Print this page
Monday, 03 December 2018 00:00

የሜቴክ ሙስና ተጠርጣሪዎች የድርጊት ተሣትፎ ለፍ/ቤት በዝርዝር ቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

ፖሊስ ረቡዕ እለት ጉዳዩን እየተከታተለ ለሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት፤ በቀድሞ የሜቴክ ም/ኃላፊ ብ/ጀነራል ጠና ቁርንዲ የምርመራ መዝገብ ስር በሚገኙ 26 ተጠርጣሪዎች ላይ በ14 ቀናት ውስጥ ያከናወነውን የምርመራ ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት፤ እያንዳንዳቸው በድርጊቱ ነበራቸው ያለውን ተሳትፎ በዝርዝር አቅርቧል፡፡
ብርጋዴር ጀነራል ጠና ቁርንዶ ኤጄታ
ከ2004 እስከ 2005 ዓ.ም የግዥ ዘመን፣ ከግዢ መመሪያ ውጪ አለማቀፍ የጨረታ ውድድር ሳይደረግ፣ ከመ/ቤቱ ሃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በመሆን፣ ሃምሣ ስድስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ አርባ ሶስት ሺህ ስምንት መቶ (56,943,800.00) ዶላር በማውጣት፣ በህገወጥ መንገድ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ግዥ እንዲፈፀም በማድረግ፣ መንግስት ከጨረታ ውድድር ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም አሳጥተዋል ብሏል፡፡
“ቴክኖኦሬድ” ከተባለ የጣሊያን ኩባንያ፣ ከግዥ መመሪያ ውጪ፣ ያለ ጨረታ፣ የክሬን ግዥ እንዲፈፀም በማድረግም መንግስት ከጨረታ ውድድር ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም በማሳጣትም ተጠርጥረዋል፡፡
ከሌሎች የኮርፖሬሽኑ የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን፣ “አባይ ወንዝ” እና “አብዮት” የተባሉ አሮጌ መርከቦች፣ በቁርጥራጭ ብረትነት ከተገዙ በኋላ ጥገና ተደርጐላቸው ወደ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲገቡ በሚል፣ በተገቢ ጥናት ላይ ያልተመሠረተ ውሣኔ በመስጠት፣ ለጥገና በሚል ከአምስት መቶ አርባ አራት (544,000.000) ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስት ገንዘብ ያለአግባብ እንዲባክን አድርገዋል፣ መርከቦቹም ከጥገና በኋላ የሠሩበት የክፍያ ገንዘብ ለመንግስት ገቢ ባለመደረጉ፣ የ29 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ሀገሪቱ እንድታጣ አድርገዋል - ይላል የፖሊስ ምርመራ ውጤት፡፡
እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2012 ያለ ጨረታ፣ በድርድር የ “በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ ፓወር ፕላንት” ግንባታ ግዥ ውል አጽድቀዋል በሚልም ተጠርጥረዋል፡፡
ብርጋዴር ጀነራል ብርሃ በየነ
ከግዥ መመሪያ ውጪ፣ ያለ ጨረታ የሪቬራ ፕላስቲክ ፋብሪካና የሆቴል ግዥ ኮሚቴ ውስጥ በመሳተፍ በቃለ ጉባኤ በተደገፈ ድርድር፣ በአንድ መቶ ሃያ ስምንት ሚሊዮን ብር (128.000.000) ግዥ እንዲፈፀም በማድረግ፣ መንግስት ከጨረታ ውድድር ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም በማሳጣት፣ ሶስተኛ ወገን እንዲጠቀም በማድረግ፣ ሃላፊው መጠርጠራቸውን ያትታል - የምርመራ መዝገቡ፡፡
ብርጋዴር ጀነራል ጥጋቡ ፈትለ መርሳ
በኮርፖሬሽኑ የግዥ ዕቅድና ፍላጐት ሣይኖር፣ ከግዥ መመሪያ ውጪ፣ ያለጨረታ የ5 አውሮፕላኖች ግዥ በመፈፀም፣ በመንግስትና በህዝብ ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል፤ የተገዙ አውሮፕላኖችም ህጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው፣ በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ መጠርጠራቸውን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ብርጋዴር ጀነራል ሃድጉ ገ/ጊዮርጊስ ገ/ስላሴ
ሆሞች ጥይት ፋብሪካ ኢንዱስትሪ ሃላፊ በነበሩ ጊዜ ጥይት በማይመለከታቸው የሀገር ውስጥ ድርጅቶችና ግለሰቦች ያለአግባብ እንዲሸጥ በማድረግ ተጠርጥረዋል።
የግዥ መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ፣ ያለ ጨረታ ከሌሎች ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር በ2010 ዓ.ም ሊጅዋንኪ ቴክኖ ኃ/የተ/የግ/ማህበር 19 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ውል በማጽደቅ፣ መንግስት ከጨረታ ውድድር ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም በማሳጣት፣ ሶስተኛ ወገን እንዲጠቀም በማድረግ መጠርጠራቸውንም - የፖሊስ የምርመራ ያመለክታል፡፡
ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታ ተስፋሁን
ከግዥ መመሪያ ውጪ የግዥ ዕቅድና ፍላጐት ሳይኖር፣ ከሌሎች ግለሰቦች ጋር በጥቅም በመተሳሰር፣ በተጋነነ ዋጋ የመኖሪያ ቤት ግዥ ፈጽመዋል፤ ያለ ጨረታ ከግዥ መመሪያ ውጭ የ4 አውሮፕላኖች ግዥ በመፈፀም፣ እነዚህ አውሮፕላኖች ፍላጐትና እቅድ ሳይኖር ስለተገዙ፣ ያለ አገልግሎት በመቀመጣቸው በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፤ የተገዙት አውሮፕላኖችም ህጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው፣ በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ መጠርጠራቸው ተመልክቷል፡፡
ኮሎኔል ሙሉ ወ/ገብርኤል  ገ/እግዚአብሔር
የኮርፖሬሽኑ ም/ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ ስልጣንና ሃላፊነታቸውን በመጠቀም፣ የግዥ መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ፣ የግዥ እቅድና ፍላጐት ሳይኖር፣ ተገቢው ጨረታ ሳይወጣ፣ ኮርፖሬሽኑ የፈፀማቸውን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ግዥዎችን ከተለያዩ ሃላፊዎች ጋር በመመሳጠር፣ በበላይነት ግዢዎችን በመምራት ተጠርጥረዋል፡፡ ሪቬራ ሆቴልና ፕላስቲክ ፋብሪካ፣ ክሬኖችና የነዳጅ ማምረቻ ፋብሪካ ግዥዎችን ከህግ አግባብ ውጪ እንዲፈፀሙ በማድረግ፣ ለራሳቸውና ለሶስተኛ ወገን ያለአግባብ ጥቅም በማስገኘት መጠርጠራቸውም ተመልክቷል፡፡
ከሌሎች የኮርፖሬሽኑ የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን፣ “አባይ ወንዝ” እና “አብዮት” የተባሉ አሮጌ መርከቦች፤ በቁርጥራጭ ብረትነት ከተገዙ በኋላ ጥገና ተደርጐላቸው ወደ ትራንስፖርት እንዲገቡ በሚል በተገቢ ጥናት ላይ ያልተመሠረተ ውሣኔ በመስጠት፣ ለጥገና በሚል ከ544 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲባክን እንዲሁም መርከቦቹ ከጥገና በኋላ የሠሩበትን የክፍያ ገንዘብ ለመንግስት ገቢ ባለመደረጉ፣ የ29 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ አሳጥተዋል በሚል ተጠርጥረዋል - ይላል የፖሊስ የምርመራ መዝገብ፡፡
ኮ/ል ዙፋን በርሄ
የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ሃላፊ ከሆነው ባለቤታቸው ጋር በመመሳጠር፣ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች አልባሳት ንፅህና መስጫ ማሽን ቢገዛ አዋጭ እንደሚሆን የሚያስረዳ ጥናት ቀርቦ እያለ፣ ጥናቱን በመተው በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት የግል ድርጅት የልብስ ንጽህና አገልግሎት እንዲሰጥ በማስደረግ፣ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም በማግኘት መጠርጠራቸው ተመልክቷል፡፡
ሌ/ኮ/ል አስመረት ኪዳኔ አብርሃ
በተለያዩ የኮርፖሬሽኑ የግዥ ኮሚቴዎች ውስጥ በመሳተፍ፣ የግዥ እቅድና ፍላጐት ሳይኖር፣ የግዥ መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ፣ ጨረታ ሳይወጣ የኪያማሉክ ኢንተርናሽናል ኃ/የተ/የግ ማህበር G+5 ህንፃ ግዥ ፈጽመዋል፣ ከተለያዩ የተሽከርካሪ አስመጭዎች፤ የተሽከርካሪ ግዥ ከህግ አግባብ ውጪ እንዲፈፀም አድርገዋል፤ የግዥ እቅድና ፍላጐት ሣይኖር፣ ከመመሪያ ውጭ ያለ ጨረታ በተጋነነ ዋጋ የ20 ደብል ጋቢና ፒክ አብ ተሽከርካሪ ግዥ እንዲፈፀም የውሣኔ ሃሳብ በማቅረብ ግዥ እንዲፈፀም በማድረግ፣ በዚህም ያለ አግባብ፣ ለራሳቸውና ለሶስተኛ ወገን ጥቅም በማስገኘት ተጠርጥረዋል፡፡     
ኮሎኔል አለሙ ሽመልስ ብርሃን
አሮጌ መርከቦች ቁርጥራጭ ብረት በሚል ከተገዙ በኋላ ጥገና ተደርጎላቸዉ፣ ወደ ትራንስፖርት አገልግሎት ይገባሉ በሚል፣ በተገቢ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ፣ የጥገና ሥራ እንዲሠራ ያለአግባብ ዉል ፈርመዋል፣ ያለአግባብ አውሮፕላኖች እንዲገዙ በማድረግ፣ ለራሳቸውና ለሶስተኛ ወገን ያለአግባብ ጥቅም አስገኝተዋል በሚል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡
ኮሎኔል ያሬድ ኃይሉ
ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የተከለለ ቦታ ላይ የሚገኘውን ጫካ ምንጣሮ ስራ በበላይነት እንዲከታተሉ ኃላፊነት ወስደው እያለ፣ የምንጣሮ ሥራው ሳይጠናቀቅ እንደተጠናቀቀ በማስመሰል፣ ያለአግባብ የመንግስት ገንዘብ ወጪ እንዲሆን በማድረግ፣ ለራሳቸውና ለሌሎች ያልተገባ ጥቅም በማስገኘት፣ የህዝብና የመንግስት ገንዘብ እንዲባክን አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ፡፡
ኮ/ል ተከስተ ኃ/ማርያም አድሃኖም
ከሌሎች የኮርፖሬሽኑ የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን “አባይ ወንዝ” እና “አብዮት” የተባሉ አሮጌ መርከቦች በቁርጥራጭ ብረትነት ከተገዙ በኋላ ጥገና ተደርጎላቸዉ ወደ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲገቡ በሚል፣ በተገቢ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ ውሳኔ በመስጠት፣ ለጥገና በሚል ከ544,000,000.00 ብር በላይ የመንግስት ገንዘብ አለአግባብ እንዲባክን አድርገዋል፣ መርከቦቹም ከጥገና በኋላ የሠሩበትን የክፍያ ገንዘብ ለመንግስት ገቢ ባለመደረጉ የ29,000,000.00 ዶላር የውጭ ምንዛሪ ሀገሪቱ እንድታጣ በማድረግና ለዚህም ድርጊት በውጭ ሀገር ከሚገኙ ድርጅቶች ጋር በጥቅም በመተሳሰር፣ የኮሚሽን ክፍያ እንዲሠጣቸው በማድረግ፣ ለራሳቸውና ሌሎች ያልተገባ ጥቅም በማስገኘት የተጠረጠሩ ናቸው፡፡
ኮሎኔል አዜብ ታደሰ
አሮጌ መርከቦች በቁርጥራጭ ብረትነት ከተገዙ በኋላ ያለአግባብ ጥገና ወደሚደረግላቸው ዱባይ በመሄድ ከተገዙበት አላማ ውጪ የንግድ ሥራ እንዲሰሩ በማድረግና በከፊል የጥገና ውሎች ላይ በመፈረም፣ ለራሳቸውና ሌሎች ያልተገባ ጥቅም በማስገኘት የተጠረጠሩ ናቸው፡፡
ሻለቃ ይክኖአምላክ ተስፋዬ ሀጎስ
አሮጌ መርከቦች በቁርጥራጭ ብረትነት ከተገዙ በኋላ ለመርከቦቹ አዋጭ ያልሆነ ጥገና ተደርጎ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሠጡ፣ የጥገና ሥራውን በበላይነት ሲከታተሉ በነበረበት ወቅት ከኮርፖሬሽኑ የበላይ አመራሮችና ውጪ ካሉ ድርጅቶች ጋር በጥቅም በመተሳሰር ህገወጥ ድርጊት በመፈፀም፣ ሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንድታጣ በማድረግ፣ ለራሳቸውና ለሌሎች ያልተገባ ጥቅም በማስገኘት የተጠረጠሩ ናቸው፡፡
ኮ/ል ደሴ ዘለቀ ብርሃን
የአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኃላፊ ሆነው በሱማሌ ክልል ሀረዋና ኩለን፣ በአፋር ክልል ደግሞ ሱሉታ መስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶች በሚሰሩበት ወቅት ከሌሎች ግብረአበሮች ጋር በመሆን፣ የሙስና ወንጀል ድርጊቶችን በመፈፀም፣ በፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል፣ ለአካባቢው አርሶአደሮች አገልግሎት የሚውሉ ትራክተሮች በህገወጥ መንገድ ግዢ እንዲፈፀም በማድረግ፣ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ፣ ለራሳቸውና ለሌሎች ያልተገባ ጥቅም በማስገኘት የተጠረጠሩ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
ሻለቃ ሰለሞን በርሄ
ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የተከለለ ቦታ ላይ የሚገኘውን ጫካ ምንጣሮ ስራ በበላይነት እንዲከታተሉ ኃላፊነት ወስደው እያለ፣ የምንጣሮ ሥራው ሳይጠናቀቅ እንደተጠናቀቀ በማስመሰል ያለአግባብ የመንግስት ገንዘብ ወጪ እንዲሆን በማድረግ፣ ለራሳቸውና ሌሎች ያልተገባ ጥቅም በማስገኘት፣ የህዝብና የመንግስት ገንዘብ እንዲባክን አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡
ሻለቃ ይርጋ አብርሃ
ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመበት ዓላማ ዉጭ፣ ከግለሰቦች ጋር በመመሳጠር፣ የባንክን ስራ ተክቶ ለተለያዩ ግለሰቦች የመንግስትን ገንዘብ ያለአግባብ በብድር እንዲሰጥ በማድረግና ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር የጥቅም ግንኙነት በማድረግ፣ የስፖንሰር ገንዘብ እንዲያገኙ በማድረግ ለራሳቸው እና ሌሎች ያልተገባ ጥቅም በማስገኘት የህዝብና የመንግስት ገንዘብ እንዲባክን አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ መሆናቸው ተጠቅሷል - በመዝገቡ፡፡
ኮ/ል ግርማይ ታረቀኝ
የግዢ ዕቅድና ፍላጎት ሳይኖር ከግዢ መመሪያ ውጪ፣ ያለጨረታ በተጋነነ ዋጋ የ20 ደብል ጋቢና ፒክ ካፕ ተሽከርካሪዎች ግዥ እንዲፈፀም ሃሳብ በማቅረብ፣ ግዥዉን እንዲፈፀም ማድረግ፤ የሜቴክ የሎጅስቲክና ንብረት አስተዳደር ኃላፊ ሆነው በሚሰሩበት ወቅት ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ቁርጥራጭ ብረቶች ወደ ብረታብረት ፋብሪካ እንዲሰበሰቡ በተያዘዉ ዕቅድ መሰረት፤ ሜቴክ በራሱ አቅም ማሰባሰብ እየቻለ፣ ከተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ፣ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲወጣ ትዕዛዝ ሰጥተዋል በሚል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡
ሻምበል ገ/ስላሴ ገ/ጊወርጊስ
ያለጨረታ ግዥና መመሪያን በመጣስ፣ የአገልግሎት ግዥ እንዲፈፀም በመወሰን ግዥ ፈፅመዋል፣ ሜቴክ ለተለያዩ ለመ/ቤቱና አባላት ላልሆኑ ግለሰቦች፣ ከህግና መመሪያ ውጭ “የትምህርት ዕድል” በሚል ከድርጅቱ ገንዘብ ወጭ እየተደረገ እንዲማሩ በሚል፣ በመንግስት ገንዘብ ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል መጠርጠራቸው ተጠቁሟል፡፡
ሻ/ል ሰለሞን አብርሃ
ያለ ጨረታ የግዢ መመሪያን በመጣስ፣ የአገልግሎት ግዢ እንዲፈፀም፣ በቃለ-ጉባኤ በመወሰን ግዢ እንዲፈፀም አድርገዋል፣ የመርከቦች ጉዳይ ኮሚቴ አባል ሆነው ሲሰሩ፣ የመርከቦች የጥገና ዋጋ አለአግባብ ወደ 6.2 ሚሊየን ዶላር ከፍ እንዲል የሚያደርግ የውል ስምምነት ፈፅመዋል፣ በሚል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡
ሌ/ኮ/ል ይስሃቅ ኃ/ማሪያም አድሃኖም
ያለ ዕቅድና ፍላጎት፣ያለ ጨረታ ግዥ መመሪያ፣ በተጋነነ ዋጋ የ20 ደብል ጋቢና ፒክ ካፕ ተሸከርካሪዎች ግዥ እንዲፈፀም ሃሳብ በማቅረብ፣ ግዥዉን እንዲፈፀም አድርገዋል በሚል ተጠርጥረዋል፡፡
ሻለቃ ክንደያ ግርማይ
ያለ ዕቅድና ፍላጎት፣ ያለጨረታ ግዥ መመሪያ ዉጭ በተጋነነ ዋጋ የ20 ደብል ጋቢና ፒክ ካፕ ተሸከርካሪዎች ግዥ እንዲፈፀም ያወጣና ሃሳብ በማቅረብ ግዥዉን እንዲፈፀም አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡
ሌ/ኮ/ል አዳነ አጋርነው
የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የንብረት አስተዳደር ሆነው በሚሠሩበት ወቅት የግዢ መመሪያን ባልተከተለ መንገድ የተገዙ ተሽከርካሪዎች ምርመራ ሳይደረግባቸውና ይህንኑ ጉዳይ የሚያስረዳ ሠነድ ሳይኖር ተረክበዋል፣ በሚል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡  
ሻለቃ ጌታቸው አፅበሃ
ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የግዢ መመሪያው ከሚፈቅደውና ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመበት አላማ ውጪ የተለያዩ ህንፃዎችንና መኖሪያ ቤቶችን በመግዛት ሂደት ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡
አያልነሽ መኮንን አራጌ
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ የሚያርፍበት ቦታ ጫካዎች ምንጣሮ ሥራ፣ ከሃላፊዎች ጋር ባላት የቅርብ ግንኙነት የራሷን ድርጅት፣ በልጇ ሥም በማቋቋም፣ ያለምንም የግዢ ጨረታ ሥራውን በመውሰድ፣ ያለአግባብ ሥራው ሳይሰራ ክፍያ እንዲፈፀምላት በማስደረግ፣ የሕዝብ ገንዘብ ያለአግባብ በመውሰዷ፣ እንዲሁም የብ/ጄኔራል ሀድጉ ገ/ጊዮርጊስ ፀሃፊ ሆና ስትሰራ የቆየች ሲሆን ተጠርጣሪው በሙስና ወንጀል እንደሚፈለግ እያወቀች፣ የኮርፖሬሽኑ ሲቪል ሰራተኞች ከሥራ ቀን ውጪ ወደ ቢሮ መግባት የማይቻል ሆኖ እያለ ወይም ማስፈቀድ ሲገባት ከሌላ ተጠርጣሪ ጋር በመሆን ቢሮ በመግባት ለተጀመረው የምርመራ ሥራ ለማስረጃነት የሚያገለግሉ ፅሁፎችን ከኮምፒውተር አጥፍታለች በሚል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡
ሻ/ል ጌታቸው ገ/ሥላሴ
ከኮርፖሬሽኑ የግዢ መመሪያ ውጪ ያለጨረታ፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ግዢ እንዲፈፀም በመወሰንና ግዢው እንዲፈፀም በማድረግ፣ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል በሚል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡  
ፖሊስ በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎች ማሰባሰቡን፣ የምስክሮች እንዲሁም፣ የተጠርጣሪዎችን የተከሣሽነት ቃል መቀበሉን ለፍ/ቤቱ አስረድቶ፤ በቀጣይ የኦዲት ሪፖርቶችን ማሰባሰብ፣ በመንግስትና በህዝብ ሃብት ላይ የደረሰውን ጉዳት በባለሙያ ማስገመት፣ ቀሪ የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ፣ ሰነዶችን ወደ አማርኛ ቋንቋ ማስተርጐምና የፎረንሲክ ምርመራዎችን ማከናወን ይቀረኛል ሲል፣ ፍ/ቤቱን ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው፤ ከዚህ በላይ የምርመራ ጊዜ ሊፈቀድ አይገባም፤ እኛም በዋስ ሆነን ጉዳያችንን እንከታተል የሚል አቤቱታ ለፍ/ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን ፍ/ቤቱ ሐሙስ በዋለው ችሎት ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡

Read 4989 times