Saturday, 20 October 2018 13:27

ልዩ የምስጋና ስጦታዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)


        ለኃይሌ ገ/ስላሴና ለገ/እግዚአብሄር ገ/ማርያም

  . ‹‹በሩስያ 2018 የፊፋ ዓለም ዋንጫ የተሳካ ቆይታዬ አመሰግናለሁ፡፡›› ግሩም ሠይፉ
  . ‹‹አዲሱን የፈጠራ ውጤታችንን ጀግኖች በማመስገን ማስተዋወቃችን ከልብ አስደስቶኛል፡፡›› ኢንጅነር ሳምሶን ጌታቸው
 . ‹‹ጀግኖችን በተለያዩ የጥበብ ስራዎች መዘከር ከአይከን ስቱድዮ ዓላማዎች አንዱ ነው፡፡›› ሰዓሊና ዲዛይነር ዳዊት ሙሉነሕ


   በ21ኛው የዓለም ዋንጫ የተሳካ ቆይታዬ ላደረጉት ድጋፍ  ለሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እና ለአትሌት ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም ከአይከን ስቱድዮ ልዩ የምስጋና ስጦታ ተበረከተላቸው፡፡ በሩስያው የዓለም ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያን በብቃት በመወከል ከነበረኝ ሃላፊነት በተጨማሪ፤  ከ‹‹አይከን ስቱድዮ›› ከኢንጅነርና ከሰዓሊ ጋር የፈጠርኩት ጥምረት ‹‹እኔ ከኢትዮጵያ ነኝ›› ከሚለው ሃሳብ  ‹‹አመሰግናለሁ›› እስከ የሚለው ሃሳብ እንድሰራ አስችሎኛል፡፡ በአይከን ስቱድዮ ተዘጋጅቶ የወጣው የምስጋና ስጦታ 15 ሴንቲ ሜትር ቁመት እና 10 ሴንቲ ሜትር ስፋት ባለው የአልሙኒዬም ብረት ላይ ተሰርቷል፡፡ በኢንጅነር ተቦርቡሮና በሰዓሊ ተውቦ የተዘጋጁት  የሁለቱን ታላላቅ አትሌቶች የፊት ምስሎች ናቸው፡፡ ‹‹በሩስያ 2018 የፊፋ ዓለም ዋንጫ የተሳካ ቆይታዬ አመሰግናለሁ፡፡›› ግሩም ሠይፉ የሚል ፅሁፍም ተካቶበታል፡፡
 ሰዓሊና ዲዛይነር ዳዊት ሙሉነህ  እና መካኒካል ኢንጅነር ሳምሶን ጌታቸው  ከስፖርት አድማስ ጋር በመተባበር የምስጋና ስጦታውን ሰርተውታል።  ‹‹አዲሱን የፈጠራ ውጤት ጀግኖች በማመስገን ማስተዋወቃችን ከልብ አስደስቶኛል›› በሚል የተናገረው ኢንጅነር ሳምሶን ጌታቸው ነው፡፡ ሰዓሊ ዳዊት ሙሉነሕ በበኩሉ ‹‹ ጀግኖችን በተለያዩ የጥበብ ስራዎች ማድነቅ ከአይከን ስቱድዮ ዓላማዎች አንዱ ነው›› ብሏል፡፡
ሁለቱ የአይከን ስቱድዮ ባለሙያዎች  ‹‹እኔ ከኢትዮጵያ ነኝ›› በሚል ሃሳብ ሩስያ ላይ ኢትዮጵያን በከፍተኛ ደረጃ እንዳስተዋውቅ ልዩ እገዛ አድርገውልኛል፡፡ የ21ኛው የዓለም ዋንጫ ማስታወሻዬንም በምስጋና እንድቋጭ ልዩ ስጦታውን በ1 ወር  ውስጥ ሰርተውታል፡፡
ኢንጅነር ሳምሶን ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት ‹‹የምስጋና ስጦታው የሰራነው በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ለነበረህ የተሳካ ቆይታ ሙሉ ማስታወሻ እንዲሆን ነው፡፡ የፈጠራውን ውጤት በምስጋና ለማስተዋወቅም ነው፡፡ ሙሉው የፈጠራ ስራው በአገር ውስጥ አዲስ የምርምር ውጤት ነው። ገና ወደ ሰፊው ሜዳም አልወጣም፡፡  ማንኛውም አይነት የብረት ዘር እንደየተግባሩ ይቦረቦራል። በተቦረቦረው ላይም ፎቶ ፤ የተለያዩ ምስሎች፤ ፅሁፎችና የመሳሰሉትን መቅረጽ ይቻላል፡፡›› በማለት  ተናግሯል፡፡
ሰዓሊና ዲዛይነር ሙሉነህ በበኩሉ ‹‹በአልሙኒዬም ላይ የተቦረቦረውን ምስል ስመለከተው  አዲስ የፈጠራ ውጤት ለአገራችን መበርከቱን  ተረድቻለሁ፡፡  የፈጠራ ውጤቱ ለምስጋና የሚሰጥ በመሆኑ የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማድረግ ፈልጌ፤ በሚክስድ ሚዲያ ላስውበው በማለት ለፈጠራ ባለቤቱ ኢንጅነር ሳምሶን ነገርኩት። በዚያው ተስማምተን 5 ቀለማትን በመጠቀም በአልሙኒዬም ፕሌቶቹ ላይ ተቦርቡረው የወጡትን ወደ ባለሙሉ ቀለም በመቀየር የጀግኖቹን ምስሎች አስውቢያቸዋለሁ፡፡›› ሲል ተናግሯል፡፡
ከአይከን ስቱድዮ ባለሙያዎች የምስጋና ስጦታ ሆኖ የቀረበው የፈጠራ ውጤት ሁሉንም ዓይነት የብረት አይነቶች በመቦርቦር ሊሰራ ይችላል። ልዩ የፈጠራ ስራው ታላላቅ የኢትዮጵያ ሰዎች፤ ጀግኖችና ባለታሪኮችን… ለረጅም ጊዜ በቋሚ ቅርስነት ታሪካቸውን ለማቆየት እና ለማድነቅ ያስችላል፡፡ ከብረት የሪልፍ ቅርፃ ቅርፅ እና ተያያዥ ስነጥበብ ጋር በተያያዘም በአገራችን ለመጀመርያ ጊዜ በምርምር ተግባራዊ ሊሆን የበቃ የፈጠራ ውጤት ነው፡፡ ከውጭ አገር ውድ ቴክኖሎጂን በማስገባት የሚኖረውን ወጭ ያስቀራል፡፡  አዲስ አይነት የጥበብ መንገድ ወይም ሚዲዬም በመጠቀም እስከዛሬ በብዛት ውጭ አገር የሚላኩትን የተለያዩ የጥበብ ውጤቶች በአገር ውስጥ ባለሙያዎች እንዲሰሩ እድል ይፈጥራል፡፡ የፈጠራ ውጤቱ በተሰቀለበት ቦታ ሁሉ ከማናቸው የእሳት እና መሰል አደጋዎች ሊተርፍ ይችላል፡፡ በፋብሪካ ደረጃ መሰረታዊ የማምረቻ ቴክኖሎጂዎችን በአገር ውስጥ መስራትም የሚያችል ይሆናል፡፡ ሁለቱ ባለሙያዎች ለስፖርት አድማስ እንዳብራሩት ….
የፈጠራ ውጤቱ የኢትዮጵያን ጀግኖች፤ ባለታሪኮችና ተምሳሌቶች በማያረጅ ቅርስ ለማድነቅ የሚያመች ምርጥና ልዩ አማራጭ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን፤ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ … በአዳራሾች በመተላለፊያ ኮሪደሮች እና አመቺ ስፍራዎች የስፖርተኛ አትሌቶችን ምስሎች ተለጥፎ ተመልክተናል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ልዩ ልዩ የስፖርት ማዕከላትና ስታድዬሞች ጀግና ስፖርተኞች ስማቸው መታሰቢያ እንደሆነ ይታወቃል። የማስታወሻ እና የመታሰቢያ ምስሎችን በወረቀት የፎቶ ህትመቶች፤ በእንጨት እና በመስታወት በሚሰሩ ፍሬሞች መለጠፍ የተለመደ ሆኖ ቆይቷል፡፡  በኢንጅነር ሳምሶን ጌታቸው የተፈጠረውና በተለያዩ የብረት አይነቶች ላይ  ተቦርቡሮ የሚሰራው የፈጠራ ውጤት ከላይ በተዘረዘሩት ስፍራዎች ያሉትን ሁኔታዎች በአሳማኝ ሁኔታ ሊቀይር ይችላል፡፡ የታሪክ ማስታወሻዎችን ረጅም እድሜ ባላቸው ብረቶች መቀየር እንደሚያስፈልግ በማመን የምስጋና ስጦታውን ልዩ ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፡፡
ካሳንቺስ 28 ሜዳ አካባቢ የሚገኘው አይከን ስቱድዮ በሰዓሊና ዲዛይነር ዳዊት ሙሉነህ የተመሰረተ  ሁለገብ የስነጥበብ ማዕከል ነው፡፡ አይከን ስቱድዮ ከ21ኛውን የዓለም ዋንጫ በፊት  እና በኋላ እንደካምፕ ተገልግየበታለሁ፡፡ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ከ‹‹እኔ ከኢትዮጵያ ነኝ›› እስከ ‹‹አመሰግናለሁ›› ድረስ የላቁ ሃሳቦች የፈለቁበት ይህ ስቱድዮን አስመልክቶ እና በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ በፋና ቲቪ ዘወትር እሁድ ከጠዋቱ 4 እስከ 5 ሰዓት በሚተላለፈው የስፖርት ዞን ኢትዮጵያ ያደረጉት ቃለምልልስን ነገ እና በሚቀጥለው ሳምንት መከታተል ትችላላችሁ፡፡
በአይከን ስቱድዮ  በርካታ ወጣት ምሁራንና ባለሙያዎች ይሰባሰባሉ፡፡  ዶክተር፤ ኢንጅነር፤ ሰዓሊ፤ ቀራፂ፤ አንትሮሎጂስት፤ የቱሪዝም ባለሙያ፤ ፊልም ሰሪ፤ የኮምፒውተር ኢንጅነር፤ ባንከኛ፤ ሙዚቀኛ….  ይገኙበታል፡፡  ዓለም ዋንጫን ለመዘገብ  በፊፋ  ከኢትዮጵያ ከተጋበዙት የስፖርት ጋዜጠኞች አንዱ መሆኔን ካወቁ በኋላ ሁሉም የሞራል ደጋፊዎቼ ነበሩ፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዳቸው በየሙያ ዘርፋቸው ኢትዮጵያን ማገልገልና ማስጠራት የሚወዱ ናቸው፡፡  ስቱድዬው በሚገኝበት ግቢ የተሰበሰቡ  ቤተሰቦችም ተመሳሳይ ናቸው።  የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያን በጎበኘችበት ወቅት ከኮካ ኮላ በተሰጠችኝ የኳስ ስጦታ በዚህ ስቱድዮ አሁንም ትገኛለች፡፡ በአይከን ስቱድዮ የሚሰባሰብ እና በዙርያ ያሉ ቤተሰቦች ሁሉ  የራሽያው ጉዞዬ እንዲሳካልኝ መልካም ምኞታቸውና ፊርማቸውን አኑረውባታል።  ከአይከን ስቱድዮ ሰዓሊና ዲዛይነር ዳዊት ሙሉነህ፤ኢንጅነር ሳምሶን ጌታቸው፤ የሻማ አርቲስት ቀራፂ አስናቀ ክፍሌ እና ሌሎችም … በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ከስፖርት ጋዜጠኝነቱ ባሻገር ‹‹እኔ ከኢትዮጵያ ነኝ›› የሚለውን ሃሳብ በአማርኛ እና በራሽያኛ በቲሸርቶች ላይ በማተም ኢትዮጵያን እንዳስተዋውቅ በማድረጋቸውና ከዓለም ዋንጫ መልስ ድጋፍ የሰጡኝን እንዳመሰግን ልዩ የፈጠራ ውጤት በማዘጋጀታቸው ከስፖርት አድማስ ልዩ ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡

Read 1883 times