Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 19 May 2012 11:00

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ቡናው ፈላ፡፡ የሚጠበቀው ሰው አልመጣም፡፡ አደፍራሽ ካለ ንፁህ ውሃ መጠጣት ያዳግታል ይላሉ፡፡ ውሃውን ማን ደፍርስ አለው? የማንም ደካማ ውሃ በደፈረሰ፡፡ ቡናና ወሬ መችም ቦላሌና ዚፕ ናቸው፡፡ ቦላሌው ሃፍረት መሸፈኛ፡፡ ቦላሌዎች ሁሉ ደካማ ባለቀዳዳ ሊከዱ ያኮበኮቡ፡፡ ዚፑም ይኼን የድክመት ሃፍረት መሸፈኛ፡፡ መሸፈኛ በመሸፈኛ፡፡ ስለሌላ ስለሌላ ይወራል፡፡ ቄንጠኛ ቁጭ በሉ፡፡ በስንዴው ምርት አፍሮ ስለ ዘንጋዳ እያደነቀ እንደሚያወራ መንግስት፡፡ ቆቅ ወዲያ ምዝግዝግ ወዲህ፡፡

“እናንተዬ ለምን በጉራማይሌ ታወራላችሁ?”

“ለምዶብን” አለ ልጁ

“ለምን አስለመዳችሁት?” አሉ መልሰው፡፡

“አይገል ምናለ?” አለች ልጅቷ፡፡

“ምን የመሰለ ቋንቋ እያላችሁ ተአማርኛው ጋር ጉራጊኛ ብትቀላቅሉ ትግርኛ፣ ወረሞ ብትቀላቅሉ አይሻልም?”

“እስዋን ጠይቂያት” አለች ልጃቸው፡፡

“ምኑን?”

“ጉራጊኛ መቀላቀሉን”

“”ጉራጌ ናት እንዴ?”

“አልነገረሽም እሱ?”

“ኧረ ትዝ አይለኝም”

ትዝ ብሎአቸዋል፡፡ አድንቆ የማይጀመር ወሬ የሚፈዝም መስሎአቸው ነው፡፡ ግን አልቀናቸውም፡፡ አመላለሳቸው ክፈፍ ይጐለዋል፤ ድምፃቸው ንቀትና ሸካራነት ያነገበ ነው፡፡

“ጉራጌ ድንቅ ሰው ነው…እነሱ ባይኖሩ ፈረንጅ ይገለን ነበር”

“ጉራጌ አልወድም ስትይኝ አልነበረም” አለች ልጃቸው፡፡

እናቷ ተናደዱ፡፡ ይኼቺ ልጅ የልጃቸው እጮኛ ናት፡፡ የወደዳትን ሴት ጐጥ እያጥላሉ ሊያርቋት አይፈልጉም፡፡ ከማራቅ ደሞ ዋርሳን መለጐም፣ መጋለብ ይሻላል፡፡ ነፋስ ደሞ ለማንም ጤነኛ ነገር ነው፡፡

“አልወጣኝም እቴ…ደሞ…ጉራጌ ነገር አይወድም ሥራ ነው፡፡ ጉራጌ ይረዳዳል፡፡ ሰው አይመርጥም…ትንሽ ገንዘብ ይወዳሉ…ገንዘብ የሚወድ ሰው ደሞ ጥሩ አይደለም”

“ገንዘብ ማን ይጠላል?” አለች እንግዳዋ ልጅ፡፡

ደብሪቱ ኰስኰሶአቸው ሊቀጧት ፈለጉ፡፡ ቢያንስ ቅጣት መሰላቸው፡፡

“እኔ እውነቴን ነው…አንዴ እዚህ የሚቆፈር ጉድጓድ ነበረኝ፤ ሠራተኛ ስፈልግ አንዱ ጉራጌ መቼም እነሱ ሥራ ይቀናቸዋል ሲቅለበለብ መጥቶ ካልሰራሁ አለ፡፡ ተአለባበሱም ከዐይኑም መቁለጭለጭ ደሐ መሆኑን አይቼ እሱም እንዲጠቀም በል ስራልኝ አልኩትና በአምስት ብር ተዋዋልን፡፡ ትራክተር አይሰራውም የሰራውን ሥራ፡፡ ዕውነቴን ነው የምለው፡፡ ምጥማጥ እንደዚያ አትምስም…ከጨረሰ በኋላ “የተዋዋልነው አሥር ብር ነው” አይለኝ መሰላችሁ…” ለአንተ ስድስት ላድርግልህ ብለው “ሞቼ እገኛለሁ…አይሆንም” ብሎ ቀበሌ ወረደ፡፡ ሔጭ እንደው እኔ…ከማንም ጋር እነዚህ ሰዎች ጋ አልወርድም ብዬ…ቢበላው እንኳን አንጀቱ ጠብ እንዳይል ረግሜ የዋሸውን ሰጠሁት፡፡ ዘረፈኝ ልበል እንጂ፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው እባክሽ?...መንገድ ላይ በድጋፍ ሲሄድ አግኝቼው እንደው ለወሬ ጠጋ ብዬ ብጠይቀው …አፍሮኝ እሱ እንኳን አልተናገረም… “መኪና ገጨው” አሉኝ…እውነቴን ነው አዘንኩ…በልቤ የኔ ጡር ይሆናል እያልኩ…ይኼን ወሬ እንኳን ያመጣሁት…”

ወላ የልጃቸውን እጮኛ እንኳን አይምሩም፡፡ ግን እቤታቸው ግቢ ጉድጓድ አስቆፍረው አያውቁም፡፡ የልጃቸው እጮኛ ተረበሸች፡፡ ታሪኩ የተዋቀረ ቀስት ሆኖ በላይዋ ላይ እንደሚያንዣብብ ሲገባት እዚህ መምጣቱና ቡና መጠጣቱ ቅር አላት፡፡

ልጁ፤ “ዝም ብለሽ ነው እማማ” አለ

“አየሽ…..” አሉ ወደ ልጅቷ ዞረው፡፡

(“ሕማማትና በገና” ከተሰኘው የአዳም ረታ አዲስ የአጭር ልብወለዶች መድበል የተቀነጨበ)

 

 

 

Read 5852 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 11:05

Latest from