Saturday, 08 December 2018 14:53

ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን ማዕከላት ዛሬ ያስመርቃል

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

 331 የሕክምና ዶክተሮችና የማስተርስ ተማሪዎች ይመረቃሉ


     ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለግቢው ተማሪዎች፣ ለአካባቢው ኅብረተሰብና የጎረቤት አገራትን ጭምር ማገልገል እንዲችሉ ሲያስገነባቸው የቆየውን 4 ትላልቅ ማዕከላት ዛሬ ያስመርቃል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ ምረቃውን አስመልክተው ባለፈው ማክሰኞ ቦሌ በሚገኘው የዩኒቨርሲቲው ካምፓስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የተገነቡት የአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ያላቸው ስለሆኑ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በ2025 ከአፍሪካ ቀዳሚና በዓለም የታወቀ ዩኒቨርሲቲ የመሆን ራዕዩን አንድ ደረጃ ከፍ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
የሚመረቁት ማዕከላት የጅማ የሕክምና ማዕከል (ሆስፒታል)፣ ልዩ የሲቪክ ማዕከል (ሚኒ ስታዲየም)፣ ዘመናዊ የኮንፈረንስ ማዕከል፣ ዘመናዊ ስታዲየምና የስፖርት አካዳሚ ሲሆኑ፣ ዘመኑ የደረሰበት የመጨረሻ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የተገጠሙለት ሆስፒታሉ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ለሚኖሩ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦች፣ ከሁሉም የአገሪቷ ክፍሎችና ለጐረቤት አገራት ጭምር አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡
ሆስፒታሉ፣ ባሉት ዘመናዊ መሳሪያዎች፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ አልጋዎችና የሕክምና አሰጣጥ ደረጃ በአገሪቷ ቀዳሚው ይሆናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ሆስፒታሉ 800 አልጋዎች፣ 12 የኦፕሬሽን ክፍሎች፣ 12 የፅኑ ሕሙማን አልጋ፣ የኩላሊት እጥበት ማዕከል፣ የዲጂታል (ኤሌክትሮኒክ) ኤክስሬይ፣ ሲቲ ስካንና ኤም አር አይ (MRI) ያካተተ ሲሆን ለሕሙማንና ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለሕክምና ባለሙያዎች አስፈላጊው ቴክኖሎጂ የተሟላለት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ሆስፒታሉ በአሁኑ ወቅት 16 የአገልግሎት ማዕከላትና ዲፓርትመንቶች፣ ከ70 በላይ ስፔሻሊስትና ሰብስፔሻሊስት ሐኪሞች፣ ከ500 በላይ ነርሶች፣ ከ60 በላይ የፋርማሲና ከ60 በላይ የላቦራቶሪ ባለሙያዎች ሲኖሩ፣ በቀን ከ1 ሺህ በላይ ሕሙማን አገልግሎት የሚያገኙበት እንደሆነ ታውቋል፡፡  
የሜዲካል ማዕከሉን (ሆስፒታሉን) ዘመናዊ ከሚያሰኙት ነገሮች መካከል፡- ዘመናዊ ዝግ የቆሻሻ ማቃጠያ፣ ዘመናዊ   የኦክሲጅን ማምረቻና የባዮሜዲካል፣ እንፋሎትና ሙቅ ውሃ የሚሰጥ ማዕከላዊ ማሞቂያና የአየር አንቡላንስ አገልግሎት መስጫ የሄሊኮፕተር ማሳረፊያ ቦታ እንዳለው ተገጿል።
ልዩ አገልግሎት የሚሰጠው የሲቪክ ማዕከል (ሚኒ ስታዲየም) ካፊቴሪያ፣ ሱቆች፣ ጋለሪ፣ ሚኒ ሚዲያ፣ ቲኬት ቢሮዎች፣ የገበያ ማዕከል፣ 17 መፀዳጃ ቤቶችና 22 መታጠቢያ ክፍሎች እንዲሁም የመሰብሰቢያ፣ ልዩ የእንግዳ ክፍሎች፣ 6‚000 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ሚኒ ስታዲየም፣ የመረብ፣ የቅርጫት ኳስና የእጅ ኳስ መጫወቻ ሜዳዎች፣ የሰርከስና የሙዚቃ ኮንሰርት ማቅረቢያ ስፍራ፣ አውደ ርዕይ፣ ለኮንፈረንስና ለተማሪዎች ምረቃ ከመሆኑም በላይ የማነቃቂያ ንግግሮች፣ የአካዳሚክ ውይይቶችና የሕዝብ ክርክር መድረክ በመሆን እንደሚያገለግል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ዘመናዊው የኮንፈረንስ ማዕከሉ፤ የተፈጥሮ ደን፣ ቡና፣ ማራኪ ወንዞች፣ አረንጓዴ መስኮችና ሸንተረሮችን አካቶ የያዘው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በከፍተኛ ትምህርትና በቱሪዝም ዘርፍ በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ሲሆን 4‚500 ተመልካቾች መያዝ የሚችል አዳራሽ፣ 1‚500 ሰዎች ማስተናገድ የሚችል ካፊቴሪያ፣ 250 ሰዎች መያዝ የሚችሉ ሁለት አነስተኛ አዳራሾች፣ 32 ቢሮዎች፣ 78 መፀዳጃና መታጠቢያ ክፍሎችና 4 ሲንዲኬት ክፍሎች ሲኖሩት፣ የተለያዩ የምርምር ኮንፈረንሶች፣ አውደ ርዕዮች፣ ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ስብሰባዎች የሚስተናገዱበት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
ዘመናዊው ስታዲየምና የስፖርት አካዳሚው፤ ለሀገሪቷ ስፖርት ውጤታማ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ባለሙያዎችን ለማፍራት፣ ለስፖርት አፍቃሪዎችና ለማኅበረሰቡ አማራጭ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ የተገነባ መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ፍቅሬ፤ ስታዲየሙ 40 ሺህ ተመልካቾች መያዝ እንደሚችል፣ የስፖርት አካዳሚ ትምህርቶች እንደሚሰጡበት የእጅ፣ የአትሌቲክስ፣ የሜዳ ቴኒስ ሜዳዎችና ቢሮዎች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባንኮችና ኢንሹራንሶች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ መደብሮች፣ የኑትሪሽን ቤተሙከራ፣ ጂምናዚየም፣ የልጆች መጫወቻ ሜዳ፣ መመገቢያ አዳራሽ፣ 46 መፀዳጃ ቤቶች እንዳሉት፣ ጅማ ከተማን የስፖርትና የኮንፈረንስ ማዕከል ሊያደርግ የሚችል ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየምና የስፖርት አካዳሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጨረር ሕክምና ከሚሰጠው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውጭ የጨረር ሕክምና ለመስጠት ከተመረጡ 6 ሆስፒታሎች አንዱ የጅማ ሆስፒታል እንደሆነ የጠቀሱት የጅማ ሕክምና ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኢሳያስ ከበደ፤ ቀደም ባሉት ዓመታት 6 እና 7 የሕክምና ዶክተሮች የሚያስመርቀው ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ግን በአንድ ጊዜ ብዛት ያላቸው 331 ዶክተሮች፣ በማስተርስ ዲግሪ፣ በስፔሻሊቲና በሰብ ስፔሺያሊቲ ያስተማራቸውን፣ እንዲሁም አንድ የካንሰር ሐኪም በሰብ ስፔሻሊቲ እንደሚያስመርቅ አስታውቀዋል፡፡
ሆስፒታሉ ዓለምአቀፍ የጥራት ደረጃ ያሟላ በመሆኑ፣ የተሻለ ሕክምና ፍለጋ ከአገር ውስጥ  ወደተለያዩ አገራት የሚሄዱና ከምሥራቅ አፍሪካ ጐረቤት አገራት የሚመጡ ሕሙማንን በብቃት ማከም ይችላል ሲሉ ዶ/ር ኢሳያስ ገልፀዋል፡፡
ተቋማቱ ረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉና ዓለምአቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው የተሠሩ ስለሆነ  የተሠሩበት ዋጋ ወደድ ይላል ያሉት ፕሮፌሰር ፍቅሬ፣ ዘመናዊው ሆስፒታል በመጀመሪያ 230 ሚሊዮን ብር ለማስፋፊያው 420 ሚሊዮን ብር፣ ዘመናዊው የኮንፈረንስ ማዕከል ምናልባት በአፍሪካ የመጀመሪያው እንደሚሆን ጠቅሰው 165 ሚሊዮን ብር መፍጀቱን፣ ዘመናዊው የኮንፈረንስ ማዕከል 217 ሚሊዮን ብር፣ ስታዲየሙና የስፖርት አካዳሚው ቀሪውን የጣሪያ ክዳን ማልበስ ጨምሮ 500 ሚሊዮን ያህል ብር እንደሚፈጅ መገመቱንና አጠቃላይ ወጪዎቹ 1‚315 ቢሊዮን ብር ሲሆን ሙሉ በሙሉ በመንግሥት የተሸፈነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

Read 3030 times