Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 19 May 2012 10:25

“ጣሊያን ሊማሊሞን በመድፍ ሲደበድበው አደረ” ቢለው፤ “ተወው ይበለው፣ እሱም መገተሩን አብዝቶት ነበር” አለው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የዱር አራዊት ንጉሥ አያ አንበሶ አንዳንድ አስቸጋሪ እንስሳትን እየከታተለ ወደ ችሎቱ እንዲያቀርብለት ነብርን ይሾመዋል፡፡

መቼም “ማዘዝ ቁልቁለት ነው” ይባላልና ነብር ደግሞ በበኩሉ ዝንጀሮን የቅርብ ጆሮ ጠባቂው አድርጐ ይሾመዋል፡፡ በየጠዋቱ ነብርና

ዝንጀሮ እየተገናኙ ይወያያሉ፡፡

“እህስ ደኑ እንዴት አደረ?” ይላል ነብር፡፡

“ዛሬ ደህና ነው ያደረው፡፡ በጣም ሰላም ነው” ብሎ ይመልሳል ዝንጀሮ

ሌላ ጠዋት፡፡

“እህስ ደኑ እንዴት አደረ?” ይጠይቃል ነብሮ፡፡

“ደህና ነው፡፡ ብቻ ጐሽና ግሥላ ተጣልተው ጥቂት ጉዳት ደረሰ” አለ ዝንጀሮ፡፡

“በምን ተጣሉ?”

“አንድ የሞተ እንስሳ አግኝተው እኔ ነኝ ቀድሞ ያየሁት በሚል የባለቤትነት ጥያቄ ነው”

አያ ነብሮም፤

“አይ ይሄ እንኳ የግል ጠብ ነው እኛን አይመለከትም” ይላል፡፡

ወደማታ አያ ነብሮ ወደ ንጉሡ ይሄድና ሁኔታዎች ምን መስለው እንዳደሩ ያስረዳል፡፡

እንዲህ እንዲህ እያሉ የደኑን ፀጥታ በተመለከተ ክትትል እያደረጉ ይከርማሉ፡፡

ከእለታት አንድ ጠዋት ዝንጀሮ ወደ አያ ነብሮ ሲሮጥ ይመጣና፤

“ጌታ ነብሮ” ይላል እያለከለከ፡፡

“እህስ ደኑ እንዴት አደረ?” አለ አያ ነብሮ፡፡

“ኧረ ጌታዬ ዛሬ ሌሊት የዱር እንስሳቱ ዋና ዋና አባላት፣ ማለትም እነ ዝሆን፣ አጋዘን፣ ጐሽ፣ ግሥላና ጉሬዛ ተሰብስበው ‘የዱር አስተዳደሩ

አልተስማማንም… ሹሙ ይቀየርልን… የተፈቀደልን የአደን ቦታ አድልዎ አለበት… እንደልባችን በደላችንን ለመግለፅ አያ አንበሶ ዘንድ አድርሱን

ስንል ‘በእኛ በኩል ካልሆነ በቀጥታ መናገር አይቻልም’… እያሉ በደል አድርሰውብናል፡፡ ስለዚህ አያ አንበሶን አግኝተን ብሶታችንን መናገር

አለብን፡፡ ካልሆነ ግን የነ አያ ነብሮን መኖሪያ ደረማምሰን አያ አንበሶ ያሉበት ድረስ እንገባለን!” ሲሉ ሲማከሩ አድረዋል አለ ዝንጀሮ፡፡

“ታዲያ ምን ማድረግ ይበጀናል?” ሲል ጠየቀ ነብሮ፡፡

“የሚሻለው የርሶን የነብሮ ጥበቃ ኃይል ተጠቅሞ ሁሉንም ይዞ፤ ጥፋተኝነታቸውን በአያ አንበሶ ፊት አምነው፤ ሁለተኛ እንደማይለመዳቸው

ቃል ገብተው ፀጥ ለጥ ብለው እንዲያድሩ ማድረግ ነው” ሲል ዝንጀሮ ምክሩን ለገሰ፡፡

አያ ነብሮም በሀሳቡ ተስማምቶ፤

“በጣም ጥሩ ሀሳብ ነው፡፡ በጣም አመሰግናለሁ” ብሎ አያ ዝንጀሮን አሰናብቶ ወደ አያ አንበሶ ሄደ፡፡ ሁኔታውን በቃሉ ካስረዳ በኋላ፤

“ጌታዬ እንግዲህ የነብሮን ኃይል አሰማርቼ ሁሉም እርሶ ፊት እንዲቀርቡ ላደርግ ነው፡፡ ምን ይመስልዎታል?”

አያ አንበሶም፤

“ይሄ ምንም የሚያጠያይቅ ነገር አይደለም! በአስቸኳይ እርምጃ ይወሰድ!”

በሶስተኛው ቀን የተባሉት እንስሳት አያ አንበሶ ዘንድ ቀረቡ፡፡

የተባለውን ስብሰባ ማካሄድ አለማካሄዳቸውን አያ አንበሶ ጠየቃቸው፡፡

“አድርገናል፡፡ ምክንያታችንም ይሄ ይሄ ይሄ ነው” ብለው የተመካከሩትን አስረዱ፡፡

አያ አንበሶም፤

“መልካም ጉዳዩን እኔ አስብበትና ውሳኔ እሰጣለሁ፡፡ እስከዛ ድረስ ግን ምንም ስብሰባ እንዳታደርጉ፡፡ በሰላም ተቀመጡ!” አለ፡፡

በማህል ግን ከእንስሳቱ ውስጥ አንድ ድምፅ ተሰማ፡፡ ሁሉም ድምፁን ወደሰሙበት ዞሩ፡፡

ጦጢት ናት ድምፅ ያሰማችው፡፡

አያ አንበሶ ወደሷ ዞሮ፤

“አንቺ የዋና ዋና ዱር እንስሳት አባል አደለሽም፤ እዚህ ለምን አመጡሽ? ለምን አሰሩሽ?”

ጦጣም፤

“አያድርስብዎ ጌታዬ! አንድ ቀን፤ ለእርሶም ቢሆን ያው ነው!” ብላ ምርር ብላ መለሰች፡፡

***

“ማዘዝ ቁልቁለት ነው!” ከሚባልበት ሥርዓት ይሰውረን፡፡ ትክክለኛ ጥያቄን በትክክለኛው መንገድ ለመጠየቅ መሰብሰብ ትክክለኛ መንገድ ሆኖ ሳለ አግባብነት የለውም ከሚል ሰብቀኛ ያድነን፡፡ ለሌላው በትር ይሆነኛል ብለን የመለመልነው ሽመል አንድ ቀን ለኛ ለራሳችን መገረፊያ እንዳይሆን ቢያንስ ከአልቃይዳ ታሪካዊ አመጣጥ እንማራለን፡፡ “ለእርሶም ቢሆን ያው ነው” የምትል ጦጣ ጥሩ የማስጠንቀቂያ ደወል ናት! በማይተናነስ ደረጃ፤ “ዝሆን ሊታሰር ነው!” ሲሏት የምትሮጠው ጥንቸል፤ “አንቺ ዝሆን አይደለሽ ምን ያስሮጥሻል?” ብትባል፤ “እስኪጣራ ብለው ቢያስሩኝስ?” ማለቷም ታላቅ ተመክሮ ነው (የደርግ ዘመን ትሁን የሌላ ጊዜ ጥንቸል፤ እስከዛሬ አልተጣራም)

በንጉሡ ዘመን “ሚኒስትሮቹ ናቸው ጥፋተኞች! ንጉሡ አልሰሙም!” ይባል ነበር፡፡ “ንጉሡ ሰሙ!” አገሪቱ ግን ያው ናት፡፡ በቀጠለው ዘመን ለጓዶቻቸው “የምታደርጉትን ሁሉ እናውቃለን!” የሚሉ መሪ መጡ፡፡ አገሪቱ ግን ያው ናት! በቀጣጠለው ዘመን “ሚኒስትሮቹ ምን ያውቃሉ? ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ ምን ያውቃሉ? ባለሟሎቹ ምን ያውቃሉ? የሚያውቁት እሳቸው ብቻ ናቸው፤ የሚባልበት ዘመን መጣ፡፡ አገሪቱ ግን ያው ናት! ከፊውዳሊዝም ፌርማታ ተነስተን፤ በሚሊታሪዝም (ሶሻሊስት-ዲክታተርሺፕ) አቋርጠን፤ ወደ ሶሺዮ-ካፒታሊዝም ስንጓዝ፤ ያጠንናቸው መቅደሶች፣ የካደምናቸው መጅሊሶችም ሆኑ ቄጠማ የነሰነስንባቸው የፓርላማ ሸንጐዎች፣ መሪዎች እንደ ህዝበ-ሱታፌ የጐደላቸው ናቸው፡፡ ሁሉም ለህሩያን ህዳጣኑ (ለጥቂቶቹ ምርጦች) እንደየ ሥርዓት ባህሪያቸው የተመቻቹ ናቸው - ለመሳፍንቱና ለመኳንንቱ፤ ለመኰንኖቹ እና ለጓዶቹ ለተጋዳላዮቹ… ሁላቸውም የፊውዳሊዝም ልጆችና ልጅ-ልጆች… አንድም ሶስትም ናቸው! ወደላይ ከመሳፍንቱ ወደታች ከሰፊው ህዝብ ዘር መቋጠር የአበሻ ባህል ነውና አይፈረድብንም! በየትኛውም ሥርዓት አንድ ዘፈን የጋራ ሆኖ እናገኘዋለን:-

“እንተኛም ካላችሁ፤ እንገንድሰው

መኝታ እንደሆነ፣ ቀርቷል ከአንድ ሰው!”

እንቅልፍ… እንቅልፍ… እንቅልፍ… አንድ ሰው… አንድ ሰው… አንድ ሰው፡፡ ጥቁር ሰው አልነው ጥቁር ግስላ… ሥዩመ-አርሶ-አደር… ሁሉም ስለ አንድ ሰው ነው!

ደረጃው ስትራቴጂው፣ የዘመኑ ኋላ ቀርነትና ቀዳሚነት፣ ይለያይ እንጂ ሁሉም ስለ ሀገር አውርተዋል፡፡ መሰረተ-ሀዲድ… መሰረተ-ትምርት… መሰረተ-ልማት… ሁሉም ስለመሰረት ተናግረዋል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን መሰረተ-ህዝቡ ነው፡፡ ለህዝቡ ምን ጠብ አለ? የዘመን ማወዳደሪያው ይሄ ቢሆን መልካም ነው፡፡

በጤና፤ በሥራ-ዕድል፤ በኑሮ ውድነት፤ በትምህርት፣ በፕሬስ፣ በፍትህ በወዘተ. አኳያ ህዝብ ምን ተጠቀመ? በሙስናው፣ በብልሹው አስተዳደር፣ በፍትህ መጓደል፣ በኑሮው ጫና አኳያ ህዝብ ምን ተጠቀመ? እንበል፡፡ መሰረተ-ህዝቡን እናስብ!

“በአንድ እጇ ሞባይል፤ በአንድ እጇ ሞፈር

ያገር ቤቷ ቆንጆ፤ እዩዋት ስታምር”

የሚል ዘፈን በተንቀሳቃሽ ስልክ ላደረግነው እርምጃ ልናወጣ እንችላለን፡፡

“አጥንቴም ይከስከስ፤ ደሜም ይለቅ ፈሶ

ያገሬ ኢንቨስትመንት፤ ከማይ ተቀልብሶ”

የሚል ዜማም ልናወጣ እንችላለን! (ለዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም በአፍሪካ) ተቀዳሚው ጥያቄ ግን የህዝባችን ሆድ ሞልቷል ወይ? ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ደጋግመን እንስማ፡፡ ኑሮ ውድነቱን እናሰላስል፡፡ ባለሙያዎችን እናነጋግር፡፡ መረጃ ያለው ህዝብ ይኑረን (Informed Public) እጐናችን ይቆም ዘንድ! አለበለዚያ አንድ ያገራችን ሰው፤

“ጣሊያን ሊማሊሞን በመድፍ ሲደበድበው አደረ!” ቢሉት፤

“ተወው ይበለው፤ እሱም መገተሩን አብዝቶት ነበር!” አለ እንደተባለው ይሆንብናል - ሁሉም ነገር!

 

 

Read 3841 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 10:27