Saturday, 15 December 2018 15:48

ለአዕምሮ ህሙማን ፍቅር መስጠት

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

  በኢትዮጵያ 27 ሚሊዮን የአዕምሮ ሕሙማን ይገኛሉ

   በጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ የአዕምሮ ህክምና ክፍል ባልደረቦች፤ “የአዕምሮ ጤናን ቀን” ለማክበር ወዲያና ወዲህ ተፍ ተፍ ይላሉ። በስፍራው ጋዜጠኞች፣ የህሙማን ቤተሰቦች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ ይኸኔ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ሽዞፈርኒያ የተባለው የአዕምሮ ሕመም ያለበት ሰው ዛፍ ላይ ወጥቶ ይቀመጣል፡፡ ሰዎች “ና ውረድ! ትወድቃለህ!” … እያሉ ቢያስፈራሩት፣ ቢጮኹበትም --- አልተሳካላቸውም፡፡ እንዲያውም ዛፉ ላይ ተደላድሎ ተቀመጠ፡፡
ይኼ ሲሆን ሲስተር ወርቅነሽ ተሰማ ዝግጅት ላይ ስለነበሩ፣ የተፈጠረውን አያውቁም ነበር፡፡ “ና ውረድ! ውረድ!” የሚለውን የሰዎች ጩኸት ሰምተው፣ ወደ ስፍራው ሲመጡ፣ የሚያውቁት ሽዞፈርኒያ የሚባለው የአዕምሮ ሕመምተኛ ያለበት ሰው፣ ዛፉ ላይ ወጥቶ ተቀምጧል፡፡ ተረጋግተው ወደ ዛፉ ስር በመሄድ፣ የሕመምተኛውን ስም ጠርተው፤ “እኔ ነኝ፣ ሲስተር ወርቅነሽ ነኝ… አሁን አንተ ከዛፉ ላይ ስትወርድ፣ አብረን የምንሰራው ሥራ ስላለ እንድታግዘኝ እፈልጋለሁ --- እኔ ስላለሁ ማም አይነካህም፤ ና ውረድ!” አሉት፡፡ ቀስ ብሎ ወረደ፡፡ “ሥራ እሰጥሃለሁ” ብለው ቃል በገቡለት መሰረት፣ለእንግዶች ወንበር እንዲያቀርብ ነገሩት። ሕመምተኛውም ለእንግዶች ወንበር ማቅረቡን ተያያዘው፡፡  
“በዚህ የተነሳ ሰው ተገረመ” የሚሉት ሲስተር ወርቅነሽ፤ ”ነገር ግን ምንም የሚያስገርም ነገር የለውም” ይላሉ፡፡” “በእኛ ሙያ ይህን ነገር ቨርቫልስታሌሽን ይባላል፡፡ ምን ማለት ነው፤ በቃላት ሰውን ማረጋጋት- ይባላል፡፡ የንግግር ቅላፄያችን፣ ቀስ ባለና ፍቅርን ባከለና፣ ቀለል ባለ አማርኛ፣ በሚረዳው ቃል እንክብካቤ እንደሚያገኝ አሳይተንና ደህንነቱን ከጠበቅንለት፣ ሕመምተኛው ጐጂ አይደለም፡፡ 30 ዓመታት አብሬአቸው ሰርቻለሁ፤ አንድም ቀን አንድም ሕመምተኛ ያደረገኝ ነገር የለም፤ የአዕምሮ ሕሙማን የሚፈልጉትን ነገር ለይቻለሁ፡፡ ለአንድ ሰው የሚጥመው ነገር ስሙ ስለሆነ፣ ረጋ ብሎ ስሙን መጥራት፣ ረጋ ባለና ግልጽ በሆነ ድምጽ መጥራት፣ ቁጣን ያላማከለ፤ ምን እንደሚፈልግ ተረድቶ፣ የሚፈልገውን ማድረግ ነው” በማለት አስረድተዋል፤ ሲስተር ወርቅነሽ፡፡
ሲስተር ወርቅነሽ ተሰማ፤ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ሕክምና ክፍል፣ መምህርትና ክሊኒካል ሐኪም በመሆን ለ30 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ እርሻ ኮሌጅ ተገናኝተን ስናወራ፣ ስለ አዕምሮ ሕመም ያጫወቱኝ ነገር ጣመኝና፣ ስለ አዕምሮ ሕክምና እንዲነግሩኝ ጠየኳቸው፡፡ በደስታ አወጉኝ፡፡
“የአዕምሮ ሕመም እንደ ማንኛውም የአካል ሕመም ነው፡፡ ሆኖም ግን ምክንያቶቹ እጅግ በርካታ ናቸው። ከሕመሙ መንስኤ በርካታነት የተነሳ ይኼኛው መድኃኒት ያክመዋል ወይም ያድነዋል ተብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ ከአዕምሮ ሕመም መንስኤዎች አንዱ ዘረ መል ወይም ሄሬዲታሪ፣ ሶሻል ወይም ኢንቫይሮመንታል የሥነ ልቡና ጫና ናቸው። እነዚህ አንድ ላይ ሲደመሩና ሰውዬውን ተጋላጭ ሲያደርጉት፣ ታማሚው ለአዕምሮ ሕመም ይጋለጣል፡፡
“የአዕምሮ ሕመም ፆታ፣ ሃይማኖት፣ ጎሳ፣ ብሔር፣ አይለይም፡፡ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ ደረጃ (ሥልጣን) ላይ ያለ የተማረ፣ ያልተማረ፣ … በአዕምሮ ሕመም ሊጠቃ ይችላል፡፡ ዋናው ቁም ነገር፤ በአዕምሮ ሕመም የተያዘ ሰው፤ በሽታው እንዳለበት ሲታወቅ፣ በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም - ክሊኒክ፣ ጤና ጣቢያ፣ ሆስፒታል መውሰድ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
“የአዕምሮ ሕመሞች በርካታ ሲሆኑ ከ400 በላይ ናቸው፡፡ ከቀላል እስከ ከባድ የአዕምሮ ሕመም አለ። ለምሳሌ፡- የጭንቀት የድብርት (ድባኔ)፣ በሱስ የሚመጣ፣ … የአዕምሮ ሕመሞችን፣ ከጭንቀት፣ ከድብርት፣ ከሱስ በማውጣት በቀላሉ ማከም ይቻል። ከፍተኛው የአዕምሮ አስተሳሰብ ክፍልን የሚይዝና ከዚህ ካለንበት የገሀዱ ዓለም የሚያወጣው ሕመም ሸዞፈርንያ (Schizophhrenia) የሚባለው ነው። ይህ ሕመም ያለባቸው ሰዎች፤ ሌሎች ሰዎች ማየት የማይችሉትን ሊያዩ፣ ሌሎች መስማት የማይችሉትን ሊሰሙ ይችላሉ፡፡ ሰዎች ሊገድሉኝ ይከታተሉኛል፣ … በማለት ያስባሉ፡፡ ይኼ በአስተሳሰባቸው ምክንያት የሚመጣ ችግር ነው፡፡
“የአዕምሮ ሕሙማን እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱ፣ ለራሳቸውም ሆነ ለሌላው ሰው ያላቸው ግምታዊ እሳቤ ይቀየራል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ሰዎች ይሸሿቸዋል፣ ያገሏቸዋል ወይም የተለየ ስያሜ ይሰጧቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ማግኘት ያለባቸውን ሕክምና፣ እንክብካቤ ወይም እርዳታና ምክር ሳያገኙ ይቀራሉ፡፡ ሕክምናና ድጋፍ ሳያገኙ ቀሩ ማለት ወደ ከፋ ወይም ወደ ተባባሰ ደረጃ ይደርሳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አክሞ ለማዳን ያስቸግራል፣ ይከብዳል፡፡ ቶሎ ወደ ሕክምና መምጣት ለእኛ አክሞ ለማዳን ይቀለናል፡፡
“ሽዞፈርኒያ የተባለው ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የአዕምሮ ሕመም ያለባቸው ሕሙማን፤ ከገሃዱ ዓለም ያፈነገጡ ስለሆነ ጤነኛ ሰዎች የማያደርጓቸውን ነገሮች ለምሳሌ ቆሻሻ መሰብሰብ፣ እርቃን መሄድ፣ ቆሻሻዎችን በላያቸው ላይ እንደኒሻን ደርድሮ ወይም ለብሶ መሄድ፣ አልባሌ ቦታ ላይ መተኛት፣ በጣም ሲከፋም ከቆሻሻ ገንዳ ውስጥ አውጥቶ መብላት ወዘተ… አፀያፊና ነውር የሆኑ ነገሮችን የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የሚያገናዝበው የአዕምሯቸው ክፍል ስለተጎዳ፣ “ይኼ ይጎዳኛል፣ ይኼ ነውር ነው፣ ይኼ ቆሻሻ ነው” ማለት ባለመቻላቸው በጤነኛ ሰዎች የማይሰሩ፣ ወጣ ያሉ ነገሮች ይሰራሉ፡፡ እነዚህ በሽተኞች ሕመሙ እንደያዛቸው፣ አንድ ሦስተኛ (ከሦስት በሽተኞች አንዱ) ወደ ህክምና ማዕከል ቢመጡ ሊድኑ ይችላሉ፡፡ ሁሉም እንኳ ባይሆኑ አንድ ሦስተኞቹ፣ እዚያው ባለበት መቆጣጠር ይቻላል። ሰው ርኅራሄና ፍቅር ቢሳያቸው፣ እኔ ዘመዱ፣ ልጁ፣ ጎረቤቱ፣ … ብሆንስ…. ብሎ ካላሰበ፣ ግማሽ ራቁታችንን እንደመሄድ ነው፡፡
“የኅብረተሰባችንን አስተሳሰብ ያየን እንደሆን፣ ብዙ ጊዜ የአዕምሮ ሕመም የሚመጣው በልክፍት፣ በቡዳ ወይም በሰይጣን፣ … ስለሚባል የአዕምሮ ሕሙማን በፍጥት ወደ ህክምና ተቋም አይወሰዱም፡፡ ፀበል ወስደው፣ የአገረሰብ መድኃኒት አድርገውላቸው፣ … እንቢ ሲላቸው ነው፣ ወደ ሐኪም ቤት የሚመጡት፡፡ ያኔ ደግሞ በሽታው ስር ስለሰደደ ለማዳን ይከብደናል። እዚህ ላይ ባህላዊ ህክምና አያስፈልግም ማለቴ አይደለም፤ ባህላዊ ህክምናን ከሳይንሳዊ ህክምና ጋር ብናቀናጀው የተሻለ ያማረ ይሆናል፡፡
“ለአዕምሮ ህመም እንክብካቤና ፍቅር መስጠት፣ እነሱን ማገልገል፣ እንደ አንድ የአገር ዜጋ መገንዘብና ማሰብ ያስፈልጋል እላለሁ፡፡ በኢትዮጵያ 27 ሚሊዮን የአዕምሮ ሕሙማን አሉ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የህዝቡን ቁጥር አንድ አራተኛ ይዘዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በ2010 በኢትዮጵያ ውስጥ ከአራት ሰዎች አንዱ የአዕምሮ ሕመም እንዳለበት ገልጿል፡፡ በዚህ ዓይነት በቅርበት ካሉን ወላጆቻችን፣ ከቤተሰቦቻችን ወይም ከወለድናቸው ልጆች መካከል አንዱ የአዕምሮ ሕመም ሊኖረው ይችላል፡፡ ስለዚህ ይኄ ጉዳይ የምንገፋው ወይም አላየሁም በማለት የምንክደው አይደለም። እራሱን እየገደለ የሚመጣ ሕመም ስለሆነ ከወዲሁ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራ አሳስባለሁ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ መምከር የምፈልገው፣ ከዘር የሚወረስ የአዕምሮ ህመም ያለባቸው ሰዎች እንደ ሐሺሽ፣ ጫት፣ .. ያሉ ሱሶች ወደ ከፋ ደረጃ ያደርሳቸዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወላጆች፣ መንግሥታት በአጠቃይ ማኅበረሰቡ ለአዕምሮ ሕመም ትኩረት ይስጡ፡፡
“እኛ ስለምናሸሻቸው ይሸሹናል፤ ስለምንመታቸው ይመቱናል፣ ውሃ ስለምንደፋባቸው ቁጠኛ ይሆናሉ። ነገር ግን አቅርበናቸው፣ አጥበናቸው፣ ያለንን አሮጌ ልብስ አልብሰናቸው፤ በቀላል ቋንቋ ወይም ዝግ ባለ ፍቅር ባለው፣ በለሰለሰ ቃላት ብናናግራቸው፣ መልካም ሰዎች ናቸው፡፡
“የአዕምሮ ሕመም ከሚያደርሰው ጉዳት በላይ በእነሱ ላይ የሚደርሰው ጥቃት በእጥፍ የጎላ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ እነሱ ከሚያደርሱት ጉዳት በላይ በእነሱ ላይ አካላዊ፣ ወሲባዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ስሜታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ ስለዚህ ሕሙማኑን ሳንክድ፣ የእኛ ዘመዶች መሆናቸውን አውቀን በማቅረብ ፍቅር ማሳየት፣ ተገቢ ያልሆኑ ስሞችን ያለመለጠፍ፣ (ይኼ ጦሽ ነው፣ የአዕምሮ ዘገምተኛ ነው፣ እብድ ነው፣) … በሚል ማግለልና መድልዎ ባንፈጽም፣ ጥሩ ውጤት እናመጣለን” በማለት ሲስተር ውርቅነሽ ፤ለኀብረተሰቡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡   

Read 2771 times