Monday, 03 December 2018 00:00

ዘመን ባንክ ከ270 ሚ. ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

   ለ6 በጐ አድራጐት ድርጅቶች አንድ ሚሊዮን ብር ለመለገስ ወሰነ


    ዘመን ባንክ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባደረገው እንቅስቃሴ በሁሉም የሥራ ዘርፎች መልካም ውጤት ማስመዝገቡን አስታወቀ፡፡
ባንኩ፣ ባለፈው ሳምንት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባደረገው 10ኛ መደበኛና ዘጠነኛ ድንገተኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ፣ የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አበበ ድንቁ ባቀረቡት የሥራ ሪፖርት፤ ባንኩ፣ 270.3 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ገልፀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የተገኘው ትርፍ በአንድ አክሲዮን በአማካይ ሲሰላ 28.6 በመቶ እንደሆነ የጠቀሱት የቦርድ ሰብሳቢው፤የባንኩ አጠቃላይ የአምስት ዓመት ትርፍ ክፍፍል ከአቻ ባንኮችና ከባንክ ኢንዱስትሪው ከፍ ብሎ መቀጠሉን ያሳያል ብለዋል፡፡
ባንኩ በ2010 በጀት ዓመት ያገኘው አጠቃላይ ገቢ 1.1 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህ ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 151 ሚሊዮን ብር ወይም 15.3 ጭማሪ ማሳየቱን፣ ለገቢው መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው ከወለድ የተገኘው 712 ሚሊዮን ብር ወይም የ62.7 በመቶ መሆኑን ፣ በበጀት ዓመቱ የባንኩ አጠቃላይ ወጪ 794 ሚሊዮን ብር መድረሱን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ 178.5 ሚሊዮን ብር ወይም የ29 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ፕሮፌሰር አበበ አስረድተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የዘመን ባንክ አጠቃላይ ሀብት 12.4 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ2.7 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱን፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በወዲያኛው ዓመት ከነበረበት 8 ቢሊዮን ብር  የ2.2 ቢሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት 10.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ ለተለያዩ ክፍላተ ኢኮኖሚዎች የተሰጠው ብድር ከቀዳሚው ዓመት ወደ 5 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን፣ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከነበረበት 850 ሚሊዮን ብር፣ 1.1 ቢሊዮን መድረሱን የቦርድ ሰብሳቢው አመልክተዋል፡፡
ባንኩ ደንበኞችን በቅርበት ለማገልገልና ተደራሽነቱን ለማስፋት የቅርንጫፎቹን ብዛት 26 ማድረሱን፣ ብዛታቸው 63 በደረሱት አውቶማቲክ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች (ATM) በቀን 2 ሚሊዮን ብር ያህል፣ በዓመት 728.6 ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን፣ በኢንተርት ባንኪንግ ለ8880 ያህል ደንበኞች አገልግሎት መስጠቱንና በዚህም ዘዴ 155.3 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ልውውጥ መደረጉን፣ በተንቀሳቃሽ ባንኪንግ በ2605 አገልግሎቶች 1.1 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር መፈጸሙን፣ በበጀት ዓመቱ ለ20 ሺህ የደንበኞች ሠራተኞች ደመወዝ የ330 ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል፡፡
ዘመን ባንክ 10ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን ኅዳር 15 ቀን 2011 ዓ.ም ማምሻውን በኢንተርኮንቲኔታል ሆቴል ያከበረ ሲሆን በዚሁ ወቅት ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ ለ6 በጐ አድራጐት ድርጅቶች ማለትም ለኢትዮጵያ ማየትና መስማት ለተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር፣ ለሴቶች ማረፊያና ልማት ማኅበር፣ ለጐጆ የሕሙማን ማረፊያ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጐ አድራጐት ማህበር፣ ለብሩህ የአዕምሮ ዕድገት ውሱንነት ማዕከል፣ ለኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጐ አድራጐት ድርጅት እና ለትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማህበር አንድ ሚሊዮን ብር እንዲከፋፈል የዲሬክተሮች ቦርድ መወሰኑን፣ እንዲሁም የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ 38.16 በመቶ መድረሱን የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አበበ ድንቁ ገልፀዋል፡፡


Read 3346 times