Saturday, 13 October 2018 11:30

የመስከረም ግጥም

Written by  ነ.መ
Rate this item
(40 votes)

  ነ.መ

መቼም ጥም አይቆርጥም
የመስከረም ግጥም!
ውብ ዐይን የሌላችሁ
ውብ ዐይን እዩ በቃ
ተማምነን ተምረን እንድንበቃቃ
ሁሉንም እንድንሆን በሁሉም ደቂቃ
እንሸነፍ ዛሬ ለነገ እንድንበቃ
ማን ወልዳ ታቃለች ተኝታ ሳትነቃ!
የመስከረም ግጥም
መቼም ጥም አይቆርጥም
ይኸው ነው ጉልበቱ ተኝቶ ሲያስታምም!
እየነቃ ሲልም
እየተኛ ሲፍም
ጮሆ ጮሆ ሲያልቅ፣
ዝም ይላል ዘላለም!
ጮሆ ጮሆ ሲልቅ ይላል ዘላለም!
ይሄ ነበር ኑሮም
ይሄ ነበር ነገም
የመስከረም ግጥም
ሌላ ወር አያቅም!
ኢትዮ/ ሳትኖር እኛኮ የለንም
እኛ ሳንኖርላት ኢትዮ/የለችም!!
መስከረም - ጥቅምት 2011 (ለአዲስ ሀሳብ)
እንዳንጠፋፋ
ትዝ ይልሻል ውዲት
ሰንደቅ አላማው ሥር
ፍቅር ይዘን ነበር
ተሳስመን ነበር
ተጨቃጭቀን ነበር
ተደራድረን ነበር
ተዋውለን ነበር
 ሲመሽም ሲነጋም
ሲሰቀል አይተናል
ሲወርድም አይተናል
የልጅነት ፍቅር ፀንሰን ወልደን ኩለን
ወግ ማዕረግ አይተናል
ውዲት!
እዚያው ሰንደቅ ዙሪያ
በጉልምስናችን ቀጠሮ አለን ዛሬም
እጅግ መናፈቄን አቃለሁ አትረሺም
የልቤ ገብቶሻል
መምጣትሽ አይቀርም
ግን አደራ ፍቅሬ መንገዱ አልተገራም
መሰናክል ሩጫው ሜዳ ሙሉ ሆኗል
ሳትሰሚው አትቀሪም
ባንዲራ አብዝተናል
እናም ተጠንቀቂ ወደኔ ስትሮጪ
በተለይ ጎዳና ሳታቆራርጪ
ብዙ ነገር ጠፍቷል በልክ የተሰራ
ባንዲው ረዝሟል
እንዳይጠልፍሽና እንዳንጠፋፋ!
(ለሁላችን) መስከረም 2011

Read 6824 times