Saturday, 19 May 2012 10:42

በቆሻሻ ላይ የተጀመረው ዘመቻ - በድሬ!

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

በድሬዳዋ ከተማ በቀን 98ሺ ኪሎ ቆሻሻ ያመነጫል

ፍሳሽ ቆሻሻዎች እየደረቁ ለተፈጥሮ ማዳበሪያነት ይውላሉ

አዲስ አበባን ጨምሮ ከክልል ከተሞች ሁሉ በጽዳታቸው ከሚጠቀሱት ጥቂት የአገሪቱ ከተሞች አንዷ ናት - ድሬዳዋ፡፡ ተፈጥሮ የለገሰቻት አሸዋማ መሬቷ የከተማዋን ጽዳት በመጠበቆ ረገድ የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ አሁን አሁን በበርካታ ከተሞች እየተለመደ የመጣው የኮብልስቶን መንገድ ሥራ ጀማሪ እንደሆነች የሚነገርላት ከተማዋ፤ ዋናው የአስፋልት መንገዷም ሆነ የውስጥ ለውስጥ መንገዶቿ ሁሌም ፅዱ ናቸው፡፡

ከተማዋ በስፋት የምትታወቅበት ጫት እንኳን ገረባው እንዲሁ በዘፈቀደ በየሜዳው ተጥሎ አይታይም፡፡ ቆሻሻው በአግባቡና በተገቢው ሥፍራ ይጣላል፡፡ የከተማዋን የቆሻሻ አወጋገድ ሥራ የማየት እድል ከሰሞኑ ገጥሞን ነበር፡፡ KFW በተባለ የጀርመን ልማት ተራድኦ ድርጅት እርዳታ በ12.8 ሚሊዮን ብር ወጪ በ1998 ዓ.ም በተሰሩት ሁለት የፍሳሽና የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታዎች ቆሻሻዎቹ በአግባቡ እንዲወገዱ ይደረጋል፡፡

ለከተማው እጅግ ቅርብ በሆነ ቦታ ላይ በመኖሪያ ቤቶችና በትምህርት ቤቶች መሀል ላይ ከቀብር ሥፍራዎች ጋር ተጠግቶ ለ50 ዓመታት የቆሻሻ መጣያ ሆኖ ያገለግል የነበረውን ቦታ ሙሉ በሙሉ ሥራውን እንዲያቆም በማድረግ፣ ቆሻሻው በአዲሱ የመጣያ ሥፍራ እንዲጣል ከተደረገ ሰነባብቷል፡፡

የቀድሞው የቆሻሻ መጣያ ሥፍራ ላይ እንደተራራ የተከረመውን ቆሻሻ ወደ አርቴፊሻል ተራራነትና የመዝናኛ ሥፍራነት ለመቀየር ጥናት ተደርጐ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ባጀት ተመድቦለታል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ የጽዳትና ውበት ኤጀንሲ ከፍተኛ የቆሻሻ ማኔጅመንት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሽመልስ ዘውዴ፤ በጀርመን ልማት ተራድኦ ድርጅት የተሰራው ሳንተሪ ላንድ ፊል/ የቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራ/ ሁለት ዋና ዋና ጠቀሜታዎች አሉት ይላሉ፡፡ የቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራው ከሥር በሸክላ አፈር ተጠቅጥቆ የተሰራ በመሆኑ ወደ መሬት ውስጥ የሚገቡ በካይ ነገሮች እንዳይኖሩ ያደርጋል፡፡

ከቆሻሻ የሚመነጩና የሚሟሙት ንጥረ ነገሮች ወደ መሬት ውስጥ ሠርገው በመግባት የከርሰምድር ውሃን ይበክላል፡፡ ይህንን ችግር ለማስቀረት የተሰራው ሥራ እጅግ አስተማማኝ ነው፡፡ የላንድፊሉ ሌላው ጠቀሜታ ቆሻሻ ዝም ብሎ ሲጣል የሚያመነጨውና ለአካባቢ ብክለት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርገው ሚቴን የተባለው ጋዝ እንዳይፈጠር በማፈንና ቆሻሻው እዛው እንዲብላላ በማድረግ ውሃውን ለብቻው የማስወገድ ሥራ ይሰራል፡፡

ከከተማዋ በየቀኑ ዘጠና ስምንት ሺ ኪሎ ግራም ቆሻሻ እንደሚመነጭ የሚናገሩት አቶ ሽመልስ፤ ከዚህ ውስጥ 52% የሚሆነው ቆሻሻ በአግባቡ እንዲወገድ እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡ የቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራውን ለመጐብኘት በሥፍራው በተገኘንበት ወቅት፣ እጅግ በሚያስገርም መልኩ አንዳችም ሽታና መጥፎ ጠረን በአካባቢው አልነበረም፡፡ በ32 ሴሎች እየተከፋፈለ የተሰራው የፍሳሽ ማስወገጃ ሥፍራው፣ ከከተማው የሚሰበሰበው ፍሳሽ ቆሻሻ ይጠራቀምበትና ለሃያ አንድ ቀን በፀሐይ ሃይል እንዲደርቅ ይደረጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፍሳሹን እየመጠጠ በሌላ የማጠራቀሚያ ሥፍራ እንዲጠራቀም በሚያደርግ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ደረቅ ቆሻሻውን የማውጣቱ ሥራ ይካሄዳል፡፡

ለሃያ አንድ ቀን በፀሐይ ሃይልና በውሃ መምጠጫው ቴክኖሎጂ ታግዞ የደረቀው ቆሻሻ (አይነምድር) በማህበር በተደራጁ ወጣቶች ተሰብስቦ ለተፈጥሮ ማዳበሪያነት እንዲውል ይደረጋል፡፡ ይህንን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ እየሰሩ እንደሚገኙና ለጊዜው በማህበር የተደራጁት ወጣቶች የሚያመርቱትን የተፈጥሮ ማዳበሪያ የከተማዋ የጽዳትና ውበት ኤጀንሲ ከተማዋን ለማስዋብ ሥራና ለግሪን ኤሪያዎች እየተጠቀመበት እንደሚገኝ አቶ ሽመልስ ተናግረዋል፡፡

በማህበር የተደራጁት ወጣቶች ለተፈጥሮ ማዳበሪያነት የሚውለውንና የደረቀውን ዓይነምድር የሚሰበስቡበት መንገድ ጥንቃቄ የጐደለውና እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ያለአንዳች መከላከያ በባዶ እግራቸው የደረቀው አይነምድር ላይ እየቆሙ፣ ጓንት አልባ በሆነ እጃቸው ሲሰበስቡ ማየቱ ያሳቅቃል፡፡

ይህ ሁኔታ የኮሶ ትልን ጨምሮ ሌሎች በአይነምድር አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ ሊተላለፉ በሚችሉ በሽታዎች የመያዝ እድልን በእጅጉ ከፍ ያደርገዋል፡፡ የከተማው የጽዳትና ውበት ኤጀንሲም በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊያስብበትና አፋጣኝ እርምጃ ሊወስድበት ይገባል የሚል አምነት አለን፡፡

ኤጀንሲው በሁለት የመንግስትና አንድ የግል የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ መኪናዎችና በአምስት የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃዎች እየታገዘ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሽመልስ፣ ለሁለት መቶ ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንና ከጤና አኳያ ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሥራ እየሰሩ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

ቆሻሻውን ለይቶ እንደገና በጥቅም ላይ እንዲውል የማድረግ ሥራ እንዳልተሰራ የሚናገሩት አቶ ሽመልስ፤ ቆሻሻን ከቤት ጀምሮ የመለየቱን ሥራ እንዲሰራ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጡ ተግባር ላይ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡ “በካዮች ይክፈሉ” በሚለው መርህ፤ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርና ቴሌኮሚኒኬሽን እንዲሁም የተለያዩ መጠጥ አምራች ድርጅቶች ለከተማዋ ፅዳት የበለጠ አስተዋፅኦ የማድረጉን ሥራ ተግባራዊ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን አቶ ሽመልስ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ የጫት ተጠቃሚዎች ብዙ ቢሆኑም የጫት ገረባ በየቦታው ተጥለው አይታዩም፡፡ ይልቁንም ሰዎች ህይወታቸውን የሚመሩበትና ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩበት የገቢ ምንጭ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ሃይረዲን ከድር፤ በጫት ገረባ ሽያጭ ቤተሰቡን ያስተዳድራል፡፡ አምስት ልጆቹን፣ ባለቤቱንና አንድ የእህቱን ልጅ ጨምሮ ስምንት ቤተሰቦቹን በዚሁ ሥራ እያስተዳደረ ነው፡፡ ክረምት ከበጋ በማይነጥፈውና እሱ በቂ ነው በሚለው የጫት ገረባ ሽያጩ ልጆቹን እያስተማረ ነው፡፡

በከተማዋ የተለያዩ ሥፍራዎች ቋሚ ደንበኞች እንዳሉትና በየዕለቱ እየሄደ የጫት ገረባዎቹን በመሰብሰብ ለሆቴሎች፣ ለሬስቶራንቶች፣ ለእንጀራ አቅራቢ ማህበራት እንደሚሸጥና በዚህም ህይወቱን በመምራት አመታት ማስቆጠሩን አጫውቶኛል፡፡ የዚህ ሰው ተግባር ከተማዋን ከቆሻሻ ከማፅዳቱም በላይ ህብረተሰቡ ለማገዶ ፍጆታ ደን በመጨፍጨፍ አካባቢውን እንዳያራቁት መጠነኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ በአጠቃላይ ከተማዋ በቆሻሻ አወጋገድ ሥራ ላይ እያከናወነች ያለው ተግባር የሚበረታታ ቢሆንም በቆሻሻ አወጋገድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጐችን ጤና መጠበቅና ቅድሚያ ጥንቃቄ ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

 

 

 

Read 2613 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 10:48