Saturday, 15 December 2018 14:41

“ከእንግዲህ እንቅልፍ የለችም፣ የዕረፍት አድባር አጣች መቅኖ ማክቤዝ እንቅልፍን ገደላት፣ በእኩለ-ሌሊት አፍኖ”

Written by 
Rate this item
(11 votes)

 ሼክስፒር
        ትርጉም- ፀጋዬ ገ/መድህን


    የናዚ ዘመን ታሪክ ከተከሰተ ረዥም ጊዜ ቢሆነውም፣ እስከዛሬ ግን ተተርኮ አላለቀም፡፡ ይፈለፈላል፣ ይዘረዘራል፡፡ ይተረተራል፡፡ ድብቁ ይገለጣል፡፡ የተገለጠው ይብራራል፡፡
የእኛስ?
ገና መፃፍ አልተጀመረም ብንል ይቀላል፡፡
ማስረጃው የሰሞኑን ዓይነቱ መራራና ጭካኔ የተሞላ ዶኩመንታሪ ነው፡፡ ጥቂት ቀልብን ሰብስቦ አድርጎ፣ መፃፍ መጀመር አለበት፡፡
ለዛሬ በናዚ ተረት እናዝግም፡፡
* * *
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የናዚ ጄኔራል፣አንድ መገደል ያለበት ሰው እንዲገደል ለጋሻ ጃግሬዎቻቸው ትዕዛዝ እየሰጡ ነበር፡፡
ጄነራል፤
“ትሰሙኛላችሁ?”
አንደኛው ጋሻ ፤-
“አቤት ክቡር ጄኔራል? ምን እንታዘዝ?”
ጄኔራል፤
“አንተኛውስ?”
ሁለተኛው፤
“እያዳመጥኩ ነው”
ጄኔራል፤
“በደምብ ስሙ! አንድ ከከተማ ውጪ ተወስዶ መገደል ያለበት ፀረ- መንግሥት ሰው አለ፡፡ መገደል ያለበት በጣም ራቅ ያለ ቦታ ተወስዶ ሲሆን፤ ምንም ዓይነት የጥይት ድምፅ የከተማችን ህዝብ መስማት የለበትም፡፡ ምክንያቱም ህዝባችን ከተረበሸ ሰላም ይደፈርሳል! ስለዚህ ማንም ሰው የጥይት ድምፅ ቢሰማ ወዮላችሁ!!” አንደኛው - ጋሻ ጃግሬ (ሰላምታ እየሰጠ)፤
“ታዛዥ ነን ጄኔራል!”
ሁለተኛው - ጋሻ ጃግሬ፤
“ፍፁም ታዛዥ ነን ጄኔራል!”
ቀጠሉ ጄኔራል፡፤
“ደግሞ ቢያመልጥ ወይም ቢድን፤ በገመዱ እንደምትገቡ እወቁ፡፡ እያንዳንድሽን አንጠለጥልሻለሁ!”
ሁለቱም ባንድ ድምፅ፤
“በፍፁም ጄኔራል ሆይ!”
ጄኔራል፤
“ነገ ጠዋት ይፈፀም!”
ሁለቱም፤
“ዝግጁ ነን ጄኔራል!”
ጄኔራል፤
“አሰናብቻችኋለሁ!”
ጋሻ ጃግሬዎቹ ወደ ክፍላቸው ሄዱ፡፡ በነጋታው እሥረኛውን አስጠርተው፣ እጆቹን አሥረው ወደ መገደያው ሥፍራ መንገድ ጀመሩ፡፡ መንገዱ ቢሄዱት ቢሄዱት እንደ አዳል መጫኛ የረዘመ ሆነ፡፡ ሰው ጥይት አይሰማም የሚሉበት ቦታ ለመድረስ የአንድ ቀን ጉዞ ሆኗል!
እሥረኛው ሰውነቱ ዛለ፡፡ ተዝለፈለፈ፡፡ እዚያው እንዲጨርሱት ፈለገ፡፡ ስለዚህ ቆመና፤ “ጌቶቼ፤ ልትገድሉኝ እንደምትወስዱኝ ተገንዝቤአለሁ፡፡ እባካችሁ ብዙ ሳልደክም፣ እዚሁ ብትጨርሱኝ ምናለበት?”
ጋሻ ጃግሬዎቹም፤
“ዝም ብለህ ሂድ! አንተስ እዛው ስትደርስ ትገላገላለህ፡፡ እኛ አለን አደለም እንዴ ገና ይሄን ሁሉ መንገድ የምንመለሰው?!” ብለው እየገፈተሩ ይዘውት ሄዱ!
* * *
ሰሞኑ የተሰሩ ግፎችን የምንቆርጥበት መሆኑ መቼም የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ጭካኔያችን ለከት አጥቷል፡፡ አረመኔያዊ ድርጊታችን፣ ይህ ወሰንህ፣ ይህ ዲካህ የሚባል አይደለም፡፡ ስለ ሰላም እያወራን፣ ምድራዊ ሲዖል ስንፈጥር ከረምን፡፡ ስለ ነፃነት እያወራን፣ አሰቃቂ ባርነትን በወገኖቻችን ላይ ጫንን፡፡ ስለ ልማት እየሰበክን ዘረፍን፣ መዘበርን። በህዝብ ላብ ፎቅ አቆምን፡፡ ችግር ከማባባስ በቀር የመፍትሄው አካል መሆን አቅቶናል፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰት የቆየ ያመረቀዘ ቁስል ነው፡፡ ህብረተሰቡ የመከላከል አቅሙን እንዳያጠነክር ተቋማት ራሳቸው አቅመ - ቢስና ለቋሳ ናቸው፡፡ አፍአዊ ሳይሆን ልባዊ ሆነን ግፍን በተግባር መዋጋት አለብን፡፡
O Justice thou hast flown to Beasts!
ፍትህ ሆይ! ወደ አውሬዎች ተሰደድሽ!
የተባለውን የሼክስፒር ጥቅስ ቀልብሰን፤ፍትህ ለተገፉ እንድትቆም ለማድረግ ሌት ተቀን መለፋት አለበት፡፡ የማታ ማታ በዳይ የእጁን ማግኘት ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ ጫንቃ ኢ-ዲሞክራሲያዊነትን፣ ሐሳዊ - ፍትሕን፣ ምዝበራንና ኢ-ሰብአዊነትን ለመሸከም ከእንግዲህ ምንም ቦታ ሊኖረው አይችልም፡፡
ጭካኔና አረመኔያዊ ድርጊት በተፈረካከሰ ኢኮኖሚ ላይ ሲጫን፣ ዘግናኝ ትርዒት ነው የሚሆነው፡፡ የሰው ልጅን ዘቅዝቆ ከመስቀል፣ ለወራት አንጠልጥሎ ከማቆየት እስከ ከፎቅ መወርወር ድረስ ምን አሰየጠነን? ኢትዮጵያን በመሰለች ሃይማኖታዊ አገር ላይ ይህን መሳይ ግፍ ሲፈፀም፣ እያየንስ ግፉን እንዳናስቆም ምን ልባችንን ደፈነው? ከእንግዲህ ዐይናችንን ወደ ውስጥ ገርተን፤
“ኧረ ምረር ምረር፣ ምረር እንደቅል
አልመርም ብሎ ነው፣ ዱባ እሚቀቀል!”
የሚለውን ማሰላሰል ይኖርብናል፡፡ “የቆቅ ለማዳ የለውም፡፡” የሚለውን ተረትም አለመዘንጋት ነው፡፡ ግፈኞችን ለፍርድ ማቅረብን ዛሬ ብቻ ሳይሆን መቼም ወደ ኋላ የማንልበት ልማድ ማድረግ አለብን፡፡ የመከራችንን ስፋት ያህል የፍርድ ሂደቱም ብዙ ሳንካ እንደሚኖርበት አምነን፣ እንቅፋቶቹን ለመቀነስ ጨክነንና ቆርጠን መነሳት ግድ ነው፡፡
ህዝብ ግፍ እንደተፈፀመበት መረዳት ሲጀምርና ሲያውቅ፣ ግፈኛው ከእንቅልፍ ጋር መለያየቱ አይቀሬ ነው፡፡ የሼክስፒሩ ማክቤዝ፤ ያለ የሌለ ግፉን ፈፅሞ፣ እጁን በደም ታጥቦ፣ የመጨረሻዋ ሰዓት ስትደርስ የሚከተለው ተባለ፡-
“ከእንግዲህ እንቅልፍ የለችም፣ የእረፍት አድባር አጣች መቅኖ
ማክቤዝ እንቅልፍን ገደላት፣ በእኩለ - ሌሊት አፍኖ”
ግፍ ሰርቶ ተኝቶ ማደር የለም፣ ነው የሚለን!! ጥናቱን ይስጠን!!

Read 13939 times