Saturday, 19 May 2012 10:54

ባጐረስኩ….

Written by  አንድነት ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

በመንገድ ስንሄድ ነው፡፡ አንድ ህጻን ያለቅሳል፡፡ ቢበዛ አስራ ሶስት ወይም አስራ አራት አመት ቢሆነው ነው፡፡ በእጁ የፕላስቲክ ጐድጓዳ ሰሃን ይዟል፡፡ ምርር ብሎ ያለቅሳል፡፡ ከግንባሩ ስር ካሉ ትናንሽ አይኖቹ የሚፈልቀው እንባ የማይነጥፍ ምንጭ ያለው ይመስላል፡፡ የሚፈልቅባቸው ቀዳዳዎቹም በጭራሽ እነዛ ትንንሽ አይኖቹ አይመስሉም፡፡ የሚመነጩትም ከዛ ስንጥር ሰውነቱ መሆኑ ያጠራጥራል፡፡ እሱ ቢጨመቅም ሰውነቱ ያን ያህል ፈሳሽ የሚኖረው አይነት አይደለም፡፡ ብቻ እንባው ይንዶለደላል፡፡ ከእግሩ ስር ሽንብራ ተደፍቷል፡፡ የያዘው ሰሃን ስር ትንሽ ሌላ መስፈሪያ እቃ አለች፡፡ “የሚሸጠው ቆሎ ተደፍቶበት ነው” አለ አጠገቡ ጋ ያለ - በሁሉ ነገር እኩያ ሚሆነው በእድሜም፣ በሰውነትም፣ በአለባበስም፡፡ ለሚመጣው ሁሉ ይህንን ያውጃል፡፡

ሰው አምስት፣ አስር፣ ስሙኒ ሳንቲሞች አንዳንዴም ብር ፕላስቲኩ ላይ ያስቀምጣል፡፡

ሌላ ገዘፍ ያለ በሰላሳዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኝ የሚመስል ወጣት “ወጣ ወጣ አድርጉ፤ የማትረዱት ከሆነ አትክበቡት” ይላል፡፡

ከከበቡት መንገደኞች ግማሹ ተጠራጥረዋል፡፡ “ልጁስ እሺ ይሄ ወጠምሻ ምን መሆኑ ነው…” እርስ በእርስ ይጠያየቃል፡፡

“እሱም በሚችለው መንገድ እየረዳው ነዋ፡፡” አለ ከመጀመሪያው ጀምሮ ነበርኩ የሚል ሰው፡፡

“እስካሁን የተሰበሰበው አይበቃህም” ሌላው መሃል ሰፋሪ፡፡

“ሰሃን ሙሉ እኮ ነው የተደፋው” መለሰ እኩያው - እንደ የኢኮኖሚ አማካሪ እየቃጣው፡፡ ቀጥልበት/በሚል አይነት፡፡ ተደራድሮ በሚሸጥ ሰው ሁኔታ ወይም የደፋውን ሰው ይዞ ለማስከፈል በሚከራከር ሰው አይነት፡፡

“ወይ የኔ ልጅ/ይሄኔ የላከችው እናቱ ስንት ትጠብቃለች” ዘንቢል የያዙ፣ ነጠላ የደረቡ እናት ናቸው፡፡

ህጻኑ የተሰበሰበውን ብር ለመመዘን አይኖቹን እንደጨፈነ እጆቹን ወደ ፕላስቲኩ ሰደደ፡፡ ብሮቹ ጥቂት ናቸው፡፡ ከአስር ላይበልጡ ይችላሉ፡፡ መቼም ከዛ ውስጥ ድፍን አስር ወይም አምስት ብር እንደማይኖር ገብቶታል፡፡ ምክንያቱም ለቆሎ ያን ያህል የሚሰጥ ሰው የለም፣ ከሰማይ የወረዱ የዛ አይነት ሰዎች ደግሞ እንዳልቀረቡት ያውቃል፡፡

አምስት እና አስር ሳንቲሞች ናቸው የሚበዙት፡፡

ዙሪያውን ያሉ ጐረምሶች በእጁ ሚያደርገውን አይተው ሳቁበት፡፡ ልጁ የገንዘቡን ማነስ ሲያረጋግጥ ኡኡታ ከጀለው፡፡ ምርር ብሎ ለቅሶውን ገፋበት፡፡

“ምን ያድርግ እውነቱን እኮ ነው፡፡ በአሁን ገበያ ይሄ የተሰበሰበው አንድ ኪሎ ሽንብራም አይገዛ” ከመሃል ሌላ ሴት፡፡

“ቆይ ሰው አሁን አምስት ሳንቲም ምን ያደርጋል ብሎ ነው የሚሰጠው?“ ወጠምሻው

“እንደውም ሰው ለምዶበት ነው እንጂ አሁን ጭራሽ የሚረዳዱበት ዘመን አይደለም” ሌላው

ሰው ይመጣል፤ ያዘነው፣ አስር ሳንቲም፣ ስሙኒ  ይጥላል፡፡

በእርግጠኝነት የተሰበሰቡትን ሳንቲሞች የልጁ እንባ ዘለላዎች በቁጥር ይበልጧቸዋል፡፡

ልጁ ለቅሶው እየባሰበት ሄደ፡፡ ተሰብሳቢውም ግማሹ ሲጠራጠር፣ ያዘነውም አስር ሳንቲም፣ አምስት ሳንቲም ሲሰጥ ጀምበሩዋም ልታዘቀዝቅ ሆነ፡፡

በህጻኑ፣ በተመልካች እና በጀምበር መካከል ያለውን ፍጥጫ የምታረግብ ድንገት የህጻኑን እንባ ያስቆመች ሴት መጣች፡፡ ጉርድ ቀሚስ ከኮት ጋር ለብሳለች፡፡ የተተኮሰችው ፀጉሩዋ ትከሻዋ ላይ ተኝቷል፡፡ ጉርድ ቀሚሷ ያጋለጠው ባትዋ ቅላቷን ሃዘን ከዳበሰው ፊቷ ይልቅ ያውጃል፡፡

በራስ መተማመን በተሞላበት ወደ ልጁ አመራች “አንተኮ ለስራ እድሜህ ገና አልደረሰም” ብላ ብር በእጁ አስጨበጠችው፡፡ ህጻኑ ከሁሉም በላይ ግድ ያለው (ከለስላሳ እጁዋ…ከሽቶዋ ይልቅ) የብሩ መጠን ነው፡፡ በቅጽበት እንባ መርጨት ያቆሙ አይኖቹ አዩ፡፡ ሃምሳ ብር ነው፡፡ ቢጫ፣ ሰፊ የኢትዮጵያ ብር፡፡

“እሰይ እመቤቴ” አሉ ባለዘንቢሉዋ አሮጊት - የልጁ ለቅሶ ማቆም በዋዛ እንዳልሆነ ገብቷቸው፡፡ እስካሁን ስንቱ ሲሰጠው እንኳን ሊያቆም መቼ ለቅሶውን ቀነስ አደረገና፡፡ በእርግጥ አለባበሷና ሙሉ ሁኔታዋ ሌላ ምስክር ነው፤ እንባ ማበስ እንደማይሳናት፡፡

“ካልተያዙ ሌብነትም ስራ ነው ተብሏል”ቀጠለ ተጠራጣሪ፡፡

እንባውን ያበሰችው ሴት ድንገት ሃሳብ መጣላትና የተደፋውን ቆሎ በጫማዋ ከመሬቱ ጋር ታሽ ጀመረች፡፡ በአንድ በኩል መሬቱን አዳርሳ በሌላው በኩል ትዞራለች፡፡

“ዋጋውን ከፍላለች እንደፈለገች ታድርገው” አለ አንዱ የህጻኑን በሚረገጠው ቆሎ ዙሪያ የሚቁለጨለጩ አይኖች አይቶ፡፡

“አፍሰው ለሌላ ሊሸጡት ይችላሉ” ደገፈ ወጠምሻው፡

“ይህማ ለጤናም ጥሩ አይደለም” ተቀብሎ ሌላው

በዚህ መሃል አንድ የጦፈ ድምጽ ያሰማ ጥፊ በሴቷ ላይ አረፈ፡፡ የተነሰነሰ ፀጉሩዋን ከፊቷ ጋር የሚያጣብቅ አይነት፡

“የሚበላ እህል እኮ ነው” ጥፊውን ያሳረፈው ጐልማሳ…በጥፊው ግራ ለተጋባው የተመልካች ክፍል በማብሪሪያነት፡

“ነውር እኮ ነው፡፡ እህል አይረግጥም” ባለዘንቢሏ አሮጊት፡፡

“የሰው ጤና ይበልጣል” ለጥፊው ተቃውሞ

“ቢበላውም የባሰበት ነው” ለጥፊው ድጋፍ

የተሰበሰበው ሰው በሃሳብ ተለያየ፤ ባለሀምሳ ብሩዋ ጥፊው በፈጠረባት ብዥታ ውስጥ ትዋኛለች - ደግሞ በተራዋ ጤናዋ ተደፍቶባት፡፡

 

 

Read 3471 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 10:59