Print this page
Monday, 12 November 2018 00:00

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከአዲስ አድማስ ጋር … (ስለ ለውጡ … ምን ይላሉ?)

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 ከ7 አመታት የአሜሪካ የስደት ኑሮ በኋላ ባለፈው ሐሙስ ወደ ሀገራቸው የተመለሱትን የህግ ባለሙያና ፖለቲከኛ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ብዙዎች “የፅናት ተምሳሌት” ያደርጓቸዋል። ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም “ብርቱካን የፖለቲካ ነጋዴ አይደለችም” ሲሉ በአደባባይ አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡ ወ/ሮ ብርቱካንስ ምን ይላሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በትላንትናው ዕለት፣ በተጣበበ የጊዜ ሰሌዳ፣ በአጭሩ አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-

    የተደረገልዎትን አቀባበል እንዴት አገኙት?
የሠፈሬ ልጆች ለየት ያለ፣ የደመቀ አቀባበል አድርገውልኛል፡፡ ደስ ብሎኛል ብል አይገልፀውም። ስሜቱ ከቃላት በላይ ነው፡፡ በእርግጥ የኛ አካባቢ ማህበራዊ ትስስር እጅግ ጠንካራ ነው፡፡ ውጭ ሀገር ስትሆን ሀገር ይናፍቃል፡፡ የአካባቢዬን ልጆች ደስታቸውን ማየት፣ ለኔ ትልቅ እርካታ ነው፡፡ የናፍቆት መወጪያም ነው፡፡
አሜሪካ ከሄዱ በኋላ ድምፅዎ አልተሰማም …?
ከውጭ ሀገር ሆኖ በሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እምነት የለኝም፡፡ ራሴን በዚያ ሁኔታ አስቀምጬ፣ የምሠራው ነገር ብዙም አልታየኝም፡፡ ሀገር ቤት ያለው የለውጥ ሂደት አካል ሳልሆን .. ውጭ ሆኜ የማደርገው ነገር ብዙም አላሳመነኝም ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ 4 አመታት ደግሞ በትምህርት ነው የጠፉት፡፡ ልጅ የማሳደግ ኃላፊነትም ነበረብኝ፡፡ ከዚህ አንፃር ነው የጠፋሁት፡፡
ዶ/ር ዐቢይ “ብርቱካን የፖለቲካ ነጋዴ አይደለችም” ሲሉ ምን ተሠማዎ?
ዶ/ር ዐቢይን የሚያህል የሀገር መሪ፣ በስም ጠርቶ፣ ላደረግከው አስተዋጽኦ እውቅና ሲሰጥ በጣም ደስ ይላል፡፡ እኔ ደግሞ ፊት ለፊት በሚዲያ ወጥቼ አልናገር ይሆናል፡፡ ነገር ግን አንድም ቀን ስለ ሀገሬ ከማሰብ ወደ ኋላ ብዬ አላውቅም፡፡ ሀገሬ ላይ የሚሆነውን ነገር ከመከታተል አልቦዘንኩም። በአጠቃላይ ከስቃዩ አልዳንኩም፡፡ የራሴ ጓደኞች፣ የማውቃቸውም የማላውቃቸውም መልሰው ሲታሰሩ፣ ህፃናት ወጣቶች ሲገደሉ፣ ሲታሰሩ … የህመሙ መጠን እንደኔ ባለ ሰው ላይ ይበረታል፤ ምክንያቱም ያለፍኩበትን ነገር ያስታውሰኛል። እነ ዶ/ር ዐቢይ ያንን ምዕራፍ ለመዝጋት መሰጠታቸውን ማሳየታቸው፣ ሃሳባቸውን መግለፃቸው … እንደገና እኔን ለመሰሉ ለሠብአዊ መብት መከበር ለተሰለፉ  ግለሰቦች እውቅና መስጠታቸው … ለኔ በጣም ትልቅ የመንፈስ መታደስ ነው፡፡ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ያን አባባላቸውን አክብሬያለሁ፣ አድንቄያለሁ፡፡
ለውጡ ከታገለሉት አላማ አንፃር የሚያረካ ደረጃ ላይ ደርሷል ይላሉ?
የሚያረካ ደረጃ ላይ አይደለም፡፡ በአጭር ጊዜም የሚያረካ ይሆናል የሚል እሣቤ የለኝም፡፡ በጣም የተረጋጋ የ100 አመታት የዲሞክራሲ ልምምድ ያላቸው ሀገሮች፤ ስርአቶቻቸው ተቋሞቻቸው ሁሌ የሚሻሻል ነገር አላቸው፡፡ እና ሁልጊዜ ሂደቱ የሚያቋርጥ አይደለም፡፡ ካለፈው 10 ዓመታት አንፃር አሁን ወደፊት ሊያስኬደን የሚችል በር ተከፍቷል፡፡ እድሉ አለ ብዬ ማሰቤ ነው ተስፋ የሚሰጠኝ፡፡ ለመስራት እድሉ መኖሩ ነው እንጂ የተቋማት ግንባታ … ገና ከዜሮ የሚጀመር፣ በርካታ ሂደትና ልፋት የሚጠይቅ እንደሆነም እረዳለሁ፡፡
ወደ አገር ቤት ሲመጡ በምን ዓይነት ስሜት ውስጥ ነበሩ?
ስጋት የኖራል፡፡ ከህግ የበላይነት፣ ከሰላምና መረጋጋት አኳያ ብዙ ስጋቶች እንዳሉ እያየን ነው። ግን እነዚያ ስጋቶች በአንድ በኩል እያደጉ፣ በሌላ በኩል ለመሻሻል እድሉ እያለ … በእነዚያ ስጋቶች ተውጠን ከቀረን፣ እንደ ሃገር ማፈርም ያለብን ይመስለኛል፡፡
ምክንያቱም እድሉ ካለ እነዚያን ስጋቶች አንቆ ማስቀረት ይቻላል፡፡ ተቋማትን ገንብቶ ዲሞክራሲን በማሳደግ፣ እነዚያን ስጋቶች መቅረፍ የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችን መሬት ላይ አውርዶ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ባለፉት ወራት እንደሆነው፤ መልካሙ ነገር በአንድ በኩል እያበበ ሲሄድ፣ ስጋቱም በዚያው ልክ እያደገ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ግን ወደ ኋላ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ እድሉን እየተጠቀሙ፣ ስጋቱንና መጥፎ አንድምታውን መቀነስ የሚቻልበት ሁኔታ አለ፡፡
ወደ ሃገር ቤት የመጡት አቅደው ነው ድንገት?
ብዙ ጋዜጠኞች ይሄን ይጠይቁኛል፡፡ ከመንግስት ጋር ውይይት ነበረኝ፡፡ ውይይቱም ለውሳኔዬ በጣም ረድቶኛል፡፡ እንደገና ይሄ ሃገሬ ነው፤ ቤቴ ነው፡፡
በርካቶች “የፅናት ተምሳሌት” መሆንዎን ይናገራሉ፡፡ ፅናትዎ ከምን የመጣ ነው?
እኔ ሁልጊዜ ለምወደው ነገር፣ ለምወደው ሃሳብ መቆሜን፣ ፅናት የሚጠይቁ ነገሮችን ማድረጌን፣ ማድረግ ካልቻልኩ ደግሞ ለማድረግ መሞከሬን ነው የማውቀው፡፡ ያደረግሁት ማድረግ ያለብኝን ነገር ነው፡፡ ሳላደርግ የቀረሁትን ደግሞ ለማድረግ ለወደፊት ጠንክሬ እሰራለሁ፡፡ ይሄ ከምን የመጣ ነው ላልከኝ … ከብዙ ነገር የመጣ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ነው ብዬ መናገር የምችል አይመስለኝም፡፡ እዚህ አካባቢ (ፈረንሳይ ለጋሲዮን) ነው ተወልጄ ያደግሁት፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ቦታ ብቻ ነው የኖርኩት፡፡ አንድም ፈረንሳይ ለጋሲዮን ነው፤ አንድም ቃሊቲ ነው፡፡ ሁለት አድራሻ ብቻ ነው የነበረኝ፡፡
እዚህ በምኖርበት ጊዜ (ፈረንሳይ ለጋሲዮን) ለወገን ለጐረቤት ማሰብ፣ የቻልከውን ድጋፍ መስጠት፣ መተጋገዝ … በጣም የለመድነው ነገር ነው፡፡ ጉድለትን አይቶ እርስ በእርስ መደጋገፍ የኖርንበት ነው፡፡ እኔን የቀረፀኝ የኖርኩበት ማህበረሰብ ነው፡፡
አባቴ ትምህርት ቤት ሄደው አያውቁም፣ ብዙም ሃብት የላቸውም፤ ግን በምንኖርበት አካባቢ ላይ ማንኛውንም ችግር ሲያዩ፣ ልክ ግዴታቸው አድርገው ነው ለመፍታት የሚንቀሳቀሱት፡፡ የሚችሉትን በታማኝነት ማገዝ አስተምረውኛል፡፡
የእነሱን አርአያነት፣ በጐነት፣ መልካምነት … እያየሁ የመንፈስ ቅናት እያደረብኝ ነው ያደግሁት፡፡ የኔ የህይወት አርአያ ይሄ ነው። የቀለም ትምህርት ደግሞ የሚሰጠን የራሱ ነገር አለ፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ መሻት፣ ፍቅር ካለህ … የፈለግኸውን ነገር ለማግኘት ፅናትን ይፈጥርልሃል። ከዚህ በተለየ ግን በራሴ ላይ የተለየ ፅናት አላይም፡፡


Read 3849 times Last modified on Saturday, 10 November 2018 12:54