Saturday, 17 November 2018 11:22

የእናት ጡትን ማለብና ወተቱን በጥንቃቄ ማስቀመጥ…

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)


    በቀን ውስጥ ውሎዎን ለመወሰን ከሚያስቸግሩ ሁኔታዎች መካከል ጡት የሚጠባ ልጅ በቤት ውስጥ ትቶ መሄድ አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም ወደስራ ወይንም የማይቀርበት ሌላ ጉዳይ ሊገጥም ይችላል፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ልጅዎ እንዳይራብ ወይንም ገና ስድሰስት ወር ሳይሞላው ሌላ ተጨማሪ ምግብ እንዲወስድ ላለማስገደድ የሚረዳዎ የእናት ጡት ወተትን አልቦ በማስቀመጥ በቤት ውስጥ ያሉ ተንከባካቢዎች እንዲመግቡት ማድረግ ነው። ይህን ማድረግ ከተቻለ ልጁ የእናት ጡት ወተትን ሳያቋርጥ እንዲጠባ ማድረግ ይቻላል ማለት ነው፡፡
የእናት ጡት ወተትን ለማለብ እንደቅድመ ሁኔታዎች የሚቀመጡ ነገሮች አሉ፡፡
በመጀመሪያ እጅን በሳሙናና በውሀ በደንብ መታጠብ…ምናልባት ሳሙናና ውሀ ባይኖር እንኩዋን አልኮሆል ያለባቸው የጽዳት መገልገያዎች እስከ 60 % የሚሆን አልኮሆል ስለሚኖራቸው በዛ መጠቀም ይገባል፡፡
የጡት ወተት ለማለብ የተዘጋጁበትን አካባቢ እና የሚገለገሉባቸውን እቃዎች በደንብ የጸዱ መሆኑን አስቀድሞ ማረጋገጥ ይገባል፡፡
ልጅዎ ጡት ሳይጠባ ወተት እንዲፈስልዎት ወይንም ወተቱን ለልጁ አልቦ ለማስቀመጥ ሲያስፈልግዎ፤
ልጅዎን በሚመለከት የሚወዱት ነገር ካለ ማሰብ…የልጁን ፎቶ ወይንም የሚለብሰውን ልብስ ወይንም ከልጁ ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ የሚውሉ ነገሮችን በቅርበት አድርጎ መመልከት ወይንም ማሽተት፤ ሰውነት እንዲፍታታ እና ወተት እንደልብ እንዲታለብ ለማመንጨት ያግዛል፡፡
በጡት አካባቢ ሞቃታማ የሆነ እና በመጠኑ እርጥበት ያለው ልብስ መልበስ፤
በዝግታ ጡቶችን በእጅ እንደማሸት ወይንም ማላላት፤ መነካካት፤
በዝግታ የጡት ጫፍን እንደማጽዳት እያረጉ አሸት አሸት ማድረግ፤
ወተት ሲፈስ በስሜት ለማየት መሞከር፤
በእርጋታ መቀመጥ እና ዘና ማለትን ማሰብ፤
እናቶች የጡት ወተትን ለማለብ የግድ ኤሌክትሪካል ማለቢያ ካልኖረ በሚል መቸገር የለባ ቸውም፡፡ በቅድሚያ በእጃቸው ወይንም በእጅ በሚሰራ ማለቢያ ለመጠቀም እራሳቸውን ማዘጋ ጀት ይጠቅማቸዋል፡፡ በእርግጥ ኤሌክትሪካል የሆነው የጡት ማለቢያ መሳሪያ በተሻለ ወተትን ለማመንጨት ሊረዳ እንደሚችል መገመት ትክክል ነው፡፡ ካልተገኘ ግን ጡት ለማለብ ዝግጁ በመሆንና በመዘጋጀት በእጅ ወይንም በእጅ በሚሰራ ማለቢያ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ብዙ ሴቶች ጡት ሲያልቡ ወተት ለማግኘት ይቸገራሉ። ነገር ግን ጡት የሚጠባን ልጅ ስድስት ወር ሳይሞላው ከቤት ትቶ ለመውጣት የሚያስገድደው ጊዜ ከመድረሱ በፊት በሳምንት አንድ ቀን ወይንም ሁለት ቀን መለማመድ ያስፈልጋል፡፡ ጡትን ማለብ ከተቻለ ልጁ ለመጥባት በሚፈል ግበት ወቅት ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ ካልሆነ ግን ጠዋት፤ በምሳ ሰአትና ከሰአት በሁዋላ ባለው ጊዜ ማለብ ጥሩ ነው፡፡
ጡትን ለማለብ ሲታሰብ ከፊት ለፊት ደረት ጋ ሊከፈት የሚችል ልብስ መልበስ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ጠቀሜ ታም በይበልጥ ጡት ማለብ የተፈለገበት ሰአት እና ቦታ በመንገድ ላይ፤ በመኪና ውስጥ፤ በስራ ቦታ ቢሆን ምቹ እንዲሆን ነው፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ጡት ለማለብ ሲታሰብ እራስን ምቹ በሆነ ሁኔታ ማስቀመጥ ግድ ይሆናል፡፡ ለምሳሌም በመጀመሪያዎቹ (10-15) ሴኮንዶች የጡት ጫፍ የመወጠር ስሜት ቢኖረው እና የጡት ጫፍ ተወጣጥሮ በመቆየቱ በሚታለብበት ጊዜ የህመም ስሜት ሊኖረው ይችላል፡፡ በእርግጥ ማለ ቢያው ኤሌክትሪካል ከሆነ ሕመሙ በመጠኑ ሊሆን ይችላል፡፡ ለማንኛውም ግን ማለቡን ማቋ ረጥ ሳይሆን የሚገባው በተቻለ መጠን ሰውነትን ፈታ አድርጎ ጡቱን ለማለሳለስ መሞከር እና ካልተቻለም የህክምና ባለሙያን ማማከር ይገባል፡፡ ምናልባትም ሕጻኑ በቅርብ እርቀት ካለ የጡቱን ውጥረት ለማርገብ እንዲቻል ማጥባትም ይመከራል። ወተት  በሚታለብበት ጊዜ በፍጥነት እና በትክክል የማይወጣ ከሆነ ልጁን ማሰብ፤ ከተቻለም በቪድዮ የልጁን ምስል መመልከት፤ ወይንም የተነሳውን ፎቶ እየተመለከቱ እራስን እያዝናኑ የሚፈለገውን ያህል ወተት ማግኘት ይቻላል፡፡ ባጠቃላይም እናትየው ለራስዋ በቂ ጊዜ መስጠት እና ያለበችውን ወተትም በተገቢው ቦታ ማስቀመጥ ይገባታል፡፡
የታለበውን ወተት ማስቀመጥ፤
አንዲት እናት ለልጅዋ የምታስቀምጠው የጡት ወተት በሳይንሳዊ ዘዴው የተተመነለትን የሙቀትና ቅዝቃዜ ሁኔታ ባሟላ መልኩ መሆን አለበት፡፡ ይህ ካልተስተካከለ ወተቱ ይበላሻል፡፡
ማቀዝቀዣ በሌለበት በቤት ውስጥ በተስተካከለ የአየር ሁኔታ ማቆየት፤ የጡት ወተት ከታለበ በሁዋላ የቤት ውስጥ  የአየር ሁኔታ እስከ 77/ዲግሪ ፋራናይት ድረስ ከሆነ እስከ 4/ሰአት ድረስ ሳይበላሽ መቆየት ይችላል፡፡
የጡት ወተት ከታለበ በሁዋላ በማቀዝቀዣ ውስጥ እስከ 4/ቀን ድረስ ቢቀመጥ ጥቅም ላይ ይውላል።  የታለበ የጡት ወተት ከበረዶ ጋር በማድረግ በደንብ በሚታሸግ ማስቀመጨ እስከ 24/ ሰአት ድረስ ከፍሪጅ ውጪ በማስቀመጥ መጠቀም ይቻላል፡፡
የእናት ጡት ወተትን ካለቡ በሁዋላ በማቀዝቀዣ ውስጥ ለማስቀመጥ የተዘጋጁ ማስቀመጫዎ ችን መጠቀም ይገባል፡፡ ካልሆነም ንጹህ የሆኑ ክዳን ያላቸው እንደ ጠርሙስ ያሉ እቃዎችን መጠቀም ጥሩ ነው፡፡ ከአንድ ጊዜ ጥቅም በሁዋላ እንዲጣሉ የታዘዘባቸውን እንደ የታሸገ ውሀ መሸጫ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን መጠቀም ትክክል አይደ ለም፡፡ወተቱ ከእናት ጡት ከታለበ በሁዋላ ለማስቀመጥ ግልጽ የሆነ ምልክት ሊደረግለት ይገባል፡፡
የታለበው ወተት ከማቀዝቀዛ ውስጥ ሲገባ፤
በማስቀመጫው ላይ በግልጽ ወተቱ መቼ እንደታለበ እና ወደፍሪጅ እንደገባ የሚያሳይ በማስቀመጫው ላይ በግልጽ የሚታይ ጽሁፍ ያስፈልገዋል፡፡ ምናልባትም ይህን አገልግሎት የሚፈልጉ ከአንድ በላይ የሆኑ ልጆች ካሉ የታለበው የጡት ወተት ለማንኛው እንደሆነ በሚያሳይ መልክ የልጁን ስም ጭምር መጻፍ ያስፈልጋል፡፡
ወደማቀዝቀዣው ውስጥ የሚገባው ወተት መጠኑ ከሩብ እስከ ግማሽ ስኒ ባይበልጥ ይመረጣል፡፡
ወተቱን ወደማቀዝቀዣ ሲያስገቡ እቃው እስከመጨረሻው እንዳይሞላ የተወሰነ ክፍት ቦታ ሲቀረው መተው ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም በረዶ ሲሰራ መጠኑ ስለሚጨምር ነው፡፡
ባጠቃላይም አንዲት እናት እስከስድስት ወር ድረስ ከእናት ጡት ወተት በስተቀር ለልጅ ምንም ተጨማሪ ምግብ መስጠት አያስፈልግም የሚለውን መመሪያ ለማክበር እና ጤነኛ ልጅ ለማሳደግ ስትል ከልጅዋ በምት ለይበት ወቅት ልጁ የሚመገበውን የጡት ወተት አልቦ እና አዘጋጅቶ መውጣት ተገቢ በመሆኑ የጡት ወተትን አልቦ በጥንቃቄ ማስቀመጥ ከእናቶች የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡
ምንጭ/ WWW.breastfeeding-problem.com
www.breastmilkcounts.com

Read 4421 times