Print this page
Monday, 03 December 2018 00:00

ዳሸን ባንክ 1.14 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ዳሽን ባንክ አ.ማ ሰኔ 23 ቀን 2010 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባደረገው እንቅስቃሴ፣ ከታክስ በፊት 1.14 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡ ትርፉ ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ የ8.3 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡
ባንኩ ትናንት በሸራተን አዲስ ሆቴል ባደረገው 24ኛው የባለአክሲዮኖች ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ፤ የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ነዋይ በየነ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፤ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ችግሮት ተከስተው እንደነበር ጠቅሰው፣ በዚህ ችግር የተነሳ አንዳንድ የባንክ ቅርንጫፎች ተዘግተው እንደነበርና ጥሬ ገንዘብ እንደተፈለገው እንዳይዘዋወር እንቅፋት ፈጥሮ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
የተጠቀሱት ችግሮች ቢኖሩም ባንኩ እነዚህን ችግሮች ተቋቁሞ ባደረገው እንቅስቃሴ፤ 8.1 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉን ጠቅሰው፣ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 36 ቢሊዮን ብር መድረሱንና ጭማሪውም 29.2 በመቶ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የባንኩ ገቢ ከቀደመው ዓመት የ21.7 በመቶ ዕድገት በማሳየት 4.4 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ በበጀት ዓመቱ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 45.4 ቢሊዮን ብር መሆኑን ጠቅሰው፤ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በዓመቱ 300 ሚሊዮን ብር በመጨመር፣ አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታል 2.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ ባንኩ ከተለያዩ ዘርፎች በዓመቱ ያገኘው ገቢ የ869.1 ሚሊዮን ብር ዕድገት በማሳየት፣ 4.3 ቢሊዮን መድረሱን አመልክተዋል፡፡
2.4 ቢሊዮን ብር የነበረው የቀደመው ዓመት አጠቃላይ ወጪ፣ በተጠናቀቀው በጀት 3.3 ቢሊዮን ብር መሆኑንና አንድ አክሲዮን የሚያስገኘው ገቢ 43 በመቶ ጨምሮ፣ 430 ብር እንዲሆን መወሰኑን አመልክተዋል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ደግሞ በቀደመው ዓመት ከነበረው በ26 በመቶ ጨምሮ 45.4 ቢሊዮን መድረሱን አቶ ነዋይ ገልጸዋል፡፡  
በመላው አገረቱ በበጀት ዓመቱ 70 ቅርንጫፎች በመክፈት፣ የቅርንጫፎችን አጠቃላይ ብዛት 373 ያደረሰው ዳሸን ባንክ፤ ከ70ዎቹ ቅርንጫፎች 58ቱ ከአዲስ አበባ ውጪ የተከፈቱ ናቸው፡፡

Read 2075 times