Saturday, 17 November 2018 11:17

ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የጥርስ ሕክምና የሚሰጠው ግሪን ላይፍ ክሊኒክ ሥራ ጀመረ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

  ሕሙማን አሜሪካና አውሮፓ ሄደው የሚያገኙትን ጥራት ያለው የጥርስ ሕክምና እዚሁ ለመስጠት ዓለም በወቅቱ በደረሰበት የመጨረሻ ቴክኖሎጂ ተደራጅቶ አገልግሎት መጀመሩን ግሪን ላይፍ ልዩ የጥርስ ሕክምና ክሊኒክ አስታወቀ፡፡
ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ላለው የጥርስ ሕክምና ክሊኒኮች የሚሰጠውን “ግሪን ላይሰንስ” ይዞ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ሥራ የጀመረው የጥርስ ክሊኒክ ባለፈው ሳምንት ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶችና ጋዜጠኞች ክሊኒኩ ባለበት ቦሌ አትላስ አካባቢ ራካን የገበያ ማዕከል በሰጠው መግለጫ፣ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችና የውጭ አገር ዜጐች እንዲታከሙበት ታስቦ በቴክኖሎጂ የተደራጀ መሆኑን የክሊኒኩ መሥራችና ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሮቤራ ጫላ ገልፀዋል፡፡
ክሊኒኩ፣ ለጥርስ ተከላ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚያክም፣ ቀደም ባሉ አመታት ሜታሎ ሴራሚክ የሚባል የጥርስ ተከላ ይከናወን እንደነበር የጠቀሱት ዶ/ር ሮቤራ አሁን ግን በቅርብ ጊዜ ሥራ ላይ በዋለ ቢማክስ ዝርኩኒ በተባለ ኬሚካልና ካድካም በተባለ ቴክኖሎጂ በመጠቀም  ሰው ሠራሽ ጥርሶችን እንሠራለን። የታካሚው ጥርስ ኤክስሬይ ተነስቶ ሞዴል ይሠራለታል፡፡ እያንዳንዱ ሞዴል ስካን ተደርጐ ካድ ካም ውስጥ ይገባና መሳሪያው ራሱ ዲዛይን አድርጐ የተፈጥሮ የመሰለ ጥርስ ይሠራል። ያንን ነው ለደንበኞቻችን የምንተክለው በማለት አብራርተዋል፡፡ ካድ ካም መሳሪያ እጅግ ውድ ስለሆነ የታካማውን ጥርስ ሞዴል ወስደን ወደ ኢንተርናሽናል ክሊኒክ ይላክና ሰው ሰራሽ ጥርሱ ይሠራል። የዚህ ዓይነት ሕክምና ባደረጉትም አገሮች በጣም ውድ ስለሆነ ዳያስፖራዎች ወደዚህ አገር ሲመጡ አጋጣሚውን በመጠቀም በተመጣጣኝ ዋጋ ያሠራሉ፡፡
የውጪዎቹ አገራት ዋጋ እኛ የምንጠይቀውን አራት እጥፍ ይሆናል፡፡ በዚህ 40 ከመቶ የሆኑት ዳያስፖራ ታካሚዎቻችን በጣም ደስተኞች ናቸው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ሁሉንም የጥርስ ሕክምናዎች እንሠራለን ያሉት ዶክተሩ፤ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ለሚጠይቁት ለብሬስ ኦርቶዴንቲክና ለመደበኛ ፊክስድ ፕሌቲንግና ኢንቪዝላይን ለተባሉት ሕክምናዎች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ፤ ከዚህ አሠራር የሚጠቀመው ኅብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን አገርም ትጠቀማለች። ምክንያቱም የውጭ አገር ዜጐች እዚህ መጥተው ሲታከሙ የሚከፍሉት በዶላር ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
ለጥርስ ሕክምና ሦስት ነገሮች ማለትም ትክክለኛ ክህሎትና ባለሙያ መሆን፣ የሚጠቀሙበት መሳሪያና የአላቂ ዕቃዎች ጥራት፣ እንዲሁም አጋዥ የጥርስ ሕክምና ያስፈለጋል ያሉት ዶ/ር ሮቤራ እውቀት ወደ ክህሎት ካልተለወጠ በስተቀር ስኬታማ ሥራ ማከናወን አይቻልም ብለዋል፡፡
ክሊኒኩ ለሕፃናትም የጥርስ ሕክምና የሚሰጥ ሲሆን፤ ማህበራዊ ኃላፊነት ከመወጣት አኳያ አርብ ከሰዓት በኋላ የገንዘብ አቅማቸው ደካማ ለሆነ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ፣ ምንም ገንዘብ የሌላቸው ከሆኑ ደግሞ በነፃ አገልግሎት እንደሚሰጡ ዶ/ር ሮቤራ ጫላ ገልፀዋል፡፡

Read 3187 times