Saturday, 17 November 2018 11:29

በአፍሪካ አብዛኛው የሕፃናት ቀዶ ሕክምና ከተፈጥሮ ችግሮች ጋር የተያያዘ ነው ተባለ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(9 votes)

 ብሩንዲ፣ ደ.ሱዳንና ናምቢያ አንድም የህፃናት ሐኪም የላቸውም
                    
     በመላው አፍሪካ አብዛኛው የሕፃናት ቀዶ ሕክምና ከአፈጣጠር ችግሮች ጋር የተያያዙ እንደሆኑ አንድ የሕፃናት ቀዶ ሕክምና  ባለሙያ ገለጹ፡፡
12ኛው የአፍሪካ ሕፃናት ቀዶ ሕክምና ማኅበር አጠቃላይ ዓመታዊ ጉባኤ ባለፈው ሳምንት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ሲካሄድ፣ የኢትዮጵያ የሕፃናት ቀዶ ሐኪሞች ማኅበር ሊቀመንበርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕፃናት ቀዶ ሕክምና ባለሙያ ፕሮፌሰር ሚሊያርድ ደርበው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ የአፍሪካ ሕፃናት ቁጥር ከአፍሪካ አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ቢበልጥም ከተፈጥሮ ጋር የተያያዙ ችግሮች ትኩረት አልተሰጣቸውም ብለዋል፡፡
ከሰሐራ በታች ባሉ አገራት ከውልደት በፊት የሚከሰቱ ችግሮችና አደጋዎች አደገኛና የተወሳሰቡ ከመሆናቸውም በላይ ቀዳሚ የሞት መንስኤዎች ቢሆኑም ትኩረት የተነፈጉ ናቸው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የምሥራቅ ማዕከላዊና ደቡባዊ አፍሪካ (ኮሜሳ) አባል አገራት የሕዝብ ቁጥር ከ450 ሚሊዮን በላይ ቢሆንም፣ ያላቸው የሕፃናት ቀዶ ሐኪሞች ቁጥር 54 ነው፡፡ በዚህ ዓይነት አንድ የሕፃናት ሐኪም ለ7 ሚሊዮን ሕዝብ ማለት ነው፡፡ ደቡብ ሱዳን፣ ብሩንዲና ናሚቢያ ጭራሹኑ አንድም የሕፃናት ሐኪም የላቸውም፡፡ ከሦስት አገሮች፣ (ዚምባብዌ፣ ማላዊና ናሚቢያ) በስተቀር ሌሎች አገሮች  ኢትዮጵያን ጨምሮ አንድም የሕፃናት ሆስፒታል የላቸውም በማለት አስረድተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ማሊያርድ በተለይ ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ማኅበሩ የምሥራቅ፣ ምዕራብና ሰሜን አፍሪካ ሐኪሞች ያቋቋሙት እንደሆነ ጠቅሰው፣ ዓላማውም ጥራቱን የጠበቀ የሕፃናት ቀዶ ሕክምናን ጥያቄ በአፍሪካ ማዳረስ፣ በአፍሪካ ሕፃናት ቀዶ ሕክምና ዙሪያ ያሉትን ችግሮች በመለየት በዚህ ላይ ያተኮሩ ምርምሮችና ጥናቶች በማድረግ ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን መፍትሔ ማፈላለግ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በሁሉም የአፍሪካ አገሮች በቀዳሚነት የሚታዩት ከአፈጣጠር ጋር የተያያዙ ጉድለቶች ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ከ3-7 በመቶ ያህል ሕፃናት ከአፈጣጠር ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳሉባቸው ይነገራል፡፡ በአፍሪካ ግን ቁጥሩና የችግሩ ውስብስብነት በጣም ብዙ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሰሐራ በታች ባሉ አገራት የሚሞቱት ጨቅላ ሕፃናት ቁጥር ከ90 በመቶ በላይ ነው፡፡ ችግሩ በመላው ዓለም ሆኖ ሳለ፣ የአፍሪካ ሕፃናት ሞት ለምን በዛ? ለሚለው ጥያቄ፣ የባለሙያ እጥረት ዋነኛው ችግር እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ሚሊያርድ የሕፃናት ሐኪሞችን እጥረት በምሳሌ ሲያስረዱ፣ አፍሪካ ከአንድ ቢሊዮን ሕዝብ በላይ አላት፡፡ ከዚህ ቁጥር ውስጥ አብዛኛው ወጣት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ20 ዓመት በታች ያሉት 60 ከመቶ ይሆናሉ፡፡ ከ15 ዓመት በታች ደግሞ ከ45-50 በመቶ ይሆናሉ። ሕፃናት በሚበዙበት አህጉር ያሉት የሕፃናት ሐኪሞች ቁጥር ደቡብና ሰሜን አፍሪካን ጨምሮ 500 አይሞላም፡፡
አብዛኛው ሕዝብ አዋቂ በሆነባት አሜሪካ በሕፃናት የዕድሜ ክልል የሚገኙት ከ7 በመቶ በታች ነው፡፡ 300 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት አሜሪካ በሕፃናት ሕክምና ላይ የተሰማሩ ከ2000 በላይ ሐኪሞች አሉ፡፡ ከአንድ ቢሊዮን ሕዝብ በላይ ላለው አህጉር ግን ያሉት ሐኪሞች ቁጥር 500 ነው፡፡ ይህንን ከፍተኛ የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ ምን ማድረግ እንዳለብን ነው የተነጋገርነው፡፡
ለዚህ እንደ መፍትሔ ይሆናል ያልነው ትብብር (Partnership) መፍጠር ነው፡፡ እኛ በአፍሪካ ውስጥ ያለነው  ተደራጅተናል፡፡ በዓለም ላይ አቅም ካላቸው የሕፃናት ሕክምና ማኅበራት ጋር ሆነን፣ ለዚህ ዓለም አቀፍ ችግር ዓለም አቀፍ መፍትሔ መፈለግ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
የሕፃናት ሐኪሞች ቁጥር አነስተኛ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጹ፤ የሕፃናት ሕክምና ሥልጠና ረዥም ጊዜ ይወሰዳል፡፡ አንድ ሐኪም ከ6-7 ዓመት ተምሮ የሕክምና ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ሁለት ዓመት ሰርቶ  ቀዶ ሕክምና ለማጥናት 4 ዓመት፣ ከዚያ በኋላም 4 ዓመት ተጨማሪ ይማራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የማሠልጠኛ ቦታ የለም፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ የሕፃናት ቀዶ ሕክምና ሐኪሞች 2 ብቻ ነበርን፡፡ እኛም ሥልጠና ያገኘነው ከውጭ አገር ነው፡፡ ከ2011 ጀምሮ በአገር ውስጥና ከሌሎች አገሮች ጋር በመተባበር በአገር ውስጥ ማሠልጠን ጀምረናል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በካናዳ ከቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ጋር፣ በሕንድ ደግሞ ከቨነር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን 8 የሕፃናት ቀዶ ሐኪሞች አስመርቀናል። አሁን ደግሞ የሕክምና ትምህርት ከጨረሱና 2 ዓመት ከሠሩ በኋላ ለ5 ዓመት ሰርጀሪ (ቀዶ ሕክምና) እንዲማሩ እያደረግን ነው፡፡ ሁለቱን ዓመት ጀነራል ሰርጀሪ፣ ሦስቱን ዓመት ደግሞ የሕፃናት ቀዶ ሕክምና ይማራሉ። በዚህ ዓይነት የሚማሩ ከ20 በላይ ሐኪሞች አሉን። ይህ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራትም የሚሠራበት ስለሆነ በአጭር ጊዜ የሕፃናት የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እንሰጣለን ብለን እናስባለን። እስካሁን ድረስ የሕፃናት ቀዶ ሕክምና የሚሰጠው በአዲስ አበባ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን በክፍለ ሀገሮች በሐዋሳ አጠቃላይ ሪፌራል ሆስፒታል፣ በቅዱስ ጳውሎስና በሚኒልክ ሆስፒታል፣ በጐንደር፣ በመቀሌና በጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርቱ እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ የመንግሥት ተሳትፎን ምን ሊሆን እንደሚገባ ሲያስረዱ፤ እኛ ከሁለት ተነስተን 13 የደረስነው በመንግሥት ድጋፍ ነው፡፡ አሁንም አቅማችን በፈቀደ መጠን ከሌሎች የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ሥልጠናውን ማስፋፋት እንፈልጋለን። መንግሥት፣ የሕፃናት ሕክምናን ለማሻሻል የተለየ የሕፃናት ብቻ የሆነ ሆስፒታል ማቋቋም አለበት። ቢቻል ደግሞ ጨቅላ ሕፃናትና በካንሰር ሕመም የሚሰቃዩ፣ ከፍተኛ አደጋ የደረሰባቸውና የመናገር ችግር ያለባቸውን የሚያክም ሆስፒታል ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአፈጣጠር ችግር ምን ያህል እንደሆነ ሲያስረዱ፣ የከንፈር መሰንጠቅ ያለባቸው ከ500 ሕፃናት መካከል በአንዱ ላይ፣ የዘር ፍሬ ያልወረደላቸው ወንድ ሕፃናት ከ400 በአንዱ፣ የጉሮሮና የአየር መተላለፊያ ችግሮች ከ3000 ሕፃናት መካከል በአንዱ ሕፃን ላይ እንደሚከሰት አመልክተዋል፡፡
አሁን የምናክማቸው ሕፃናት ከ45 በመቶ በላይ ከአፈጣጠር ጋር የተገናኙ ችግሮች፡- የሰገራ መውጫ የሌላቸው፣ የዘር ፍሬ ያልወረደላቸው ወንዶች ልጆች፣ የመዋጫ ችግር ያለባቸው …ናቸው። አንዳንዶቹ ያልተለመዱና ለሕክምናም አስቸጋሪ የሆኑ ለምሳሌ ተጣብቀው የተወለዱና አንድ ብልት (Organ) ለሁለት የሚጠቀሙ ሊሆኑ ይችላሉ በማለት ፕሮፌሰር ሚሊያርድ ደርበው አስረድተዋል። 

Read 3383 times