል፡፡ ይሄ የማይሆን ነው፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲን የሚከተል ገዥ ፓርቲ፤ የሊበራል አስተሳሰብ የሆነውን ነፃ ገበያ ስርአት ሊከተል አይችልም፡፡ ከዚህ አንፃር ርዕዮተ አለማቸው ወደ ሊበራል ዲሞክራሲ ካልዞረ፣ ነፃ ገበያን ሙሉ ለሙሉ እተገብራለሁ ማለት አስቸጋሪ ነው። ርዕዮተ ዓለሙን ከቀየረ ይችላል፡፡ የኛ ሃገር አብዛኛው ምጣኔ ሀብት ማንቀሳቀሻው በመንግሥት እጅ የተያዘ ነው፡፡ ይሄን መቀየር ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አንፃር ነው መታየት ያለበት፡፡ በዋናነት ግን የህግ የበላይነት ጉዳይ አሁንም እንደ አቅጣጫ መያዝ አለበት። የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር ቤት መግባታቸው ጥሩ ነው፤ ግን እንዴት እንደሚመሩ አቅጣጫ መቀመጥ አለበት፡፡ ፕሬዚዳንቱ በዚህ በኩል ያሉት ነገር የለም፡፡ መንግስት በእኒህ ላይ አተኩሮ መንቀሳቀስ አለበት፡፡Read 2675 times