Saturday, 13 October 2018 11:47

አደባባይ የተነፈገው የዘንድሮ የሰንደቅ ዓላማ ቀን

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

 11ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ እንደሚከበርና ዘንድሮ በዓሉ በአደባባይ እንደማይከበር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አስታውቀዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች አለመግባባቶችና ግጭቶች እየተፈጠሩ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የጠቆሙት አፈጉባኤዋ፤ ይህንን ችግር ለማስቀረትና በሰንደቅ አላማ ሰበብ ግጭቶች እንዳይከሰቱ ለማድረግ ሲባል፣ በዓሉ በአደባባይ እንዳይከበር መወሰኑን ገልፀዋል፡፡
ሰንደቅ ዓላማ የአንዲት ሉአላዊት አገር መገለጫ ምልክት እንደሆነ የተናገሩት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፤ ሰንደቅ ዓላማውን ህዝቡ የማይቀበለው ከሆነ፣ በህጋዊ  መንገድ፣ የህዝብ ውይይት ተደርጎበት ሊቀየር እንደሚችል ጠቁመው፣ አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት በህጋዊነት የሚቀበለው ሰንደቅ አላማ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሆኖ መሀሉ ላይ በሰማያዊ ቀለም አርማ ያለውን ሰንደቅ አላማ ነው  ብለዋል፡፡
ህዝቡ በሰንደቅ አላማው ላይ የሚያነሳውን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ተከታታይነት ያለው ውይይት ከህዝቡ ጋር ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ አንድና ሁለት እንደሚያመለክተው፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ፣ በመሃሉ ብሔራዊ አርማ ይኖረዋል። ከሰንደቅ አላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ አርማ፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ይሆናል ሲል ይገልፃል፡፡
በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የፕሬዚዳንትነት ዘመን የተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 48/1998 የሰንደቅ አላማ አርማ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 2 ንዑስ ቁጥር 1 ደግሞ፤ ሰንደቅ ዓላማው ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በክብ ሰማያዊ መደብ ላይ የተቀረፀ ብሔራዊ አርማ ይኖረዋል ይላል፡፡
ይሁን እንጂ ቀደም ባሉት ዓመታት በድብቅ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በገሃድ፣ አርማ የሌለው ሰንደቅ አላማና ሌሎች የቀድሞ ዘመን ሰንደቅ አላማዎች በስፋት ሲውለበለቡ ማየት የተለመደ ጉዳይ ሆኗል። ህዝቡ በሰንደቅ አላማ ጉዳይ ላይ አገራዊ መግባባት ላይ መድረስ አለመቻሉ፣ ለተለያዩ አለመግባባቶችና ግጭቶች መፈጠር ምክንያት እየሆነ መጥቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሰንደቅ አላማው፤ የአንዲት ሉአላዊት አገር መገለጫ ከመሆን አንሶ፣ የፖለቲካ አመለካከቶች የሚወከሉበት ምልክት እየሆነ መምጣቱን የህግ ባለሙያው አቶ ኤልያስ አድማሱ ይገልፃሉ፡፡ ሰንደቅ አላማ ከአገር ውክልና ወርዶ የግለሰቦችና የድርጅቶች የፖለቲካ አመለካከቶች ማሳያ እየሆነ መሄዱ አሳሳቢ  ጉዳይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ አንዲት በመንግስት በምትተዳደር ሉአላዊት አገር፣ በህጋዊ መንገድ በስርዓት ያልተቀየረን ሰንደቅ አላማ፣ በግለሰቦች ፍላጎትና ፍቃድ ብቻ እንዲቀየር ማድረግ ህገ-ወጥነት ነው ያሉት የህግ ባለሙያው፤ ይህ ሁኔታም አለመግባባቶች እንዲቀሰቀሱና በዚህ ሳቢያም የሰዎች ህይወት እንዲጠፋ አድርጓል ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ አሁን ስራ ላይ ባለው ሰንደቅ አላማ ላይ ያለውን ተቃውሞ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲገልፅ መኖሩን ያስታወሱት የህግ ባለሙያው፤ መንግስት የህብረተሰቡን ፍላጎት ሊሰማና ሊያስተናግድ የሚችልበት መድረክ አመቻችቶ፣ውይይት በስፋት ከተደረገ በኋላ ለጉዳዩ ውሳኔ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
ዘንድሮ በዓሉ በአደባባይ እንዳይከበር መደረጉ በሰንደቅ አላማው ልዩነት ሳቢያ ሊቀሰቀሱ የሚችሉ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን ሊያስቀር መቻሉ አይካድም ያሉት አቶ ኤልያስ፤ሆኖም ግን ጉዳዩ መሰረታዊና የማያዳግም ውሳኔ ሊሰጥበት እንደሚገባ  አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን ቅሬታና አለመስማማት፣በሰንደቅ አላማው ላይ እንዲንፀባረቅ አድርጓል ይላሉ፤የህግ ባለሙያው፡፡
የአገሪቱ ህገ መንግስት አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ አንድና ሁለትም ሆነ የተሻሻለው የሰንደቅ አላማ አዋጆች፤ የአገሪቱን ሰንደቅ አላማ በመወሰን፣ ከዚህ ውጪ ሰንደቅ አላማዎችና አርማዎች ሁሉ ህገ ወጦች መሆናቸውን ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጂ መንግስት በጉዳዩ ላይ ቸልተኝነት በማሳየቱ፣ ችግሮች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ መታየታቸውን ጠቁመው፤ አሁንም ቢሆን አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባው የህግ ባለሙያው አበክረው ይናገራሉ።
የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ፤ ሁላችንም ልናከብረውና ልንቀበለው የሚገባ ነው ያሉት አቶ ኤልያስ፤ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ከፌደራሉ ሰንደቅ አላማ ይልቅ የክልል አርማዎችንና ሰንደቅ አላማዎችን ይዞ መውጣት እየተለመደ መምጣቱን በመግለፅ፤ ለፌደራሉ ሰንደቅ አላማ እውቅናን የመንፈግ ተግባር ሊወገዝ ይገባዋል ብለዋል፡፡  

Read 2431 times