Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 19 May 2012 11:52

ኦባማና ተፎካካሪያቸው አንገት ለአንገት ተናንቀዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የ29 ዓመቷ ሂዘር ቤክማን የዲሞክራት ፓርቲ ደጋፊ ብትሆንም በመጪው ህዳር ወር በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ድምፅዋን ለማን እንደምትሰጥ አልወሰነችም፡፡ ሆኖም ለኦባማ እንደምታደላ አልደበቀችም፡፡ ፕሬዚዳንቱ ኢኮኖሚውን ወደ ትክክለኛው ቦታው ይመልሱታል ብላ ታምናለች - ወጣቷ፡፡ ብቻቸውን ግን አይደለም፡፡ “የሆነ ጊዜ ላይ ሪፐብሊካንና ዲሞክራቶች በአንድ ላይ ሆነው ኢኮኖሚውን መለወጥ አለባቸው፤ አገሪቱንም ጭምር” ብላለች - ለአሶሼትድ ፕሬስ፡፡ለ68 ዓመቱ አዛውንትና ለሪፐብሊካኑ ሮኒ ሌቬል ግን ኢኮኖሚውን ከገባበት አዘቅት ማውጣት የሚችሉት ሮምኒ ብቻ ናቸው፡፡ “በጣም ትላልቅ ኩባንያዎች ከፋይናንስ ችግራቸው እንዲወጡ አድርገዋል” የሚሉት ጡረተኛው የት/ቤት አስተዳዳሪ፤ “ኦባማ ሊሰራው እንደማይችል አረጋግጦልናል፤ አሁን ደግሞ ሌላ ሰው የሚሞክርበት ጊዜ ነው” ባይ ናቸው፡፡

በአሶሼትድ ፕሬስ ተሰርቶ ሰሞኑን ይፋ የተደረገው ቅኝታዊ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ አሜሪካውያን በአገራቸው ኢኮኖሚ ላይ ብዙም ተስፋ የሚታያቸው አይመስሉም፡፡ አንዳንዶች ከጥቂት ወራት በፊት የነበራቸው ተስፋም እየጨላለመ እንደመጣ ነው ጥናቱ የሚጠቁመው፡፡ ካለፈው የካቲት ወር ወዲህ “ኢኮኖሚው ጥሩ ነው” የሚሉ የአሜሪካውያን ቁጥር በ10 ነጥቦች አሽቆልቁሏል፡፡ ሁለት ሦስተኛ ያህሉ የአሜሪካ ህዝብ ኢኮኖሚው “ደካማ ነው” ብሎ እንደሚያምንም ታውቋል፡፡ ባለፈው የካቲት ወር ኢኮኖሚው “ተሽሎታል” የሚሉ አሜሪካውያን 28 በመቶ ያህል እንደነበሩ የጠቆመው ጥናቱ፤ አሁን ግን ወደ 22 በመቶ መውረዱን አመልክቷል፡፡ዲሞክራቶች ከሪፐብሊካኖችና ገለልተኞች በበለጠ ኢኮኖሚው በመጪው ዓመት መሻሻል ያሳያል የሚል ብሩህ ተስፋ ቢኖራቸውም፤ ካለፈው የካቲት ወር ወዲህ ቁጥራቸው በ10 ነጥቦች አሽቆልቁሏል፡፡

ለበርካቶች ጊዜው አስቸጋሪ እንደሚሆን ያልሸሸጉት ኦባማ፤ ሁኔታዎች ቀስ በቀስ እንደሚሻሻሉ ጠቁመው፤ ህዝቡ ኢኮኖሚው ሙሉ በሙሉ እንዲያገግም ከፈለገ እኔን የሙጥኝ ይበል ብለዋል (በድምፁ ማለታቸው ነው) ዩኤስኤ ቱዴይ የሰራው ቅኝታዊ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ኢኮኖሚውን በመምራት አቅም የቀድሞው የቢዝነስ ባለሙያ ሮምኒ ከፍተኛ ነጥብ አግኝተዋል፡፡

በተለያዩ ተቋማት ከተሰበሰበው የህዝብ አስተያየት መረዳት እንደሚቻለው፤ ኦባማ ከነዳጅ ዋጋ መጨመር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ተቃውሞ ተሰንዝሮባቸዋል - ምንም እንኳን ዋጋው አሁን የቀነሰ ቢሆንም፡፡ በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ የአንድ ሊትር ነዳጅ አማካይ ዋጋ 3.94 ዶላር የነበረ ሲሆን አሁን ወደ 3.75 ዶላር እንደወረደ ታውቋል፡፡የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የነዳጅ ዋጋን በተመለከተ አቅማቸው ውስን ነው፤ ምክንያቱም የነዳጅ ዋጋ ምንጊዜም በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የተሞረኮዘ ነው ያለው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ሥልጣን ላይ የሌለ ሃይል ሁሉ ጣቱን የሚሰነዝረው ግን ዋይት ሐውስ ውስጥ ወደተቀመጠው ሰው ነው ብሏል፡፡ በ2008 እ.ኤ.አ ኦባማ ለነዳጅ ዋጋ መወደድ ሥልጣን ላይ የነበሩትን ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ተጠያቂ አድርገው እንደነበረው ሁሉ፤ አሁን ደግሞ ሮምኒ ኦባማ ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል ብሏል - አሶሼትድ ፕሬስ፡፡

ለኢኮኖሚ ድቀቱ ምስጋና ይግባውና በዘንድሮ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዋነኛው የመፎካከርያ አጀንዳ ኢኮኖሚው ሆኗል፡፡ የኢኮኖሚ ድቀቱ በይፋ የተጠናቀቀው በ2009 (እ.ኤ.አ) ቢሆንም የሥራ አጥ ቁጥር በመጋቢት መጨረሻ በነበረበት 8.1 በመቶ ላይ ሲሆን 12.5 ሚሊዮን አሜሪካውያን ከሥራ ውጭ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

እስካሁን የምርጫ ክርክር አጀንዳው በኢኮኖሚ ላይ ማነጣጠሩ ለሪፐብሊካኑ እጩ ተመችቷቸው እንደነበረ የሚጠቁሙ መረጃዎች፤ ባለፈው ሳምንት ኦባማ ያነሱት የተለየ አጀንዳ ግን ድንገተኛ ሆኖባቸው ይላሉ፡፡

ኦባማ ባለፈው ሳምንት የግብረ ሰዶማውያንና የሌዝቢያን ጥንዶችን የጋብቻ መብት አከብራለሁ ብለዋል፡፡ በዚህ ውሳኔያቸውም 1/3ኛው የአሜሪካ ህዝብ ድጋፉን ሲሰጣቸው፤ የዚያኑ ያህል ህዝብ  ደግሞ ድጋፍ ነስቷቸዋል፡፡ ኦባማ የግብረ ሰዶማውያን ጋብቻን መደገፍ የግል ውሳኔዬ ነው ቢሉም ይሄ ውሳኔ በቀጣዩ ዓመት ህዳር ወር ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይጠቅማቸዋል አይጠቅማቸውም የሚለው ጉዳይ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ሙግት አስነስቷል ተብሏል፡፡ ለእሳቸው ተቀባይነት ማግኘት ግን የፈየደላቸው ነገር የለም፡፡

ኦባማ የግብረ ሰዶማውያንን ጋብቻ መብት እቀበላለሁ በማለታቸው 31 በመቶ አሜሪካውያን ስለእሳቸው ያላቸው ግምት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ያመለከተው ጥናቱ፤ 30 በመቶ ያህል አሜሪካውያን ስለእሳቸው የነበራቸው ግምት እንዳሳነሰባቸው ጠቁሟል፡፡ 40 በመቶ ያህሉ ደግሞ ጉዳዩ ስለ ፕሬዚዳንቱ ባላቸው ግምት ላይ ምንም ተፅዕኖ እንደማይፈጥር ተናግረዋል፡፡ ኒውዮርክ ታይምስ ባሰባሰበው የህዝብ አስተያየት፤ አብዛኛዎቹ አሜሪካውያን ኦባማ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት በፖለቲካዊ ምክንያት እንጂ “ትክክል ነው” ብለው በማሰብ አይደለም ብለው እንደሚያምኑ ጠቁሟል፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት የተሰራ ቅኝታዊ ጥናት፤ ሁለቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪዎች አቻ የተቀባይነት ደረጃ እንደነበራቸው የሚጠቁም ቢሆንም አሁን ግን የተቀባይነት ነጥቡ ወደ ሪፐብሊካኑ እጩ ያጋደለ ይመስላል፡፡

ኒውዮርክ ታይምስ እና CBS News ሰሞኑን ያወጡት የህዝብ አስተያየት ቅኝት እንደሚጠቁመው፤ የሮምኒ የህዝብ ተቀባይነት 46 በመቶ ሲሆን፤ የኦባማ 43 በመቶ እንደሆነ ታውቋል፡፡

============================================

አሜሪካ 100ሺ የሳይንስ መምህራን ለማፍራት እየተጋች ነው

የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች በሳይንስ ትምህርት ደካማ ናቸው

የአሜሪካ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች በሳይንስ ትምህርት ከሁለት ዓመት በፊት የነበራቸውን የብቃት ደረጃ እንዳሻሻሉ የገለፀው የአሜሪካ መንግስት፤ አሁንም ግን ከ10 ተማሪዎች ሰባቱ በቂ ክህሎት እንደሌላቸው አስታወቀ፡፡

ከተማሪዎቹ ሁለት በመቶ ያህሉ ብቻ ወደ ሳይንስ ሙያ ዘርፍ የሚያስገባ ብቃት እንዳላቸው ብሄራዊ የትምህርት ግስጋሴ ግምገማ ሪፖርት ይጠቁማል፡፡

ብሄራዊ የሳይንስ መምህራን ማህበር መሪ የሆኑት ጌሪ ዊለር፤ የታየው ለውጥ እዚህ ግቢ የማይባል ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

በቀረበላቸው የግምገማ ፈተና በቂ ክህሎት ወይም የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡት 31 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑ ነው መረጃው የሚያመለክተው፡፡ በየት/ቤቶቹ የላቁ የሳይንስ መምህራንን ቁጥር በማሳደግ የተማሪዎችን የሳይንስ ትምህርት ውጤት ለማሻሻል የትምህርት ዲፓርትመንትና የአሜሪካ መንግስት በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ዲፓርትመንቱ በዘርፉ የብቃት ማረጋገጫ ለሚወስዱ መምህራን ማበረታቻና ቦነስ በመስጠት በቀጣዮቹ አስር ዓመታት 100ሺ አዳዲስ የሳይንስ አስተማሪዎችን የማዘጋጀት ግብ እንዳለው አስታውቋል፡፡

እንደ ጆርጂያ ያሉ የአሜሪካ ግዛቶች ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉ የኮሌጅ ተማሪዎችን ቁጥር ለማሳደግ በሚል ለሳይንስ መምህራን ሌሎች ትምህርቶችን ከሚያስተምሩ ባልደረቦቻቸው የበለጠ ደሞዝ ይከፍላሉ፡፡“ይሄ በት/ቤቶችና በአገሪቱ ክልሎች አቅም ለመገንባት በትጋትና በፍጥነት መስራት እንዳለብን ይጠቁመኛል” ብለዋል የትምህርት ሚኒስትሩ ኤሚ ዱንካን - በሳይንስ ትምህርት ከፍተኛ ነጥብ የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ቁጥር ባለበት መርገጡን በመጠቆም፡፡ “ነገሮችን በተለየ መንገድ ማከናወን አለብን፤ ለዚህም ነው የትምህርት ተሃድሶ በጣም ወሳኝ የሆነው” ብለዋል - ሚኒስትሯ፡፡

የመገምገሚያ ፈተናው ባለፈው ዓመት ከ7ሺ 300 ት/ቤቶች ለመጡ 120ሺ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን በፈተናው ላይ ከተሳተፉ 47 ግዛቶች በውጤታቸው ትንሽ ለውጥ ያሳዩት 16ቱ ብቻ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ አብዛኞቹ ግዛቶች ከ2009 ጋር ሲወዳደር “የሾቀ” ውጤት ነው ያገኙት ብሏል የትምህርት ዲፓርትመንቱ መረጃ፡

የብሄራዊ ፈተና ፕሮግራም ሃላፊነቱ የኮንግረስ ሲሆን ፕሮግራሙ የ4ኛ፣ 8ኛና 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ሂሳብ፣ ንባብና ሌሎች ትምህርቶችን መፈተንን ያካትታል፡፡ የፈተና ውጤቱ በግዛቶቹ መካከል ያለውን ከፍተኛ ልዩነትም ይጠቁማል፡፡ የፈተናው (መመዘኛው) ውጤት እንደሚያመለክተው፤ በሚሲሲፒ 18 በመቶ ያህሉ ተማሪዎች ብቻ በሳይንስ ትምህርት በቂ ክህሎት ያስመዘገቡ ሲሆን አንድም ተማሪ የላቀ ውጤት የሚለው ዘርፍ ውስጥ አልገባም፡፡ ሞንታና እና ሰሜን ዳኮታ ምርጥ ውጤት አሳይተዋል ተብሏል - 44 በመቶ ያህሉ ተማሪዎች የላቀ ክህሎት ወይም ብቃት በማስመዝገባቸው፡፡

ለዚህ ደካማ ውጤት የተለያዩ ጉዳዮች አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን የሚናገሩት የትምህርት ባለሙያዎች፤ በዋናነት “ወደኋላ የሚተው አንድም ህፃን የለም” የሚለውን ህግ ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ ምክንያታቸውን ሲያቀርቡም፤ ህጉ ከሳይንስ፣ ታሪክ፤ አርትና ሌሎች የትምህርት ዘርፎች ይልቅ ለሂሳብና ለንባብ ትኩረት ስለሚሰጥ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

 

 

 

 

 

 

Read 3455 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 12:49

Latest from