Saturday, 20 October 2018 13:42

የጠ/ሚኒስትሩ አዲስ ካቢኔ በምሁራንና በፖለቲከኞች እይታ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ አዲስ ካቢኔ አዋቅረዋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ለፓርላማ አቅርበው ሹመታቸውን ካስጸደቁላቸው 20 ሚኒስትሮች መካከል 10 ያህሉ ሴቶች ሲሆን ይህም የካቢኔያቸውን 50 በመቶ በሴቶች የተያዘ ያደርገዋል፡፡ አዲሱ የካቢኔ አወቃቀር ከቀድሞው በምን
ይለያል? ሴቶች እኩሌታውን የሚኒስትርነት ቦታ መቆጣጠራቸው ምን አንደምታ አለው? ከካቢኔ አባላቱ ምን ይጠበቃል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ምሁራንና ፖለቲከኞችን አነጋግሮ ሃሳባቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡


       “በመጨረሻም ፍትህ ተፈፀመ”
         ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ (የግል ቢዝነስ መሪ)

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሴቶችን በካቢኔያቸው 50 በመቶ ማካተታቸውን ሳውቅ የተሰማኝ ነገር፤ “በመጨረሻም ፍትህ ተፈፀመ” የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም የሴቶች ጥያቄ የነበረው የሰብአዊ መብት ጥያቄ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከእኩልነት ጥያቄ በፊት የሚመጣው የሰብአዊ መብት ጥያቄ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡  ስለዚህ ፍትህ በመጨረሻ ተፈፀመ የሚለው ትክክለኛ አገላለፅ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የተሰማኝ፤ ይሄ አካሄድ በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የገባ ትልቅ የለውጥ ምዕራፍ ነው። ይሄ የለውጥ ምዕራፍ ከአሁን በኋላ ለሚመጣው ተጨማሪ ጉልበት የሚሆንና ወደ ኋላ እንዳይመለስ ሆኖ የተከሰተ ነው፡፡ አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡ ለሀገሪቱም አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የፖለቲካ በጎ ፍቃደኝነት ወሳኝ እንደሆነ ነው ያስተዋልኩት፡፡ ሁሉም ነገር በመንግስት በሆነበት እንደ ኢትዮጵያ ያለ አገር፣ የፖለቲካ በጎ ፍቃደኝነት ወሳኝ ነው፡፡ የፖለቲካ በጎ ፍቃደኝነት ሲኖር፣ ብዙ ነገር ሊቀየር እንደሚችል የተማርኩበት ነው፡፡ መንግስት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡም 50 በመቶ አካሉ አቅም የለውም ብሎ ካመነ፣ ሀገር የለውም ማለት ነው፡፡ ይሄን አስተሳሰብ እንዲቀይር ቢያንስ እንዲያጤን የሚያደርግ አንድምታ ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አሁን የተሾሙት ሴቶች ከዚህ በኋላ የሰውን ትኩረት በእጅጉ ይስባሉ፡፡ ሰዎች ከእነሱ ጉድፍ ለመፈለግ ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ አሁን ከእነሱ ጉድፍ ለመፈለግ ከሌላው ጊዜ በተለየ የሰዎች መነፅር ከፍተኛ ሊሆን ስለሚችል በዚህ በኩልም ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህ ሚኒስትሮች በመጀመሪያ ማድረግ ያለባቸው ሊረዳቸው የሚችል ኃይል በዙሪያቸው ማሰባሰብ ነው፡፡ ሴት ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን መሪ መሆን ማለት በዙሪያው የሚረዳው ኃይል ማሰባሰብ እንጂ በራሱ እጅ ብቻ ማጨብጨብ ማለት አይደለም፡፡ መሪ መሆን ማለት ትክክለኛ ረዳት ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ፈልጎ፣ በትክክለኛው ቦታ ማስቀመጥ ማለት ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ የመሪ ስኬትም የሚመጣው ከዚህ ነው፡፡ እነዚህ ሴት ተሿሚዎችም ይሄን የመሰብሰብ አቅማቸውን ከፍ ቢያደርጉ ጥሩ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የኮሚኒኬሽን ስልታቸውን ከፍ ቢያደርጉና በዚህ ዙሪያ የተለየ ጥረት ቢያደርጉ ጥሩ ነው፡፡ የኔትወርክ ስልታቸውንም ቢያሰፉ የተሻለ ስኬት ሊያስመዘግቡ ይችላሉ፡፡

--------------

             “ሚኒስትሮች ቢሮክራሲውን በሚገባ መፈተሽ አለባቸው”
                አቶ አብዱራህማን አህመድ (የቀድሞ የፓርላማ አባል)

    አሿሿሙ ለየት የሚያደርገው በተለይ የፆታ ስብጥርን ለማመጣጠን ጥረት በመደረጉ ነው፡፡ ከሴቶች ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ያልተጠቀምነውን አቅም ነው፤ አሁን ለመጠቀም መንገድ የተጀመረው። አቅማቸውን ለመጠቀም ጥረት መደረጉ ጥሩ ነው፤ በበጎነት ሊታይ የሚገባው ነው። እንደ ሩዋንዳ ያሉት ሀገራት ከፓርላማ አባላት 60 በመቶ ሴቶች ናቸው፤ እኛ ጋ ደግሞ በሚኒስትሮች ደረጃ ነው ለማመጣጠን የተሞከረው፡፡ ይሄ ከዚህ በፊት ያልተለመደ ነው። መበረታታት ያለበትም ነው፡፡ በዚህ መሃል ግን የተመረጡት የካቢኔ አባላት፣ የኢህአዴግ አባልነትን መሰረት አድርገው የተመረጡ ናቸው፡፡ ግን ለውጡን ወደፊት ይዘው ሊሄዱ ይችላሉ የሚባሉ፣ ፖለቲከኛ ያልሆኑ ሙያተኛ ቢሆኑ የተሻለ ነበር፡፡ አሁንም ሙያተኛ የሆነን ማንኛውንም ዜጋ ለሹመት ማጨት መጀመር አለበት፡፡ በአሿሿም ጉዳይ ላይ የኢህአዴግ አሰራርና ደንብን ማሻሻል ካስፈለገም መሻሻል አለበት፤ መመዘኛው የፖለቲካ ታማኝነት ሳይሆን የሙያ ብቃት መሆን አለበት፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ታማኝ ነው፡፡ የተሰጠውን የመንግስትና የሃገር አደራ መወጣት የሚችል ነው፤ሁሉም ኢትዮጵያዊ፡፡ ስለዚህ አሿሿሙ ወደፊት ለሁሉም እውቀትና ችሎታ ላላቸው ዜጎች ክፍት መሆን አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሴቶችን የሾምነው ታማኝ ስለሆኑ ነው ያሉት ግን አላሳመነኝም፡፡ ሰው ሁሉ ታማኝ ነው በሚል እምነት ነው የሚሾመው እንጂ እንደ ጨው እየተቀመሰ አይደለም፡፡
በሌላ በኩል፤ፓርላማ ሳያጸድቀው አስፈጻሚ አካላትን ማደራጀት የሚያስችለው ሥልጣን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መሰጠቱ ጠቃሚ አይመስለኝም፡፡ የፓርላማውን ተግባር የሚነጥቅ ነው። ፓርላማው የሰዎችን ሹመት ሲያፀድቅ የህዝብ አደራ ነው የሚሰጣቸው፡፡ መከታተል የሚችለውም ራሱ ሹመቱን ያፀደቀለትን ሰው ነው እንጂ በሌላ የተሾመን አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር አካሄዱ ተገቢ አይደለም። ከዚህ ውጪ ለስብጥሩ የተደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ እነዚህ ሚኒስትሮች እንግዲህ ለሁለት አመት (ምርጫ እስከሚካሄድ) የሚሰሩ ናቸው፡፡ በአጭር ጊዜ ብዙ ርቀት ይጓዛሉ ተብሎ ባይጠበቅም፣ በቢሮክራሲ የተተበተቡ ተቋማትን አሰራራቸውን በመፈተሽ ፈታ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች ታይቶ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል። ለምሳሌ የጉምሩክ፣ የንግድ ፍቃድ አወጣጥና አመላለስ-- መጥቀስ ይቻላል። ስለዚህ ሚኒስትሮች ቢሮክራሲውን በሚገባ መፈተሽ አለባቸው፡፡

-----------

            “ተሿሚዎቹ መገምገም ያለባቸው በውጤታቸው ነው”
               አቶ ሞሼ ሰሙ (የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኝ)

    እነዚህ አዳዲስ ሚኒስትሮች ግፋ ቢል የአንድ ዓመት ከ6 ወር ጊዜ ነው ያላቸው፡፡ ምን ተግባር ያከናውናሉ የሚለውም፣ ከዚህ የጊዜ ሰሌዳ አንፃር ነው መታየት ያለበት፡፡ በሌላ በኩል፤ አዳዲስ የተፈጠሩት መዋቅሮች በዚሁ አጭር ጊዜ ውስጥ ምን ሊያከናውኑ ይችላሉ የሚለውንም ለማየት አሁን ያስቸግራል፡፡ አንዳንዶቹ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መታጠፋቸው ተገቢ ነው፡፡ በአብዛኛው አዲሱ አደረጃጀት የተዋቀረበት መንገድ ቴክኒካዊ ነው፡፡ ይሄ ደሃ ሃገር ይሄን ሁሉ ቢሮክራሲ መሸከም አለበት ወይ የሚለው ዋነኛው ሆኖ ቀርቧል። በእርግጥም ሃገሪቱ ድሃ ነች፤ የሰው ኃይልና ገንዘብ ማባከን አያስፈልግም፣ ያለውን የሰው ኃይልና ገንዘብ በተገቢው አሰናስኖ መጠቀም የሚለው ሃሳብ ጠቃሚ ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንድ አስፈላጊ ጉዳዮች በቸልታ የታለፉበትም አደረጃጀት ነው፡፡ አደረጃጀቱ ለኪነ ጥበብ፣ ለባህል፣ ለስነ ጥበብ የሚሰጠው ግምት አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ ባህልና ቱሪዝም እና ስፖርት አንድ ላይ ተደርበው ነው የቀረቡት፡፡ እያንዳንዳቸው ግን ራሳቸውን ችለው ለማህበረሰቡም ሆነ ለሀገር ጠቃሚ ናቸው፡፡ ባህልን በተመለከተ ተፈትሾ ያላለቀ ትልቅ አቅም ነው፡፡ ቱሪዝም ያልተጠቀምንበት ትልቅ አቅም ነው፡፡ እንደ ኬንያ ያሉ ሀገራትን ቀጥ አድርጎ የያዘ ዘርፍ ነው፡፡ ስፖርት ራሱን የቻለ ትኩረት የሚያስፈልገው  ነው፡፡ በዚህ አንድ አመት ተኩል ውስጥ እንዴት በዚህ አደረጃጀት ይመራል የሚለው በቀጣይ የሚታይ ነው፡፡
በዚህ የአደረጃጀትና የካቢኔ ለውጥ ውስጥ ለብሔር ወንበር ከማከፋፈል መወጣቱ የሚበረታታ ነገር ነው፡፡ ሌላው መሰረታዊ ነገር የሴቶች ሚና ከፍ ማለቱ ነው፡፡ አለምንም ያነጋገረ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ህዝቧ ከ52 በመቶ በላይ ሴቶች ይዛ፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በሰፊው እያንቀሳቀሱ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ሆነው ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቶ ነበር፡፡ አሁን ለዚህ ዋጋ ሰጥቶ ሚናቸውን ለማሳደግ የተወሰደው እርምጃ ጠቃሚ ነው፡፡
በዚህ አሿሿም ውስጥ ደካማው ጎን፣ ሀገራቸውን በሙያቸው፣ በእውቀታቸው ማገልገል የሚችሉ የፓርቲ አባል ያልሆኑ ሰዎች ቦታ መነፈጋቸው ነው፡፡ ከፓርቲ አጥር አለመውጣታቸውና ለሙያተኞች እድል አለመሰጠቱ ብዙዎች ሀገራቸውን ለማገልገል ተስፋ ያደረጉ ሙያተኞችን ተስፋ የሚቀንስ ነው፡፡ የመጀመሪያ መስፈርት ኢህአዴግ መሆኑ ወደ ኋላ እንደተመለስን ነው የቆጠርኩት፡፡ የሴቶቹን አሿሿምንም ስንመለከት፣ ኢህአዴግ መሆናቸው ነው የሚታየው፡፡ አንዱ ደካማ ጎን ይሄ ነው፡፡
በቀጣይ ግን እነዚህን ሰዎች በውጤትና በስራቸው መገምገሙ ነው ጥሩ የሚሆነው፡፡ አሁን ይችላሉ አይችሉም ብሎ ፍርድ ውስጥ መግባት ተገቢ አይደለም፡፡ መገምገም ያለባቸው በሚያመጡት ውጤት ነው መሆን ያለበት፡፡ ኢህአዴግ በዚህ የካቢኔ ለውጥ የሴቶች ቁጥር መጨመሩ ነው እንጂ ወጣ ያለ አዲስ ነገር አላሳየንም፡፡
 ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ እንኳ ለአራት ጊዜያት ያህል ሹም ሽር ተደርጓል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ነጥሮ ወጥቶ በህዝብ የተመሰገነ ተሿሚ ማግኘት አልተቻለም፡፡ አዲሶቹ ተሿሚዎች ለሀገራቸው ታማኝ ሆነው እንዲሰሩ ነው የምመኘው፡፡

-------------

             “በዚህ መጠን ሴቶች ወደ ካቢኔ መምጣታቸው ትልቅ ለውጥ ነው”
               ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (አንጋፋ ፖለቲከኛ)

    ሴቶች በዚህ መጠን ወደ ካቢኔ መምጣታቸው ከዚህ በፊት ያልነበረ፣ ነገር ግን በጣም አስፈላጊ ለውጥ የተደረገበት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አስተዋፅኦዋቸው አነስተኛ ነበር፡፡
አሁን ግማሽ በግማሽ ሴቶች መደረጋቸው በጣም አስፈላጊ እርምጃ ነው፡፡ ለሀገሪቱ መጪ የፖለቲካ ሁኔታም በብዙ መንገድ ጠቃሚ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ካቢኔ ባስተዋወቁበት ወቅት ካቢኔያቸው የሚመራበትን ስነ ምግባርና የስራ አካሄድ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተናግረዋል፡፡ በቃላቸው መሰረት ተፈፃሚ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የስራ ውጤቱንም በዚህ ተስፋ ውስጥ ሆነን እንጠብቃለን፡፡

Read 4164 times